የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
276 subscribers
366 photos
3 videos
137 files
97 links
ይህ የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት ቻናል ስለኢትዮጵያ ሕጎች)ማብራሪያ የሚሰጥበት፣ አዳዲስ ሕጎች የሚጋሩበት፣ ሕግ ነክ ዜናዎችና መረጃዎች የሚተላለፉበት፣ በዳይሬክቶሬቱ የተሰጡ የንቃተ-ሕግ ስልጠናዎች፣ የሕግ መልዕክቶች፣ በራሪ ጽሑፎች እና መሰል ሰነዶች የሚለቀቁበት ነው።
መልካም ቆይታ!
Download Telegram
ጤና ይስጥልኝ!!!
አዲሱን ዓመት ከጀመርን 13 ቀናት አልፈው መስከረምን አጋምሰነዋል፡፡ ይህ የሆነው በጤና በመኖራችን አይደል!
በዚህ ሳምንት የጤና ሚኒስትርዋ ለብዙሀን መገናኛዎች በሰጡት መግለጫ ኮቪድን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት አካል የሆነውን ክትባት መውሰድ የቻሉት 2.6 ሚሊዮን ሰዎች ብቻ መሆናቸውንና ሌሎችን ለመከተብ በሀገሪቱ 1.5 ሚሊዮን ክትባቶች ቢሰራጩም ሕዝቡ ለመከተብ ያለው ፍላጎት ዝቅተኛ መሆኑን ይህ ደግሞ የመከላከል ጥረቱን አድካሚ አድርጎታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ውድ የዚህ መልዕክት አንባቢ ከዚህ በፊት በ2013 መጀመሪያ የወጣውን መመሪያ ቁጥር 30/2013 በዚህ ቴሌግራምም ሆነ በሌሎቹ መገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ የተወራና በዝርዝር የቀረበ ቢሆንም ምን ያህል ተግብረዋል?
የተከለከሉት ተግባራት፡-
ርቀትን ሳይጠብቁ መሄድም ሆነ ብዙ ሰው ባለበት መገኘት፤
የፊት መሸፈኛ ሳያደርጉ ከሰው ጋር አለመቀላቀል፤
በማንኛውም መልኩ አለመጨባበጥና አለመሳሳም፤
ከ50 ሰዎች በላይ በቀብር ጊዜ እንዳይገኙ ማድረግ፤
በቂ የኮቪድ መከላከያ ንጽህና መጠበቂያ ግብዓቶችን ሳያሟሉ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን ክፍት አለማድረግ፤
በስብሰባ፣ በስልጠና፣ በክብረበዓላትና በሰርግ አዳራሹ መያዝ ከሚችለው 1/4/ ብቻ መገኘት እንዳለበት የተደነገገው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተጥሶ ኮቪድ እንደመጣ በየአገልግሎት መስጫ ተቋማቱ በር ላይ ይደረግ የነበረው መታጠቢያ ውሃና ሳሙና የት አለ?
የእጅ ንጽህና መጠበቂያ አልኮል የትኛው ድርጅት ያቀርባል?
በጤና ሚንስትሯ ገለጻ እንደተገለጸው በአዲስ አበባ በፊት የፊት መሸፈኛ ያደርግ የነበረው ነዋሪ እስከ 83 ፐርሰንት ደርሶ የነበረ ቢሆንም አሁን ሶስተኛው ማዕበል እየተስፋፋ ባለበት ወቅት ከ52 ፐርሰንት በላይ የማያደርግ ሕዝብ ሲሆን ከአዲስ አበባ ሲወጣ የማያደርገው ሰው እስከ 100 ፐርሰንት ይደርሳል፡፡
እባካቹን ለራሳችን ባናስብ በኛ ቸልተኝነት የቅርቦቻችን፤ የለፉብንን ወላጆችና ሀገር ባናከስርና ለኛ ጤና ሲባሉ የወጡ ሕግጋትን እናክብር!!
ለሕግ አክባሪዎች ክብርና ጤንነት ይሁን!!
