የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
276 subscribers
366 photos
3 videos
137 files
97 links
ይህ የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት ቻናል ስለኢትዮጵያ ሕጎች)ማብራሪያ የሚሰጥበት፣ አዳዲስ ሕጎች የሚጋሩበት፣ ሕግ ነክ ዜናዎችና መረጃዎች የሚተላለፉበት፣ በዳይሬክቶሬቱ የተሰጡ የንቃተ-ሕግ ስልጠናዎች፣ የሕግ መልዕክቶች፣ በራሪ ጽሑፎች እና መሰል ሰነዶች የሚለቀቁበት ነው።
መልካም ቆይታ!
Download Telegram
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 6/2002ን በመሻር “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 56/2010 መታወጁ ይታወቃል፡፡ ይህ አዋጅ በአንቀጽ 42 ንዑስ አንቀጽ (3) የተመለከተውን የወሊድ ፍቃድ በሚመለከት ረገድ ከታህሳስ 6 ቀን 2ሺ10 ዓ.ም ጀምሮ፤ ሌሎች ድንጋጌዎችን በሚመለከት ረገድ ከሚያዝያ 17 ቀን 2ሺ10 ዓ.ም ጀምሮ የጸና እንደሆነ ከአዋጁ መረዳት ይቻላል፡፡አዋጁ ካካተታቸው ነጥቦች የተወሰኑትን በተከታታይ ክፍሎች እንደማቀርብላችሁ እያሳወኳችሁ ሰላምታዬን አስቀድሜ ላካፍላችሁ ወደወደድኩት ነጥብ ልምራችሁ!
የደመወዝ ክፍያን በተመለከተ
ማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት በየወሩ መጨረሻ ለሠራተኞቹ ወይም ለሕጋዊ ወኪሎቻቸው የደመወዝ ክፍያ ይፈጽማል፡፡
የማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ፣
ሀ) ሠራተኛው ስምምነቱን በጽሐፍ ሲገልጽ፣ ለ)በፍርድ ቤት ትዕዛዝ፣ ሐ) በሕግ በተደነገገው መሠረት ካልሆነ በስተቀር ሊያዝ ወይም ሊቆረጥ አይችልም፡፡
ከላይ በ2(ለ) ወይም (ሐ) መሠረት ከሠራተኛ ደመወዝ በየወሩ የሚቆረጠው ከደመወዙ አንድ ሦስተኛ አይበልጥም፡፡
የመንግሥት ሠራተኛ ሆኖ ለመቀጠር የማያስችሉ ሁኔታዎችን በተመለከተ
የሚከተለት የመንግሥት ሠራተኛ ሆነው ሊቀጠሩ አይችለም፡-
ሀ) ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነ ሰው፤ ለ)ቅጣቱ ከተፈጸመ፣ በይርጋ ከታገደ ወይም በይቅርታ ከተሠረዘ በኋላ አምስት ዓመት ያልሆነው ካልሆነ በስተቀር የሙስና፣ የእምነት ማጉደል፣ የስርቆት፣ የማጭበርበር ወይም የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈጽሞ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት የተፈረደበት ማንኛውም ሰው፤ ሐ) የብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ የሌለው ሰው፤ መ)በዚህ አዋጅ አንቀጽ 17 መሠረት ቃለመሀላ ለመፈጸም ፍቃደኛ ያልሆነ ሰው፡፡
ከላይ በ(ለ) ስር የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ከማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት በዚህ አዋጅ አንቀጽ 88 መሠረት በዲስፕሊን ጉድለት ምክንያት ከሥራ የተሰናበተ ሰው ከሥራ ከተሰናበተበት ጊዜ ጀምሮ አምስት ዓመት ከመሙላቱ በፊት በመንግሥት ሠራተኛነት ሊቀጠር አይችልም፡፡
ከላይ በ(ሐ) ስር የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም አመልካች በመንግሥት ሥራ ተቀጥሮ ለማገልገል ብቁ መሆኑን ለማረጋገጥ ከኤች.አይ.ቪ./ኤድስ ምርመራ በስተቀር የጤንነት ማረጋገጫ የሕክምና ምርመራ እና ከላይ በ(ለ) ስር ከተጠቀሱት ወንጀሎች ነጻ መሆኑን የሚያረጋግጥ ከፖሊስ የተሰጠ ማስረጃ የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡
ከላይ በ(ለ) ስር የተደነገገው ቢኖርም ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት በላይ የሆናቸውና አሥራ ስምንት ዓመት ያልሞላቸው ወጣቶች ስለሚቀጠሩበትና ስለሥራ ሁኔታቸው ቢሮው መመሪያ ያወጣል፡፡
ይቀጥላል
ሰናይ 4/03/2013 ዓ.ም! (ኦምኒኤል)
ሰላም!ባለፈው አርብ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 56/2010 ላይ አንዳንድ ነጥቦችን በተከታታይ ክፍል እንደምናይ በነገርኳችሁ መሠረት ቀጣይ ክፍሉን ከታች አስፍሬላችኋለሁኝ፡፡መልካም ንባብ!
