የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
276 subscribers
366 photos
3 videos
137 files
97 links
ይህ የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት ቻናል ስለኢትዮጵያ ሕጎች)ማብራሪያ የሚሰጥበት፣ አዳዲስ ሕጎች የሚጋሩበት፣ ሕግ ነክ ዜናዎችና መረጃዎች የሚተላለፉበት፣ በዳይሬክቶሬቱ የተሰጡ የንቃተ-ሕግ ስልጠናዎች፣ የሕግ መልዕክቶች፣ በራሪ ጽሑፎች እና መሰል ሰነዶች የሚለቀቁበት ነው።
መልካም ቆይታ!
Download Telegram
ሰላም እንዴት ሰነበታችሁ በዛሬ ጽሁፋችን ስለ ዋስትና ስናነሳ ባለእዳዉን በተመለከተ በፍርድ አፈጻጸም ምክንያት ስለማይወሰዱ ሃብቶች አቅርበናል መልካም ንባብ፡-
ከዉልም ሆነ ከዉል ዉጭ በሚመነጭ ግዴታ የባለዕዳዉ ንብረት ከእርሱ ላይ ገንዘብ ሊጠይቁ ለሚችሉ ባለመብቶች ሁሉ የጋራ መያዣቸዉ ነዉ፡፡ ባለገንዘቦቹ ከባለዕዳዉ ጋር የተለየ ስምምነት ማድረግ ሳያስፈልጋቸዉ ባለገንዘብ በመሆናቸዉ ብቻ የዚህ መብት ተጠቃሚዎች ይሆናሉ፡፡ በባለዕዳዉ ላይ የሚያቀርቡትን ጥያቄ በፍርድ ካረጋገጡ አፈጻጸሙን በንብረቱ ላይ በፍ.ብ.ሕ.ቁ 1988(1) መሠረት ለባለዕዳዉ ግዴታ አፈጻጸም ማረጋገጫ የሚሆነዉ ሊያዝበት አይገባም ተብሎ በሕግ ከተደነገገዉ በቀር የመጠየቅ መብት ይኖራቸዋል፡፡
ህድአት ጥር/2013 ዓ.ም
እነዚህ ባለገንዘቡ መብቱን/ገንዘቡን የማይጠይቅባቸዉ ወይም በፍርድ አፈጻጸም ምክንያት የማይወሰዱ የባለዕዳዉ ንብረቶች/ሃብቶች የሚከተሉት ናቸዉ፡፡
• ለፍርድ ባለዕዳዉና ለቤተሰቡ የዕለት አገልግሎት የሚጠቅሙ ልብሶች የምግብ ማብሰያ የሆኑ የቤት ቁሳቁስ የመኝታ አልጋ የአልጋ ልብሶችና የብርድ ልብሶች
• ለዕለት ሞያ ሥራዎቹ አገልገሎት ለንግድ ሥራዉ ማከናወኛ ተገቢ የሆኑ ዕቃዎች
• የፍርድ ባለዕዳዉ ገበሬ ወይም በእርሻ ሥራ የሚተዳደር ሲሆን በፍርድ ቤቱ አስተያየት ለዚሁ ሥራዉ አገልግሎት በቂ ሆነዉ የሚገመቱ የቀንድ ከብቶች የዘር እሕልና ሌላም ፍጹም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች
• ለራሱና ለቤተሰቡ ለሶስት ወር መተዳደሪያ የሚበቃ ገንዘብና ለዕለት ምግብ ጠቃሚ የሚሆን ሥንቅ
• ለጡረታዉ የሚከፈለዉ ገንዘብና ባል ሚስቱን ከፈታ በኋላ ለወር ቀለቡዋ የሚከፍላት ገንዘብ
• የፍርደ ባዕዳዉ የወር ደመወዝ ሁለት ሶስተኛዉ እጅ
• እንዳይበር እንዳይሸጥና ለዕዳ መክፈያ እንዳይሆን በማናቸዉም ሕግ ላይ የተወሰነ ማናቸዉም ዓይነት ሀብት ወይም ንብረት
ምንጭ የኢትዮጵያ ዉል ሕግ መሰረተ ሀሳቦች/ጥላሁን ተሾመ/
የፍ.ብ.ሕ
የፍ.ብ.ሥ.ሥ.ሕ
ህድአት ጥር/2013 ዓ.ም
ጤና ይስጥልኝ
ዉድ አንባቢያን የጥላቻ ንግግር፤ የሐሰት ወሬ እና የሐሰት መረጃ ይዋል ይደር እንጂ እዉነቱ መዉጣቱ የማይቀርና ይህንን በሚጠየፍ ሕብረተ-ሰብ ዘንድም የማህበራዊ ቅጣትን የሚያስከትል መሆኑ እንዳለ ሆኖ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊትም በሕግም ቅጣት ሊጣልበት ግድ የሚለዉ በመሆኑ " የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አዋጅ ቁጥር 1185/2012" ወጥቶ ሥራ ላይ የዋለና እኔም በዚህ ላይ መጠነኛ ግንዛቤ ለመፍጠር ይረዳ ዘንድ የሚከተለዉን ለማቅረብ ወደድኩ፡-
መልካም ንባብ
የዲሞክራሲ መብቶች ከሆኑት አንዱ ሀሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ ቢሆንም ይህ መብት ግን ሕገ-መንግሥታዊ ጥበቃ የሚደረግለትን ያህል በአጠቃቀም ረገድ በሌላ ሰዉ ላይ ወይም የጦርነት ቅስቀሳን የሚያነሳሳ የጥላቻ ንግግር ማድረግን ወይም የሐሰተኛ መረጃ ማሰራጨትን በሕገ-መንግሥቱም ሆነ ከዚህ በላይ በገለጽኩት አዋጅ ቁጥር 1185/2012 የተከለከለና ቅጣት የሚጣልበት መሆኑን ስንገልጽ ከዚህ አንጻር የጥላቻ ንግግርን በብሮድካስት፤ በሕትመት ወይም በማሕበራዊ ሚዲያዎች ወይም በሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎች አማካኝነት በጽሑፍ ፤ በምስል፤ በድምጽ ወይም በቪዲዮ ማሰራጨት መሆኑንና ይህም የተከለከለ መሆኑን፤
የሐሰት መረጃን ማሰራጨት ማለት ደግሞ የሐሰት መረጃዉን በአደባባይ ስብሰባዎች በብሮድካስት፤ በሕትመት ወይም በማህበራዊ ሚዲያዎች ወይም በሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎች አማካኝነት በጽሑፍ፤ በምስል፤ በድምጽ ወይም በቪዲዮ ማሰራጨት የተከለከለ መሆኑን እና አነዚህኑ ማለትም ሐሰተኛ መረጃዎች ማሰራጨት እስከ አንድ መቶ ሺህ ብርና እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ የእስራት መቀጮን የሚያስከትል ይሆናል፡፡
ህድአት ጌታቸዉ
የካቲት/2013 ዓ.ም
Election ppt Omi.pptx
450.9 KB
ዳሬክቶሬታችን ከሚያከናውናቸው ተግባራት ውስጥ አንዱ በተለያዩ ሕጎች ዙሪያ ነዋሪው በሕገ መንግስቱና በቻርተሩ የተሰጡትን መብቶችና ነጻነቶች እንዲያውቅና እንዲጠቀም ተገቢውን የሕግ ስልጠና ይሰጣል፡፡በዚህም መሠረት በየካቲት 10 እና 11 ቀን 2013 ዓ.ም የዳሬክቶሬቱ 2 ዐቃቤ ሕጎች በ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና ተያያዥ ሕጎች ዙሪያ ለቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 3 እና 4 ምክር ቤት የሰጠውን ስልጠና በተመለከተ ለእናንተም በርዕሱ ላይ የተነሱትን ነጥቦች ለማጋራት ስለወደድኩኝ ስልጠናው ላይ የተነሱ ነጥቦችንና የተሳታፊዎችን ፎቶ በመጨመር ከታች አስፍሬላችኋለው፡፡
የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያቶች በአዋጁ መግቢያ ላይ የተዘረዘሩ ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች በመዋሀድ፣ ግንባር በመፍጠር ወይም በመቀናጀት ሊንቀሳቀሱ የሚችሉበትን ሁኔታ ለመደንገግ፣ለፍትሃዊ፣ ሰላማዊ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሥርዓት መስፈን በምርጫ የሚሣተፉ የፖለቲካ ድርጅቶችና የግል ዕጩዎች ገንቢ አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን ግልፅ አሰራር ለመዘርጋት፣ምርጫዎች በመልካም ሥነ ምግባር የሚመሩ ነጻ፣ ፍትሃዊ ፣ሰላማዊ፣ ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆኑና እንዲሁም በህዝብ ዘንድ ተቀባይነትን እንዲያገኙ ለማድረግ በምርጫ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣እጩዎች፣ አባላት እና ደጋፊዎች የሚመሩባቸውን የሥነ ምግባር መርሆች ለመደንገግእና በምርጫ ሂደት ለሚነሱ አለመግባባቶች አስተዳደራዊ እና የዳኝነት መፍትሔ የሚሰጡ ተቋማትን እና አሰራራቸውን ለመወሰን የሚሉት ይገኙበታል፡፡
የአዋጁ ተፈፃሚነት ወሰኑን በተመለከተ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚደረግ ጠቅላላ ምርጫ እንዲሁም እንደ አግባብነቱ የአካባቢ ምርጫ፣ የማሟያ ምርጫ፣ የድጋሚ ምር
…የድጋሚ ምርጫ እና በሕገ መንግሥቱ መሠረት በሚካሄድ ሕዝበ ውሳኔ ላይ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ ለሚመሠርቱ ዜጎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ኃላፊዎች፣ አባላት፣ ወኪሎች እና ተጠሪዎች፣ የፓርቲና የግል እጩ ተወዳዳሪዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅንጅት፣ ግንባር ወይም ውህደት ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን በአዋጁ አንቀጽ 3 የተደነገገ ሲሆን የምርጫ ሥርዓትን በተመለከተ በፌደራል ሕገ መንግስታት እና በክልል ሕገመንግስታት የሚል ክፍፍል ቢኖርም የክልል ምክር ቤት አባላት ምርጫን የሚመለከቱ የክልል ሕጎች በሕገ መንግሥቱና በአዋጁ ከተቀመጡ ምርጫን የተመለከቱ ድንጋጌዎች ጋር የተጣጣሙ መሆን እንዳለባቸው በአንቀጽ 4 ስር ሰፍሯል፡፡
ስለ ምርጫ መርሆዎች፣በኢትዮጵያ ስለሚካሄዱ የምርጫ ዓይነቶች፣ስለ ምርጫ ማስፈጸሚያ አደረጃጀቶች፣ስለ መራጮች እና ዕጩዎች መብትና ገዴታ፣ስለ ምርጫ ዘመቻ፣ስለ የድምፅ ቆጠራና ውጤት አገላለፅ፣በምርጫ ወቅት ስለሚነሱ አቤቱታዎችና መፍትሔዎቻቸው እንዲሁም ደግሞ በምርጫ ሂደት ስለ ተከለከሉ ተግባራትና ቅጣቶች ሌሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ የተደረገባቸው ነጥቦችን ሲሆኑ በሁለቱም ቀን የነበሩት ተሳታፊዎቻችን በጥሞና ያዳመጡንና ስልጠናው ሲያልቅም ያነሷቸው ጥያቄዎች ጥሩ የስልጠና እና የውይይት መድረክ ኢንዲኖር ስላደረገ ተሳታፊዎቻችንን እመሰገንኩኝ የተነሱት ነጥቦችን በተመለከተ ከተዘጋጀው power point ማግኘት ስለሚቻል ከታች power pointውን ስላሰፈርኩላችሁ መልካም ቀን በመመኘት ለዛሬ አበቃው፡፡
ሰናይ ዕለተ አርብ ቀን 12/06/2013 ዓ.ም! (ኦምኒኤል)
ስለንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ሕግ (ክፍል አንድ)
መግቢያ
ሀገራት ከሚከተሉት የኢኮኖሚ ሥርዓት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ወይም የዕዝ ገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን ሁለቱንም የገበያ ኢኮኖሚ ባማከለ መልኩ የቅይጥ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓትም ተጠቃሽ እንደሆነ ከተለያዩ ፅሁፎች መረዳት ይቻላል፡፡ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት የንግዱን ህብረተሰብ ከፀረውድድር እና ተገቢ ካልሆኑ የገበያ ተግባራት እንዲሁም ሸማቹን ከሚያሳስቱ የገበያ ሁኔታዎች የሚከላከል ሥርዓት መዘርጋት እና ለነፃ ገበያ ውድድር አመቺነት ያለው ሥርዓት ማስፈን አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል፡፡ የንግድ እንቅስቃሴዎች ማደግን ተከትሎ የሸማቾችን ጤንነትና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ የንግድ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን መስፋፋት ለመግታት እንዲቻልና ተጠቃሚዎች ላወጡት ዋጋ ተመጣጣኝ የሆኑ የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት እና ሌሎች ምክንያቶች ተደማምረው የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 ታውጇል፡፡ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃን ስናስብ ነጋዴዎች እና ሸማቾች የገበያው ተዋንያን በመሆናቸው በዋናነት በተዘረጋው ሥርዓት መሠረት ሊኖራቸው የሚገባ መብትና ግዴታዎቻቸውን በቅጡ ሊያውቁት ይገባል፡፡
ስለ ነፃ ገበያ ምንነት
ዓለማችን የምትመራባቸው ሶስት የኢኮኖሚ ሥርዓቶች ሲኖሩ አነሱም፡- የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ፣ የዕዝ ገበያ ኢኮኖሚና የቅይጥ ገበያ ኢኮኖሚ በመባል ይታወቃሉ፡፡ የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ስርዓት ማለት ገበያው ያለመንግስት ጣልቃ ገብነት እራሱን በራሱ የሚመራበት ስርዓት ማለትም ነጋዴዎች መንግስት በሚያወጣላቸው ዕቅድና መመሪያ ሳይሆን በተጨባጭ በገበያ ላይ ባለ ፍላጎትና አቅርቦት መሰረት መስራት የሚያስችላቸው ስርዓት ነው፡፡ የእዝ ገበያ የኮኖሚ ስርዓት የሚባለው ሀገራችን በደርግ ዘመነ መንግስት ትከተለው የነበረ የኢኮኖሚ ስርዓት ሆኖ ገበያው የሚመራው በፍላጎትና አቅርቦት ኃይሎች ባለ ነፃ መስተጋብር ሳይሆን ሙሉ በሙሉ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ኖሮበት የሚመራ የገበያ ስርዓት ነው፡፡ የቅይጥ ገበያ የኢኮኖሚ ስርዓት የሚባለው ደግሞ የነፃ ገበያና የዕዝ ኢኮኖሚ የገበያ ስርዓቶች ድብልቅ ሆኖ ሁለቱም አካላት የየራሳቸው ሚና መጫወት የሚያስችል የገበያ ምህዳር ሲኖር ማለት ነው፡፡