ሲሳይ ሰማኝ (መስከረም 13/2014 ዓ.ም
የተከራይ አከራይ፡- ማለት አንድን ቤት ከአከራይ ተከራይቶ ለሌላ 3ኛ ወገን በኪራይ ማስተላለፍ ነዉ፡፡ በዚህ ጊዜ የተከራይ አከራይ ግብር የሚመለከተዉ ዋናዉን አከራይም 3ኛ የሆነዉ ወገንም ሳይሆን ከአከራይ ተከራይቶ ለ3ኛ ወገን በኪራይ የሰጠዉን ግለሰብ ነዉ፡፡ የሚከፍለዉም ግብር ለዋናዉ አከራይ የሚከፍለዉ ኪራይ እንዲሁም ገቢዉን ለማግኘት ያወጣቸዉ ሌሎች አስፈላጊ ወጪዎች ከተቀነሱ በኋላ ከሚቀረዉ ገንዘብ ነዉ፡፡
ህድአት
መስከረም/2014 ዓ.ም
ተርን ኦቨር ታክስ turnover tax (T.O.T)፡- በንግድ ግንኙነት ዉስጥ ፍትሃዊነትን ለማስፈን ተጨማሪ እሴት ታክስ (value-added tax) ታክስ የሚከፈልበት አመታዊ ግብይት ከ500 ሺ ብር በላይ በመሆኑ በዚህ ግብር ያልተመዘገቡ ሰዎች ግዴታቸዉን እንዲወጡ እና የታክስ ሥርዓቱን ሽፋን የተሟላ ለማድረግ በተርን ኦቨር ታክስ አዋጅ በተቀመጠዉ ተመን መሰረት በማስተካከያነት እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡
ህድአት
መስከረም/2014 ዓ.ም
"የፌደራል የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008"
በቤት ኪራይ ገቢ ላይ ግብር ስለመጣል
1/ ቤት በማከራየት ገቢ የሚያገኝ ሰው በአዋጁ በተመለከተው ምጣኔ ወይም ምጣኔዎች መሠረት በእያንዳንዱ የግብር ዓመት የቤት ኪራይ ገቢ ግብር ይከፍላል፡፡
የኪራይ ገቢ ግብር መጣኔዎች
1/ በድርጅቶች የኪራይ ገቢ ላይ ተፈፃሚ የሚሆነው የግብር መጣኔ 30% (ሰላሳ በመቶ) ነው፡፡
2/ በግለሰቦች የኪራይ ገቢ ላይ ተፈፃሚ የሚሆኑት መጣኔዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ግብር የሚከፈልበት የኪራይ ገቢ በዓመት የኪራይ ገቢ ግብር መጣኔ

0-7,200 0%
7,201-19,800 10%
19,801-38,400 15%
38,401-63,000 20%
63,001-93,600 25%
93,601-130,800 30%
ከ130,800 በላይ 35%

ህድአት
መስከረም/2014 ዓ.ም
ጤና ይስጥልኝ!!
በየትኛውም የሰው ልጆች ዕንቅስቃሴ በተለያዩ ምክንያቶች ልዩነት መኖሩ ተፈጥሯዊ መሆኑ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገር ግን ልዩነቱን ለጉዳት ሳይሆን ለጥቅም በሚውልበት መልኩ እውቅና መስጠት የጤናማና ስልጡን ማህበረሰብ ምልክት በመሆኑ የእዚሁ አስተሳሰብ ክፍል የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 56/2011 በአምስተኛ ክፍሉ ከአንቀጽ 48 እስከ አንቀጽ 50 ባሉት አንቀጾች ልዩ ድጋፍ በቅጥር፣ በምደባ፣ በዝውውር፣ በደረጃ እድገት፣ በቢሮ ምደባ፣ በግብዓት ማሟላት፣ በረጅምና በአጭር የትምህርት እድሎች፣ እና በመሳሰሉት ለእነዚህ ሰራተኞች ሊደረጉ ስለሚገባቸው ልዩ ድጋፎች በግልጽ የደነገገውን ከዚህ እንደሚከተለው እንካቹህ!!
