የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
276 subscribers
366 photos
3 videos
137 files
97 links
ይህ የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት ቻናል ስለኢትዮጵያ ሕጎች)ማብራሪያ የሚሰጥበት፣ አዳዲስ ሕጎች የሚጋሩበት፣ ሕግ ነክ ዜናዎችና መረጃዎች የሚተላለፉበት፣ በዳይሬክቶሬቱ የተሰጡ የንቃተ-ሕግ ስልጠናዎች፣ የሕግ መልዕክቶች፣ በራሪ ጽሑፎች እና መሰል ሰነዶች የሚለቀቁበት ነው።
መልካም ቆይታ!
Download Telegram
ኮቪድ 19ን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ ተፈጻሚ በማድረግ የህዝቡን ጤንነት ለመጠበቅ የሚደረገው የጋራ ጥረት ቀጥሏል፡: ይሁንና መሰረታዊ በሆኑ እና ማብራሪያ በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ተከታዮቹን መረጃዎች ለመስጠት ወደናል፡-

1. ስለ ስብሰባ፤ ስለ ስብሰባ የሚደነግገው አንቀጽ ውይይት ማድረግ የሚፈልግ የትኛውም ተቋም የተሳታፊዎቹን ቁጥር ከ50 እንዳይበልጥ የሚከለክል ሲሆን ከ50 በላይ
ተሳታፊዎችን የሚያቅፉ ውይይቶች አስገዳጅ ሲሆኑ የአዳራሹን ወይም የመወያያውን ስፍራ ሰው የመያዝ አቅም አንድ አራተኛውን በመጠቀም እና ለሰላም ሚኒስቴር ወይም በተዋረድ ላሉ የክልል፣ ዞን እና ወረዳ የሰላምና ፀጥታ መዋቅሮች (በአቅራቢያ ላለ ፖሊስ ጣቢያ) በማሳወቅ ዉይይቱን ሊያከናውን ይችላል፡፡ በተጨማሪም በተሳታፊዎቹ መካከል የሚኖረው አካላዊ ርቀት ከሁለት የአዋቂ እርምጃ ሳያንስ እንዲሁም የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እንዲጠቀሙ እና የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እንዲሟላ በማድረግ ማከናወን የሚቻል መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ከዚህ እና መመሪያው ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎች ድርጊትን የሚከለክሉ ሳይሆኑ ገደብ የሚጥሉ በመሆናቸው ገደቦቹን በማክበር የተፈለገውን ዓላማ ማሳካት የሚያስችል ህግ ነው፡፡

2. ከምርጫ ጋር በተገናኘ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በሙሉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን መስፋፋት ለመከላከል ሊወሰዱ ስለሚገባቸው የጥንቃቄ ርምጃዎች ተፈፃሚ የሚሆነው
ይህ መመሪያ ሳይሆን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ የሚያወጣው መመሪያ ነዉ፡፡

3. መመሪያው በመንግስት ተቋማት ላይም ተፈጻሚነት ያለው ስለመሆኑ፤ ለቋማችን እየቀረቡ ካሉት ጥያቄዎች መካከል አንዱ መመሪያው በመንግስት ተቋማት ቢጣስ ተጠያቂነትን ያስከትላል ወይ የሚል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ከመመሪያው የምንረዳው የወጣበት ዓላማ ሁሉንም የማህበረሰብ አካል በእኩል ለመግዛት ነው፡፡ ይህ ማለት በመመሪያው የተጣሉትን ገደቦችም ሆነ ግዴታዎች ጥሶ የሚገኝ ማንኛውም የመንግስት ተቋም እንደ የግል ተቋማት እና ግለሰቦች ሁሉ በህግ ከመጠየቅ የሚድንበት ሁኔታ አይኖርም ማለት ነው፡፡ የመንግስት ተቋት የግል ድርጅቶች እና ግለሰቦች በህጉ የተጣለባቸውን ግዴታ እንዲወጡ ምሳሌ ሆነው መቅረብ አለባቸው፡፡

4. ስለ ቅጣት፤ የኮቪድ ወረርሽኝ ካለው በቀላሉ የመሰራጨት ዕድል የተነሳ ሰዎችን ማሰር አማራጭ አይሆንም፡፡ በመሆኑም ወደ እስር ከመገባቱ በፊት ህዝቡን ማስተማር እና ማስጠንቀቅ የግድ ይላል፡፡ ሆኖም ትምህርቱን እና መስጠንቀቂያውን ችላ ብለው በወንጀል ተግባር ተሰማርተው የሚገኙ ሰዎችን በወንጀል መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ መመሪያው ያመላከተው የወንጀል ህጉም አንቀጽ 522 በድርጊቱ ጥፋተኛ የተባለ ሰው እስከ 2 ዓመት ቀላል እስራት ይቀጣል ይላል፡፡ ይህ ማለት አንዳንድ ሚዲያዎች እንደሚሉት በኢትዮጵያ ማስክ አለማድረግ 2 ዓመት ያስቀጣል በሚል መረዳት አደጋ አለው፡፡ ድንጋጌው ቀላል እስራቱ እስከ 2 ዓመት ቀላል እስራት ነው የሚለው፤ እስከ ከተባለ 2 ዓመት ጣራው ሆኖ መነሻ የእስራት መጠን አለው ማለት ነው፡፡ በወንጀል ህጋችን ጠቅላላ ክፍል ቀላል እስራት መነሻው 10 ቀን እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም ወንጀሉ የሚያስጠይቀው በ2 ዓመት ሳይሆን ከ10 ቀን እስከ 2 ዓመት ሊደርስ በሚችል ቀላል እስራት ነው ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ተፈጸመ የተባለው የህግ ጥሰት ውስጥ ያሉ የድርጊት እና የሀሳብ ክፍል ከግምት ገብቶ እንደ ወንጀሉ ክብደት ደረጃ ወጥቶለት የሚወሰን ነው ማለት ነው፡፡ በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት አንድ አጠገቡ ካለ ሰው ከ2 ሜትር በታች በሆነ ርቀት ውስጥ ተጠግቶ የቆመ ሰው እና በሽታው እንዳለበት እያወቀ ከሌሎች ጋር የተቀላቀለ፤ አብሮ የተንቀሳቀሰ ወይም ምግብ የተመገበ ሰው የወንጀል ባህሪ (አደገኝነታቸው) እኩል ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም ሰው መቀጣት ያለበት ባጠፋው ልክ በመሆኑ ቅጣት ሲጣል ይህንን ከግምት የሚያስገባ ይሆናል፡፡