ከአዋጁ መግቢያ መገንዘብ እንደሚቻለው ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትመራው በነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ስርዓት ነው፡፡ የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ስርዓት ትከተላለች ማለት ግን የንግዱን ዘርፍ ልቅ መተው ማለት አይደለም፡፡ የሀገር ኢኮኖሚ አደጋ ላይ እንዳይወድቅና ሸማቹ ማህበረሰብ እንዳይጎዳ ቁጥጥርና ወጥ የሆነ ስርዓት ማበጀት ከመንግስት በእጅጉ ይጠበቃል፡፡




ስለሸማቾች ጥበቃ እና ስለንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ስርጭት
የሸማች መብቶች (አንቀጽ 14)
ሸማች ማለት ለማምረት ሥራ ወይም መልሶ ለመሸጥ ሳይሆን ዋጋዉን ራሱ ወይም ሌላ ሰዉ የሚከፍልለት ሆኖ ለራሱ ወይም ለቤተሰቡ ፍጆታ የሚሆን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት የሚገዛ የተፈጥሮ ሰው ነው (አን. 2(4))፡፡ ማንኛውም ሸማች እንደ ሸማች የተለያዩ መብቶች በአዋጁ መሠረት የተቀመጠ ሲሆን እኚም መብቶች፡- መረጃ ወይም መግለጫ የማግኘት፣ አማርጦ የመግዛት፣ እንዲገዛ ያለመገደድ፣ በአክብሮት የመስተናገድ እና ካሣ እንዲከፍሉት የመጠየቅ ናቸው፡፡
ሀ. መረጃ ወይም መግለጫ የማግኘት መብት፡- ማንኛውም ሸማች ስለሚገዛው ዕቃ ወይም አገልግሎት ጥራትና አይነት አስመልክቶ በቂና ትክክለኛ መረጃ ወይም መግለጫ የማግኘት መብት አለው፡፡
ለ. አማርጦ የመግዛት መብት፡- ሸማች መግዛት ወይም መሸመት የሚፈልገው የተለያዩ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ይኖራሉ፡፡ እነዚህን ለመሸመት የሚፈልጋቸውን ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን አማርጦ የመግዛት መብት አለው፡፡
ሐ. እንዲገዛ ያለመገደድ፡- የዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን ጥራት ወይም አማራጮችን ጥራት ወይም አማራጮችን በማየቱ ወይም የዋጋ ድርድር በማድረጉ ምክንያት እንዲገዛ ያለመገደድ መብት አለው፡፡
መ. በአክብሮት የመስተናገድ መብት፡- ሸማች ወይም ገዢ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በሚፈልግበት ጊዜ፣ በሚመርጥበት ጊዜ እና በሚገዛበት ጊዜ በትህትናና በአክብሮት የመስተናገድ መብት ይኖረዋል፡፡ በተጨማሪም ሸማች በነጋዴው ከሚደርስበት የስድብ፣ የዛቻ፣ የማስፈራራት እና የስም ማጥፋት ተግባር የመጠበቅ መብት አለው፡፡
ሠ. ካሣ እንዲከፍሉት የመጠየቅ መብት፡- ሸማች ወይም ገዢ የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በመግዛቱ ወይም በመጠቀሙ ምክንያት የደረሰበት ጉዳት ካለ፣ ለደረሰበት ጉዳት ካሳ የማግኘት መብት አለው፡፡ ይህን ካሳ የመክፈል ግዴታ ያለባቸው በአምራችነት፣ በአስመጪነት፣ በጅምላ ሻጭነት፣ በችርቻሮ ሻጭነት ወይም በሌላ ማንኛውም ሁኔታ በአቅርቦቱ የተሳተፉ ሰዎች ናቸው፡፡ ሸማቹ ከነዚህ አካላት በተናጠል ወይም በጋራ ካሳ የመጠየቅ መብት አለው፡፡

ይቀጥላል
ፌናን ተጊበሉ
የካቲት 15/2013 ዓ.ም
ጤና ይስጥልኝ
በዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓት ዉስጥ ሦስት የሥልጣን አካለት ያሉና እነዚህም አባላት የየራሳቸዉ የሆነ ሥልጣንና ተግባር ያላቸዉና እርስ በ'ርሳቸዉም አንዱ ሌላዉን ያለአግባብ እንዳያከናዉን የሚቆጣጠሩ (check and balance) ሆነዉ የሚቋቋሙ ሲሆን አነዚህም አካላት፡- ሕግ አዉጪ (ፓርላማ) ፤ ሕግ አስፈጻሚ (ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ምክር ቤት) እና ሕግ ተርጓሚ (ዳኝነት) ናቸዉ፡፡
ለዚህ ጽሑፍ የምንመለከተዉ የሕግ ተርጓሚዉንና ዳኝነቱን ከፌደራል ፍ/ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1988 እና በተለይ አሁንና ወደፊት ልናቀርባቸዉ ስለአሰብነዉ የሰበር ችሎቶች የተደነገገበት አዋጅ ቁጥር 454/1997 የአዋጆቹ መንፈስ የተወሰነ በማቅረብ ለወደፊቱ የሰበር ችሎቱ የሰጣቸዉን አንዳንድ ዉሣኔዎችና በማቅረብ ይሆናል፡፡
መልካም ምንባብ፡-
በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 78 እና ተከታዮቹ አናቅጽት ነጻ የዳኝነት አካል እንደሚቋቋም በተደነገገዉ መሠረት የፌደራል ፍ/ቤቶች አ/ቁጥር 25/1988 የወጣና ይህዉ አዋጅም በአዋጅ ቁጥር 138/91፤ በአዋጅ ቁጥር 321/1995 እና በአዋጅ ቁጥር 454/1997 ተሻሽሎ እየተሰራበት የሚገኝ ሲሆን አሁን ከያዝነዉ ጉዳይ አንጻር በአ/ቁጥር 25 እና በአ/ቁጥር 454 ላይ ስለተጠቀሰዉ የሰበር ችሎት ስንመለከት በፍርድ ቤት ታይተዉ የመጨረሻ ዉሣኔ የተሰጠባቸዉና መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለባቸዉን ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት የሰበር ችሎት የሚሰጠዉ የሕግ ትርጉም በየትኛዉም ደረጃ ላይ በሚገኝ የፌደራል ወይም የክልል ፍርድ ቤት ላይ አስገዳጅነት ያለዉ ዉሣኔ የሚሰጥ ሲሆን ይህንኑ የአስገዳጅነት ዉሣኔም ፍ/ቤቶች አንደ ሕግ ወስደዉ ዉሣኔ የሚሰጡበት መሆኑን ለግንዛቤ ስንገልጽ ለወደፊቱ ይህዉ የሰበር ሰሚ ችሎት ከሰጣቸዉ ዉሣኔዎች የተወሰኑትን እንደምናቀርብ በመግለጽ ተሰነባበትን፡፡
ደረጀ ማርቆስ
የካቲት 2013
በኢትዮጵያ የምርጫ፣የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 46 መሠረት የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ ማድረግ የተከለከለባቸው ቦታዎች የሚከተሉት ናቸው፡-
ቤተ ክርስትያኖች፤ መስጊዶች፣ወታደራዊ ካምፖች እና ፖሊስ ጣቢያዎች የመማር ማስተማር ሂደት ተግባር እየተከናወነ በሚገኝበት ወቅት በትምህርት ቤቶች እና በትምህርት ቤቶች አካባቢ በ2 መቶ ሜትር ርቀት ዙሪያ፤ ህዝብ የዕለት ተለት ግብይት በሚፈፅምባቸው እና በተወሰኑ ቀናት በገጠርም ሆነ በከተማ በይፋ ገበያ እየተካሄደ በሚገኝባቸው ቦታዎች በ2 መቶ ሜትር ዙሪያ ክልል፤ የመንግሥት ወይም የህዝብ መደበኛ ሥራ በመከናወን ላይ የሚገኙባቸው የመንግሥትና የህዝብ ተቋማት ሥራቸውን በሚያከናውኑበት መደበኛ የሥራ ሰዓት እና ቦታ፣ እንዲሁም ሌላ ህዝባዊ ስብሰባ እየተካሄደ ባለባቸው ቦታዎች እና አካባቢዎች፡፡