ለሴት ሰራተኞች የሚጠበቁ የስራ ሁኔታዎች
1. ማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት ሴት የመንግስት ሰራተኞች ለማብቃትና በውሳኔ ሰጪ የስራ ቦታዎች ላይ እንዲመደቡ ለማድረግ የሚያስችሉ የተጨማሪ ድጋፍ እርምጃዎች መውሰድ አለበት፡፡
2.ሴቶች በቅጥር በደረጃ እድገት በዝውውር በድልድል በትምህርትና ስልጠና አፈጻጸም የተጨማሪ ድጋፍ እርምጃ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡
3.ነፍሰ ጡር የሆነችን የመንግስት ሰራተኛ በቅጥር ወይም በደረጃ እድገት ከተመደበችበት የስራ መደብ ወደ ሌላ የስራ መደብ መድቦ ማሰራት የተከለከለ ነው ሆኖም ለራሷ ጤንነት ወይም ለጽንሱ አደገኛ መሆኑ በህክምና ማስረጃ ሲረጋገጥ ተስማሚ ወደ ሆነ የስራ መደብ ወይም የስራ ቦታ ተመድባ እንድትሰራ መደረግ አለበት፡፡
3.ማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት ሴት የመንግስት ሰራተኛ ነፍሰጡር በሆነችበት ጊዜና ከወለደችበት ቀን ጀምሮ በአራት ወር ጊዜ ውስጥ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 87 መሰረት በሚደረገው የሰራተኛ ቅነሳ ከስራ ሊያሰናብታት አይችልም፡፡
4.ማንኛዋም ሴት የመንግስት ሰራተኛ አንድ አመት ያልሞላውን ህጻን ልጇን ለማሳከም በህክምና ማስረጃ ለተረጋገጠ ጊዜ ደመወዝ የሚከፈልበት ፈቃድ ይሰጣታል በተለያየ ምክንያት እናት ባትኖር ይህ ፈቃድ የመንግስት ሰራተኛ ለሆነ ልጁ አባት ወይም አሳዳጊ ይሰጣል፡፡
5.ማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት ሴት የመንግስት ሰራተኞች ህጻናት ልጆቻቸውን የሚያጠቡበትና ህጻናቱን የሚንከባከቡበት ህጻናት ማቆያ ማቋቋም አለበት፡፡
ለአካል ጉዳተኞች የሚጠበቁ የስራ ሁኔታዎች
1.አካል ጉዳተኞች በቅጥር በደረጃ እድገት በዝውውር በድልድል በትምህርትና ስልጠና አፈጻጸም የተጨማሪ ድጋፍ እርምጃ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡
2.ማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት የስራ አካባቢው ለአካል ጉዳተኛ ሰራተኞች ምቹ መሆኑን ማረጋገጥ ለስራ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችንና ቁሳቁሶችን ማሟላትና ስለአጠቃቀማቸው አስፈላጊውን ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ አለበት፡፡
3.ማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት ረዳት ለሚያስፈልገው የአካል ጉዳተኛ የሆነ የመንግስት ሰራተኛ ተገቢውን ድጋፍ ሊሰጥ የሚችል ረዳት እንዲመደብለት የማድረግ ሃላፊነት አለበት፡፡
4.በሌሎች ሕጎች በአዋጅ ቁጥር 568/2000፣ በአለማቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት ለአካል ጉዳተኞች የተሰጡ መብቶች ለዚህ አዋጅ አፈጻጸም ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡
አነስተኛ ብሔራዊ ተዋጽኦ ስላላቸው ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚጠበቁ የስራ ሁኔታዎች
1.በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ የሚፈጸም የሰራተኛ ስምሪት የብሄር ብሄረሰብና ህዝቦች ሚዛናዊ ተዋጽኦ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት፡፡
2.በመንግስት መስሪያ ቤቱ ውስጥ አነስተኛ ብሔራዊ ተዋጽኦ ያላቸው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በቅጥር በደረጃ እድገት በዝውውር በድልድል በትምህርትና ስልጠና አፈጻጸም የተጨማሪ ድጋፍ እርምጃ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡
ሲሳይ ሰማኝ (መስከረም 15/2014 ዓ.ም)
ጤና ይስጥልኝ!!
