የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
276 subscribers
366 photos
3 videos
137 files
97 links
ይህ የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት ቻናል ስለኢትዮጵያ ሕጎች)ማብራሪያ የሚሰጥበት፣ አዳዲስ ሕጎች የሚጋሩበት፣ ሕግ ነክ ዜናዎችና መረጃዎች የሚተላለፉበት፣ በዳይሬክቶሬቱ የተሰጡ የንቃተ-ሕግ ስልጠናዎች፣ የሕግ መልዕክቶች፣ በራሪ ጽሑፎች እና መሰል ሰነዶች የሚለቀቁበት ነው።
መልካም ቆይታ!
Download Telegram
pro.no.56.pdf
839.7 KB
…የቀጠለ
በራስ ፈቃድ የሥራ ውል ማቋረጥን በተመለከተ
የሥራ ውል በራስ ፈቃድ፣በሕመም ምክንያት፣በችሎታ ማነስ ምክንያት እንዲሁም ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ሊቋረጥ እንደሚችል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 56/2010 ዓ.ም ከአንቀጽ 83 እስከ አንቀጽ 86 ስር ባሉት ድንጋጌዎች አስቀምጧል፡፡ከተዘረዘሩት ድንጋጌዎች ውስጥ በራስ ፈቃድ የሥራ ውል ማቋረጥን በተመለከተ የሰፈረውን በመጥቀስ ሌሎቹን በተመለከተ ከአዋጁ ላይ እንድታነቡ አዋንጁንም ጭምር በማስቀመጥ በዚህ አዋጅ ዙሪያ በተከታታይ ያቀረብኩላችሁን ጽሑፍ እዚህ ላይ እቋጫለው፡፡
ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በማንኛውም ጊዜ የአንድ ወር ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ሥራውን በፈቃድ ሊለቅ የሚችል ሲሆን መስሪያ ቤቱ ሠራተኛውን በቀላሉ ሊተካው የሚችል ከሆነ የአንድ ወሩን ጊዜ ሳይጠብቅ ስንብቱን ሊፈቅድለት ይችላል፡፡ሆኖም የተመለከተውን የአንድ ወር የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ አገልግሎቱን ያቋረጠ የመንግሥት ሠራተኛ ግዴታውን ባለመወጣቱ ለሚደርሰው ጉዳት እንደተገቢነቱ በፍትሐ ብሔር እና በወንጀል ሕግ መሠረት ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ የመንግሥት ሠራተኛው ለሥራው እጅግ አስፈላጊና በቀላሉ ለመተካት የማይቻል ሆኖ ሲገኝ ወደ ፊት ከሚቀጠርበት መስሪያ ቤት ጋር በመስማማት የመልቀቂያውን ጥያቄ ሠራተኛው ካመለከተበት ቀን ጀምሮ ከሦስት ወር ለማይበልጥ ጊዜ ሊራዘም ይችላል፡፡
ሰናይ ረቡዕ! (13/3/2013 ዓ.ም)(ኦምኒኤል)
ጤና ይስጥልኝ
ባለፈው ጽሑፋችን የምርጫ ማስፈጸሚያ አደረጃጀቶችን የተመለከትን ሲሆን በዚህ ጽሑፍ ስለምርጫ አፈጻጸም የምናቀርብ ይሆናል፤
መልካም ንባብ!
ስለምርጫ አፈጻጸም በምንመለከት ጊዜ መራጭ እና ተመራጭ መኖራቸው የግድ የሚልና ለመራጭነትም ሆነ ለተመራጭነት ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆንና ለዚሁ ሲባል በተዘጋጀ ሰነድ ላይ የመመዝገብና በሕግ ክልከላ ያልተደረገበት መሆን የሚያስፈልግና ለመራጭነት ዕድሜ 18 ዓመት ለተመራጭነት ዕድሜ 21 ዓመት በምዝገባ ዕለት የሞላው መሆን ግድ ይላል፡፡
የምዝገባ ቦታ ለመራጮች በምርጫ ጣቢያ ሲሆን ለተመራጮች በምርጫ ክልል ሆኖ ቦርዱ በሚወስነው መሠረት የምዝገባ የጊዜ ስሌዳ የሚበጅለትና በተለይ ተመራጮች በዕጩነት ለመመዝገብ በሕግ ላይ የተቀመጠውን በተለይም የድጋፍ ፊርማንና የመሳሰሉትን መስፈርት በሟሟላት መሆን ይገባዋል፡፡ሆኖም አንድ ዕጩ ቢሞት ሊከናወን ስለሚገባው ሥነ-ሥርዓት ለዚሁ ሲባል ከወጣው አ/ቁጥር 1162/2011 መመልከት እንደሚቻል እናስታውሳለን፡፡
ለምርጫ የተመዘገቡ ዕጩዎች ምርጫው እስኪጠናቀቅ ድረሰ እጅ ከፍንጅ ካልተያዙ በስተቀር በወንጀል ተጠርጥረው እንደማይያዙ የተገለጸ ሲሆን ዕጩ ተወዳዳሪዎች ቦርዱ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ሕግ የጣለውን ግዴታ በማክበርና ቦርዱ በሚያወጣው የሥነ-ምግባር ደንብ መሠረት በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉትን መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻን ከተከለከለባቸው ቦታዎች ውጪ የሚያደርጉ ሲሆን ከዚህ በኋላ በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የድምፅ መስጠቱ ሥርዓት በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 54/1 መሠረት ነፃ፣ቀጥተኛ ና ትክክለኛ በሆነና በሚስጥር ድምፅ የሚሰጥና ቦርዱ በሚወስነው ቀን መሠረት አንድ ላይ በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የሚሰጥና የድምፅ ቆጠራ ድምፅ በሚሰጥበት ምርጫ ጣቢያ ተደርጎ ከምርጫው ቀን ቀጥሎ ባሉት 10(አስር) ቀናት ውስጥ ውጤቱ የሚገለጽ ሲሆን በድምፅ አሰጣጥ ወቅት ያሉትን ዝርዝር ጉዳዮችን በአዋጁ ላይ እንድትመለከቱ በመጋበዝ ጽሑፉን ቋጨን፡፡
መልካም ዕለት!
ደረጀ ማርቆስ
ሕዳር 2013 ዓ.ም
election board 1133.pdf
311 KB
ጤና ይስጥልኝ
ውድ አንባቢዎች የሰው ልጅ ሌላው ያለውን ይስማ ዘንድ ግድ የሚለው ሲሆን እኛም ለባለፉት ጊዜያት ስለኢትዮጵያ የምርጫ ሕግና ስለብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የተለያዩ ጽሑፎች ስናቀርብ ብንቆይም ከባልደረቦቻችንም ሆነ ጽሑፉን ሲመለከቱ ከቆዩ ወዳጆቻችን በየጽሑፉ ላይ ዝርዝሩን ይመልከቱ የሚለውንም ከግምት ውስጥ በማስገባት አዋጆቹም ሊያያዙ ይገባል የሚል ምክር በማቅረባቸው የዚህኑ ምክር አግባብነትና ተገቢነትን ከምስጋና ጋር ተቀብለን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 እና የኢትዮጵያ የምርጫ፣ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 በዚህ መልክታችንን ስናያይዝ ለወደፊቱ ከዚሁ ጋር ተያይዘው ስለሚወጡበት ደንብና መመሪያዎች በተገኘው አጋጣሚ እንደአገኘን ለአንባቢዎቻችን እንዲያውቁት የምናደርግ መሆኑን ስንገልጽ ለዛሬው አዋጆቹን እንድትመለከቱ እንደዚሁም ከምርጫ ጋር ተያይዞ ስለሚፈጸሙ ወንጀሎች ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ እንድትመለከቱ ከ”የ1996 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐፕሊክ የወንጀል ሕግ” ላይ የተመለከቱ ድንጋጌዎችን አያይዘን አቅርበናል፡-
የወንጀል ሕግ
አንቀጽ 466፡- ለምርጫ የሚደረግ ስብሰባንና የምርጫ ሂደትን ማወክና ማሰናከል
አንቀጽ 467፡- የምርጫ ድምጽ የመስጠትን ወይም የመመረጥን መብት መንካት
አንቀጽ 468፡- በምርጫ ላይ ሰለሚሰጥ መደለያ
አንቀጽ 469፡- የማይገባ አሠራር
አንቀጽ 470፡- በአመዘጋገብ ላይ የሚፈጸም ማጭበርበር
አንቀጽ471፡- በድምፅ አሰጣጥ ጊዜ የሚሰጥ የማጭበርበር ድርጊት
አንቀጽ 472፡- የወንጀሎች መደራረብ
አንቀጽ 473፡- የድምፅ አሰጣጥ ምስጢር አጠባበቅን መጣስ
አንቀጽ 474፡- የድምፅ መስጫ ወረቀቶችንና የምርጫ ሣጥኖችን መውሰድና ማጥፋት...
ከላይ የቀጠለ
አንቀጽ 475:- ተጨማሪ ቅጣቶች
ከሕዝባዊ መብት መታገድ)
አንቀጽ 476:- ቅጣትን የሚያከብዱ ምክንያቶች
መልካም ዕይታ!
ደረጀ ማርቆስ
ሕዳር 2013 ዓ.ም
የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛና ለመከላከል የወጡ የሕግ ማዕቀፎች እና የሚያስከትሉት ተጠያቂነት

የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ምንነት፡- ሕፃን የሚለዉ ቃል የማሕበራዊ ትርጉሙ እንደ የማሕበረሰቡ አኗኗርና ባህላዊ ሁኔታ የሚለያይ ሊሆን ይችላል። የተባብሩት መንግስታት
የሕጻናት መብቶች ስምምነት አንቀፅ 1 ላይ ሕጻን ማለት ማንኛዉም ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነ ሰው ማለት ነው በማለት ገልፆታል። በሀገራችንም ሕጻን ማለት ዕድሜው ከ18
ዓመት በታች የሆነ ማንኛውም ሰው መሆኑ በሰው የመነገድና ሰውን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1178/12
ዓንቀፅ 2(10) ስር ሰፍሮ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ሕጻን የሚለዉ ትርጉም 18 ዓመት ያልሞላው ለአካለ መጠን ያልደረሰ ሰው መሆኑ በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር ውስጥ ሕግ የተረጋገጠ ነው ማለት ይቻላል።

የሕጻናት ስራ ማለት ማንኛውም ሕፃን ሀገሪቱ ከደነገገችው ዝቅተኛ የስራ ቅጥር የዕድሜ ገደብ በታች ሆነው የሚሰሩት ለዕድሜያቸዉ የማይመጥን ስራ ማለት ነው። ሆኖም ግን
የሕጻናት ጉልበት ስራ ጉዳት በማያስከትልና ጤናማ በሆነ መልኩ ሊከናወን ይችላል። የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ግን የዚህ ተቃራኒ ሆኖ ማለትም በሕግ ከተፈቀደው ሁኔታ ውጭ
ወይም ለሕጻኑ አካል ወይም ዕድሜ በተፃረረ መልኩ ስራ እንዲሰራ ወይም አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ስለመሆኑ በአዋጅ/ቁ 1178/12 አንቀፅ 2(5) ላይ ሰፍሯል፡፡

የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ዓይነቶች፡- ምንም እንኳን ሕጻናት በብዙ ዓይነት ስራ ተሰማርተው ስለሚገኙ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ዓይነቶችን መለየት አስቸጋሪ ቢሆንም ዋና ዋናዎቹ
የሚከተሉት ናቸው።

(ሀ) የቤት ውስጥ ስራ፡- ይህ የስራ ዓይነት ሕጻናት በወላጆቻቸው ወይም በአሳዳጊዎቻቸው ቤት ሆነው የሚሰሩት ስራ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በክፍያ ከቤተሰባቸው ውጭ በቤት ሰራተኛነት የሚሰሩ ሕጻናትም በዚሁ ስር የሚካተቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ህጻናት ከእይታ የራቁና መረጃ የማይገኝባቸው በመሆናቸው ለብዙ ዓይነት ብዝበዛና ጥቃት የተጋለጡ ናቸው። ይህ ማለት ግን ሕጻናቱ አቅማቸው የሚችለውን ያክል ቤተሰቦቻቸውን መርዳታቸው ብዝበዛ ነው ማለት አይደለም፡፡

(ለ) የደመወዝ ስራ፡- ይህ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ዓይነት መደበኛ ወይም ኢ-መደበኛ፣ ህጋዊ ወይም ህገወጥ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያክል በኮንስትራክሽን ድርጅት፣ በማምረቻ
ድርጅት፣ በማእድን ስራ፣ በአግሮ ኢንደስትሪ እንዲሁም በወንጀል ስራ ሕጻናት የሚቀጠሩባቸው መስኮች ናቸው።

(ሐ) ከቤት ውጭ ያለ ያለክፍያ ስራ፡- ይህ የስራ ዓይነት በብዛት የተለመደው በግብርና ስራዎች ላይ ነው። በተለይ በታዳጊ ሀገሮች ሕጻናት በግብርና ስራ ላይ ቤተሰቦቻቸውን
ለመርዳት በለጋ እድሜያቸው ስራ ይጀምራሉ።

(መ) ባርነት ወይም የግዴታ ስራ፡- ሕጻናት ምንም በማያውቁት ሁኔታ በገንዘብ ለስራ ይሸጣሉ። አንዳንዴም ባለሀብቶች ከሰራተኞቻቸው የሕጻን ልጆቻቸውን ጉልበት ይገዛሉ።
በሌላ በኩል ሕጻናት የወላጆቻቸው ዕዳ መያዣ ይሆናሉ። ይኸውም የሕጻኑ ወላጆች ያለባቸውን ዕዳ መክፈል ሲያቅታቸው ሕጻን ልጃቸውን ለባለ መብቱ አሳልፈው ይሰጣሉ።

የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ መንስኤዎች፡- ብዙ ጊዜ ሕጻናትን ለጉልበት ብዝበዛ ተጋላጭ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች ድህነት በቀዳሚነት ተጠቃሽ ይደረጋል። ብዙ ደሃ ቤተሰቦች
ኑሯቸውን ለመደጎም ሲሉ ለስራ ያልደረሱ ሕጻናትን የተለያዩ ስራዎችን እንዲያከናዉኑና ለቤተሰቡ ተጨማሪ ገቢ እንዲያስገኙላቸዉ ይጥራሉ። ሆኖም ግን ድህነት ብቻውን ለሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ መንስኤ ሊሆን አይችልም።
ሕጻናትን ለጉልበት ብዝበዛ የሚያጋልጣቸው ሌላው ምክንያት ከባህላችንና ከልምዳችን ጋር የተያያዘ ነው። አብዛኛው ሰው ሕጻናት በለጋ ዕድሜያቸው የተለያዩ ዕውቀቶችና ክህሎቶች
እንዲኖራቸው በማሰብ በስራ ላይ እንዲሰማሩ ይደግፋሉ ይገፋፋሉም። ከድህነቱ በተጨማሪ አንድ ሕጻን አካል ጉዳተኛነቱ ለጉልበት ብዝበዛ ተጋላጭ መሆኑን ይበልጥ ያጠናክረዋል።
የትምህርት ዕድል ያለመኖርም ሌላው ገፊ ምክንያት ነው። የወላጆች ሞት፣ በቂ የገቢ ምንጭ አለመኖር፣ የወላጆች የትምህርት ደረጃ ማነስ፣ የቤተሰብ መፍረስ፣ ግጭትና የቤት
ውስጥ ጥቃቶች የመሳሰሉትም በመንስኤነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ የሚያስከትለው ጉዳት፡- የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ በህፃናቱ ላይ ከሚያሰከትለው ከፍተኛ የአካላዊ፣ ስነልቦናዊ፣ ማህበራዊና የመሳሰሉት ጉዳቶች ባለፈ
በህብረተሰብና በሀገር ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው። በሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ምክንያት በሕፃናቱ ላይ በቀጥታ ከሚደርሱ ጉዳቶች መካከል አንዱና ዋነኛው የጤና ጉዳት ነው። የብዝበዛ ሰለባ የሆኑ ህፃናት ከቀላል የአካል ጉዳት እስከ ሞት ለሚደርስ ጉዳት ይጋለጣሉ ወይም ለዕድሜ ልክ ለማይሽር አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ጉዳት ሊዳረጉ ይችላሉ።
በሕፃናቱ ላይ ከሚያስከትለው ተፅእኖ በተጨማሪ በማህበረሰቡም ላይ የሚኖረው ጉዳት ቀላል አይደለም። የአዘዋዋሪዎች መስፋፋት በማህበረሰቡ ውስጥ ህገወጥነትንና ወንጀል እንዲበራከት ዓይነተኛ ምክንያት ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ የብዝበዛ ሰለባ የሆኑት ሕፃናት
ራሳቸው ለአደንዛዥ ዕፆችና ለተለያዩ ሱሶች ስለሚጋለጡ ወደ ወንጀል ነክ ተግባራት እንዲገቡ ያደርጋል።

የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ የሀገር ኢኮኖሚ ላይም አሉታዊ ተፅእኖ ያስከትላል። ከድህነት ጋር በተያያዙና በልዩ ልዩ ምክንያቶች በሀገር ውስጥም ሆነ ወደ ውጭ በሚደረገው የህገወጥ የሕፃናት ዝውውር የወደፊት ሀገር ተረካቢ ሊሆን የሚችለውን በርካታ አምራችና ብቁ የሰው ኃይል ማጣትን ሊያስከትል ይችላል።

የህጻናት ጉልበት ብዝበዛን የሚመለከቱ የሕግ ማእቀፎች፡- በሀገራችን በአሁኑ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣውን የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ዓለም አቀፋዊም
ሆነ ሀገራዊ የሕግ ማእቀፎች መኖራቸው ችግሩን ለመቅረፍ የሚጠቀስ ምቹ ሁኔታ ነው። ሆኖም ግን ከሕግ ክፍተቱ ባሻገር ህግን የማስፈጸም እንቅስቃሴዎች በሚገባ የዳበሩ
ባለመሆናቸው ችግሩ ከህግ አንጻር ተገቢውን ትኩረት አግኝቷል ለማለት አያስችልም።

ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች፡- በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ካጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ የሕጻናት መብቶች ኮንቬንሽን፣ የአፍሪካ ሕጻናት መብቶችና ደህንነት
ቻርተር፣ የዓለም ስራ ድርጅት አነስተኛ የስራ ስምሪት ዕድሜ መወሰኛ ስምምነት ቁጥር 138/1973 እና የአስከፊ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ማስወገጃ ስምምነት ቁጥር 182/1999 የሚጠቀሱ ናቸው። በእነዚህ ስምምነቶች የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ላይ ክልከላ የሚያደርጉ አንቀጾች ተካተዋል።

ሀገር አቀፍ ህጎች፡- በኢትዮጵያ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ላይ ክልከላና ጥበቃ የሚያደርጉ ህጎችና ድንጋጌዎች አሉ። ከእነዚህም ዋና ዋናዎቹ በኢፌድሪ
ሕገመንግስት፣ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ፣ በኢፌድሪ የወንጀል ሕግና በአዋጅ ቁጥር 1178/12 ውስጥ የሚገኙ ናቸው። እነዚህ ሕጎች የሕጻናት መብቶችን የሚያስከብሩ፣
ዝቅተኛ የስራ ስምሪት ዕድሜን የሚወስኑ ወዘተ ድንጋጌዎችን የያዙ ሲሆን ድንጋጌዎቹ ተጥሰው ሲገኙ ደግሞ ከ7-15 ዓመት ሊደርስ በሚችል የእስራት ቅጣት ድርጊቱ በከባድ ሁኔታ ተፈፅሞ ከተገኘም እስከ 25 ዓመት ብሎም በዕድሜ ልክና በሞት ቅጣትም የሚያስቀጡ ሕጎች ናቸው፡፡ (አዋጅ ቁጥር 1178/12 ዓንቀፅ 3 እና 4ን ይመልከቱ)