የሙከራ ጊዜን በተመለከተ
የሙከራ ጊዜ ዓላማ አዲስ የተቀጠረ የመንግሥት ሠራተኛ ስለሥራ አፈጻጸሙ ክትትል እየተደረገ ብቃቱን ለማረጋገጥ ይሆናል፡፡
የተመረጠው አመልካች የሥራ መደቡን መጠሪያ፣ የተመደበበትን ደረጃ፣ ደመወዙንና ሥራውን የሚጀምርበትን ቀን የሚገልጽ በአሰሪው መሥሪያ ቤት የበላይ ኃላፊ ወይም ሠራተኛን ለመቅጠር ውክልና በተሰጠው የሥራ ኃላፊ የተፈረመ የሙከራ ቅጥር ደብዳቤ በሥራ መደቡ ከሚያከናውነው የሥራ ዝርዝር መግለጫ ጋር የሚሰጠው ሲሆን የሠራተኛው የሙከራ ጊዜ በተቀጠረበት የሥራ መደብ ላይ ለስድስት ወር ሆኖ የሥራ አፈጻጸም ምዘና ውጤቱ ከመካከለኛ በታች ሆኖ ከተገኘ የሙከራ ጊዜው ለተጨማሪ ሦስት ወር ሊራዘም ይችላል፡፡ ሆኖም በተራዘመው የሙከራ ጊዜ ውስጥ ሠራተኛው መካከለኛ ወይም ከዚያ በላይ የተጠቃለለ የሥራ አፈጻጸም ምዘና ውጤት ካላገኘ ከሥራ ይሰናበታል፡፡
የአስተዳደሩ የፐፕሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮው የሥራ አካባቢ ደህንነትና ጤንነት የመጠበቂያና የመከላከያ ዘዴዎችን ያጠናል፤ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሥራ ላይ እንዲያውሉት ሥልጠና ስለሚሰጥበት ሁኔታ ያመቻቻል እንዲሁም በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሥራ አካባቢ ደህንነትና ጤንነት ተግባራዊ መሆኑን ይቆጣጠራል፤ የአደጋ መከላከያ እርምጃዎችን በተመለከተ በመመሪያ ይወሰናል የሚሉት ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው በሙከራ ላይ ያለ የመንግሥት ሠራተኛ በሥራ ምክንያት በሚመጣ በሽታ ወይም በሥራ ላይ በሚደርስ አደጋ ምክንያት ከሥራ የቀረ እንደሆነ ያልጨረሰውን የሙከራ ጊዜ ከሕመሙ ወይም ከጉዳቱ ከዳነበት ጊዜ አንስቶ እንዲጨርስ ይደረጋል፡፡
ከላይ የተቀመጠው ድንጋጌ ቢኖርም በወሊድ ምክንያት ከአንድ ወር በላይ በሥራዋ ላይ ያልተገኘች የሙከራ ሠራተኛ የወሊድ ፈቃዷ እንድተጠናቀቀ የሙከራ ጊዜ እንድትጨርስ ይደረጋል፤ ሆኖም በሙከራ ሥራዋ ላይ ያልተገኘችበት ጊዜ ከአንድ ወር በታች ከሆነ የሥራ አፈጻጸም ምዘና ውጤቷ በሥራ ላይ በቆየችበት ጊዜ ታስቦ ይሞላላታል፡፡
በሙከራ ላይ ያለን የመንግስት ሠራተኛ የሥራ አፈጻጸም ወቅቱን ጠብቆ ያልሞላ የሥራ ኃላፊ በዲሲፕሊን ተጠያቂ ይሆናል፡፡