ይህ ሰሞን ክልሎቻችንም ሆነ ፌደራል መንግስታችን በስድስተኛው ዙር በተካሄደ ምርጫ ውጤት መሠረት ለቀጣይ አምስት ዓመት ሀገር ለመምራት በምስረታ እና ዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ ምስረታ የሚካሄደው በሕገመንግስቱ በተሰጣቸው ሥልጣንና ተግባር መሠረት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከሚቋቋሙት የመንግስት አካላት አንዱ የሕገ መንግስት ተርጓሚነት ሥልጣን የተሰጠው የፌደሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ በዚህም መሠረት በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 62 ስር ስለ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የተቀመጠውን እነሆ አንብቡልኝ!
1.የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤን ያደራጃል፡፡
2.የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠን መብትን በተመለከተ በሚነሱ ጥያቄዎች ላይ በሕገ መንግሥቱ መሰረት ይወሰናል፡፡
3.በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው የሕዝቦች እኩልነትና በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት ሥር እንዲሰድና እንዲዳብር ያደርጋል፡፡ (ይንኑ ለማሳካት ከሚደረጉ ተግባራት በየዓመቱ በየክልሎቱ በተራ በበሚዘጋጅ ዓመታዊ የሕዳር 29 የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን ያስታውሷል፡፡)
4.ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በጣምራ የተሰጡትን ሥልጣኖች ያከናውናል፡፡
5.በክልሎች መካከል ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሄ ይፈልጋል፡፡
6.የክልሎችና የፌዴራሉ መንግሥት የጋራ ተብለው የተመደቡ ገቢዎች በሁለቱ መካከል የሚከፋፈሉበትን፤ እንዲሁም የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች ድጐማ የሚሰጥበትን ቀመር ይወስናል፡፡
7.በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕግ ሊወጣላቸው የሚገቡ የፍትሐብሔር ጉዳዮችን ይለያል፡፡
8.ማንኛውም ክልል ይህን ሕገ መንግሥት በመጣስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ያዛል፡፡
9.የምክር ቤቱን የተለያዩ ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎች ያቋቁማል፡፡
10.ምክር ቤቱ የራሱን አፈጉባኤና ምክትል አፈጉባኤ ይመርጣል፤ የራሱን የሥራ አፈጻጸምና የውስጥ አስተዳደር ደንብ ያወጣል፡
ሲሳይ ሰማኝ (መስከረም 15/2014 ዓ.ም)
👍1
ሰላም ውድ የቴሌግራም ተከታታዮቻችን!
በቦሌ ክ/ከተማ አስተዳደር በዐቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ስር ካሉ ሁለት ዳይሬክቶሬቶች አንዱ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት ሲሆን ይሁ ዳይሬክቶሬት በአዋጅ ቁጥር 64/2011ዓ/ም አንቀጽ 18 መሰረት በተሰጠው ስልጣን በፌደራልና በከተማው አስተዳደር የወጡ አዋጆች እና ደንቦች ላይ ግንዛቤ መስጠት አንዱ ተግባሩ ስለሆነ በአዋጅ ቁጥር 56/2010፣ ተያያዥ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ ለሁለት ቀን በቦሌ ክ/ከተማ አስተዳደር ውስጥ ላሉ ሁሉም ጽ/ቤቶች የሥራ ሂደቶች እንዲሁም በቦሌ ክፍለ ከተማ ስር ላሉ ከሁሉም ወረዳዎች ለተውጣጡ የሥራ ሂደቶች ግንዛቤ ለመፍጠር መስከረም 18 እና 19 ቀን 2014 ዓ/ም ባዘጋጀው መድረክ ላይ የተነሱትን ነጥቦች የያዘ ‘power point’ እንዲሁም የአዋጅ ቁጥር 56/2010ን ‘soft copy’ እነሆ ብለናል፡፡
ኦምኒኤል ከበደ (ዐቃቤ ሕግ) (መስከረም 19/2014 ዓ.ም)
ጤና ይስጥልኝ፡!!
በመንግስት ሰራተኝነት ተቀጥረን ስንሰራ
በከባድ ዲሲፕሊን ጥፋት ሊያስቀጡ የሚችሉት ጥፋቶችን ከዚህ እንደሚከተለው አንብባችሁ ራሳችሁን እንድታድኑ ይሁን፡፡!