ምንጭ፡- የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ
መጋቢት 28/2013 ዓ.ም
ሰላም እንዴት ሰነበታችሁ በዛሬ ጽሁፋችን በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 ከተካተቱት የስነ ምግባር ጥሰቶች ሁለቱን እንመለከታለን መልካም ንባብ
ክፍል 1
አንድ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የግል እጩ ተወዳዳሪ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅንጅት፣ ግንባር፣ ጥምረት፣ ንቅናቄ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ መሪ፣ ኃላፊ፣ እጩ፣ አባል፣ ወኪል ወይም ተጠሪ:-
• ማንኛውንም መደለያ ወይም ጉቦ የሰጠ ወይም የተቀበለ፤
• በድምጽ አሰጣጡ ወይም በቆጠራው ጣልቃ የገባ ወይም ያወከ፤
• ኃይል በመጠቀም፣ መደለያ በመስጠት ወይም በሌላ በማንኛውም አድራጎት መራጩ ሕዝብ ለአንድ ፓርቲ ወይም እጩ ድምጽ እንዲሰጥ ወይም እንዳይሰጥ ወይም ከመስጠት እንዲታቀብ ያደረገ፤
• የድምጽ መስጫ ጣቢያን በሀይል የተቆጣጠረ ወይም በሕገ-ወጥ መንገድ ድምጽ ለማግኘት የሞከረ፤
• ሥልጣኑን መከታ በማድረግ መደለያ ወይም ቅጣት ወይም ሌላ የማስፈራሪያ ዘዴ የተጠቀመ፣
• ማንኛውንም መደለያ በመስጠት ኃይል በመጠቀም፣ ወይም በማንኛውም ዓይነት ድርጊት እጩ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀርቡ ወይም እንዳይቀርቡ ወይም ከእጩ ተወዳዳሪነት እንዲወጡ ወይም እንዳይወጡ ያደረገ፤
• የመንግሥት ሰራተኛ እና ኃላፊ ሆኖ በራሱ የግል ሳይሆን በመንግሥት የስራ ሰዓት እና ኃላፊነት ተቋሙን በመጠቀም እጩዎችን ያስተዋወቀ ወይም ሌሎች እጩዎች ራሳቸውን በሕጋዊ መንገድ እንዳያስተዋውቁ ያደናቀፈ፤
• የመንግሥት ንብረት ለምርጫ ቅስቀሳ የተጠቀመ እንደሆነ፤ የስነ ምግባር ጥሰት እንደፈጸመ ይቆጠራል፡፡

አዋጅ ቁጥር 11/62 አንቀጽ 142
ህድአት ጌታቸዉ
ሚያዚያ/2013 ዓ.ም
ክፍል 2
ማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ፣ የግል እጩ ተወዳዳሪ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅንጅት፣ ግንባር፣ ጥምረት፣ ንቅናቄ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ መሪ፣ ኃላፊ፣ እጩ፣ አባል፣ ወኪል ወይም ተጠሪ:-
• በምርጫ ሂደት ጫና ወይም ተጽዕኖ በመፍጠር ጣልቃ የገባ፤
• ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችሀሳባቸውንበነጻነት እንዳያሰራጩ ስጋት እና ፍርሀት የፈጠረ፤ ፫/ በማንኛውም መንገድ የሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመራጩን ሕዝብ እንቅስቃሴ ያደናቀፈ ወይም ያወከ፤
• ሕዝባዊ ቅስቀሳ ወይም ስብሰባ ወይም ውይይት ወይም ትምህርትና ስልጠና እንዳይካሄድ ያደናቀፈ ወይም ሁከት የፈጠረ፣
• ሕዝብ ድምጽ ሲሰጥ ያወከ ወይም ድምጽ እንዳይሰጥ ችግር የፈጠረ፤
• የሌሎች ፓርቲዎች ወይም እጩ ተወዳዳሪዎች የምርጫ ዘመቻ እንዲስተጓጐል ወይም እንዲቋረጥ ወይም እንዲበላሽ ወይም እንዲዳከም ያደረገ፤
• ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ፣ ስብሰባ፣ የእግርጉዞ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ያደናቀፈ ወይም ሌላ ሰው እንዳይሳተፍ የከለከለ፤
• መራጮችን የሰደበ ወይም ያንጓጠጠ ወይም የመምረጥ መብታቸውን ያደናቀፈ፤
• ለምርጫው ሂደት የምርጫ አስፈፃሚዎችን እና የዕጩ ተወዳዳሪዎችን ፀጥታና ደህንነት ለማረጋገጥ በሚደረግ ጥረት ከጊዜና ቦታ አኳያ እገዛ ማድረግ እየቻለ ያላደረገ ወይም ያወከ፤
• በማንኛውም ዓይነት መንገድ መራጩ ህዝብ እንዳይመዘገብ ወይም እንዳይመርጥ ያደረገ፤
• የድምጽ አሰጣጡን ሚስጢራዊነት ያላከበረ ወይም እንዲከበር እገዛ ማድረግ ሲገባውያላደረገ፤
• የሥነ ምግባር አዋጁ ተጥሷል በሚል ሽፋን የሀሰትና የተጋነነ አቤቱታ በማቅረብ ቅሬታ የማሰማት መብቱን ያለአግባብ የተጠቀመ እንደሆነ፤ የሥነ ምግባር ጥሰት እንደፈፀመ ይቆጠራል፡፡

አዋጅ ቁጥር 11/62 አንቀጽ 143
ህድአት ጌታቸዉ
ሚያዚያ/2013 ዓ.ም
አማራጭ የሙግት መፍቻ ዓይነቶችና ምንነታቸው፡-

በሀገራችን በተለያዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦችም ሆነ በሌሎች የዓለም ሀገራት አለመግባባትን.ለማስወገድ ረዥም ታሪክ ያለዉና የህብረተሰቡን ፣የድርጅትን እና የግለሰብን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ እንዲሁም ኢኮኖሚዉን ለማረጋጋት አይነተኛ መሣሪያዎች ሆነዉ የሚያገለግሉት
አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች ናቸዉ፡፡ አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች ተብለዉ በአብዛኛዉ የሚታወቁት ድርድር / Concillation / ፣ እርቅ / Medition /፣ ግልግል /
Arbitration / እና ስምምነት / Negotiation / የሚጠቀሱ ሲሆን በሀገራችን ከሚሰራባቸዉ የሽምግልና አይነቶች ዉስጥ ድርድር፣ እርቅ እና ግልግል ይገኙበታል፡፡

1. ስምምነት / Negotiation / ከአማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች ዉስጥ አንዱ ሲሆን ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ሰዎች ፣ድርጅቶችና ተቋማት በሆነ ጉዳይ ባለመስማማት ወደ አልተፈለገ ጭቅጨቅና ግጭት እንዳያመሩ ይህንኑ ያልተስማሙበትን ጉዳይ ለጋራ ጥቅምና ደኅንነት ሲባል ቁጭ ብለዉ ሌላ 3ኛ ወገን ጣልቃ ሳይገባ በስምምነት የችግሩ
መነሻ በሆነዉ ጉዳይ ላይ መፍትሔ የሚያስቀምጡበት ዘዴ ነዉ፡፡ ይህ የድርድር ስምምነት በተቻለ መጠን በስምምነት የተጨረሰዉ ዕድሜ ያለዉ፣ ሰላምን ይዞ የሚመጣ እና
ለስምምነቱ መሰረት ሆነዉ ጉዳይም ወደ ኋላ የመመለስ ዕድሉም በጣም ዝቅተኛ ነዉ፡፡

2. ድርድር / Concillation / የሚባለዉ የሽምግልና ዘዴ 3ኛ ወገን ባለበት ግራቀኙ ተሸማጋይ ወገኖች የሚደራደሩበት መንገድ ሲሆን 3ኛ ወገን ከመታዘብ በስተቀር በድርድሩ
ጣልቃ አይገባም፡፡ ነገርግን 3ኛ ወገንኖች ተደራዳሪዎች ስሜታዊ ሊሆኑ ስለሚችሉ ተገቢ ወደ አልሆነ አቅጣጫ እንዳያመሩ ለማድረግ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አላቸዉ፡፡ ይህ ድርድሩ የብቻን ወይም የጋርዮሽ ጥቅምን ለማግኘት የሚድረግ ሊሆን ይችላል፡፡