ቸር ሰንብቱ
ፌናን
ህዳር 18/2013 ዓ.ም
ሕጉ ምን ይላል
ስለ ፍርድ አፈፃፀም-
፨ ፍርድ አፈፃፀም ማለት ፍ/ቤት የሰጠውን ፍርድ በእራሱ አማካኝነት ወደ ተግባር የሚለውጥበት ሥርዓት ነው።
፨ የፍርድ አፈጻጸም ስርአት ህጉን መሰረት በማድረግ የፍትሐ ብሔር ስነ-ስርዓት ህጉን መሰረታዊ ዓላማ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በአነስተኛ ወጪ፣ ጊዜና ጉልበት በተፋጠነና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲፈፀም በሚያስችል አግባብ ተግባራዊ መደረግ ይኖርበታል፡፡
፨ ስለ ፍርድ አፈፃፀም የተደነገጉት ድንጋጌዎች(የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 378-417) በመከተል ፍርድን በተግባር መተርጎም እንደመሆኑ መጠን የማስፈፀሚያ ሥርዓቱ በጥቅሉ የተጠቀሱትን የፍ/ብሄር ሥነ ሥርዓት ሕጉን መሰረታዊ ዓላማ ተከትሎ መፈጸም አለበት።
፨ የፍርድ ባለዕዳው(ውሳኔ የተወሰነበት ወገን) በፈቃዱ እንደፍርዱ ፈፅሞ ከተገኘ የአፈፃፀም ክርክር አስፈላጊ አይሆንም። በፈቃደኝነት ፈፅሞ ባልተገኘ ግዜ ግን የፍርድ ባለመብቱ(ውሳኔ ያሰጠው ሰው) በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 378(1) መሰረት ውሳኔውን ለሰጠው ፍ/ቤት ማመልከቻ በማቅረብ እንዲፈፅም ማስገደድ(ንብረቱን ማሸጥ፣ ከደመወዝ 1/3ኛ ማስቆረጥ) የመሳሰሉትን በፈፃሚው ፍ/ቤት ትዕዛዝ ማሰጠት አስፈላጊ ይሆናል።
Mr zed
ምንጭ
የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ ሕ
በይነመረብ
በ1996 ዓ.ም የወንጀል ህግ ስለህጋዊ መከላከል /አልሞት ባይ ተጋዳይነት/ የደነገገውን በስፋት እናያለን፡፡
ህጋዊ መከላከል /አልሞት ባይ ተጋዳይነት/ ምን እንደሆነና አንድ ሰው የፈፀመው ድርጊት አፈጻጸሙ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ከሆነ ቅጣትን የማያስከትል መሆኑ የተደነገገው በዚሁ ህግ ጠቅላላ ክፍል በቁጥር 78 ላይ ነወ፡፡ በዚህ አንቀጽ መሰረት አንድ ድርጊት በአልሞት ባይ ተጋዳይነት የተፈፀመ ነው፡፡ የሚባለው ምን ምን ሁኔታዎች ተሟልተው ስገኙ እንደሆነ ከዚህ ቀጥሎ በዝርዝር እንመለከታለን፡፡
3.1) አስቀድሞ የተሰነዘረ ወይም በርግጠኛ ሊደርስ የሚችል ህገወጥ ጥቃት መኖር
በወንጀል ህግ አንቀጽ 78 ላይ እንደተመለከተው አንድን ድርጊት ራስን ወይም ሌላውን ፣ የራን ወይም የሌላውን ሰው መብት ለመከላከል ስባል የተደረገ ነው ለማት በዚሁ መካከል በተደረገለት መብት ላይ አስቀድሞ የሰነዘረ ወይም በእርግጠኛ ሊደርስ የሚችል መሆኑን ማረጋገጥ የሚቻለው እንዴት ነው? ተከላካዩ ሊደርስብኝ ነው ብሎ ማመኑ በቂ ሊሆን ይችላል ወይ? ጥቃቱስ እስኪፈፀም መጠበቅ ያስፈልጋል ወይ? የሚሉት ናቸው፡፡
በብዙ ሀገሮች የወንጀል ህጎች እንደተደነገገው አንድ ሰው መብቱን ከህገወጥ ጥቃት የሚከላከለው ጥቃቱ በተግባር ሲፈጸምበት ብቻ አይደለም፡፡ ጥቃቱ ገና በተግባር ባይፈጸምበትም በእርግጠኛ ወዲያዉኑ ሊደርስ የሚችል መሆኑ በታመነ ጊዜ የመከላከል መብትን መጠቀም ይቻላል፡፡ የእኛም ህግ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ በወንጀል ህግ ቁጥር 78 ላይ ‹‹የራሥን ወይም የሌላውን ሰው መብት ህገወጥ ከሆነ ጥቃት ለማዳን›› የሚለው ሐረግ አጥቂው በማጥቃት ላይ ያለ መሆኑን የሚያመለክት ሲሆን‹‹በቅርብ ከሚደርስ ጥቃት›› የሚለው ሐረግ ደግሞ አጥቂው ጥቃቱን ለመፈጸም ወይም ለማድረስ ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ መነሳቱን የሚያመለክትና በነገሮች ልማዳዊ ሂደት (in the normal course of things) የዚያን አይነት ውሳኔ አድርጎ የተነሳ ሰው በእርግጥ ይፈፅመዋል ተብሎ የሚታመን መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ይህም ጥቃቱ በተግባር ከመፈጸሙ በፊትም ተከላካዩ መብቱን ለመከላከል የሚያስችል መሆኑን ያመለክታል፡፡
በህጉ መሰረት ጥቃቱ ተፈፅሞ ያለፈ ወይም ደግሞ ከመፈፀም ወይም ከመድረስ ገና ብዙ የራቀ መሆን የለበትም፡፡ ጥቃቱ ተፈፅሞ ወይም ደርሶ ካለፈ በኋላ ህጋዊ መከላከል መብት አይኖርም፡፡ ተጠቂዉ ጥቃቱ ተፈፅሞበጽ ካለፈ በኋላ የሚሰነዘረው የአጸፋ ጥቃት (counter-attack) የበቀል እርምጃ እንጂ ህጋዊ መከላከል ባለመሆኑ ድርጊቱ ህጋዊ መከላከል መሆን ቀርቶ ህገወጥ ይሆናል፡፡
አንድ ህገወጥ የሆነ ድርጊት ወይም ጥቃት ተፈፅሞ ያለፈው ወይም ያቆመው በዚህ ደቂቃና ሴኮንድ ላይ ነው ብሎ በትክክል መናገር ባይቻልም ከነገሩ ሁኔታ በመነሳት መገመት አያስቸግርም፡፡ ጥቃት አድራሹ ይፈፅም የነበረውን ህገወት ድርጊት አቁሞ ከጥቃቱ ቦታ ወይም ከተጠቂው ከራቀ ጥቃቱ ያለፈ መሆኑን በቀላሉ መገመት ይቻላል፡፡ በርግጥ ጥቃት የተፈፀመበት ወይም የደረሰበት ሰው በጥቃቱ ምክንያት የፍርሃ፣ የድንጋጤ፣ የደም ፍላት ወዘተ ስሜቱ ወዲያውኑ ሊበርድለት ስለማይችል ነገሩን የማመዛዘን ችሎታውን ለጊዜው ሊያጣ ይችል ይሆናል፡፡ በተለይ አጥቂዎቹ በርካታ በመሆን በአንድ ግለሰብ ላይ ጥቃትን በሚደርሱብት ጊዜ የተክላካዩ በጥቂቶቹ ላይ የወሰደው የመከላከል እርመጃ ጥቂቱን ለጊዜው ጋብ ሊደርገው ይችላል፡፡ ነገር ግን ከአጥቂዎቹ መካከል ቀሪዎቹ ጥቃቱን የሚቀጥሉ መስሎ ከታየው በነሱ ላይ የሚወስደው የመከላከል እርመጃ ጥቃቱ ከቆመና ሰሜቱ ከበረደልት በኋላ ያደረገው አያሰኘውም፡፡
በአንድ ወቅት ስለተፈጸመ ከዚህ ሁኔታ የቅርብ ግንኙነት ስላለው እንደ ጉዳዩ እንመልከት፡፡ አንድ ግለሰብ አምስት ሰዎች በመተባበር ጥቃት ሲያደርሱበት ከመካከላቸው አንዱን መትቶ ከገደለውና ስሜቱ ከበረደለት በኋላ ሌላወን ሆን ብሎ ተኩሶ አቁስሏል ትብሎ ተከሷል፡፡ ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰጠው ውሳኔ ‹‹…መልስ ሰጭ የማሰጠንቀቂያ ተኩስ አከታሎ ወደ ሰማይ ከተኮሰ በኋላ ድብደባው የሚቀጥል በመሆኑ ሟችን ተኩሶ ሲጥለው የግል ተበዳይ (ከሞች ግብረ አበሮች መካከል የሞች ወንድ የሆነው) ወደ ሟች ሊሄድ ሲል መመታቱ በመልስ ሰጪው ላይ አድኖ የነበረው ስሜት ካፈ በኋላ የተፈፀመ ነው ሊባል የማይችልና ተነጣጥሎ የማይታይ ነው›› በማለት በዐቃቤ ህግ አማካኝነት የቀረበው ይግባኝ ውድቅ አድርጐ መልስ ሰጭውን በነፃ አሰናብቷል፡፡
አንድ ህገወጥ የሆነ ጥቃት በእርገጠኛ ወዲያወኑ ሊደርስ የሚችል ነው የሚባለው ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው አጥቂው ድርጊቱን ለመፈፀም ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ሲነሳና በነገሮች ልማዳዊ ሂደት ያንን ቁርጥ ውሳኔ ያደረገ ሰው ድርጊቱን በእርግጥ የፈፅመዋል ተብሎ ሲታመን ነው፡፡ ከዚሀም በተጨማሪ እርመጃዎችን ሊወስድ ይችላል፡፡ ለዚህ ግልጽ ግንዛቤ እንዲኖረን አንድ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተወሰነ ጉዳይ እንመልከት፡፡ አንዲት ሴት የህግ ባሏን በመጥረቢያ ቆራርጣ ገድላለች ተብላ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ክስ ቀርቦባት እድሜ ልክ ፅኑ እስራት ይፈረድባትና ጉዳዩ በይግባኝ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡ ከፍርድ ቤቱ መዝገብ ለመረዳት እንደተቻለው ይግባኝ ባይና ሟች በባልና ሚስትነት ለዘጠኝ አመታ ያህል አብረው የኖሩ ሲሆን ሟች በየጊዜው ይግባኝ ባይን እየደበደበ ያሰቃያታል፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ሰክሮ በመምጣት ሲደበድባት እሳት አጥፍታ ጓዳ ትደበቃለች፡፡ ሟች ‹‹የት አባሽ ትገቢያለሽ›› በማለት ተከታትሎ መጥረቢያ አንስቶ ሊመታት ሲል ቀድማ መጥረቢያውን በመቀማት መትታ ገድላዋለች፡፡ በዚህ አድራጐቷ ተከሳ ቀርባ የከፍተኛው ፍርድ ቤት የእድሜ ልክ ፅኑ እስራት ፈርዶበታል፡፡ ጉዳዩን በይግባኝ ቀርቦለት የመረመረው ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰጠው ፍርድ ይግባኝ ባይ የሰጠችውን የእምነት ቃል ጥፋተኛ ከተባለችበት ከወንጀል ህግ አንቀጽ 539 ጋር በማገናዘብ እንደመረመር ነው አድራጐቱን የፈፀመችው ሟችን ለመግድል አስባና ቅደመ ዝግጀት አድርጋ ሳይሆን ሟች ከዚህ ቀደም በየጊዜው ያደርስባት ከነበረው ሰቃይ ሌላ በእለቱ ሰክሮ በመምጣቱ ሲጠጋት እንደለመደችው እንዳያያት እሳቱን አጥፈታ ብትደበቅም የትአባሽ ትገቢያለሽ ብሎ ከበሩ ላይ የእንጨት መፍለጫ መጥረቢያ በመያዝ ሊገድላት በፍለጋ ላይ እንዳለ መጥረቢያውን ከእጁ ነጥቃ መምታቷን ሲሆን በዚህ በግልፅ መገንዘብ የሚቻለው በወቅቱ (በእርግጠኛ) እንደሚገላት በእሶም በኩል ሕይወቷን ለማትረፍ ሟች እንዳያያት እሳት ማጥፋቷ ከዚያም ከጓዳ ገብታ መደበቋና ሟችም አድራጐቱን ሳይገታ እየገፋ መጥቶ ሊገላት የእንጨት መጥረቢያ ይዞ እሶን መፈለጉ ቀድማ በፍርሃትና በሽብር መጥረቢያውን በመንጠቅ መትታ ገድለዋለች፡፡ እሱም ቢቀድማ ኑሮ የእሱን ፅዋ እንደምትቀበል በወቅቱ ከደረሰው ሁኔታ ይህ ፍርድ ቤት ተገንዝቦል፡፡ ሟች መጥረቢያ ይዞ እየተሳደበ እና ይጋባኝ ባይ መብራት አጥፍታ ብትደበቅም ባለመታገስ መጥረቢያ ይዞ ሊገድላት ሲፈልግ ሳይገላት ቀድማ መምታቷ በህጋዊ መከላከል (አልሞት ባይ ተጋዳይነት) የፈፀመችው በመሆኑ አድራጐቷ በወንጀል ህግ አንቀፅ 78 የሚሸፈን ነው በማለት ይግባኝ ባይዋን በነፃ አሰናብቷታል፡፡ ከዚህ ውሳኔ መገንዘብ እንደሚቻለው ይግባኝ ባይዋ መከላከል ከማድረጐ አስቀድማ በሕይወቷ ላይ በእርግጠኛ ወዲያዉኑ ሊደርስ የሚችል ህገወጥ የሆነ ከባድ ጥቃት አንዣቦ እንደነበርና ጥቃቱንም ለማስወገድ መብራት በማትፋትና በጨለማ ጓዳ በመደበቅ የተቻላትን ሁሉ ጥረት አድርጋ ከጥቃቱ መዳ