መልካም ምንባብ!!!
በአዋጅ ቁጥር 56/2010 አንቀጽ 70 ከባድ የዲሲፕሊን ቅጣት የሚያስከትሉ ጥፋቶች፡-
የሚከተሉት ጥፋቶች ከባድ የድስፕሊን ቅጣት የሚያስከትሉ ጥፋቶች ናቸው፡፡
1. ሕጋዊ ትእዛዝን ባለማክበር፣ በቸልተኝነት፣ በመለገም፣ ወይም ሆን ብሎ የአሠራር ሥነ-ሥርዓት ወይም የመንግስትን ፖሊሲ ባለመከተል በሥራ ላይ በደል ማዴረስ፤
2. ጉዳዮችን ሆን ብሎ ማዘግየት ወይም ባለጉዳዮችን ማጉላላት፤
3. ሥራ እንዳይሠራ ሆን ብሎ ማወክ ወይም ከሚያውኩት ጋር መተባበር፤
4. በቀላል የዲስፕሊን ቅጣት እርምጃዎች ባለመታረም ያለበቂ ምክንያት በተደጋጋሚ ከሥራ መቅረት ወይም የሥራ ሰዓት አለማክበር፤
5. በሥራ ቦታ በጠብ አጫሪነት መተባበር፤
6. በልማዳዊ ስካር ወይም በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ በመመረዝ ሥራን መበደል፤
7. ጉቦ መቀበል ወይም እንዲሰጠው መጠየቅ፤
8. በሥራ ቦታ ለሕዝብ ሞራል ተቃራኒ የሆነ ድርጊት መፈጸም፤
9. የሌብነት ወይም የእምነት ማጉደል ድርጊት መፈጸም፤
10. የማታለል ወይም የማጭበርበር ድርጊት መፈጸም፤
11. በመሥሪያ ቤቱ ንብረት ላይ ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት ጉዳት ማድረስ፤
12. በሥልጣን አላግባብ መጠቀም፤
13. በሥራ ቦታ ላይ ፆታዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት መፈፀም፤
14. በዚህ አንቀጽ ከተዘረዘሩት ጋር ተመሳሳይ ክብደት ያለው ሌላ የዲስፕሊን ጉድለት መፈጸም፡፡
ቸር ይግጠምን!
ሲሳይ ሰማኝ (04/02/2013)
ቅምሻ ስለሕገመንግስቱ፡-
ጤና ይስጥልኝ!
ባለ 11 ምዕራፍና ባለ 106 አንቀጹ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገመንግስት የሀገሪቱ የህጎች ሁሉ የበላይና የስልጣንም ምንጭ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡
በዚች መልዕክት በፓርላመንታዊው መንግስት የፕሬዝንዳንትና የጠቅላይ ሚንስትሩን ስልጣንና ሀላፊነት ባጭሩ እናያለን፡፡
ሀ. ፕሬዝዳንቱ/ፕሬዝዳንቷ፡-
የሪፓፕሊኩ ርዕሰብሄር፤ የሁለቱንም የፌደራሉን የሕግ አውጭዎች የጋራ ስብሰባ ይከፍታሉ፤
በአመቱ መጀመሪያ የጋራ ስብሰባ የመንግስቱን የአመት ትኩረት እቅዶች የሚገልጽ ንግግር ያደርጋሉ፤
መንግስቱ ስራውን በሕገመንግስቱ መሰረት ማከናወን ካልቻለ በጠቅላይ ሚንስትሩ ጥያቄ ፓርላማውን በመበተን በስድስት(6) ወራት ውስጥ ጠቅላላ ምርጫ እንዲካሄድ ያደርጋል፤
ፓርላማው ያጸደቀውን አዋጅ በፊርማው ያውጃል፤
በሀገሪቱ ፍርድቤቶች የሚወሰንን የሞት ቅጣት በፊርማ የማጽደቅ፣ወደ ዕድሜ ልክ የመቀየር፣ ታራሚዎችን የይቅርታ ቦርድ በሚያቀርበው ግምገማ ላይ በመመስረት ምህረት የማድረግ፤