በሙከራ ላይ የሚገኝ የመንግሥት ሠራተኛ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ከአንድ ወር በታች በሥራው ላይ ካልተገኘ በሥራው ላይ የተገኘበት ጊዜ ብቻ ታስቦ የሥራ አፈጻጸም ይሞላለታል፡፡
የውስጥ ዝውውርን በተመለከተ
አንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ለሥራው አስፈሊጊ ሆኖ ሲያገኘው ግልጽ የሆነ አሠራርን በመከተል አንድ የመንግሥት ሠራተኛን በዚያው መስሪያ ቤት ውስጥ እኩል በሆነ የሥራ ደረጃና ደመወዝ ወደ ሌላ የሥራ መደብ ወይም ከአንድ የሥራ ቦታ ወደ ሌላ ሥራ ቦታ በማዛወር ሊያሠራ ይችላል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ አንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት በመሥሪያ ቤቱ ላይ አደጋ እንዳይደርስ ለመከላከል ወይም አደጋው ያደረሰውን ጉዳት ለማስተካከል ሲባል አንድን የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዙ ሳይቀነስ፣ ደረጃው ወይም የሥራው ዓይነት ሳይጠበቅ ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ በጊዜያዊነት አዛውሮ ማሠራት ይችላል፡፡
የመንግሥት ሠራተኛ በጤና መታወክ ምክንያት በያዘው የሥራ መደብ ወይም ባለበት የሥራ ቦታ ላይ ሊሠራ አለመቻሉ በሐኪም ማስረጃ ሲረጋገጥ፡-
በተመሳሳይ ደረጃ ሊመደብበት የሚችል ክፍት የሥራ መደብ ካለ በያዘው ደረጃ ወይም በተመሳሳይ ደረጃ ሊመደብ የሚችልበት ክፍት የሥራ መደብ ከሌለና ሠራተኛው ዝቅ ባለ ደረጃ ላይ ለመሥራት ፈቃደኛ ከሆነ ደረጃው ተቀንሶ ወደ ሚስማማው የሥራ መደብ ወይም የሥራ ቦታ ይዛወራል፡፡
የአንድ የመንግሥት ሠራተኛ የሥራ መደብ የተሰረዘ እንደሆነ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ተመሳሳይ ደረጃ ወዳለው የሥራ መደብ ይዛወራል፡፡
ሰናይ ሰኞ!(7/3/2013 ዓ.ም)(ኦምኒኤል)
ይቀጥላል
ሰላም እንዴት ሰነበታችሁ ዛሬ ደግሞ ስለ ሰብአዊ መብት ክፍሎች በሁለት ክፍል ጠቅለል ያለ መልዕክት ይዘንላችሁ መጥተናል ተከታተሉን፡፡ መልካም ንባብ
ክፍል-1
ሰብአዊ መብት Human Right ከሚለዉ የእንግሊዘኛ ሃረግ የተወሰደ ሲሆን ሰብዓዊ ማለት ሰዉን ወይም የሰዉ ፍጡርን የሚያመለክት ሲሆን መብት ማለት ደግሞ ለሰዉ ልጅ የሚገባ የተፈቀደ፤ ትክክለኛና በህግ እዉቅና ያለዉን ነገር የሚመለከት ጽንሰ ሃሳብ ነዉ፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለዉ ሰብዓዊ መብት ከሌሎች ፍጡራን በተለየ ሰዉን ብቻ የሚመለከት መሆኑን ነዉ፡፡