ን የማትችል መሆኑን ስትረዳ አጥቂውን በሃይል በማስወገድ ተከላክላለች፡፡ በመሆኑም አድራጐቷ በወንጀል ህግ አንቀጽ 78 የተጠሱትን ሁኔታዎች የሚያሞላ ሆኖ በመገኘቱ በነፃ ተሰናብታለች፡፡
በህጋዊ መካከል መብት ለመጠቀም በእርግጠኛ ሊደርስ የሚችል ህገወጥ ጥቃት ወይም አደጋ መኖር አለበት ሲባ ወደፊት ገና ያደርሳል ተብሎ የሚገመተውን ጥቃት የሚያጠቃልል አይሆንም፡፡ ጥቃቱ ይደርሳል ተብሎ በታመነበትና መከላከል በተደረገበት ወቅት መከላከል ሰፊ ጊዜና ልዩነት መኖር የለበትም፡፡ ጥቃቱ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በእርግጥ የሚደርስ መሆኑ ቢታመንም አስቀድሞ የሚወስደው የመከላከል እርምጃ በአልት ባይ ተጋይነት የተደረገ ነው አይባልም፡፡ ለምሳሌ ከበደ አወቀን ለመግደል ይፈልጋል እንበል፡፡ ሀሳቡንና ውሳኔውንም ወደ ግቡ ለማድረስ መሣሪያ ገዝቶ ሊያስቀምጥ፣ አወቀ ወደ ቤቱ የሚገባና የሚወጣበትን ጊዜ ለማወቅም ወሬ ሊጠይቅና ሌሎችንም አስፈላጊው የሆኑ ዝግጅቶችን ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህን የከበደ ዝግጅት አወቀ ተረድቶታል፤ በዚህም ምክንያት ከበደ ወደፊት ሳይገለኝ አይቀርምና ሳይቀድመኝ ልቅደመው ብሎ አወቀ ከበደን መግደሉ ተረጋግጦል እንበል፡፡ አወቀ ከበደን የገደልኩት ሊያደርስብኝ የነበረውን ህገወጥ ጥቃት ለመከላከል ስል በአልሞት ባይ ተጋይነት ነው ብሎ ሊከራከር አይችልም፡፡ ምክንያቱም ጥቃቱ በእርግጠኛ ወዲያዉኑ ልደርስ የሚችል (imminent) አልነበረምና፡፡
በዚህ ምሳሌ መሰረት ከበደ ያለው ገና በመሰናዳት ተግባር ላይ ነው፡፡ አንድን ወንጀል ለመስራት የተደረጉ የመሰናዳት ተግባሮች እራሳቸውን የቻሉ ወንጀሎች ሆነው በሚገኙበት ጊዜ ለነዚሁ ወንጀሎች የተመደበው ቅጣት ከሚወሰን በስተቀር በመሰረቱ የመሰናዳ ተግባር ህገወጥ የሆነ የወንጀል ድርጊት ነው ተብሎ ቅጣት አያስከትልም ፡፡ ይህም የሆነው ዝግጅቱን ሲያደርግ የነበረው ሰው ሊፈፅም ያሰበውን ወንጀል በተለያዩ ምክንያቶች በገዛ ፈቃዱ እርግፍ አድርጐ ሊተወው ይችላልና ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ጥቃት ሊፈፀምበት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን በትክክል የደረሰበት ሰው ሳልቀደም ልቅደም በማት ራሱ የኃይል እርምጃ ከመውሰዱ በፊት አግባብ ላለው ህግ አስከባሪ (ባለስልጣን) በማሳወቅ የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወሰድ ላድረግ የሚሰችል ጊዜ ይኖረዋል ተብሎ ስለ ሚገመትና የታሰበውም የወንጀል ድርጊት ለመፈፀም የተቃረበ (imminent) ስላልሆነ በዚህ መሰል ጉዳይ ላይ የህጋዊ መከላከል /አልሞት ባይ ተጋዳይነት/ ሁኔታ አይኖርም፡፡
ተከላካዩ ይከላከል በነበረበት ጊዜ በእርግጠኛ ሊደርስ የሚችል ህገወጥ ጥቃት ተሰንዝሮበት ወይም ከባድ አደጋ ተደቅኖበት ነበር ወይ? የሚለው ጥያቄ የሚመለሰው ከተከላካዩ ግምት ብቻ በመነሳት አይደለም፡፡ ተከላካዩ በራሴ የአእምሮ ግምት ህገወጥ የሆነ ጥቃት ደርሶብኛል ወይም ሊደርስብኝ ነው ብሎ ማመኑ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ የእርሱ ግምት (እምነት) ትክክል ላይሆን ይችላል፡፡ ተፈፀመ የተባለው ደረጊትም (ጥቃት) ህገወጥ ላይሆን ይችላል፡፡ ተከላካዩ በዚህ አይነት ግምት ተነሳስቶ የሚፈፅመው ድርጊት በሌሎች ሀገሮች ህግ ግምታዊ የሆነ የመክላክል ተግባር (imaginary defence) የሚባለው ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ድርጊት በሀገራችን ህግ በሁኔታ መሳሳት (mistake of fact) በሚለው ፅንሰ ሃሳብ ይሸፈን እንደሆነ ነው እንጂ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት የተፈጸመ ድርጊት ነው ሊባል አይችልም፡፡ ስለዚህ በተከላካዩ ላይ ሊደርስ የነበተረው ጥቃት ሚዛናዊ አስተሳሰብ ባው ሰው አዕምሮ ግምት ሊከላከሉት የሚገባ ነበር የሚያሰኝ ሆኖ መገኘትና እንዲሁም እንደነገሩ ሁኔታ አግባብ ባለው ማስረጃ መረጋገት ይኖርበታል፡፡
በመሠረቱ መብቱ ላይ ጥቃት የተሰነዘረበት ሰው መብቱን ለማሰጠበቅ ሲል በኃይል እስከመጠቀም ሊደርስ በሚችል መንገድ መከላከል ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ አስፈላጊ ባልነበረበት ሁኔታ በኃይል መጠቀም ተጠያቂነትን ያስከትላል ፡፡ አልፎ አልፎ እንደሚያጋጥመው ግለሰቦች የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ግዴታ ሳይኖር ወንጀል እየፈጸሙ በአድራጎታቸው ተከሰው የሚቀሩቡበት ጊዜ በመከላከል ያደረግነው ስለሆን ልንጠየቅ አይገባም በማለት ይከራከራሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ክርክር የሚነሳው አንድም የህጉን መንፈስ ጠንቅቆ ካለማወቅ ሲሆን በአብዛኛው ግን ተከሳሾች የተከሰሱበትን ወንጀል ለማስተባበል በማይችሉበት ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ሲያወቁ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠውን የጥፋተኛነት ውሳኔ አምኖ ከመቀበል ይልቅ አጠራጣሪና ሊታመንባቸው የማይችሉ ማረጃዎችን በማዘጋጀት ድርጊቱን የፈፀምነው በመከላከል ነው የሚለውን መስመር ይዘው ለመከራከር ስለሚመርጡ ነው፡፡ የተፈጸመው ድርጊት በመከላከል የተደረገ ነው ተብሎ እንዲታመንበት ከተፈለገ አድራጊው በኃይል እንዲከላከል ፍጹም አስፈላጊ ከሆነበት ሁኔታ ላይ ያደረሰው መሆኑ መረጋገጥ አለበት፡፡ አድራጊው ወንጀሉን መፈፀሙን አምኖ በመከላከል ያደረገው መሆኑን ለማስረዳት የሚያቀርባቸው የመከላከያ ማስረጃዎች ትክክለኛና ሊታመንባቸው የሚችሉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ባጠቃላይ ግን አንድ ተከሳሽ የፈጸመው የወንጀል ድርጊት ፍጹም አስፈላጊ በሆነ መከላከል የተደረገ መሆኑ እስካልተረጋገጠና የሚቀርበው ማስረጃ አስቀድሞ ህገወጥ ጥቃት መፈጸሙን ወይም ሊፈጸም መቃረቡን የሚያሳይና የሚያሳም እስካልሆነ ድረስ ድርጊቱን ፈጸምኩት በመከላከል ነው በማለቱ ብቻ ከወንጀሉ ነፃ አያደርገውም፡፡
ቀደም ሲል በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ህጋዊ መብትን ከጥቃት ለመከላል የሚቻለው ለመከላከል በተደረገለት መብት ላይ አስቀድሞ የተሰነዘረ ወይም በእርግጠኛ ሊደርስ የሚችል ጥቃት ሲኖር ነው ብለናል፡፡ እየደረሰ ያለው ወይም ለመድረስ የተቃረበው ጥቃት ህገወጥ መሆኑም ወሳኝነት አለው፡፡ በመፈጸም ላይ ያለ አንድ ድርጊት በመቃወም የመከላከል ህጋዊ መበትን መጠቀም የማይቻለው ድርጊቱ ህጋዊ ማለትም በህግ የተፈቀደ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በህግ የተፈቀደ ድርጊት (lawful act) ማለት እንዲደረግ በህግ የታዘዘን ወይም የተፈቀደን ድርጊት መፈጸም በአድራጊው ላይ በወንጀል ቅጣትን፣ በፍትሐብሔር ደግሞ ኃላፊነትን አያስከትልም፡፡ (የወንጀል ህግ አንቀፅ 68 እና የፍታብሔር ህገ አንቀፅ 2076(2) እና 2039(ለ)) ፡፡
ነገር ግን ህገወጥ የሆነ እስራትና ወይም የቤት ብርበራ የተፈረመበት ሰው ድርጊቱን መቃወም አይችልም ማለት አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በህግ ከተደነገገው በስተቀር በማነቸውም ሁኔታ እንደማይያዝና የመኖሪያ ቤቱም እንደማይፈተሽ የኢፌዲሪ ህገ-መንግስት ዋስትና ይሰጣል፡፡ አንድ ሰው በፍርድ ቤትም ሆነ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊያዝና በቁጥጥር ስር ሊውል እንዲሁም የመኖሪያ ቤቱ ሊፈተሽ የሚችልባቸው ሁኔታዎች በህግ በግልጽ የተደነገጉ ናቸው፡፡ ማንኛውም ህግ አስከባሪ አካል ስርዓት ባለው መንገድ የሚያደርገው ወንጀልን የመከላከልና ህግን የማስከበር ተግባር እጅግ የሚደገፍና የሚበረታ ቢሆንም ህግ ከሚደነግገው ውጭ ወይም ከህግ ወሰን አልፎ የሚፈጸም የእስራትና የብርበራ እርምጃ ህገወጥ ነው፡፡ በመሆኑም ህግና ስርዓት በሰፈነበት አገር ውስጥ የመዘዋወር ነፃነቱን ያላግባብ የተገፈፈ የመኖሪያ ቤቱም ህገወጥ በሆነ መንገድ የተደፈረበት ሰው ድርጊቱን ለመቃወምና ለመከላል ሙሉ መብት ያለው ሲሆን ድርጊቱን የፈጸመው ባለስልጣን የወንጀል ሀላፊነት ይኖርበታል፡፡
mr zed
ምንጭ
የወንጀል ሕግ
የተለያዩ ውሳኔ ያገኙ የወንጀል ፋይሎች
የወንጀል ህግ
በይነ መረብ
በፖሊስ መያዝ እና ማረፊያ ቤት መወሰድ ጋር በተያያዘ