በጠቅላይ ሚንስትሩ አቅራቢነት የአንባሳደሮችን ሹመት፣ የከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችን የማዕረግ ዕድገትና የጀብዱ ሽልማት ይሰጣሉ፤
የውጭ ሀገራት አንባሳደሮችንና ልዩ መልዕክተኞችን ሲመጡ የሹመት ደብዳቤያቸውን ሲሄዱም የስንብት ደብዳቤያቸውን ይቀበላሉ፤
የሰልጣን ዘመናቸው ስድስት አመት ሲሆን በስልጣን ከሁለት ጊዜ በላይ መመረጥ አይችሉም፡፡
የተመረጡት ከፓርላማ አባላት ውስጥ ከሆነ ሲመረጡ የፓርላማ መቀመጫቸውን ይለቃሉ፡፡ ሹመታቸውም የሚጸድቀው በፓርላማው አቅራቢነት በሁለቱም ምክርቤቶች ፊት ቀርበው ቃለምሃላ ሲፈጽሙ ይሆናል፡፡
ለ. ጠቅላይ ሚንስትር፡-
ርዕሰመንግስት ናቸው፤
የሚንስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢና የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ናቸው፤
የሚመረጡት ከፍተኛውን የወንበር ብልጫ ካገኘው ፓርቲ ሆኖ ሹመታቸው በቀጥታ በፓርላማ የሚጸድቅላቸው ይሆናል፤
የመንግስታቸውን ወይም የአስፈጻሚ አባላት ሚንስትሮችን አቅርበው በፓርላማው ፊት ያስጸድቃሉ፤
የሚንስትር ዴታዎችን፣ ኮሚሽነሮችን፣ በሚንስትር ማዕረግ የሚሾሙ ሀላፊዎችን በቀጥታ ይሾማሉ፤
የፌደራል ፍርድቤቶችን ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት፤ የጀነራል ኦዲተር ዋና ኦዲተር ሃላፊዎችን በመምረጥ ያስሾማሉ፤ የፌደራል ዳኞችን በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አቅራቢነት ለፓርላማው በማቅረብ ያስሾማሉ፤
የስልጣን ዘመናቸው የአምስት አመታት ወይም አንድ የፓርላማ ዘመን ሲሆን ተደጋግመው መመረጥ የሚከለክላቸው የሕገመንግስት ድንጋጌ የለም፡፡
ቸር ይግጠመን!!
ሲሳይ ሰማኝ
የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣ አዋጅ 721/2004
ሊዝ ምን ማለት ነዉ?
ሊዝ ማለት በጊዜ በተገደበ ዉል መሠረት የከተማ ቦታ የመጠቀም መብት የሚገኝበት የመሬት ይዞታ ስሪት ነዉ
ከተማ የምንለዉ - ማዘጋጃ ቤት የተቋቋመበት ወይም
- ሁለት ሺ ወይም ከዚያ በላይ የህዝብ ቁጥር ያለዉና
- ከዚሁ የህዝብ ቁጥር ዉስጥ 50% የሚሆነዉ የሰዉ ሃይል ከግብርና ዉጭ በሆነ ሥራ ላይ የተሰማራ ሆኖ የሚገኝበት አካባቢ ነዉ
ህድአት
ጥቅምት/2014 ዓ.ም
የሊዝ አዋጅ 721/2004 የወጣበት ምክንያቶች
• የመሬት አጠቃቀም በሕግ እንደሚወሰን በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት የተቀመጠ በመሆኑ
• የኢኮኖሚ እድገት የከተማ መሬት ፍላጎት እንዲጨምር የሚያደርግ በመሆኑና ይህን ፍላጎት ደግሞ ተገቢ የመሬት ሀብት በማቅረብ ምላሽ ሊሰጠዉ ስለሚገባ እና ሂደቱም በሕግ አግባብ መመራት ስላለበት
• ለፍትሐዊ የመሬትና መሬት ነክ ንብረት ገበያ ልማት