ሰናይ ዕለተ ማክሰኞ!(16/06/2013 ዓ.ም) (ኦምኒኤል)
በኢትዮጵያ የምርጫ፣የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 134 መሠረት ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ማንኛውንም ዓይነት ማስፈራራት ወይም ወከባ የተከለከለ መሆኑን ተቀብሎ የፓርቲው ኃላፊዎች፣ እጩዎች፣ አባላት እና ደጋፊዎች መቼም ቢሆን ማንንም ሰው የሚያስፈራሩ፥ የሚያሸማቅቁና የሚያዋክቡ ድርጊቶችን እንዳይፈጽሙ የሚከለክሉ መመሪያዎች ማውጣት፤አመፅንና አመጽ ቀስቃሽ ድርጊቶችን መቃወምና አባላቱንም ማስተማር፤ በኃላፊዎቹ፣ በእጩዎቹ፣ በአባላቱ ወይም በደጋፊዎቹ የሚፈፀሙ አውዳሚ ወይም ሰላምን የሚያናጉ ድርጊቶችን ወይም ይህን የሚጋብዝ ዛቻን በመቃወም ማስተማር፤የሌላውን ግለሰብ ሆነ ፓርቲ መብት፣ ንብረትና ጥቅሞች ማክበር ያለበት ሲሆን ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ መሪ የፓርቲው ኃላፊዎች፣ እጩዎች፣ አባላት እና ደጋፊዎች ለፖለቲካ የድጋፍ ሰልፍ፥ ለስብሰባ፣ የእግር ጉዞ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጡ ማናቸውንም ባህላዊ ወይም ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች መያዝ ክልክል መሆኑን ማስተማር፤ አለበት፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በማንኛውም የሁከት ወይም የአመጽ እንቅስቃሴ መሳተፍ ወይም እንዲደረግ መፍቀድ የለበትም፤በህዝብ ወይም በግለሰብ ንብረት ላይ ውድመት እንዳይደርስ የተቻለውን ሁሉ በማድረግ መከላከል አለበት፤ እንዲሁም ደግሞ ደጋፊዎቹ በአዋጁ ላይ የተደነገጉ ማናቸውንም ክልከላዎች እንዲጥሱ ማነሳሳት የለበትም፡፡
ሰናይ ዕለተ ማክሰኞ!(16/06/2013 ዓ.ም) (ኦምኒኤል)
ስለንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ሕግ (ክፍል ሁለት)
የነጋዴ ግዴታዎች
ሸማቾች ያላቸውን መብት ከላይ ከተዘረዘሩት መብቶቻቸው በተጨማሪም የነጋዴዎች ግዴታ ለሸማቾች መብት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ነጋዴዎች በርካታ ግዴታዎች ያሉባቸው ቢሆንም በዋናነት ግን፡- የዋጋ ዝርዝር በንግድ ቤቱ ላይ መለጠፍ፣ የንግድ ዕቃዎች ላይ መግለጫ መለጠፍ፣ ደረሰኞችን መስጠትና ቀሪዎችን መያዝ፣ የራሱን /የንግድ ስሙን/ ስለመግለጽ፣ የንግድ ማስታወቂያ ትክክለኛ መሆን ወዘተ የሚሉ ግዴታዎች አሉባቸው፡፡ (ከአንቀጽ 15-18)
ጉድለቶችን እና የተከለከሉ ድርጊቶችን በተመለከተ
ሸማች በገዛው የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ላይ ያገኛቸውን ጉድለቶችና ጉድለቶቹ ሊያስከትሉ ስለሚችሉት ጉዳት ለሚኒስቴሩ ወይም ለሚመለከተው ቢሮ ማሳወቅ ይችላል፡፡ ለሸማቹ የበለጠ የሚጠቅሙ ዋስትናዎች ወይም የሕግ ወይም የውል ድንጋጌዎች በነጋዴው ሊቀርብለት ይችላል፡፡ ሆኖም ሸማቹ ጉድለት ያለበት የንግድ ዕቃን የሚመለከት ሲሆን የንግድ ዕቃው እንዲለወጥለት ወይም ዋጋው እንዲመለስለት ሻጩን መጠየቅ ይችላል፡፡ በተጨማሪም ጉድለት ያለበት አገልግሎት ሲሆን አገልግሎቱ በድጋሜ ያለክፍያ እንዲሰጠው ወይም የአገልግሎት ክፍያው እንዲመለስለት ሻጩን መጠየቅ ይችላል፡፡ ግዥው በተፈጸመ በ15 ቀናት ውስጥ ሻጩን መጠየቅ የሚችል መሆኑን ከአዋጁ እንረዳለን፡፡
ሸማቹ በሕጉ የተሰጡትን መብቶች የሚያስቀሩ በሸማችና በነጋዴ መካከል የሚደረጉ የውል ግዴታዎች ተፈጻሚነት አይኖራቸውም::
ለማንኛውም ነጋዴ የሚከተሉትን ድርጊቶች መፈጸም የተከለከለ ነው፡- በአጠቃላይ ስለንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች የተሳሳተ መረጃ መስጠት፤ የንግድ ዕቃዎችን ሞዴል፣ አዲስ የተሠሩ፣ የተለወጡ፣ እንደገና እንደ አዲስ የተሠሩ ወይም ያገለገሉ ስለመሆናቸው ወይም በአምራቹ እንዲሰበሰቡ የተባሉ ስለመሆናቸው በትክክል አለመግለጽ፤ የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶችን በማስታወቂያ እንደተነገረላቸው አለመሸጥ ወይም ማስታወቂያው የመጠን ውስንነት መኖሩን ካልገለፀ በስተቀር ሸማቾች በሚፈልጉት መጠን ልክ አለመሸጥ፤ ከንግድ ዕቃ ወይም ከአገልግሎት ሽያጭ ጋር በተያያዘ የተገባ የዋስትና ግዴታን አለመወጣት፤ የንግድ ዕቃ የሚያስፈልገው ጥገና ግዴታን አለመወጣት፤ የንግድ ዕቃ የሚያስፈልገው ጥገና ወይም የሚተኩ ክፍሎቹ እንደማያስፈልጉት አድርጎ ማቅረብ፤ ማንኛውም አገልግሎት የመስጠት ሥራን በንግድ ሥራው ከሚታወቀው ደረጃ በታች ወይም ባልተሟላ ሁኔታ መስጠት፤ ለሰው ጤናና ደህንነት አደገኛ የሆነ፣ ምንጩ ያልታወቀ፣ የጥራት ደረጃው የወረደ፣ የተመረዘ፣ የአገልግሎት ጊዜው ያለፈ ወይም ከባዕድ ነገሮች ጋር የተደባለቀ የንግድ ዕቃን ለሽያጭ ማቅረብ ወይም መሸጥ፤ በንግድ ዕቃ ወይም የአገልግሎት ግብይት ማንኛውንም የማጭበርበር ወይም የማደናገር ተግባር መፈፀም፤ የሸማቹን መብት ለመጠበቅ ሲባል ካልሆነ በስተቀር የንግድ ዕቃን ወይም አገልግሎትን አልሸጥም ማለት፤ የደረጃዎች ማህተም መጠቀም የሚያስፈልጋቸው የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን ያለደረጃ ማህተም ለሽያጭ ማቅረብ ወይም መሸጥ፤ የንግድ ዕቃን ወይም አገልግሎትን በንግድ ዕቃው ላይ ወይም በንግድ መደብሩ ውስጥ ከተለጠፈው ዋጋ አስበልጦ መሸጥ፤ የንግድ ዕቃዎች የተሰሩበትን አገር አሳስቶ መግለጽ፤ በሸማቾች መካከል ተገቢ ያልሆነ አድልዎ መፈጸም፤ አንድን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ለመሸጥ ሸማቹ ያልፈለገውን ሌላ የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት አብሮ እንዲገዛ ማስገደድ፤ ሕገ-ወጥ በሆነ ማንኛውም የመለኪያ መሳሪያ መጠቀም እና የመሳሰሉት የተከለከሉ ናቸው፡፡
ቸር ሰንበቱ!!