3. እርቅ / Medition / ተዋዋይ ወገኖች በሚመርጡት 3ኛ ወገን አጋዥነት ከዉል ወይም ከዉል ዉጪ በሚመነጭ ህጋዊ ዉጤት ባለዉ ጉዳይ ላይ በክርክር ሂደት ወይም ወደ ፊት
ሊከሰት የሚችል አለመግባባትን ለመፍታት የሚከናወን ሂደት ነዉ፡፡ በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ አካላት ፊት ለፊት ቀርበዉ ገልልተኛ በሆነ 3ኛ ወገን ድርድሩን ለማፋጠን
የታጀበ ሲሆን 3ኛ ወገን ጭብጦቹን በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫና የዉሳኔ ሀሳብ መጠቆም ፣ ተዳራዳሪ ወገኖች ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ነገሩን ከመከላከልና ከመጠቃቃት
ይልቅ በሚያስሟሟቸዉ ነጥቦች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉና በግትርነት ሳይሆን የሚያስማማ አማራጭ ሀሳቦችን እንዲያቀርቡ ግፊት በማድረግና የግራ ቀኙን ጉዳይ በተለይም ለቅራኔ መንስኤ የተባሉትን ምክንያቶች ማድረቅ ነዉ፡፡ ሆኖም ግን 3ኛ ወገኖች ምንም ዓይነት ጫና ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ በዚህ ምክንያት የተለያዩ ወጪዎች ይቆጠባሉ፡፡ የተደራዳሪ ወገኖች ምስጢር ይጠበቃል፡፡ ሰለ ዕርቅ ሂደት በተመለከቱት የግልግል ዳኝነት እና የዕርቅ አሠራር ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1237/2013 አንቀጽ 54- 76 ስር ተደኝግጎ ይገኛል፡ ስምምነቱ
የመነጨዉ ከራሳቸዉ ፍላጎትና ነፃ ፈቃድ በመሆኑ የተሸናፊነት ስሜት የሚፈጠርበት ወገን የለም፡፡ ተደራዳሪዎች እኩል የሆነ ድል ይኖራቸዋል፡፡ ማንም አሸናፊ ወይም ተሸናፊ አይሆንም ሁሉም አሸናፊዎች ይሆናሉ / Win-Win approach / ተግባራዊ ይሆናል፡፡

4. ግልግል / Arbitration / የሚባለዉ የሽምግልና ዘዴ ደግሞ ግራቀኙ ተከራካሪ ወገኖች ጉዳያቸዉን ለ3ኛ ወገን አቅርበዉ የግልግል ደኛዉ የሚሰጠዉን ዉሳኔ የሚቀበሉበት
ድንጋጌዎች፤ በግልግል ዳኝነት እና የዕርቅ አሠራር ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1237/2013 አንቀጽ 6- 53 የተመለከቱት ድንጋጌዎችም ስለ ግልግል አደራረግና አፈፃፀም የሚገዙ
ናቸዉ፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች ይዘት የምንገነዘበዉ ጉዳይ በሕጉ አግባብ የተደረጉ የግልግል ስምምነቶች ሊፈጸሙ የሚችሉ ስለመሆኑ ነዉ፡፡ ግልግል ዉል ነዉ፡፡ ምክንያቱም የዉል
ግዴታዎች የሚያቋቁሙበት፣የሚለወጡበት ወይም ቀሪ የሚሆኑበት ስምምነት እንደመሆኑ መጠን ዉል ስለመኖሩ መሟላት የሚገባቸዉ ነገሮች በግልግል ስምምነትም ተሟልተዉ ሊገኙ ይጋባል፡፡ በመሆኑም የግራቀኙ ተሸማጋዮች ወገኖች ችሎታ ፣የግልግል ጉዳይ ሕጋዊነት እና በሕጉ
የሚፈለግ ከሆነ ፎርም ተሟልተዉ መገኘት የግልግል ስምምነት መኖሩን የምናረጋግጥባቸዉ ጉዳዮች ናቸዉ፡፡ስለሆነም በግልግል ሽምግልና ዘዴ ቀዳሚዉ እርምጃ ግራቀኙ ወገኖች በህጉ የሚፀና የግልግል ስምምነት ገብተዉ መገኘት ነዉ፡፡ በግልግል ዳኛ የሚሰጥ ዉሳኔ የመጨረሻ ነዉ፡፡

ከዚህ ላይ ልናስተዉለዉ የሚገባ ሌላዉ ጉዳይ የአስተዳደር ዉሎች እና ሌሎች በአዋጅ ቁጥር 1237/2013 አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 1-10 የተጠቀሱት በግልግል ዳኝነት አካል እንዳይታዩ ሕግ አዉጭዉ አካል ስለ መምረጡ ነዉ፡፡ በተጨማሪ የፌዴራል ሰበር ሰሚችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 127459 መስከረም 23 ቀን 2010 ዓ.ም በዋለዉ ችሎት ሰፊ ትንታኔ እና አስገዳጅ ዉሳኔ ሰጥቶበት ይገኛል፡፡

ቸር ሰንብቱ
ፌናን ተጊበሉ
ሚያዝያ 11/2013 ዓ.ም
“የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011” አንቀጽ 50 ድምጽ መስጠትን በተመለከተ የሚከተሉት ነጥቦች ተቀምጠዋል፡፡ መልካም ንባብ!
ማንኛውም መራጭ በአካል በመገኘት በሙሉ ነፃነት ድምፅ ይሰጣል፡፡
እያንዳንዱ መራጭ ድምፅ የሚሰጠው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡
ማንኛውም መራጭ በመራጭነት በተመዘገበበት የምርጫ ጣቢያ ብቻም ቢሆን ድምፅ ለመስጠት የሚችለው:-
የመራጮች መታወቂያ ካርድ ሲኖረው፤
በመራጮች መዝገብ ላይ ስሙ ሰፍሮ ሲገኝ፤ እና
ድምፅ ያልሰጠ መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ፤ ነው፡፡
ቸር ያሰማን! (15/08/2013 ዓ.ም) (ኦምኒኤል)
“የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011” አንቀጽ 52 ድጋፍ የሚፈልጉ መራጮችን በተመለከተ የሚከተሉት ነጥቦች ተቀምጠዋል፡፡
መልካም ንባብ!
አካል ጉዳተኞች፣ አረጋዊያን እና ነፍሰ ጡሮች በምዝገባም ሆነ በድምጽ አሰጣጥ ሂደት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል።
በምርጫ ድምፅ አሰጣጥ ምልክት ለማድረግና የድምፅ መስጫ ወረቀቱን ወደ ድምፅ መስጫው ሳጥን ለመክተት እርዳታ የሚያስፈልገው ማንኛውም መራጭ የሚረዳውን ሰው እራሱ የመወሰን መብት አለው፡፡
ምርጫ አስፈጻሚው መራጩ መብቱን አውቆ እንዲጠቀምበት ለማድረግ በተቻለው አቅም ያስረዳዋል፡፡
ከላይ የተደነገገው እንደ ተጠበቀ ሆኖ በድጋፍ ፈላጊው የተመረጠው ሰው ዕድሜ 18 ዓመት እና ከዚያ በላይ ሆኖ እጩ ወይም የእጩ ተወካይ መሆን የለበትም፡፡
ቸር ያሰማን! (15/08/2013 ዓ.ም) (ኦምኒኤል)
ከፍርድ_በፊት_ስለሚሰጥ_የእስራት_ትዕዛዝ (ፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 147-150)