• ለነጻ የገበያ ስርዓት መስፋፋት
• ግልጽና ተጠያቂነት ለሰፈነበት እንዲሁም የመሬት በለቤቱንና የመሬት ተጠቃሚዉን መብቶችና ግዴታዎችን ለማረጋገጥ የሚያስችል የመሬት አስተዳደር ሥርዓትን ለመገንባት እንዲያስችል ነዉ
ህድአት
ጥቅምት/2014 ዓ.ም
ጤና ይስጥልኝ፡-
አንድ የፍትሐ-ብሔር ክስ በሚገባ ከተዘጋጀ በኃላ ለተከሰሰው ግለሰብ ወይም ተቋም ክሱ በመጥሪያ የሚላክ ሲሆን ስለዚሁ የመጥሪያ አሰጣጥ በፍትሐ-ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ላይ ከተቀመጠው የሚከተለውን እንበል፡፡

መልካም ምንባብ፡-
በተለየ ድንጋጌ እስካልተቀመጠ ድረስ መጥሪያ የሚሰጠው ለተከሣሹ ለራሱ ሲሆን ተከሣሹ ወኪል ያለው ከሆነም ለወኪሉ፣ መ/ቤት ከሆነም በመዝገብ ቤት በኩል፣ክሱ በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ከሆነም ለንብረቱ ጠባቂ ለሆነ ወይም በዚሁ ንብረት ላይ ለሚገኝ ሰው በመስጠት እንደዚሁም ለተከሳሹ ቤተሰብ ወይም በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ወይም በተከሣሹ መኖሪያ ቤት ላይ በመለጠፍ ወይም በፖስታ ቤት እንዲላክ የሚደረግ ሲሆን ይህም ሆኖ ተከሳሹ መጥሪያ ለመቀበል እምቢተኛ ከሆነ ወይም ካልተገኘ ፍ/ቤቱ መጥሪያው ለተከሳሹ እንደደረሰዉ በመቁጠር ጉዳዩን በሌለበት በማየት ውሣኔ የሚሰጥ ይሆናል ፡፡
ጥቅምት 12/2014
ደረጀ ማርቆስ
ጤና ይስጥልኝ፡-
በፍትሐ-ብሔር ጉዳዮች ተከራካሪ የሚሆን ማንኛውም ወገን በፍ/ቤት የቀረበበትን ክስ ቀርቦ የመከራከርና ፍርድ የማግኘት መብት ያለው ሲሆን ሆኖም ግን ክስ የቀረበበት ወገን ፍ/ቤት ባልቀረበበት ሁኔታ ጉዳዩ በሌለበት ታይቶ ውሣኔ የተሰጠ እንደሆነ በሕጉ የተቀመጠውን ሥነ-ሥርዓት እንደሚከተለው እናስፍር ፡፡

መልካም ምንባብ፡-
ተከሣሽ በጉዳዩ ቀርቦ ያልተከራከረው በበቂ ምክንያት ማለትም መጥሪያ ሳይደርሰው መሆኑ ከተረጋገጠ ፍ/ቤቱ የተወሰነውን ውሣኔ በማንሳት ግራ ቀኙን ማከራከር ያለበት ሲሆን ተከሣሹ በዚሁ በፍ/ቤቱ ከተፈቀደለት በኃላም በድጋሚ ክሱ በሚሰማበት ቀነ-ቀጠሮ ያልቀረበ ከሆነም ፍ/ቤቱም ጉዳዩን እንደገና መርምሮ ውሣኔ የሚሰጥ መሆኑንና ከዚሁ ጋርም ስለመጥሪያ አሰጣጥ በምናይበት ጊዜ ለተቋም የሚላክ መጥሪያ ለመሥሪያ ቤቱ መዝገብ ቤት የሚሰጥ ቢሆንም መ/ቤቱ የመንግሥት መ/ቤት ከሆነ ግን ለመዝገብ ቤቱ ገቢ በመሆኑ ብቻ መጥሪያው ለተቋሙ እንደደረሰ ሊቆጠር የማይገባና መጥሪያውን የመ/ቤቱ ኃላፊዎች ሊያዩት የሚገባ መሆኑንም ልብ እንበል፡፡

ጥቅምት 12/2014
ደረጀ ማርቆስ
ሰላም ውድ የቻናላችን ተከታታዮች! ዕድሜ በመድረሱ የሚጠየቅን የዘለቄታ ጡረታ አበል ስሌትን በተመለከተ እና በጤና ጉድለት የዘለቄታ ጡረታ አበል ስሌትን በተመለከተ ከታች የሰፈሩትን ነጥቦች ታነቡ ዘንድ ጋበዝኳቹ!