ፌናን ተጊበሉ
የካቲት 16/2013 ዓ.ም
የአለማቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብት ጥበቃ ስምምነትና ኢትዮጵያ፡- ክፍል አንድ
መግቢያ

የዚህ ስምምነት ዓላማ መላ አካል ጉዳተኞች በሁሉም ዓይነት ሰብአዊ መብቶችና መሠረታዊ ነፃነቶች ረገድ ሙሉና እኩል ተጠቃሚነት ያላቸው ስለመሆኑ ማረጋገጥ፣ ማሳደግና ለነዚሁ ጥበቃ ማድረግ፣ ብሎም ተፈጥሮአዊ ክብራቸውን ከፍ ማድረግ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ከተዋዋይ ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ይኽንን ስምምነት በአዋጅቁጥር 676/2002 በማጽደቅ በህገመንግስቱ አንቀጽ 9/4 መሰረት የራሷ የህግ ክፍል ያደረገችው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በዚህ ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ ምን እንዳደረገች በተለይም ከህግ ማውጣትና አፈጻጸም ጋር በራሱ በስምምነቱ አንቀጾች በመመስረት ምጥን ዳሰሳ ማድረግ የዚች መጣጥፍ መነሻና መድረሻ ነው፡፡
አንቀጽ 4 አለማዳላት የሚል ርዕስ ሲኖረው፣
ሀገራት በፖሊሲ፣ በህግና በሌሎችም ስራዎች አካል ጉዳተኞችን የሚያካትቱ እንዲሆኑ ይልቁንም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አግላይ ስራዎች እንዳይሰሩ ተሰርተው ቢገኙም እርማት ለመውሰድ ስምምነት ገብተዋል፡፡ የሀገራችንም ትምህርትና ስልጠና ፖሊሲው፣ አካል ጉዳተኞች ትኩረት እንዲሰጣቸው ቢደነግግም ባለፈው የ2012 የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ ደረጃ ገብተው የሚገኙት 11 ፐርሰንቱ ብቻ ሲሆኑ የትምህርቱ ደረጃ ከፍ እያለበሄደ መጠን ቁጥሩ እየቀነሰ ይሄዳል፡፡
ተከታዩ አንቀጽ 9 ተደራሽነትን የሚመለከት ነው፡፡
አካል ጉዳተኞች ኑሯቸውን በነፃነት እንዲመሩና በየትኛውም የሕይወት መስክ ያልተገደበ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል ተዋዋይ መንግሥታት እነዚሁ ወገኖች ከሌሎች አቻዎቻቸው ጋር ባልተናነሰ ሁኔታ ቁሳዊ አካባቢን የመድረስም ሆነ በመጓጓዣ ዘዴዎች፣ የመረጃና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችንና ስርዓቶችን ጨምሮ በመረጃና መገናኛ አውታሮች እንዲሁም በከተማም ይሁን በገጠር ለሕዝብ ክፍት በተደረጉ ተቋማትና አገልግሎቶች የመጠቀም ዕድል የተመቻቸላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ ተገቢነት ያላቸውን እርምጃዎች ይወስዳሉ፡፡
በተደራሽነት ላይ የተጋረጡትን መሰናክሎችና ገደቦች መለየትና ማስወገድን የሚያጠቃልሉት እነዚህ እርምጃዎች ከሁሉ በፊት ቀጥሎ በተመለከቱት ላይ ተፈፃሚዎች ይሆናሉ፡
ሀ) ሕንፃዎች፣ መንገዶች፣ የመጓጓዣ ዘዴዎችና እንደ ትምህርት ቤቶች፣ የመኖሪያ ሥፍራዎች፣ የሕክምና አገልግሎት መስጫ ድርጅቶችና የስራ ማከናወኛ ቦታዎች ያሉ የቤት ውስጥና የቤት ውጭ መገልገያ ተቋማት!
ለ) የኤሌክትሮኒክና የአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎቶችን ጨምሮ የመረጃ፣ የመገናኛና ሌሎች አገልግሎቶች፡፡
2. ተዋዋይ መንግስታት በተጨማሪ ከዚህ በታች የተመለከቱትን በስራ ላይ ለማዋል ተገቢ እርምጃዎችን ይወስዳሉ፡፡
ሀ) ለሕዝብ ክፍት የተደረጉ ወይም የተመቻቹ ተቋማትንና አገልግሎቶችን ለመድረስ የሚያስችሉ ዝቅተኛ መስፈርቶችንና መመሪያዎችን ማዘጋጀት፣ በይፋ ማውጣትና ተግባራዊነታቸውን መቆጣጠር!
ለ) ለሕዝብ ክፍት የሆኑ አገልግሎቶችን በማመቻቸትና በማቅረብ ስራ ላይ የተሰማሩ የግል ድርጅቶች እነዚሁ አገልግሎቶች ለአካል ጉዳተኞች ጭምር ተደራሽነት እንዲኖራቸው አስፈላጊ የሆኑትን ጉዳዮች ሁሉ ግምት ውስጥ ማስገባታቸውን ማረጋገጥ!
ሐ) አካል ጉዳተኞችን በሚገጥሟቸው የተደራሽነት ችግሮች ዙሪያ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ወገኖች ስልጠና መስጠት!
መ) ለሕዝብ ክፍት በሆኑ ሕንፃዎችና ሌሎች መገልገያ ተቋማት ውስጥ በግልጽ የሚታዩ ምልክቶችን፣ ብሬሎችንና በቀላሉ አንብቦ ለመረዳት የሚያስችሉ ቅጾችን ማስቀመጥ ወይም ማቅረብ!
ሠ) የቀጥታ ድጋፍ ዓይነቶችንና መሪዎችን፣ አንባቢያንንም ሆነ በምልክት ቋንቋ አጠቃቀም የሰለጠኑ አስተርጓሚዎችን ጨምሮ ለሕዝብ ክፍት የሆኑ ሕንፃዎችንና ሌሎች መገልገያ ተቋማትን ተደራሽነት የሚያመቻቹ አማካዮችን ዝግጁ ማድረግ!