የሰብዓዊ መብቶች በ4 የሚከፈሉ ሲሆን
1ኛ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች
2ኛ የኢኮኖሚ፤ የማህበራዊና የባህል መብቶች
3ኛ የአካባቢ ደህንነትና የልማት መብቶች
4ኛ ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸዉ የህ/ሰብ ክፍሎችን የሚመለከቱ መብቶች ናቸዉ
የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች
የሲቪል መብቶች ከሰዎች ህይወት፤ ነፃነት፤ ደህንነት ጋር የተያያዙ ሲሆኑ የፖለቲካ መብቶች ደግሞ የሰዎችን በራሳቸዉ ወይም በሚመለከታቸዉ ጉዳይ ላይ ራሳቸዉ ለመወሰን የሚያስችላቸዉ፤ በማህበረሰባቸዉ እና በአካባቢያቸዉ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ዉስጥ የመሳተፍ ነፃነትን በይገባናል ስሜት የሚጠይቁበትን ሁኔታ የሚመለከት ነዉ፡፡
የሰብአዊ መብቶችን አፈፃፀም ወይም እዉነትነትን መሰረት በማድረግ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ጊዜ የማይጠይቁ ከመቅፅበት መፈፀም ያለባቸዉ መብቶች እንደሆኑ ይገልፃሉ፡፡ ለዚህም እንደምክንያትነት መብቶችን ለማክበርና እዉን ለማድረግ ብዙ ሃብትና በጀት የማይጠይቅ መሆኑን ነዉ፡፡
የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች አሉታዊ መብቶች በሚል የሚታወቁ ሲሆን የሶስተኛ ወገኖችን ጣልቃ መግባት ሳይፈልጉ በራሳቸዉ ተፈፃሚ የሚሆኑ መብቶች ናቸዉ፡፡
የኢኮኖሚ፤ የማህበራዊ እና የባህል መብቶች
ማንኛዉም ግለሰብ ሰብአዊ ክብሩን በሚጠብቅ ደረጃ በማ/ሰቡ ዉስጥ ራሱን፤ ቤተሰቡን ሌሎችንም ጠቅሞ ከማ/ቡም ተጠቃሚ ሆኖ የመኖር መብቱን በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የሚያረጋግጡለት መብቶች ናቸዉ፡፡
የኢኮኖሚ መብቶች፡- የአንድ አገር ሀብትን የመጠቀም በኢኮኖሚያዊ ዉሳኔ አሰጣጥ ሂደት ዉስጥ የመካፈል እና ከሚገኙ ዉጤቶችም የተሻለ የኑሮ ደረጃ የመድረስ መብት ላይ ያተኩራሉ፡፡
..... ይቀጥላል
ህድአት ጌታቸዉ
07/03/2013 ዓ.ም
ክፍል 2
የሰብዓዊ መብት ክፍሎች የቀጠለ.....