ከሳሹ ወይም ተከሳሹ የተከሳሽ ከሳሽ በሚሆንበት ጊዜ ሌላኛው ወገን ዋስትና እንዲሰጥ ለፍ/ቤቱ ማመልከት ይችላል፡፡
ማመልከቻው በመኃላ ቃል የተደገፈ መሆን አለበት፡፡
ማመልከቻው ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችለው በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 147 (1)(ሀ) ና (ለ) ሥር የተዘረዘሩት ሁኔታዎች ሲረጋገጡ ነው፡፡ ሁኔታዎቹም ሀ/ ተከሳሹ በማንኛውም ሁኔታ የዳኝነት ሥርዓቱን የሚያስናክል ድርጊት ሲፈጽም ወይም ለ/ተከሳሹ ከኢትዮጵያ ግዛት ለመውጣት ሲዘጋጅና መውጣቱም ፍርዱን እንዳይፈጽም የሚያደርገው ሲሆን ነው፡፡
ፍ/ቤቱ ጥያቄውን ከተቀበለ ተከሳሽ ታስሮ እንዲቀርብ ያዛል፡፡
ተከሳሹ የሚፈለግበትን ዕዳ በመያዣ ካስቀመጠ የእስር ትዕዛዙ ተፈፃሚ አይሆንም፡፡
ተከሳሹ መያዣውን ካላስቀመጠ ወይም ፍ/ቤት ቀርቦ በቂ ምክንያት ካልሰጠ በቂ መያዣ እንዲያስቀምጥ ወይም ዋስ እንዲጠራ ይታዘዛል፡፡
የዋስትናው ወይም የመያዣው ዓይነትና ልክ እንዲሁም ዋስትናው የሚቆይበት ጊዜ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 148(1) መሠረት ይወሰናል፡፡
ተከሳሹን ለማቅረብ ዋስ የሆነ ሰው ሳያቀርብ የቀረ እነደሆነ ተከሳሹ ሊከፍል የሚገባውን ገንዘብ እንዲከፍል ይገደዳል (ፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.148(2))፡፡
በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 149 በተደነገገው መሠረት የዋስትና ግዴታ ሊወርድ ይችላል፡፡ ዋስትናው ሲወርድ ተከሳሹ ሌላ ዋስ ማቅረብ ወይም ተመጣጣኝ የሆነ መያዣ ማስቀመጥ አለበት፡፡ተከሳሹ ይህን ግዴታ ለመፈፀም እምቢተኛ ከሆነ እንደሁኔታው እስከ ስድስት ወር በማረፍያ ቤት እንዲቆይ ለማዘዝ ይቻላል (ፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.150)፡፡ ተከሳሹ አዲስ ዋስ ለመጥራት ወይም መያዣ ለማስጠት ዓቅም የሌለው ከሆነ ግን ይህ ትዕዛዝ መሰጠት የለበትም፡፡ ተከሳሹ በማንኛውም ጊዜ ትዕዛዙን ከፈፀመ የማሰር ትዕዛዙ መነሳት አለበት፡፡
mr zee
ስህተት ያለበት ውሳኔ ስለማስተካከል
ፍ/ቤት በሰጠው ውሳኔና ትዕዛዝ ላይ የአጻጻፍ ስህተት፣ የቁጥር አጻጻፍ
ጉድለት ወይም ያልታሰበና ባለማስተዋል የተዘለለ ድንገተኛ የቃል ስህተት
እንዲታረም በተከራካሪዎች የሚቀርብ አቤቱታ
አንድ ፍርድ ቤት በክርክሩ ዋነኛ ጭብጥ ላይ አከራክሮ የሰጠውን ውሳኔ
ወይም ትዕዛዝ ስህተትን ማረም በሚል ሊያሻሽል ወይም ሊለውጥ አይችልም፡፡
ሰ/መ/ቁ. 37303 ቅጽ 8፣ ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 208
በማንኛውም ፍ/ቤት በሚካሄድ ክርክር ሥነሥርዓቱን ያልተከተለ ክስ የቀረበ
እንደሆነ ወይም በክሱ ሂደት ሕጉ ያስቀመጣቸው የሥነሥርዓት ደንቦች በአግባቡ
ያልተፈፀሙ እንደሆነ ፍርድ ቤት ሥርዓቱ ከሚያዘው ውጪ የተሠራውን በከፊል
ወይም ሙሉ በሙሉ ሊሰርዝ ይችላል፡፡ ይህም የሚከናወነው በተከራካሪዎች
አመልካችነት ብቻ ሳይሆን በፍርድ ቤቱ በራሱ አነሳሽነትም ጭምር ነው፡፡
በመሆኑም በዚህ መርህና ደንብ መሠረት በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ ዳኞች
በሚያካሂዱት የዳኝነት ሥራ የሥነሥርዓቱን ደንብ ያልተከተለ ክንውን
በራሳቸውም ሆነ በአስተዳደር ክፍሉ መፈፀሙን ሲያውቁ ወይም ሲደርሱበት
ስህተቱን እንዲያርሙ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በፍርድ ቤቶች አካባቢ የሚታየው የተለመደው አሠራር ዳኛ የሰጠውን
ትዕዛዝ መቀየር አይችልም፣ መቀየር የሚችለው የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ብቻ
ነው የሚል ቢሆንም ይህ በተለምዶ የዳበረው አሠራር የሥነሥርዓቱ ሕጉ
ያሰፈረውን መሠረታዊ መርህ የሚጻረር ነው፡፡ ሥነ ሥርዓት ነክ የሆነን ጉዳይ
የሚመለከት እስከሆነ ድረስ ባለጉዳዮች ወደ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት መሄድ
ሳያስፈልጋቸው ስህተቱን ለፈፀመው ፍርድ ቤት ማመልከት ይፈቀድላቸዋል፣
ዳኞችም እርግጥም ሰህተት መሠራቱን ካመኑበት ስህተቱን የማረም ሥልጣንም
አላቸው፡፡
ሰ/መ/ቁ. 17352 ቅጽ 1
Mr zee
ጤና ይስጥልኝ
አንድ ሰው በአንዳንድ ንብረቱ ላይ ያለውን መብት ከሌላው ወገን ላይ የሚጠይቅበትን ጊዜ በአንዳንድ ድጋጌዎች ላይ ተቀምጦ የምናገኘው ሲሆን ይህም ጊዜ የሕርጋ ጊዜ የሚባል መሆኑንና በዚሁ ጉዳይ ላይ የሚከተለውን አስፍረናል፤
መልካም ምንባብ!
በኢትዮጰያ የፍትሐ ብሔር ሕግ ስለ ይርጋ ተደንግጎ የምናገኘው ከቁጥር 1845 እስከ ቁጥር 1856 ድረስ ሲሆን ከእነዚህ ድንጋጌ የምንረዳው ውል እንዲፈጸም ወይም ካለመፈጸም በተነሳ የደረሰ ጉዳትን መጠየቅ የሚቻለው በአስር ዓመት ሲሆን የይርጋ ቀኑ መቁጠር የሚጀምረውም ግዴታውን ለመጠየቅ ተገቢ ከሆነው ወይም በመብቱ መሰረት ከሚጥልበት ቀን ጀምሮ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
ደረጀ ማርቆስ
መልካም ቀን!
ሚያዚያ 2013 ዓ.ም
ጤና ይስጥልኝ
ጋብቻ በፍቺ ቀሪ በተደረገ ጊዜ የጋራ ንብረታቸውን እንዲካፈሉ የሚደረግ ስለመሆኑ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ የሚመራበት አንዳድ ድንጋጌዎችን ከዚሁ ድንጋጌ ላይ በመነሳት የሚከተለውን እንበል፤
መልካ ምንባብ
ከዚሁ የቤተሰብ ሕግ እንደምንረዳው ባልና ሚስት በፍቺ ወቅት የጋራ ንብረታቸውን ለመካፈል በስምምነት ላይ ያልደረሱ ከሆነና ንብረቱ በዓይነት ሊካፈል የማይችል እንደሆነ ንብረቱ ተሸጦ የተገኘውን ዋጋ እኩል እንዲካፈሉ መደረግ ያለበትነ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
ደረጀ ማርቆስ
መልካም ቀን!
ሚያዚያ 2013 ዓ.ም
በ“የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና የብሔራዊ መታወቂያ (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር 1049/2009 መሠረት “የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና የብሔራዊ መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 760/2004” አንቀጽ 36 ስር የፍቺ ምዝገባ ቦታ ፍቺው በተፈጸመበት አቅራቢያ የሚገኝ የአስተዳደር ጽሕፈት ቤት ይሆናል የሚለው ድንጋጌ ተሰርዞ በሚከተለዉ አዲስ አንቀጽ 36 ተተክቷል፤የፍቺ ምዝገባ ቦታ ፍቺዉ የተፈጸመበት ፍርድ ቤት አቅራቢያ በሚገኝ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ወይም በተፋቺዎች መደበኛ መኖሪያ ቦታ በሚገኝ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ይሆናል፡፡
አዋጁ ያሻሻላቸውን ድንጋጌዎች በሰፊው ለመቃኘት ያስችላችሁ ዘንድ ሁለቱንም አዋጆች አያይዤላችኋለው፡፡
ቸር ያሰማን (19/09/2013 ዓ.ም) (ኦምኒኤል)
በወንጀል ሕጋችን አንቀጽ 378 መሠረት ማንም ሰው በሐሰት በተዘጋጀ ወይም ወደሐሰት በተለወጠ ሰነደ እያወቀ የተገለገለበት እንደሆነ፤ ወንጀል ሕጋችን በአንቀጽ 375 በተደነገገው ቅጣት መሠረት ከሦስት ወር በማያንሰ ቀላል እሥራት፣ ወይም ነገሩ በጣም ከባድ በሆነ ጊዜ ከአሥር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡ ሆኖም ይህ ድንጋጌ ለመተግበር ምን ምን ነጥቦች ከግንዛቤ እንደሚወሰዱ ለማውቅ ስለሚረዳ በታህሳስ 19 ቀን 2008 ዓ.ም በሰ/መ/ቁ. 101618 የተወሰነውን ውሳኔ ታነቡት ዘንድ ከታች አስፍሬላችኋለሁ፤መልካም ምንባብ!