ረ) አካል ጉዳተኞች መረጃ የማግኘት ዕድል የተጠበቀላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሌሎች ተገቢነት ያላቸውን የእርዳታና የድጋፍ ዓይነቶችን ማስፋፋት!
ሰ) አካል ጉዳተኞች የመረጃን መረብን ጨምሮ በአዳዲስ የመረጃና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችና ሥርዓቶች የሚጠቀሙበትን ዕድል ከፍ ማድረግና!
ሸ) ለወደፊቱ በዝቅተኛ ዋጋ ሊቀርቡ የሚችሉበት ዕድል እስኪፈጠር ድረስ ምቹና ተደራሽነት ያላቸውን የመረጃና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችና ሥርዓቶች ዝግጅት፣ ልማት፣ አመራረትና ሥርጭት ከመነሻው ጀምሮ ማስተዋወቅ የሚል ዝርዝር ካስቀመጠው በመነሳት ይመስላል ኢትዮጵያም የህንጻ አዋጅ 624/2001በአንቀጽ 36 ማንኛውም ህንጻ ለአካል ጉዳተኞች በተሽከርካሪ ወንበር መንቀሳቀስ በሚያመች መለኩ እንዲገነባ፣ መጸዳጃቤቶችም ለአጠቃቀም በሚያመች መልኩ መሰራት እንዳለባቸው፤
ይህንኑ አዋጅ ለማስፈጸም በወጣው ደንብ ቁጥር 243/2003 /ሰ33/3፣ እና 34የህዝብ መገልገያ ህንጻዎችን አስመልክቶ በተደነገገው ሊፍቶቹ አካል ጉዳተኞች ያለምንም ችግር ሊጠቀሙባቸው እንዲችሉ፣ በአደጋ ጊዜ መውጫ እነሱን ታሳቢ ማድረግ ብቻ ሳይሆን መታጠቢያና ልብስ መቀየሪያ ቦታ እንዲያዘጋጁ፤ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች ሲዘጋጁ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ አለማቀፋዊ ደረጃን ያሟላና አደናቃፊ ነገሮችን ያስወገደ፤ መሆን ይህንን ካላሟላ የመገልገያነት ፈቃድ ሊሰጠው እንደማይገባ ተደንግጎ ቢገኚም የክፍለ ከተማችንን ቅጥረ ግቢና ህንጻ ጨምሮ በከተማችን በጀት የሚሰሩ ረጃጅምና ለህዝብ አገልግሎት የሚገነቡና በስራ ላይ የሚገኙ ህንጻዎችና ሌሎች መሰረተ ልማቶች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ተደርገው አለመሰራታቸው ሳያንስ የርማት ሀሳብ ሲሰጥም የሚመለከታቸው አካላት ጆሮ ዳባልበስ ብለው ጉዳዩ ከመወገድና ከመቀነስ ይልቅ እየባሰ መሄዱ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡
በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1152/2012ም በአንቀጽ 41/1/5/ በደነገገው ተቋማቱ አቅም በፈቀደ መገልገያ ህንጻዎችን መንሸራተቻ እንዲኖራቸው፤ የብሬልና የድምጽ ምልክቶች እንዲኖራቸው እንዲያደርጉ፤ ደንግጎ እናገኘዋለን፡፡
ስራን አስመልክቶ ኢትዮጵያ ስለአካልጉዳተኞች በአዋጅ 568/2000 ከመድሎ፣ እንዲጠበቁ፣ ድጋፍ እንዲደረግላቸው፣ አካል ጉዳተኚነታቸውን መሰረት ያደረገ ከልካይ መድሎ ቢደረግባቸው ጭብጥ ብቻ በማሲያዝ ለፍርድቤት ክስ እንዲያቀርቡ፤ በማህበር እንዲወከሉ መብቶች የያዘ ድንጋጌ በሀገሪቱ ባሉ ክልሎች ሁሉ ተፈጻሚነት እንዳለው፣ ነገር ግን ክልሎች ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት መመሪያወችን እንዲያወጡ በፈቀደው መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክሰርቪስ ቢሮ በ2005 መመሪያ አውጥቶ በሰራ ላይ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ የሲቪል ሰሪቪስ አዋጅ ቁጥር 1064ና በአዲስአበባ ከተማየመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 56/2010 በተመሳሳይ አንቀጽ 49 ለአካል ጉዳተኞች እጩ እና ተቀጣሪ ሰራተኞች የተሻለ ፈጻሚዎች እንዲሆኑ ልዩ ድጋፎች እንዲደረግላቸው ይደነግጋል፡፡
አለማቀፉ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት ግን በይበልጥና በዝርዝር የሚከተለውን በአንቀጽ 27 አስቀምጧል-
1. ተዋዋይ መንግሥታት አካል ጉዳተኞች ከሌሉች ጋር በእኩል ደረጃ ላላቸው የመሥራት መብት ዕውቅና ይሰጣሉ፡፡ ይኸውም በነፃ የተመረጠን ወይም ግልፅ፣ ሁሉንም አካታችና ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽነት ባለው የስራ ገበያና ቅጥር የተገኘንና ተቀባይነት የተሰጠውን ሥራ ሰርቶ መተዳደሪያ የማግኘት መብትን ይጨምራል፡፡ ተዋዋይ መንግሥታት ይልቁንም ከዚህ በታች የተመለከቱትን በስራ ላይ ለማዋል ይቻል ዘንድ ሕግ ማውጣትን ጨምሮ በስራ ሂደት የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በሚያካትት መንገድ የሰዎች የመስራት መብት እንዲጠበቅና ተሻሽሎ እውን እንዲሆን የሚያደርጉ ተገቢ እርምጃዎችን ይወስዳሉ፡-
ሀ) ምልመላን፣ ጊዜያዊም ሆነ ቋሚ ቅጥርን፣ በቋሚ ስራ ላይ መቀጠልን፣ የሙያ እድገትን ደህንነቱ የተጠበቀና ጤናማ የስራ ሁኔታዎችን ጨምሮ ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች ሁሉ አስመልክቶ በአካል ጉዳት ላይ የተመሰረተ ማናቸውም አይነት አድልዎ እንዳይፈፀም መከልከል!
ለ) ከወከባ መጠበቅንና ለቅሬታዎች የመፍትሄ ምላሽ ማግኘትን ጨምሮ እኩል ዋጋ ላለው ስራ እኩል ዕድልዎችን ሆነ እኩል ክፍያ የማግኘት፣ ደህንነታቸው የተጠበቀና ጤናማ የስራ ሁኔታዎችን ጨምሮ ከሌሎች ጋር በእኩል ደረጃ ለአካል ጉዳተኞች ትክክለኛና ምቹ የስራ ሁኔታ የማግኘት መብትን መጠበቅ!
ሐ) አካል ጉዳተኞች ከሌሎች ጋር በእኩል ደረጃ በስራና በሙያ ማኀበራት የመደራጀት መብት እንዳላቸው ማረጋገጥ!
መ) አካል ጉዳተኞች የአጠቃላይ፣ የቴክኒክና ሙያ ነክ የአመራር መርሃ ግብሮች እንዲሁም የምደባ አገልግሎት፣ የሙያዊና ተከታታይነት ያለው ስልጠና ውጤታማ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ማስቻል!
ሠ) ለአካል ጉዳተኞች በሥራ ገበያ ውስጥ የቅጥርና የሙያ እድገት እድሎችን ከፍ ማድረግና እንዲሁም ሥራ ፍለጋ፣ ግኝት፣ ቆይታና የመልሶ ቅጥር ሁኔታዎች ረገድ ድጋፍ ማድረግ!