ፖሊስ ካስቆምዎ

ፖሊሱን ማናገር አይጠበቅቦትም፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ያለመናገር ወይም ዝም የማለት መብት አለዎት፡፡ ያለመናገር ወይም ዝም የማለት መብት ማለት በተጠረጠሩበት ወንጀል ምንም ዓይነት መግለጫ ያለመስጠት መብት ማለት ሲሆን ስምና አድራሻዎትን ወይም ስለማንነትዎ መናገር ግን ግዴታዎ መሆኑን ያስታውሱ፡፡

ፖሊስን ሁልጊዜ የሚታሰሩ እንደሆነ የመጠየቅ መብት አለዎት፡፡ ፖሊስ የማያስረዎት እንደሆነ ከነገሮዎት ሁልጊዜም ቢሆን ፖሊስን ትተውት ሊሄዱ ይችላሉ፡፡

ለመፈተሽ ፈቃደኛ አለመሆኖትን ሁልጊዜም ቢሆን ለፖሊስ መግለጽ ይኖርቦዎታል፡፡ ከዚህ የዘለለ ፖሊስ በሚያደርገው ፍተሻ አካላዊ ትግል ማድረግ ለበለጠ ወንጀል ኃላፊነት ስለሚያጋልጥዎ አካላዊ ትግል ከፖሊስ ባልደረባ ጋር አያድርጉ፡፡

ከፖሊስ ጋር በሚያደርጉት ንግግር ሁልጊዜ በአካባቢዎ ያሉ ምስክር ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ማስታወስ አለብዎት፡፡

ሁልጊዜ ያለመናገር ወይም ዝም የማለት መብት አልዎት፡፡ ይህንን መብትዎን ለመጠቀም ‹‹ያለመናገር ወይም ዝም የማለት መብት አለኝ ስለዚህ ጠበቃ ማናገር እፈልጋለሁ›› ማለት ይችላሉ፡፡

አብዛኛውን ጊዜ በማረፊያ ቤት ሊቆዩ ስለሚችሉ፡-
በ48 ሰዓት ጊዜ ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት እንዳልዎ ይወቁ፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በማረፊያ ቤት ሊቆዩ የሚችሉት ለ48 ሰዓት ብቻ ነው፡፡

ፖሊስ አንዳንድ ጊዜ በተፈለጉ ጊዜ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ዋስትና በማቅረብ ሊለቅዎ ስለሚችል በዋስትና ከማረፊያ ቤት መውጣት ይችሉ እንደሆን የመጠየቅ መብት አልዎት፡፡ በዋስትና ከወጡ ፍርድ ቤት በፈለገዎ ሰዓት የመቅረብ ኃላፊነት እንዳለብዎት አይዘንጉ፡፡

በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ወይም ከታሠሩ

ልብ ይበሉ፡- ፍርድ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀርቡ ጠበቃ የሚያስፈልገዎት ከሆነ ጠበቃ መቅጠር እንደሚፈልጉ ለፍርድ ቤቱ ማስታወቅ ይችላሉ፡፡ በራስዎ ጠበቃ ማቆም የማይችሉ ነገር ግን ጠበቃ ያስፈልገኛል ያሉ እንደሆነ ይህንኑ ለፍርድ ቤቱ ያስታውቁ፡፡ በተለይ ቋንቋውን በማያውቁት ክልል ባለፍርድ ቤት የሚዳኙ ከሆነ ይህ መብት እንዳልዎ ይወቁ፡፡