የማህበራዊ መብቶች፡- የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች ለምሳሌ ት/ት፤ ጤናን የመጠቀም /የመገልገል/ እና በሰፊዉ የማ/ሰቡ ማህበራዊ ህይወት ዉስጥ የመሳተፍ መብትን የሚመለከቱ ናቸዉ፡፡
የባህል መብቶች፡- ደግሞ ግለሰቦች በማህበረሰባቸዉ ባህላዊ ህይወት ዉስጥ የመሳተፍ መብትን የሚመለከቱ ናቸዉ፡፡
እነዚህ መብቶች የአንዲት አገርና መንግስት አቅም በፈቀደ መጠን ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ/ እዉን የሚሆኑ መብቶች እንደሆኑ ይጠቅሳሉ፡፡ ለተግባራዊነታቸዉ አዎንታዊ ተሳትፎን ወይም ጣልቃ ገብነትን የሚሹ፤ በዋነኛነት በግለሰብ ደረጃ ሊሟሉ የማይችሉ መብቶች ናቸዉ፡፡
የአካባቢ ደህንነትና ልማት መብቶች
በቡድን የሚጠየቁና ለቡድን መብቶች መሟላት አስተዋጽኦ ያላቸዉ ናቸዉ፡፡
የእነዚህን መብቶች መከበር ከግምት ዉስጥ መግባት ያለባቸዉ ሁኔታዎች
1ኛ የልማት መብት መከበር ማለት የግለሰብ መብቶች መከበር ማለት ነዉ፡፡ የግለሰብ መብቶች መከበር ማለት ደግሞ የልማት መብትን ማክበር ነዉ፡፡
2ኛ የልማት መብት የጋራ መብት እንደሆነ ሁሉ ግለሰብም የዚሁ መብት ተጠቃሚ መሆኑ መብቱ እንደግለሰብ መብትም ሊታይ የሚችል ነዉ፡፡
3ኛ የልማት መብት የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሆነ ብቻ መታየት አይኖርበትም የልማት መብት ሰፊና ዉስብስብ ይዘት ያለዉ ሲሆን ግቡም በህ/ሰብ ዉስጥ የኢኮኖሚ፤ ማህበራዊ፤ ባህላዊ ፖለቲካዊ ወዘተ መብቶች በጋራ መረጋገጥ ነዉ፡፡
4ኛ የልማት ጽንሰ-ሃሳብ ተነፃፃሪ እና በማያቋርጥ ዕድገት ላይ ያለ ዕድገትን የሚገልጽ ነዉ፡፡
ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸዉ የህ/ሰብ ክፍሎችን የሚመለከቱ መብቶች
ዕድሜ፤ ከተለያየየ የአካል ጉዳቶች እና ከሌሎች ምክንያቶች አንፃር የተለየ እገዛ የሚያስፈልጋቸዉ ወገኖችን የሚመለከት ነዉ፡፡
ዓላማዉ በተለያዩ ምክንያቶች ለጉዳት ተጋላጭ የሆኑትን የህ/ሰብ ክፍሎች የመብት ጥሰት ጥበቃ ማድረግን ነዉ፡፡ በዚህ ምድብ /ፈርጅ/ ስር ከሚካተቱት መካከል የሴቶች፤ የህፃናት፤ የስደተኞች፤ የአረጋዊያን፤ የተፈናቃዮች፤ በእስርና በጥበቃ ስር ያሉ ሰዎች መብቶች ናቸዉ፡፡

ህድአት ጌታቸዉ
07/03/2013 ዓ.ም
...የቀጠለ
ከሌላ መሥሪያ ቤት የሚደረግ ዝውውርን በተመለከተ
አንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ለሥራው አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘውና ላኪና ተቀባይ መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም ሠራተኛው ሲስማሙ አንድን የመንግሥት ሠራተኛ እኩል በሆነ ደረጃና ደመወዝ ቢሮውን በማሳወቅ አዛውሮ ማሠራት ይችላል፡፡ እንዲሁም የሚመለከተው መንግሥት ሠራተኛ፣ የክልሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤት እና የፌዳራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ሲሰማሙ እንዲሁም በክልሉ ዝውውርን ለማጽደቅ ስልጣን የተሰጠው አካል ሲያጸድቀው አንድን የመንግሥት ሠራተኛ ከክልል ወይም ከፌደራል መንግስት መስሪያ ቤት ወደ አስተዳደሩ የመንግሥት መሥሪያ ቤት እኩል በሆነ ደረጃና ደመወዝ አዘዋውሮ ማሠራት ይቻላል፡፡ በተመሳሳይ ደረጃ ለመቀጠር አመልክቶ በውድድሩ የተመረጠ የመንግስት ሠራተኛን በተመለከተ በዝውውር ሥርዓት እንዲመደብ የሚደረግ ይሆናል፡፡