የሰ/መ/ቁ. 101618
ታህሳስ 19 ቀን 2008 ዓ.ም
ዳኞች ፡- አልማው ወሌ
ዓሊ መሐመድ ተኽሊት ይመስል እንዳሻው አዳነ ቀነዓ ቂጣታ
አመልካች፡- የደቡብ ብ/ብ/ሕ/መ/ፀረ- ሙስና ኮሚሽን - ዐ/ህግ የቀረበ የለም
ተጠሪ፡- መስከረም ፋንታዬ የቀረበ የለም
መዝገቡን መርምረን የሚከተውን ፍርድ ሰጥተናል፡፡

ፍ ር ድ
ይህ የሰበር ጉዳይ መንግስታዊ ሰነዶችን አስመስሎ ማዘጋጀትና ወደ ሐሰት መለወጥ የሙስና ወንጀል ድርጊትን የሚመለከት ክርክር ነው፡፡ የጉዳዩ አመጣጥ ሲታይ፡- የሥር ከሳሽ /የአሁን አመልካች / ለጌድኦ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ባቀረበው ክስ ተከሳሽ የወንጀል ሕግ ቁ. 379/1/ሀ በመተላለፍ ተከሳሽ በ26/03/2001 ዓ.ም የንግድ ሥራ ፈቃድ ቁጥር የተጠቀሰ የንግድና ኢንዲስትሪ ቢሮ የንግድ ምዝገባ ፈቃድ ክትትልና ድጋፍ አሰጣጥ የሥራ ሂደት በሚል የሚጀምር እና በሀሮ ወላቦ ክ/ከተማ ንግድ ምዝገባና ፍቃድ ክትትልና ድጋፍ አሰጣጥ የስራ ሂደት የተዘጋጀ በማስመሰል በስሙ የተዘጋጀ የቡና አቅራቢነት ሀሰተኛ ንግድ ፈቃድ በሀሰተኛ ክብ ማህተም፣ ሀሰተኛ ስምና ስልጣን ቲተሮች የተዘጋጀውን ሰነድ በመያዝ በቀን 18/08/2005 ዓ.ም 9፡30 ሰዓት በሚሆንበት ጊዜ ከሀሮ ወላቡ ክ/ከተማ ንግድ ኢንዱስትሪ ጽ/ቤት ወደ ጌድኦ ዞን ንግድ ማስፋፊያ ይዛወርልኝ በማለት ሲገለገል ሊያዝ ችሏል ፡፡ በመሆኑም ተከሳሹ የሕዝብ ጥቅም የሚሰራበት ሰነድ ላይ በሀሰት የተዘጋጀ ስለመሆኑ እያወቀ በመገልገሉ በፈጸመው መንግስታዊ ወይም ወታደራዊ ሰነዶችን አስመስሎ በማዘጋጀት ወይም ወደ ሀሰት መለወጥ የሙስና ወንጀል ተከሷል የሚል ነው፡፡
የሥር ተከሳሽ/ የአሁን ተጠሪ/ ፍ/ቤት ቀርቦ ይህ ክስ ተነቦለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ቢያቀርብም ፍ/ቤቱ ሳይቀበለው በመቅረቱ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል ወንጀሉን አልፈጸምኩም በማለት ክዶ ተከራክሯል ፡፡
ከዚህ በኋላ ፍ/ቤቱ የዐ/ሕግ ምስክሮችን በመስማት ተከሳሽ እንዲከላከል ባዘዘው መሰረት ተከሳሽ ራሱ ቃሉን በመስጠት የመከላከያ ምስክር አንድ ሰው ያቀረበውን ሰምቷል ፡፡ በመቀጠልም ፍ/ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ተከሳሽ የተከሰሰበት ሐሰተኛ ሰነድ ማዘጋጀት የሚል ሲሆን ተከሳሹ የፈጸመው ድርጊት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 379/1ሀ/ ሥር የሚሸፈን አይሆንም ፣ ተከሳሽ የፈጸመው ድርጊት በወንጀል ሕግ አንቀጽ 378 ሥር የሚሸፈን ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የዐ/ሕግ ምስክሮችም በሰጡት የምስክርነት ቃል ይህ የሀሰት ሰነድ በተከሳሹ መዘጋጀቱን አናውቅም በማለት መስክሯል ፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሰረት በሐሰት የተዘጋጀ ሰነድ እያወቀ የተገለገለበት በወ/ሕ/ቁ. 375 መሰረት ቅጣት ይጣልበታል፡፡ ነገር ግን የዐ/ሕግ ምስክሮች ተከሳሹ ይህ የሐሰት ሰነድ ይዞ ከመገኘት ውጭ በሰነዱ መገልገሉን አልመሰከሩም፡፡ የተከሳሽ የመከላከያ ምስክሮች ተከሳሽ የሐሰት ሰነዱን አለማዘጋጀቱንና አለመገልግሉን፣ ይህንንም የሀሰት ሰነድ አምጥቶ ለሚስቱ የተሰጠው ተከሳሽ ለትምህርት ወደ ጎንደር ዩኒቨርስቲ በሄደበት ወቅት ጉዳይ አስፈጻሚ እንደሆነ የመሰከሩ ሲሆን እና በተባለ ጊዜ ተከሳሹ ዩኒቨርስቲ እንደነበር በዩኒቨርስቲ የተጻፈ ደብዳቤ ያመለክታል፡፡ ተከሳሹ በተጠቀሰው የሐሰት ሰነድ ምንም አይነት የቡና ንግድ ያላካሄደ መሆኑን የዲላ ዙሪያ ወረዳ ግብይትና ኃ/ሥራ ማህበር ጽ/ቤት መግለጹ እንዲሁም የሚፈለገው ምንም እዳ የሌለ መሆኑን ከገቢዎች ጽ/ቤት የተጻፉ ደብዳቤዎች ያስረዳሉ፡፡ ተከሳሹ በሀሰት ሰነድ አለመገልገሉ የግራ ቀኙ ማስረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህ ተከሳሹ ይህ ሰነድ ይዞ መገኘቱ እንደወንጀል ሊቆጠር ስለማይገባ ተከሳሹ ከተከሰሰበት የወንጀል ክስ በነጻ እንዲለቀቅ ወስኗል ፡፡ የሥር ከሳሽ ይህን ውሳኔ በመቃወም ቅሬታውን ለደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክ/መ/ጠቅላይ ፍ/ቤት እና ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረበ ቢሆንም ፍ/ቤቶች ቅሬታውን ባለመቀበል ውድቅ በማድረግ የሥር ውሳኔ በማጽናት ወስኗል ፡፡ የአሁን የሠበር አቤቱታ የቀረበው ይህን ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው፡፡ አመልካች በ27/09/2006 ዓ.