በሕግ የተወሰነው የጡረታ መውጫ ዕድሜ በመድረስ ከስራ ለሚሰናበት ሲቪል የመንግስት ሠራተኛ ለመጀመሪያ 10 ዓመት ለፈፀመው አገልግሎት 30% ከ10 ዓመት በላይ ለተፈፀመ ለእያንዳንዱ ዓመት አገልግሎት በ1.25 በማባዛት ከ30% ጋር በመደመር የሚገኘው መቶኛ ውጤት ከመጨረሻዎቹ 36 ወራት አማካይ ደመወዝ ጋር ተባዝቶ የሚሰላ ይሆናል፡፡
ለምሳሌ፡-
የ28 ዓመት አገልግሎት ያለው ሲቪል የመንግስት ሠራተኛ ለመጀመሪያው 10 ዓመት አገልግሎት 30%፣ ከአስር ዓመት በላይ ያለው 18 ዓመት አገልግሎት 18×1.25 = 22.5% ሲሆን በአጠቃላይ 30% + 22.5% = 52.5% ነው፡፡ የመጨረሻዎቹ 36 ወራት አማካይ ደመወዙ 5000.00 ከሆነ የባለመብቱ የዘለቄታ የጡረታ አበል 5,000.00 x 52.5% = 2,625.00 ብር ይሆናል፡፡
በሕግ የተወሰነው የጡረታ መውጫ ዕድሜ በመድረስ ከስራ ለሚሰናበት የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አባል ለመጀመሪያ 10 ዓመት ለፈፀመው አገልግሎት 30% ከ10 ዓመት በላይ ለተፈፀመ ለእያንዳንዱ ዓመት አገልግሎት በ1.65 በማባዛት ከ30% ጋር በመደመር የሚገኘው መቶኛ ውጤት ከመጨረሻዎቹ 36 ወራት አማካይ ደመወዝ ጋር ተባዝቶ የሚሰላ ይሆናል፡፡
ለምሳሌ:-
የ28 ዓመት አገልግሎት ያለው የመከላከያ ሠራዊት ወይም የፖሊስ አባል ለመጀመሪያው 10 ዓመት አግልግሎት 30%፣ከአስር ዓመት በላይ ያለው 18 ዓመት አገልግሎት 18×1.65 = 29.7% ሲሆን በአጠቃላይ 30% + 29.7%= 59.7% ነው፡፡ የመጨረሻዎቹ 36 ወራትአማካይ ደመወዙ 5,000.00 ከሆነ የባለመብቱ የዘለቄታ የጡረታ አበል 5,000.00 x 59.7% = 2,985.00 ብር ይሆናል ፡፡
ከ10 ዓመትና በላይ አገልግሎ በጤና ጉድለት ምክንያት ከሥራ ለሚሰናበት ስቪል የመንግስት ሰራተኛ ወይም የመከላከያ ሰራዊትና ፖሊስ አባል የጡረታአበል የሚወሰነው በዕድሜ ለጡረታ በመድረስ ምክንያት በሚሰራው የጡረታ አበል ስሌት መሰረት ነው፡፡
ሊድን የማይችል የሥራ ላይ ጉዳት የዘለቄታ ጡረታ አበል ደግሞ የመንግስት ሠራተኛው ጉዳት ከደረሰበት ቀን በፊት የነበረው የወር ደመወዙ 47 በመቶ በመያዝ ይሰላል፡፡
ለምሳሌ፡-
ሠራተኛው ላይ ጉዳት ከደረሰበት ቀን በፊት ባለው ወር ደመወዙ 4,000.00 ብር ቢሆን 4,000.00 × 47% = 1,880.00 ብር የዘለቄታየጉዳት ጡረታ አበል ያገኛል፡፡
ኦምኒኤል (12/02/2014 ዓ.ም
ምንጭ፡- https://t.me/HenokTayeLawoffice