ረ) በግል ሥራ የመፍጠር ፣ ገቢ በሚያስገኝ ተግባር የመሰማራት፣ የሕብረት ሥራ ማሕበራትን የማሳደግና የራስን ሥራ የመጀመር ዕድሎችን ከፍ ማድረግ!
ሰ) በመንግሥት የሥራ ዘርፎች አካል ጉዳተኞችን በሰራተኝነት መቅጠር!
ሸ) የድጋፍ መርሀ ግብሮችን፣ ማበረታቻዎችንና ሌሎች እርምጃዎች ሊያካትቱ በሚችሉ ተገቢ ፖሊሲዎችና እንቅስቃሴዎች አማካኝነት በግሉ ዘርፍ በኩል የኣካል ጉዳተኞችን የስራ ቅጥርና ስምሪት ማሻሻል!
ቀ) በሥራ ቦታ ለአካል ጉዳተኞች ምክንያታዊ ተቀባይነት ያለው ማስተካኪያ የቀረበላቸው መሆኑን ማረጋገጥ!
በ) ክፍት በሆነው የሥራ ገበያ ዘንድ የአካል ጉዳተኞችን የሥራ ተሞክሮ ግኝት ማሻሻልና
ተ) የአካል ጉዳተኞችን የተለየ ስልጠና፣ ሙያዊ ተሃድሶ፣ ስራ ይዞ መቆየትና ወደ ስራ የመመለስ መርሃ ግብሮችን ማስፋፋት፡፡
በሰላም ቆዩኝ
ሲሳይ ሰማኝ
የካቲት 18/2013 ዓ.ም
የአለማቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብት ጥበቃ ስምምነትና ኢትዮጵያ፡- ክፍል ሁለት
በፖለቲካዊና ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ስለመሳተፍ
ተዋዋይ መንግስታት አካል ጉዳተኞች ከሌሎቹ ጋር በእኩል ደረጃ ፖለቲካዊ መብቶች እንዳሏቸውና በእነርሱ የመገልገል እድል እንደተረጋገጠላቸው ዋስትና ሰጥተው ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቀጥሎ የተመለከተውን ለማከናወን ግዴታ ገብተዋል፡-
(ሀ) አካል ጉዳተኞች ከሌሎች ጋር በእኩል ደረጃ የመምረጥና የመመረጥ መብትንና እድልን ጨምሮ ከሁሉም ይልቅ፡-
1ኛ/ የድምፅ አሰጣጥ ሥርዓቶች፣ መገልገያዎችና ቁሳቁሶች ተገቢ፣ ምቹና ተደራሽነት ያላቸው እንዲሁም ለመረዳትና ለመጠቀም ቀላሎች እንዲሆኑ በማድረግ፣
2ኛ/ ምርጫዎችና ይፋዊ ሕዝበ-ውሳኔዎች በሚካሄዱባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ አንዳች ማስፈራራት ሳይደርስባቸው በሚስጥር የድምፅ አሰጣጥ ሥርዓት መሠረት ድምፅ የመስጠትና ተገቢ ሆኖ ሲገኝ የአዳዲስና ደጋፊ ቴክኖሎጂዎችን አጠቃቀም አመቻችቶ የኃላፊነት ቦታን በተጨባጭ ለመያዝና ሁሉንም ዓይነት ሕዝባዊ ተግባራት ለመከወን በሁሉም የመንግሥት እርከኖች እጩ ተመራጭ ሆኖ የመሰለፍ መብቶችን በመጠበቅ፣
3ኛ/ መራጮች ሆነው በሚቀርቡበት ጊዜ ፈቃዳቸውን ነፃ ሆነው ይገልጹ ዘንድ ዋስትና በመስጠትና ይህንኑ ለማሳካት ጥያቄ ሲያቀርቡም እንደአስፈላጊነቱ በድምፅ አሰጣጥ ወቅት በገዛ እራሳቸው ምርጫ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲያገኙ በመፍቀድ፣ በቀጥታም ሆነ በነፃነት በተመረጡ ወኪሎቻቸው አማካኝነት ውጤታማነቱ በተረጋገጠና በተሟላ ሁኔታ በፖለቲካዊና በሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የመሳተፍ መብት እንዳላቸው ማረጋገጥ!
(ለ) አካል ጉዳተኞች ያለ አድልዎና ከሌሎች ጋር በእኩል ደረጃ በሕዝባዊ ጉዳዮች ክንውን ውጤታማ ሙሉ ተሳታፊዎች የሚሆኑበትን እድል በንቃት ከፍ ማድረግና
1ኛ/ በሀገሪቱ ፖለቲካዊና ሕዝባዊ ጉዳዮች፣ እንዲሁም በፖለቲካ ድርጅቶች እንቅስቃሴና አስተዳደር ረገድ ባለድርሻዎች በሆኑ ማኀበራትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ውስጥ የሚደረገውን ተሳትፎና
2ኛ/ አካል ጉዳተኞችን በዓለምአቀፍ፣ በብሄራዊ፣ በአህጉራዊና በአካባቢ ደረጃ የሚወክሉ ድርጅቶችን መመስረትንና በእነዚሁ ውስጥ መግባትን ጨምሮ፣ በሕዝባዊ ጉዳዮች ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባውን ተሳትፎ ማበረታታት የሚል ሲሆን ለዚሁ አፈጻጸም ይረዳ ዘንድ ይመስላል
የኢፌድሪ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 የተደነገገ ሲሆን አካልጉዳተኞችን አስመልክቶ ጥቂት ልዩ ድንጋጌዎችን አስቀምጦ ይገኛል፡፡
ይኸውም;
1. በአንቀጽ 31/3 እጩ ሆኖ ለመቅረብ የፈለገ አካል ጉዳት አልባ ግለሰብ 5000 የድጋፍ ፊርማ ሲሆን፣ አካልጉዳተኛ ግን 3000 ብቻ ነው፤
2. በአንቀጽ 32 የእጩ አቀራረብን አስመልክቶበ32/2 በተደነገገውየፖለቲካ ‹ፓርቲዎች እጩ ሆኖ ለመቅረብ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ከሆነ፣ በሚወዳደርበት የምርጫ ክልልውስጥ ከሆኑ መራጮች ለጉዳት አልባው 2000፣ ለአካልጉዳተኛው፣ 1500 ሲሆን፤ ለክልል ምክርቤት ከሆነ ደግሞ ለጉዳት አልባው 1000፣ ለአካልጉዳተኛው 750 የዲጋፍ ፊርማ ያስፈልጋል፡፡
3. በአንቀጽ 100 ከመንግስት ለፖለቲካ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ከሚታዩ መስፈርቶች መካከል-
በንዑስ 2 በፊደል ሠ የአካል ጉዳተኛ ዕጩዎች፣ በፊደል ረ ደግሞ የአካል ጉዳተኛ አመራሮች ብዛት የሚታይ መሆኑን እናገኛለን፡፡
በአጠቃላይ የአለማቀፉ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት ባካተታቸው 35 አንቀጾች ብዙ ዝርዝር መብቶችን የደነገገሲሆን በስራ ላይከቅጥር እስከደረጃ እድገትና በተለይም በሀላፊነት ደረጃ አካልጉዳተኞችን እድል እንዲያገኙ ያለማመቻቸት፣ ከሕግ ይልቅ የግለሰቦች አመለካከትና በጎ ፈቃድ ወሳኚ መሆኑ፤ የትምህርት ተደራሽነት አሁንም ገና በጣም ገና መሆኑ፤ በሀገሪቱ በብዙ ገንዘብና ለብዙ አመታት የተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ መሰረተ ልማቶች ስምምነቱንና የሀገሪቱን ህጎች አለማሟላታቸው ላይ ትኩረትና ተጠያቂነት ባለበት ሁኔታ ካልተሰራ ግንባታዎቹ እንዳልተገነቡ፣ ህጎቹም እንዳልተደነገጉ ከመቆጠር የሚያዲናቸው ጉዳይ አይኖርም፡፡