ም የተጻፈ አቤቱታ የሥር ፍ/ቤት ለወ/ሕ/ቁ. 379/1፣ሀ/ የሰጠው የሕግ ትርጉም አግባብነት የሌለው እና መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው፡፡ የዐ/ህግ ምስክሮች ተጠሪው በሐሰተኛ የንግድ ፈቃዱ እያወቀ መገልገሉን አስረድተዋል፡፡ ስለዚህ የሥር ፍ/ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት በመሆኑ እንዲታረምልን ተጠሪ ላይ ተገቢው የጥፋተኝነት እና ቅጣት ውሳኔ እንዲወሰንበት በማለት አመልክተዋል፡፡ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን በማየት ፣ ተጠሪ ሐሰተኛ የንግድ ፈቃድ ተጠቅሞ ማህደሩ ከአንዱ የመንግስት መ/ቤት ወደ ሌላ እንዲዛወርለት ጠይቆ ይህንኑ ሂደት በማስፈጸም ላይ እያለ የተደረሰበት ሆኖ ሳለ ድርጊቱ የወንጀል ሃላፊነትን አያስከትልም ተብሎ በነጻ የመሰናበቱ፣ አግባብነት ለመመርመር ያስቀርባል በማለት ተጠሪ መልስ እንዲሰጥ በታዘዘው መሰረት ታህሳስ 06 ቀን 2007 ዓ.ም የተጻፈ መልስ አቅርበዋል፡፡ የመልሱም ይዘት ተጠሪ ሀሰተኛ ሰነድ መሆኑን እያወቅሁ ማህደር ከአንዱ የመንግስት መ/ቤት ወደ ሌላ የመንግስት መ/ቤት እንዲዛወር ያላደረግኩ ስለመሆኑ በማስረጃ አረጋግጠዋል፡፡ የሥር ፍ/ቤቶች ለወ/ሕ/ቁ. 379/1ሀ/ የሰጡት ትርጉም አግባብነት ያለው ነው፡፡ አመልካች ተጠሪ ሰነዱ ሀሰተኛ የንግድ ፈቃድ መሆኑን እያወቅኩ ስለመገልገሌ በማስረጃ ያላረጋገጠ ስለሆነ የቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት የለውም፡፡ ስለዚህ የሥር ፍ/ቤቶች አመልካች ያቀረበው ወንጀል ክስ በማስረጃ ባለመረጋገጡ ተጠሪን በነጻ በማሰናበት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የሌለው በመሆኑ ውሳኔው እንዲጸናልኝ በማለት ተከራክረዋል፡፡ አመልካች በ04/05/2007 ዓ.ም የተጻፈ የመልስ መልስ አቤቱታውን በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡
የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ እንደተመለከተው ሲሆን፤ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ እና መዝገቡ ያስቀርባል ሲባል ከተያዘው ጭብጥ አንጻር እንደሚከተለው መርምሯል፡፡ መዝገቡን እንደመረመርነው አመልካች ባቀረበው ክስ መሰረት የቀረቡት ምስክሮች በሰጡት የምስክርነት ቃል መንግስታዊ ወይም ወታደራዊ ሰነዶችን አስመስሎ ማዘጋጀት ወይም ወደ ሀሰት መለወጥ ያረጋገጡት ነገር እንደሌለ የሥር ፍ/ቤት ውሳኔ ያመለክታል፡፡ እንዲያውም የዐ/ሕግ ምስክሮች እንደገለጹት ተጠሪን ከየት አመጥተህ ነው ብሎ ሲጠይቁት እሱ ለትምህርት በሄደ ጊዜ የተወከለ ሰው እንዳወጣለት እና ተጠሪው ሰነዱን ማዘጋጀቱን እና መገልገል አመለገልገሉን እንደማያውቁ መስክረዋል ፡፡ የሥር ፍ/ቤት አመልካች ያቀረበውን ክስ ከምስክሮች ቃል አንጻር ሲታይ ተጠሪ የፈጸመው ድርጊት የተባለውን ድርጊት እንደማይሸፍን በመግለጽ ወደ ወ/ሕ/ቁ. 378 መለወጡ በአግባቡ ነው እንጂ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ፈጽመዋል የሚያስብል ነገር የለም፡፡ የሥር ፍ/ቤቶች በፍሬ ነገር ደረጃ እንዳረጋገጡት ዐ/ሕግ ያቀረባቸው ማስረጃዎች ተጠሪው ይህን ሀሰተኛ የንግድ ፈቃድ አዘጋጅቶ እያወቀ የተገለገለበት እንደሆነ የሚያረጋግጡት አይደለም፡፡ በወ/ሕ/ቁ. 378 መሰረት የወንጀል ሃላፊነት ሊያስከትል የሚችለው በሀሰት የተዘጋጀ ወይም የተለወጠ ሰነድ እያወቀ የተገለገለበት እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ተጠሪ እና ያቀረበው መከላከያ ምስክር በሰጡት ቃል ተጠሪ ይህን ሀሰተኛ የንግድ ፈቃድ እንዳላዘጋጀ እና ሐሰተኛ መሆኑን አውቆ እንዳልተገለገለበት ገልጿል፡፡ በሌላ በኩል በስር ፍ/ቤት የቀረበው የሠነድ ማስረጃ ተጠሪ በዚህ ሀሰተኛ የንግድ ፈቃፈድ በመገልገል ያካሄደው የቡና ንግድ እንደሌለ አረጋግጧል፡፡ ስለዚህ አመልካች የሥር ፍ/ቤቶች ተጠሪው ይህ ሀሰተኛ የንግድ ፈቃድ በማዘጋጀት እያወቀ የተገለገለበት መሆኑን በማስረጃ አላረጋገጠም በማለት ተጠሪ ከተከሰሰበት ወንጀል በነጻ እንዲሰናበት የሠጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጿሟል በማለት ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት የለውም፡፡ የሥር ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ስለሌለው የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡




ው ሳ ኔ

1. የጌድኦ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ . 09459 በ30/05/2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ እና የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክ/መ/ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 61255 በ26/06/2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ እና የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክ/መ/ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ. 61563 በ14/08/2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የሌለው በመሆኑ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 195/2፣ለ፣2 መሰረት ጸንቷል፡፡
2. የዚህ ውሳኔ ግልባጭ ለስር ፍ/ቤቶች ይድረስ ብለናል፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መ/ቤት ይመለስ ብለናል፡፡
የመከላከል መብት
• የተከሰሱ ሰዎች የቀረበባቸውን ማናቸውንም ማስረጃ የመመልከት፣ የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ፣ ለመከላከል የሚያስችላቸውን ማስረጃ የማቅረብ ወይም የማስቀረብ እንዲሁም ምስክሮቻቸው ቀርበው እንዲሰሙላቸው የመጠየቅ መብት
የተከሰሱ ሰዎች በህገ መንግስቱ ከተከበረላቸው ሰብዓዊ መብቶች መካከል “የመከላከል መብት” አንዱ መሆኑን ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግስት አንቀጽ 20/4/ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚህ አንቀጽ መሰረት የተከሰሱ ሰዎች “የቀረበባቸውን ማናቸውንም ማስረጃ የመመልከት፣ የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ፣ ለመከላከል የሚያስችላቸውን ማስረጃ የማቅረብ ወይም የማስቀረብ እንዲሁም ምስክሮቻቸው ቀርበው እንዲሰሙላቸው የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡” ስለዚህ የመከላከል መብት ሕገ መንግስታዊ ጥበቃ ያገኘ መብት መሆኑን ያስገነዝባል፡፡
ይህን “የመከላከል መብት” በተመለከተ ፍ/ቤቶች ያላቸው ሚና ሲታይ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 13/1/ መሰረት “የማክበርና የማስከበር ሃላፊነትና ግዴታ አለባቸው” ከዚህ አኳያ ፍ/ቤት የተከሰሱ ሰዎች የመከላከል መብታቸውን በሚገባ መጠቀም እንዲችሉ አስፈላጊውን ሁኔታ ለማመቻቸት በሕግ አግባብ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅበታል እንጂ በምንም መልኩ ይህን መብት ለሚገድብ ድርጊት አስተዋጽኦ ማድረግ የለበትም፡፡ ፍ/ቤት የተቀላጠፍ ፍትህ አሰጣጥን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተከሰሰው ሰው ምስክሮቹን ለማቅረብ ያለው አቅም እና የተመቻቸ ሁኔታ፣ በማረሚያ ቤት መሆኑን እና አለመሆኑን፣ የመከላከያ ማስረጃና ምስክሮችን ለማቅረብ የሚጠይቀውን እገዛ፣ በቂ ነው ሊባል የሚችል ጊዜ እና አጠቃላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዚህ መብት ተጠቃሚ እንዲሆን አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ስለዚህ ፍ/ቤት ይህን ሕገ መንግስታዊ ሃላፊነትና ግዴታውን በአግባቡ መወጣት አለበት፡፡
ሰ/መ/ቁ. 100860 ቅጽ 18፣ ኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግስት አንቀጽ 20/4/፣ 13/1/
በወንጀል ጉዳይ የተከሰሱ ሰዎች የቀረበባቸውን ማንኛውንም ማስረጃ የመመልከት፣ የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ፣ ለመከላከል የሚያስችላቸው ማስረጃ የማቅረብ ወይም የማስቀረብ እንዲሁም ምስክሮቻቸው ቀርበው እንዲሰሙላቸው የመጠየቅ መብት እንዳላቸው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት በአንቀጽ 20(4) ተደንግጎ የሚገኝ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ይህንን ሕገ መንግስታዊ መብት ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት ደግሞ ክስ የቀረበባቸው መሆኑን በወ/መ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 123 በተመለከተው መሰረት በሚላክ መጥሪያ እንዲያውቁት ሲደረግ ነው፡፡
ሰ/መ/ቁ. 94227 ቅጽ 16፣ ኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀጽ 20(4)
ምንጭ
የኢ/ ፌ/ዴ/ሪ/ሕገ መንግስት
የኢ/ፌ/ዴ/ሪ/ወንጀል ሕግ
mr zee
#ለወራሽነት ብቁየሚያደርጉ_ነገሮች_ምንድን_ናቸዉ
ለወራሽነት ብቁ የሚያደርጉ በሕጉ የተቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎችን ሳያሟሉ ወራሽ መሆን አይቻልም፡፡ ይልቁንም አንድ ሰዉ ወራሽ ለመሆን በሕጉየተቀመጡትን ወራሽ ለመሆን መሟላት ያለባቸዉን ቅድመ ሁኔታዎች ሟሟላት አለበት፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች ያላሟላ ወራሽ በኑዛዜ ስሙ ቢጠቀስም ወይም በሕግ ወራሽነቱ ቢገለፅም ከውርሱ ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም፡፡
ለወራሽ ብቁ ለመሆን የሚያስፈልጉት ቅድመ ሁኔታዎች፡-
(1) በሕይወት መኖር እና
(2)ለወራሽነት የማይገባ አለመሆን ናቸው፡፡

1) #በሕይወት_መኖር
✅በፍ/ብ/ሕ/ቁ 830 ላይ እንደተገለፀው አንድ ሰው ወራሽ ለመሆን አውራሹ በሚሞትበት ወቅት በሕይወት ያለ መሆን አለበት፡፡
✅በሌላ አገላለፅ ሟች ሲሞት ያልነበሩ ወይም ሟችን /አውራሽን / ቀድሞ የሞተ መውረስ አይችሉም፡፡ ነገር ግን በልዩ ሁኔታ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 834 ላይ እንደተገልፀው ሟች በሚሞትበት ወቅት በእናቱ ፅንስ ውስጥ ያለ ህፃን ተወልዶ 48 ሰዓት በሕይወት ከቆየ ውርስ ሲከፈት እንደነበረ ተቆጥሮ የመውረስ መብቱ ይጠበቅለታል፡፡

✅እዚህ ነጥብ ላይ ሌላኛው አጨቃጫቂ ጉዳይ አብሮ በአንድ ጊዜ የሞቱ ሰዎች ጉዳይ ነው፡፡
አብሮ ሟቾቹ አንዱ አንዱን የሚወርስ ከሆነ የአንደኛው ውርስ ሲከፈት ሌላኛው በሕይወት መኖር አለት የሚለውን ቅድመ ሁኔታ ለማሟላት የትኛው ቅድሚያ እንደሞተ ማረጋገጥ አዳጋች የሚሆንበት ጊዜ ያጋጥማል፡፡ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 832 ላይ ለዚህ ጉዳይ መፍትሄ አስቀምጧል፡፡ ይህም ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ሰዎች አብረው የሞቱ እንደሆነ እና የትኛው በኋላ የሞተው የሚለውን ማረጋገጥ ካልተቻለ ከአብሮ ሟቾቹ ሰዎች ኃብት ወራሽነት ምንም ሳያገኝ የነዚህ ሰዎች የያንዳንዳቸው ውርስ በመጨረሻ እንደ ሞተ ዓይነት ተቆጥር ይወሰናል፡፡

2) #ለወራሽነት_የማይገባ_አለመሆን

✅ወራሽ ለመሆን ከሚያስፈልጉት ቅድመ ሁኔታዎች ሌላኛው ለወራሽነት የማይገባ አለመሆን ነው፡፡

✅አንድ ወራሽ ለወራሽነት የማይገባ የሚሆነው በፍ/ብ/ሕ/ቁ 838 ላይ እንደተጠቀሰው በአውራሹ ወይም ወደ ታች የሚቆጠሩ ተወላጅ/ዎች/ ወይም ወደ ላይ የሚቀጠሩ ወላጆች ወይም ባል ወይም ሚስት አስቦ በመግደል የተፈረደበት ወይ ለመግደል ሙከራ የተቀጣ ወይም በሀሰት በመወንጀል ወይም
በመመስከር አንደኛውን የሞት ፍርድ ወይም ከአስር ዓመት በበለጠ የፅኑ እሥራት ቅጣትን ለማስከተል የሚያሰጋ ሆኖ የተቀጣ ከሆነ ነው፡፡ እነዚህን ከላይ
የተገለፁትን ድርጊቶች የፈፀመ እና የተቀጣ ሰው ወራሽ መሆን አይችሉም፡፡ ነገር ግን ወራሽ የሆነው ሰው በነዚህ በተጠቀሱ ሰዎች ላይ ወንጀሉን ወይም
የወንጀሉን ሙከራ ያደረገው አውራሹ ከሞተ በኃላ ከሆነ የወራሽነት መብቱን ማጣት አይፈፀምበትም፡፡