የትዳር አጋሮችን ለማገናኘት ሲባል አንድን የመንግስት ሠራተኛ በተመሳሳይ ደረጃና ደመወዝ፣ ተመሳሳይ ደረጃና ደመወዝ ካልተገኘ በሠራተኛው ስምምነት ዝቅ ባለ ደረጃ አዛውሮ ማሰራት የሚቻል ሲሆን በዚህ መሠረት የሚዛወር ሠራተኛ የአስተዳደሩ የመንግሥት ሠራተኞች ሕግ በሚያዘው መሠረት በያዘው የሥራ ደረጃና በአገልግልሎት ዘመኑ ምክንያት ያገኝ የነበረው ደመወዝና መብቶቹ እንደማይቀነሱበት አሠሪና ሠራተኛ አዋጁ በግልጽ አስቀምጦልናል፡፡

የትውስት ዝውውርን በተመለከተ
ትውስት የሚለው ቃል ሊመልሱ መውሰድን የሚያመለክት ሲሆን ከዚህ አዋጅ በተጨማሪ የፍትሐብሔር ሕጋችን ላይ ከቁጥር 2767 ጀምሮ የሰፈረ ቢሆንም ፍትሐብሔራችን ላይ ያለው የቃሉ አጠቃቀም አሠሪና ሠራተኛ አዋጁ ላይ ባለው መልኩ ባይሆንም ሊመልሱ መውሰድ የሚለው ትርጓሜ ግን ለሁለቱም ይሰራል፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጃጅን መሠረት አስፈሊጊ ሆኖ ሲገኝ ላኪው የመንግሥት መሥሪያ ቤትና ሠራተኛው ሲስማሙ አንድን የመንግሥት ሠራተኛ በሌላ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም የክልል ወይም የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም የመንግሥት የልማት ድርጅት ወይም መንግሥታዊ ወዳልሆኑ ድርጅቶች ከአንድ ዓመት ለማይበልጥ ጊዜ በትውስት ተዛውሮ እንዲሠራ ማድረግ ይቻላል፡፡በዚህ መልክ በትውስት የተዛረወረ ሠራተኛ ደመወዝና ማንኛውም ጥቅሙ በዝውውሩ ምክንያት ሳይጓደል በትውሰት አዛውሮ በሚያሰራው መስሪያ ቤት የሚፈፀም ሲሆን የሥራ አፈጻጸም ምዘና ውጤቱ በትውሰት አዛውሮ በሚያሰራው መስሪያ ቤት ተሞልቶ ለቀጣሪው መሥሪያ ቤት ይተላለፋል፡፡የዲሲፕሊን ጥፋት የፈጸመ እንደሆነ ደግሞ በትውስት ተቀባዩ መስሪያ ቤት ለቀጣሪ መሥሪያ ቤቱ ከዝርዝር ማስረጃ ጋር ያሳውቃል፣ ቀጣሪ መሥሪያ ቤቱም ጉዳዩን አጣርቶ እንደ አስፈሊጊነቱ ተገቢውን እርምጃ ይወስዳል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ አስተደደሩ በሀገር ወይም በሕዝብ ላይ የሚደርስ ድንገተኛ አደጋን ለመከላከል ወይም አደጋው ያደረሰውን ጉዳት ለማስተካከል ሲባል አንድን የመንግሥት ሠራተኛ በያዘው ደመወዝ ከአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ወደ ሌላ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም በክልሉ መንግሥት ጥያቄ መሠረት ወደ ክልል መንግሥት መሥሪያ ቤት ከአንድ ዓመት ለማይበልጥ ጊዜ በትውስት አዛውሮ ማሠራት ይችላል፡፡እንዲሁም ማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት አስፈሊጊ ሆኖ ሲያገኘው ከመንግሥት ልማት ድርጅት ወይም ከክልል መንግሥት ወይም ከፌደራል መሥሪያ ቤት ወይም መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት አንድን ሠራተኛ ከአንድ ዓመት ለማይበልጥ ጊዜ በትውስት አዛውሮ ማሠራት ይችላል፡፡