እንደገና ልብ ይበሉ፡- በአንድ የወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው ፖሊስ ጣቢያ ቀረቡ ማለት ወይም በአንድ ወንጀል ተከሰው ፍርድ ቤት ቀረቡ ማለት ወንጀለኛ ነዎት ማለት አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፖሊሶችና ዓቃቤ ሕጎች በተጋነነ የወንጀል አንቀጽ ወይም ከሚገባው በላይ ክስ ሊመሠርቱ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም በተጠረጠሩበት ወይም በተከሰሱበት ወንጀል ፍርድ ቤት ቀርበው ጥፋተኛ እስከሚባሉ ድረስ መረበሽ አይገባም፡፡


ቸር ሰንብቱ
ፌናን
ታህሳስ 5/2013 ዓ.ም
ልዩ ውክልና
ምንነት እና አስፈላጊነት
የዚህ የውክልና ሥልጣን ወሰን በአብዛኛው ለአጭር እና ነጠላ ለሆኑ ጉዳዮች የሚሰጥ ነው፡፡ እንደራሴው የወካዩን ንብረት ወይም ሥራ የሚያስተዳድር ከሆነ በተሰጠው ጠቅላላ ሥልጣን ሳይገደብ እንዲሁም ቀድሞ ምንም የሥራ ግንኙነት ከወካይ ጋር ያልነበረው ሌላ ሰው አንድን ሥራ እንዲሠራ በወካዩ ሊሾም ይችላል፡፡ የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 2205(2)ልዩ የውክልና ሥልጣን ካልተሰጠ በስተቀር እንደራሴው ስለ ወካዩ ሲል የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን መሸጥ ወይም አስይዞ መበደር፣ ካፒታሎችን በአንድ ማህበር ዘንድ ማስገባት፣ የለውጥ ግዴታን ውል መፈረም፣ መታረቅ፣ ለመታረቅ ውል መግባት፣ ስጦታ ማድረግ የማይችል ስለመሆኑ በግልጽ ይደነግጋል፡፡ የዚህ የውክልና ሥልጣን በሕግ መታቀፍ አስፈላጊነት የወካዩን ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር ወካዩ በማያሻማ መልኩ ንብረቱን መሸጥ ወይም መግዛቱን እንደፈቀደ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በጠቅላላ ውክልና የወካዩን ሥራ የሚያስተዳድረው ሰው አልያ ሥልጣኑ ያልተፈቀደለት ሌላ ማንኛውም ሰው የወካዩ የሆነውን ሥራ በተመለከተ በሚያከናውኑት ተግባር ወይም በሚገቡት ውል በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ቢያደርሱ ጉዳት የደረሰበት አካል ከወካዩ ኪሳራ ሊጠይቅ የማይችሉ በማድረግ የሚጫወተው ሚና ጉልህ ነው፡፡ አዎት ሀይለዝጊ እና አዲሱ ዳምጤ ‘’Ethiopian Law of agency’’ በሚል ርዕስ ባዘጋጁት የመማሪያ ጽሑፍ ’it requires a special authorization for an agent to mortgage a real state (immovable ). Because mortgege may ultimatliy results in desposition of the propertiy.’ ሲሉ የልዩ ውክልናን አስፈላጊነት ያሰምሩበታል፡፡ ማንኛውም ሰው ከፍቃዱ ውጪ ንብረቱን ማጣት አይገባውም፡፡ ለምሳሌ የመኖሪያ ቤቱን ወይም መኪናውን ለባንክ አስይዞ ብር የተበደረ ሰው እዳውን ከፍሎ ካልጨረሰ እና የመክፈያ ጊዜ ገደቡ ካለፈ ባንኩ በመያዣነት የያዘውን ንብረት በሀራጅ ሽጦ ገንዘቡን የማስመለስ ሕጋዊ መብት አለው፡፡ በመሆኑም ተበዳሪው ንብረቱን የሚያጣ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን የንብረት ባለቤትነት ማጣት ወኪሉ በሆነው ሰው ሥራ ሲደርስበት እና ውክልናው ወካዩ የሠራውን ሥራ እንዲሠራ የማይፈቅድ ሲሆን ንብረቱን ልያጣ እንደሚችል ቢያውቅም ግዴታውን እንዲገባለት ፈቅዶለት ወይም ሥልጣን ሰጥቶት ካልሆነ በቀር ተወካዩ በራሱ ፍቃድ ለሠራው ሥራ ንብረቱን የሚያጣበት ሕጋዊም ሆነ ሞራላዊ ምክንያት አይኖርም፡፡ ከላይ ባየነው ምሳሌ ወካዩ እንደራሴው ቤቱን አስይዞ ብር እነዲበደርለት ሥልጣን ሰጥቶት ከሆነ እና እንደራሴው ብሩን ተበድሮ መክፈል ባይቻል ባለ ገንዘቡ ክፍያውን በተመለከተ የሚጠይቀው ሸዋሚውን ነው፡፡ ምከንያቱም ተወካዩ ውሉን ይፈርም እንጂ ተጠቃሚው ወካዩ ነውና፡፡ ውሉም በወካዩ እና በሦስተኛ ወገን መካከል እነደተደረገ የሚቆጠር ይሆናል፡፡
/////
መሰል የውክልና ሥልጣን (apparent authority)
/////
ማንኛውም እንደራሴ በግልጽም ሆነ በዝምታ ከተሰጠው የውክልና ሥልጣን ውጪ ወጥቶ የሠራ እንደሆነ ሊከተሉ የሚችሉ ውጤቶችን ከላይ ባሉት ማብራሪያዎች ተመልክተናል፡፡ ይሁንና እንደራሴው ባደረበት ቅን የሆነ ልቦና ወይም መሳሳት ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ ወጥቶ ሥራዎችን ሊሠራ ይችላል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን እንደራሴው ለሦስተኛ ወገኖች ሷሚውን ወክሎ መሥራት ሥልጣን ያለው ስለመሆኑ በመግለጹ እና እነሱም ግለሰቡ ይኀው ሥልጣን ያለው ስለመሆኑ ግምት ወስደው ከዚሁ ሰው ጋር ግዴታ የገቡ እንደሆነ እንደራሴው መሰል የውክልና ሥልጣን እንዳለው ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ይሁንና ሦስተኛው ወገን ከእንደራሴው ጋር የገባሁት ውል ወካዩን ሊያስገድድ ይገባል በሚል መብቱን ለመጠየቅ የሚችለው ይህንኑ የእንደራሴውን ተግባር ሊያጸድቅለት ሲችል ነው፡፡
በአብዛኛው የዚህ ዓይነቱ ግንኙነት የሚፈጠረው እንደራሴው ከወካዩ ጋር ቀድሞ ባለው ግንኙነት ወይም ከራሱ ከሷሚው አንደበት ከሚወጣ ንግግርም ነው፡፡ ለምሳሌ ሥራን በማስተዳደር የውክልና ሥልጣኑን እየተወጣ ያለው ሰው የሷሚውን የሚንቀሳቀሱም ሆነ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን የመሸጥ ሥልጣን ሳይኖረው ነገር ግን የሥራው ባለቤት ገዢ ለሆነው ሰው የመኪናውን ሽያጭ በተመለከተ እንደራሴውን እንዲያናግር እና ከተስማሙ ሽያጭ እንዲፈጽለት ቢነግረው እና ገዢም ከእንደራሴው ጋር ውል ቢገባ እንደራሴው መኪናውን ለሦስተኛ ወገን የሸጠበት ሥልጣን መሰል የውክልና ሥልጣን (apparent authority) የሚባል ነው
ከላይ በምሳሌነት ካነሳነው በተለየ መልኩ በሚወሰድ ግምት እንደራሴው ስለ ወካዩ ግዴታ በመግባት ለሠራው ሥራ ሷሚው ካላጸደቀ በቀር ውሉ ፈራሽ ይሆናል፡፡ ሦስተኛ ወገንም ከውሉ ጋር በተገናኘ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች እንደራሴው በግሉ የሚጠየቅ ይሆናል፡፡ ይሁንና ያጸደቀው ከሆነ ውሉ እንደራሴው በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የሠራው ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በዚህ ምክንያትም ሷሚው ስለ እንደራሴው ሥራ ሀላፊ ይሆናል፡፡
በሌላ በኩል ወካዩ እንደራሴው ከሥልጣኑ ወጥቶ ለሠራው ሥራ የማያጸድቅ ከሆነ እና ነገር ግን ሥራው የተሠራው ሙሉ በሆነ ቅን ልቦና ከሆነ ውሉ ፈራሽ በመሆኑ በሦስተኛ ወገን ላይ ለሚደርስ ኪሳራ እንደራሴው ሳይሆን ሽዋሚው ኪሳራ የመክፈል ግዴታ ይኖርበታል፡፡
/////
ማጽደቅ (ratification)
/////
እንደራሴው ከተሰጠው የውክልን ሥልጣን ውጪ በመውጣት የሠራው ሥራ የወካዩን መብት ወይም ጥቅም ለማስጠበቅ ወይም ትርፋማ ያደርገዋል ብሎ በማሰብ ቅን በሆነ ልቦና የፈጸመው እንደሆነ እንዲሁም ከሥራው አጠቃላይ ባሕርይ አንጻር የተቀበለው ሥልጣን በበለጠ መስፋት ወይም ቀድሞውኑ ሥልጣኑ ሲሰጠው ግዴታውን በሚገባ ይወጣ ዘንድ ሥልጣኑ ሳይኖረው የሠራው ሥራም ሊካተት እና በሥልጣኑ ስር ሊወድቅ የሚገባ የነበረ መሆኑ የህሊና ግምት ሊወሰድበት የሚችል ከሆነ ወካዩ ዕንደራሴው ከሥልጣኑ ወጥቶ የሠራውን ሥራ ያጸድቅለታል፡፡ ማጽደቅ ማለት አንድን ቀድሞ የተሠራን ሥራ፣ የተጻፈን ጽሑፍ፣ የረቀቀን ሕግ ወይም ዕቅድ እና ሪፖርትን ገምግሞ እውቅና መስጠት ማለት ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረት በሆነው ጉዳይም ወካዩ ከሥልጣን ውጪ ለተሠራው ሥራ እውቅና መስጠት እና ግንኙነቱ የሚፈጥረውን ውጤት የሚቀበለው እና የሚገዛበት መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ከገለጸ አጽድቋል ለማለት እንችላለን፡፡ በሀገረ አሜሪካ ስለ ማጽደቅ የተሰጠው ትርጉም ‘ratifiction is the affirmance by a person of a prior act which didn’t bind him but which was done or professedly done on his account where by the act, as to some or all persons,is given effect as if originally authorized by him’
ወደ አማርኛ ስንተረጉመው ማጽደቅ ማለት አንድ ሰው በራሱ ስም የተደረጉ ወይም ሊደረጉ ቃል የተገቡ ነገር ግን ይህን ሰው ሊያሰገድዱ የማይችሉ የነበሩ ድርጊቶች በዚህ ሰው ተቀባይነት ካገኙ በኋላ ድርጊቶች ከስረ መሰረታቸው በዚሁ ሰው እንደተደረጉ የቆጠራሉ የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊታወቅ የሚገባው ነገር የወካይን ማጽደቅ ተከትሎ የሚከተለውን ውጤት ነው፡፡ ከላይ በቀረበው ጽሑፍ እንደሚያመለክተው ወካይ ተወካዩ ለሚሠራው ማንኛውም ሥራ ሊጠየቅ የሚችለው በስልጠን ውስጥ የተከለለን ሥራ በተመለከተ ነው፡፡ ይህ መር
ህ ነው፡፡ ነገር ግን ወካዩ ማጽደቅ ካደረገ በተወካዩ እና ሦስተኛ ወገን መካከል የተደረገው የውል ስምምነት በወካይ እና ሦስተኛ ወገን መካከል እንደተደረገ ይቆጠራል፡፡ ውሉን በተመለከተ እንደራሴው የገባቸው ግዴታዎች በሙሉ የወካዩ ይሆናል፡፡
በሌላ በኩል እንደራሴው ወካዩ የሰጠውን ሥልጣን እንዲያሰፋለት ወካዩን የመጠየቅ ምቹ ሁኔታ ውስጥ እያለ በቸልተኛነት ሳይጠይቅ ሥልጣኑ ሳይሰፋለት በራሱ ፍቃድ ማንኛውንም ሥራ ከሠራ ወይም ግዴታ ከገባ ወይም በዚሁ አግባብ ሥራውን አከናውኖ ለወካዩ ሳያሳውቀው የቀረ እንደሆነ ወካዩ ውሉን እንዲያጸድቅለት የመጠየቅ መብት የሌለው መሆኑን የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 2207(3) ይደነግጋል።
ምንጭ ከ ኢንተርኔት
የፍትሐብሔር ሕግ
Mr zed
የኤግዚቢቶች አመዘጋገብና አቀማመጥ (የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 97 እና 124 (2))

በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 97 መሠረት ኤግዚቢት ወይም ከወንጀል አፈፃፀም ጋር በተያያዘ ወንጀል የተፈጸመበት ወይም ወንጀል ለመፈጸም በመሣሪያነት የዋሉ ቁሶች (ነገሮች) እንዴት ሊቀመጡና በማስረጃነት ሊያገለግሉ እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡

በዚሁ መሠረት ኤግዚቢቶች ላይ የፍርድ ቤት መዝገብ ሹም ቁጥርና ምልክት አድርጎባቸው በተጠበቀ ስፍራ ሊያስቀምጣቸው እንደሚገባና ከተቀመጡበት ስፍራም ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደማይወጡ ተመልክቷል፡፡ ሆኖም በተግባር ፍርድ ቤቶች በወንጀል ጉዳዮች በኤግዚቢትነት የሚያዙ ንብረቶችን ተቀብለው አይመዘግቡም በተጠበቀ ስፍራም አያስቀምጡም፡፡

ፍርድ ቤቶች በዚህ ረገድ ኤግዚቢቶችን የሚመዘግብና በተጠበቀ ስፍራ ሊያስቀምጥ የሚችል አሠራር፣ የመዝገብ ቤት ሹም እና ኤግዚቢቶችን ለማስቀመጫነት የሚያገለግል የሚታወቅ የተጠበቀ ስፍራ የሌላቸው በመሆኑ ኤግዚቶችን የመመዝገብ እና የማስቀመጥ ኃላፊነት በፖሊስ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ፖሊስም በፌዴራል ደረጃ ወንጀል ምርመራን ከማጣራት ጋር በተያያዘ ኤግዚቢቶችን የመመዝገብና የማስቀመጥ ተግባራትን በወንጀል መርማሪዎችና ኤግዚቢቶችን ለማስቀመጥና ለመንከባከብ በተመደቡ የፖሊስ አባላት በኩል የመመዝገብና የማስቀመጥ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 124 (2) መሠረት ነገሩ በሚሠማበት ቀን ዐቃቤ ሕግና ተከሳሽ ኤግዚቢትን ጨምሮ ያሏቸውን ማስረጃዎች በሙሉ ፍርድ ቤት የማቅረብ ግዴታ እንዳለባቸው ተመልክቷል፡፡

በሥነ ሥርዓት ሕጉ መሠረት ኤግዚቢቶች ጉዳዩን በሚያየው ፍርድ ቤት ተመዝግበው በተጠበቀ ስፍራ ተቀምጠው ቢሆን ኖሮ ኤግዚቢት ባለባቸው በሁሉም ጉዳዮች ላይ ዐቃቤ ሕግ በሕጉ በተጣለበት ግዴታ መሠረት ጉዳዩ በሚታይበት ዕለት ኤግዚቢቶችን ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ማድረግ ይችል ነበር፡፡
ሆኖም በተግባር ዐቃቤ ሕግ ኤግዚቢት ያለባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ ኤግዚቢቱ ፍርድ ቤት ይቅረብ ብሎ ፍርድ ቤቱ ካላዘዘ በስተቀር የሚያቀርብበት ሁኔታ የለም፡፡ በመሆኑም የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 97 እና 124 (2) በሕጉ በሚያዝዘው መሠረት እየተፈፀሙ ባለመሆናቸው ይህ ቢታሰብበት ለወንጀል ፍትሕ አስተዳደሩ የተሻለ ጥቅም ይኖረዋል፡፡   

ቸር ሰንብቱ
ፌናን
ታህሳስ 09/2013 ዓ.ም