✅ሌላው ለወራሽነት የማይገባ የሚያደርገው ምክንያት ሟች በነፃነት እንዳይናዘዝ ተጽእኖ ማሳደር ነው፡፡ ይህም አውራሽ ከመሞቱ በፊት ባሉት ሶስት ወር ውስጥ የአውራሽን ሁኔታ ከግምት አስገብቶ ኑዛዜ እንዲይደርግ፣ እንዳይለውጥ ወይም እንዳይሽር የከለከለ እንደሆነ ወይም አስቦ ያለ ሟች ፍቃድ የመጨረሻውን ኑዛዜ ያበላሸ፣ እንዳይገኝ ያደረገ፣ ያጠፋ ወይም ጉዳየን በማወቅ በሐሰት ኑዛዜ የተጠቀመ እንደሆነ ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት አንድ ሰው ከጥፋቱ መጠቀም የለበትም ከሚለውን የሕግ መርህ በመነሳት ነው፡፡
ምንጭ
የፍትሐብሔር ሕግ
በይነ መረብ
mr zee
በምርጫ ሂደት የተከለከሉ ተግባራት እና የተቀመጡ ቅጣቶች

ሰላም እንደምን ቆያችሁ የበሌ ክ/ከተማ ዓቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ሕግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት የቴሌግራም ቻናል ተከታዮች እንደሚታወቀው ሀገራችን በቅርቡ ሀገራዊ ምርጫ የምታካሄድ ሲሆን ለዚህም ምርጫ መሳካት የምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ጸድቆ በስራ ላይ የዋለ ሲሆን አዋጁ በምርጫ ወቅት መደረግ ያለባቸው እና የተከለከሉ ተግባራት በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን ለዛሬ የመረጥንላችሁ ርዕስ በምርጫ ወቅት የተከለከሉ ተግባራትና ቅጣቶች በአጭሩ ለማብርርት ተሞክሯል መልካም ንባብ፡፡
በምርጫ ሂደት የተከለከሉ ተግባራት እና የተደነገጉ ቅጣቶች
ማንኛውም ሰው ወይም ድርጅት ከቦርዱ ፈቃድ ውጭ ማንኛውንም የምርጫ ሰነድና ቁሳቁስ ያተመ፣ ያባዛ፣ የፈበረከ ወይም በዚህ መልኩ የተዘጋጀን ህገወጥ የምርጫ ሰነድ እና ቁሳቁስ ይዞ የተገኘ ወይም ያደለ እንደሆነ በእስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል፡፡
በድምጽ መስጫ ዕለት በድምፅ መስጫ ጣቢያ አካባቢ ድምፅ ከመስጠት ወይም የተሰጠን ህጋዊ ተግባር ከማከናወን ውጭ ሌላ ማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ መሳተፍ ወይም ባልተገባ ወይም በተከለከለ ጊዜ የምርጫን ውጤት ማተም፣ ማባዛት፣ ወይም ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ጥፋቶች መፈጸም ከብር 90 ሺ እስከ ብር 100 ሺ የሚደርስ በገንዘብ መቀጮ ወይም ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ያስቀጣል፡፡
በቦርዱ ወይም በምርጫ አስፈፃሚዎች ገለልተኝነት ጣልቃ ለመግባት ከሞከረ በተለይም መደለያ ወይም የተስፋ ቃል ከሰጠ ወይም ለመስጠት ከሞከረ፣
ምርጫን ለማወክ ወይም እንዳይካሄድ ለማድረግ ወይም በምርጫው ሂደት ወይም ውጤት ላይ ጫና ለመፍጠር በማሰብ ጥላቻን ወይም ፍርሀትን የሚቀሰቅስ ወይም በምርጫው ሂደት ወይም በምርጫው ውጤት ላይ ጫና የሚፈጥር የሐሰት መረጃ አሳትሞ ያሰራጨ ወይም ለማሰራጨት ሙከራ ካደረገ፣
የምርጫ ሚስጢራዊነትን ከጣሰ፣
ከድምጽ እና ከምርጫ ቁሳቁስ ጋር የተያያዙ ክልከላዎችን ከተላለፈ፣
የቦርዱን ወይም የምርጫ አስፈፃሚዎችን እንቅስቃሴ ካወከ፣
የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ወይም የምርጫ ውጤት አገላለፅ፣
የመራጮች ወይም የፓርቲዎችን መብት አስመልክቶ የተጣሉ ክልከላዎችን ከጣሰ፤ ከብር 30 ሺ እስከ ብር 50 ሺ የገንዘብ መቀጮ ወይም ከስድስት ወር በማያንስ ከአንድ አመት በማይበልጥ ቀላል እስራትይቀጣል፡፡
ማንኛውምሰው:- ሆን ብሎ የቦርዱ፣ የምርጫ ዋና አስፈፃሚው፣ የቦርዱ ሰራተኛ ስልጣኑን ወይም ተግባሩንና ኃላፊነቱን በሚያከናውንበት ወቅት እንቅፋት የሆነ ወይም ያደናቀፈ እንደሆነ፤ ወይም፣
የቦርዱን የስብሰባ ሂደት ሆን ብሎ ያቋረጠ ወይም በነዚሁ ቦታዎች በማንኛውም ሁኔታ ያልተገባ ተግባር የፈፀመ እንደሆነ ወይም ሆን ብሎ በቦርዱ የስራ ቦታ ወይም በመታየት ላይ ባለጉዳይ ላይ በሚሰጠው ውሣኔ ወይም ትዕዛዝ ላይ ተገቢ ያለሆነ ተጽእኖ ለማሳደር ሲባል ማንኛውም የሀይል ተግባር የፈፀመ እንደሆነ፣
በ30 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ ወይም ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ይቀጣል፡፡ አንቀጽ156
ማንኛውም ሰው ምርጫ ከተጀመረበት ቀን አንስቶ ውጤት እስከሚገለፅበት ቀን ድረስ የማንኛውንም እጩ ተወዳዳሪ ፖስተርን ወይም የምርጫ
ማስታወቂያን ያበላሸ፣
ያስወገደ ወይም የቀደደ እንደሆነ ከአንድ ዓመት በማይበልጥ እስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል፡፡ አንቀጽ 158
በህገወጥ መንገድ ዓላማን ማስፋፋት የተከለከለ ስለመሆኑ
የአንድን የፖለቲካ ፓርቲ ዓላማ በኃይል ወይም በማስፈራራት ለማስረጽ ማንኛውንም ሰው ወይም ቡድን ማደራጀት ወይም ማሰልጠን ወይም ሰዎችን በግድ መመልመል በህግ ያስቀጣል፡፡
በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተገለፀውን ተግባር ሲፈጸም የረዳ ወይም የተባበረ ማንኛውም ሰው ወይም ቡድን አግባብ ባለው ሕግ ይቀጣል፡፡

በቦሌ ክ/ከተማ ዓቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ሕግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ
የተዘጋጀ ሰኔ 2013