ሰናይ ማክሰኞ!( 8/3/2013 ዓ.ም)(ኦምኒኤል)
ይቀጥላል
...የቀጠለ
ከሥራ በመጣ ጉዳት ምክንያት የሚሰጥ ህክምና እና ፈቃድ
በሥራው ምክንያት ጉዳት ለደረሰበት የመንግሥት ሠራተኛ በሀገር ውስጥ ለሚሰጡ ለሚከተሉት የሕክምና አገልግሎቶች የሚያስፈልገው ወጪ በመሥሪያ ቤቱ ይሸፈናል፡-
ሀ)የጠቅላላና የልዩ ሕክምና እንዲሁም የቀዶ ሕክምና ወጪዎች
ለ)የሆስፒታልና የመድኃኒት ወጪዎች እና
ሐ)የማንኛውም አስፈሊጊ ሰው ሰራሽ ምትክ ወይም ተጨማሪ አካሎችና የአጥንት ጥገና ወጪዎች፡፡
ጉዳት ለደረሰበት የመንግሥት ሠራተኛ ከላይ በተዘረዘሩት መሠረት የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት በግል የህክምና ተቋም እንዲሰጠው የሚደረገው አገልግሎቱ በመንግሥት የሕክምና ተቋማት ሊሰጠው የማይችል ሲሆን በሥራ ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ የጉዳቱ መጠን ታይቶ በህክምና ማስረጃ በሚገለጸው መሰረት ከጉዳቱ ድኖ ወደ ሥራው እስከሚመለስ ወይም በጉዳቱ ምክንያት ለዘለቄታ መሥራት የማይችል መሆኑ በሕክምና ማስረጃ እስከሚረጋገጥ ድረስ የሕመም ፈቃድ ከሙለ ደመወዝ ጋር ይሰጠዋል፡፡
የመንግሥት ሠራተኛው ለዘለቄታው መሥራት ያለመቻሉ በሕክምና ማስረጃ ከተረጋገጠ ከስር የተዘረዘሩ የጉዳት ጡረታ አበል እና የጉዳት ዳረጎት ጥቅሞች ይጠበቁለታል፡-
ሀ)ከሥራ በመጣ የአካል ጉዳት ምክንያት ዘላቂ ሙለ ወይም ከፊል የመሥራት ችሎታውን ያጣ ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በመንግሥት ሠራተኞች የጡረታ ሕግ የተሰጡት መብቶችና ጥቅሞች ይጠበቁለታል
ለ)ከባድ የአካል ወይም ከባድ የመልክ መበላሸትን ያስከተለ ጉዳት የመሥራት ችሎታ ማጣትን ባያስከትልም ለጉዳት ካሣ አከፋፈልና ለሌሎች ጥቅማጥቅሞች አሰጣጥ ሲባል እንደ ዘላቂ ከፊል የአካል ጉዳት ይቆጠራል
ሐ)በመንግሥት ሠራተኞች የጡረታ ሕግ የተደነገገው የአካል ጉዳት መጠን አወሳሰን ከላይ ለተገለጸው አፈጻጸም ተግባራዊ ይሆናል፤
መ)የመንግሥት ሠራተኛ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት የሞተ እንደሆነ፣ በመንግሥት ሠራተኞች የጡረታ ሕግ መሠረት የጡረታ አበል ለተተኪዎቹ ይከፈላል
ከላይ በተዘረዘሩት መሠረት የሚደረግ ክፍያ ከግብር ነፃ የሚሆኑ እንዲሁም በዕዳ ምክንያት ሊያዝ ወይም ማቻቻያ ሊደረግ ወይም ባለመብቱ ሊያስተላልፈው ባይችልም ሠራተኛው ሕክምናውን በአግባቡ ባለመከታተሉ ወይም በሐኪም የተሰጠውን ትዕዛዝ ባለማክበሩ ሕክምናውን ያጓተተ እንደሆነ ከላይ የተጠቀሰው ሕክምና እና ፈቃድ የሚቋረጥበት ይሆናል፡፡

ሰናይ አርብ!(11/3/2013 ዓ.ም)(ኦምኒኤል)
ይቀጥላል
በቦሌ ክ/ከ/ዐ/ሕ/ጽ/ቤት የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት በ2012 ዓ.ም "ዳረጎት" በሚል ስያሜ የተዘጋጀውን የሕግ መጽሔት ከታች አስፍሬላችኋለሁኝ፤መልካም ንባብ!