ሁላችንንም የመፍትሄ አካል የሚያደርግ ልቦና ይስጠንና ሀገራችንንም ሆነ ከተማችንን ለሁሉምና እኛም በየትኛውም የጤናና የእድሜ ዘመናችን ልንኖርባቸው የንችል አድርገን ለመገንባት ያብቃን፡፡
ቸር ይግጠመን፡፡
ሲሳይ ሰማኝ
የካቲት 19/2013 ዓ.ም
በሰዎች መነገድ ወይም ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሚሳተፉ የአዘዋዋሪዎች ማንነት
በኢትዮጵያ የተካሄዱ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከማንነት፣ ከአሰራርና በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሂደት ከሚኖራቸው ሚና አንፃር አዘዋዋሪዎች በአምስት ሊመደቡ ይችላሉ፡፡
1. በመጀመሪያው ምድብ የሚገኙት ተጠቂዎቹ በሚኖሩባቸው ማህበረሰቦች ውስጥ የሚገኙ የአካባቢ ደላሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ደላሎች የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨትና በሌሎች ዘዴዎች ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አመቺ ሁኔታ የመፍጠር እና ተጋላጭ ግለሰቦችን በመለየት የዝውውር ሂደቱን የመጀመረ ሚና አላቸው፡፡ ብዙውን ጊዜ የአካባቢ ደላሎች የሚንቀሳቀሱት የምልመላ እና በመደበኛና ኢ-መደበኛ መንገዶች የማዘዋወር ሂደቱን ከሚያከናውኑ ሌሎች አዘዋዋሪዎች ጋር በመሆን ነው፡፡
2. በሁለተኛው ምድብ ያሉት ደግሞ ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ ሰዎችን የሚያዘዋውሩና ድንበር የሚያሻግሩ የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ እነዚህ አዘዋዋሪዎች ሰዎችን በቡድን ከአካባቢ ደላሎች ተቀብለው ለሌሎች ተመሳሳይ አዘዋዋሪዎች በማስተላለፍ በቅብብሎሽ የሚያደርሱ ናቸው፡፡
3. በሶስተኛ ደረጃ የሚገኙት ደግሞ በትላልቅ ከተሞች የሚንቀሳቀሱና ወደ መዳረሻ ቦታዎች በመደበኛ የጉዞ መስመሮች የሚደረገውን ጉዞ የማቀላጠፍ እና ቅጥር የማመቻቸት አላፊነት የሚወስዱ ደላሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ደላሎች ከአካባቢ ደላሎች ሰዎችን ተቀብለው በመዳረሻ አገራት ለሚገኙ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች ያስተላልፋሉ፡፡ በዚህም ከሥራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ጋር ተመሳሳይ ነገርግን ህገወጥ የሆነ ስራ ይሰራሉ፡፡
4. በአራተኛው ምድብ የሚገኙት ከስደት ተመላሾችና ቤተሰቦቻቸው ሲሆኑ ሌሎች ሰዎች እነሱ ወደነበሩበት አገር በመሄድ እንዲቀጠሩ በግለሰብ ደረጃ ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በግል ትውውቅ ወደ ውጭ አገር ለመጓዝ የሚሹ ዘመድና ጎረቤቶችን ከማገዝ ባለፈ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመደበኛነት በመያዝ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡
5. በመጨረሻ የምናገኛቸው በመዳረሻ አገራት የሚገኙ እና በመደበኛና ኢ-መደበኛ መንገዶች በመዳረሻ ቦታዎች የሰዎች ዝውውር ላይ የተጠመዱ አዘዋዋሪዎች ናቸው፡፡ ከተለያዩ ምንጮች የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው እነዚህ አዘዋዋሪዎች በመዳረሻ አገራት የሚገኙ ደላሎች፣ የስራና ሰራተኛ አገናኝ ድርጅቶች ወይም ቀደም ብለው የሕገወጥ ዝውውር ሰለባ የሆኑ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ተጠቂዎችን በማታለል፣ በማስገደድ ወይም በማስፈራራት ለብዝበዛ በቀጥታ የሚያጋልጡ አዘዋዋሪዎች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜም በብዝበዛው ሂደት ቀጥተኛ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡


ቸር ሰንብቱ!!
ፌናን ተጊበሉ
የካቲት 19/2013 ዓ.ም
👍1
ጤና ይስጥልኝ
በባለፈው፡ጽሑፋችን፡በሰበር፡ችሎት፡የሚሰጡ፡ውሣኔዎች፡አስገዳጅነት፡ያለውና፡በሌላ፡በተመሳሳይ፡ጉዳይ፡ላይ፡ተፈጻሚነት፡ያለው፡ስለመሆኑ፡በአዋጅ፡ቁጥር፡25/1988፡(ስለፌደራል፡ፍ/ቤቶች፡ማቀቋሚያ፡አዋጅ)እናበአዋጅ፡ቁጥር454/1999(የፌ/ፍ/ቤቶች፡ማቋቋሚያ፡አዋጅ፡ማሻሻያ፡ስለሰበር፡ችሎት)በተደነገጉት፡ላይ፡በመነሳት፡መጠነኛ፡ማብራሪያ፡በማቅረብ፡አንዳንድ፡የሰበር፡ውሣኔዎችን፡እንደምናቀርብ፡በገለጽነው፡ መሠረት፤እነሆ፡-
መልካም፡ ምንባብ፡-

ለዛሬው በቤተሰብ ሕግ፡ ዙሪያ ስለተሰጡት የተወሰኑትን እንመልከት፡-
1ኛ. የመ/ቁጥሩ 23493 በሆነና ሰኔ 26 ቀን 2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት በፍርድ፡ ቤት ያልፈረሰ በጋብቻ፡ ላይ፡ ጋብቻ በፈጻሚው ሞት ምክንያት የፈረሰ እንደሆነ፡ የሟች ባለቤቶችን፡እኩል የጡረታ አበል የመክፈል መብት የሚሰጥ ስለሆኑ፤
2ኛ. የመ/ቁጥሩ 21740 በሆነና ጥቅምት 28 ቀን 2000 ዓ.ም በዋለው ችሎትየጋብቻ፡ጽሑፍ በሌላ፡ ጊዜ ጋብቻ መኖሩን፡ ለማስረዳት የሚቻለው የባልና ሚስትነት ሁኔታ መኖርን በማስረዳት ስለመሆኑ፤
3ኛ. የመ/ቁጥሩ፡ 23021 በሆነና ሐምሌ 12 ቀን 1999 ዓ.ም በዋለው ችሎት በፍቺ፡ ጋብቻ ከፈረሰ፡ በኋላ፡ የቀድሞ፡ተጋቢዎች እንገና አብሮ መኖር የትዳር፡ ሁኔታ መኖሩን የሚያስገነዝብ ከሆነ ጋብቻ፡መፈጸሙን የሕግ ግምት መውሰድየሚቻል ስለመሆኑ፤
ደረጀ ማርቆስ
የካቲት 22 2013 ዓ.ም