የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
275 subscribers
366 photos
3 videos
137 files
97 links
ይህ የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት ቻናል ስለኢትዮጵያ ሕጎች)ማብራሪያ የሚሰጥበት፣ አዳዲስ ሕጎች የሚጋሩበት፣ ሕግ ነክ ዜናዎችና መረጃዎች የሚተላለፉበት፣ በዳይሬክቶሬቱ የተሰጡ የንቃተ-ሕግ ስልጠናዎች፣ የሕግ መልዕክቶች፣ በራሪ ጽሑፎች እና መሰል ሰነዶች የሚለቀቁበት ነው።
መልካም ቆይታ!
Download Telegram
ክፍል 3 ስለኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማህበር (Limited Liability Partnership)፣
ስለ ማህበሩ ባህሪያት እና አመሠራረት
ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማህበር ማለት ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች የሙያና ለሙያው ደጋፊ የሆነ አገልግሎት (professional and complementary service) ለመስጠት የሚያቋቁሙት የማህበርተኞች ኃላፊነት በመዋጮዋቸው የተወሰነ የንግድ ማህበር ነው፡፡ ይህን ማህበር ሊያቋቁሙ የሚችሉት ሥልጣን ባለው መስሪያ ቤት የሙያ ፈቃድ ወይም ለሙያ ደጋፊ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት የሚችሉ ለምሳሌ እንደ ህግ ባለሙያ፣ ጤና ባለሙያ ፣ የሂሣብ ባለሙያ አይነት የተፈጥሮ ሰዎች አሊያም ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማህበራት ናቸው፡፡
ይህ ማህበር ከአባላቱ የተለየ የህግ ሰውነት ያለው ፤ እንደ መክሰስ መከሰስእና በራሱ ስም ውል መዋዋል የመሳሰሉ ህጋዊ ድርጊቶች በራሱ ስም መፈፀም የሚችል ሲሆን የሽሪኮቹ መሞት ፣ መክሰር፣ ከማህበሩ መውጣት ወይም በሽርኮቹ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ለውጥ በማህበሩ ሕልውና፣ መብት ወይም ግዴታ ላይ ተፅዕኖ አይኖረውም፡፡ ማህበሩ ስም ለማውጣት የተቀመጡት ማለትም ለሞራል ተቃራኒ አለመሆን ፣ የሌሎች ነጋዴዎችን መብት አለመጋፋት ወዘተ… የመሳሰሉ የህግ መስፈርቶች እንደተጠበቁ ሆነው የመረጠውን ሥም (Assumed Name) መጠቀም የሚችል ሲሆን ከስሙ በስተመጨረሻ ግን "ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማህበር" የሚል ሐረግ መጨመር አለበት፡፡
በአዲሱ የንግድ ሕግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማህበርን ጨምሮ ከባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ውጪ ያሉት ማህበራት በሙሉ የሚቋቋሙት በመመስረቻ ፅሁፍ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በቀድሞ ሕግ የነበረው መተዳደሪያ ደንብ በአዲሱ ሕግ ቀሪ ተደርጓል፡፡ የዚህን ዓይነት ማህበር መመስረት የሚችሉት የሙያ ፈቃድ ያላቸው የተፈጥሮ ሰዎች ወይም ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማህበራት ናቸው፡፡
ሥለ ማህበሩ ሥራ አመራር እና ኃላፊነት ወሰን
ማህበሩ ምንም እንኳን ከተፈጥሮ ሰው በተጨማሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማህበርን በአባልነት መያዝ የሚችል ቢሆንም ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኖ መሾም የሚችለው የተፈጥሮ ሰው የሆነ እና ማህበሩ አገልግሎት በሚሰጥበት ሞያ ፈቃድ ያለው ሸሪክ ብቻ ነው፡፡ የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ የማህበሩን ዓላማ ለማሳካት በማህበሩ ስም ማንኛውንም ሕጋዊ ተግባር ለማከናወን የሚችል ሲሆን ይህን ሥልጣን የሚገድቡ ስምምነቶች ሶስተኛ ወገኖችን መቃወሚያ የሚሆኑት በንግድ መዝገብ የተመዘገቡ ወይም ሦስተኛ ወገኖች የሥራ ኃላፊነቱን የሚያውቁ መሆናቸው የተረጋገጠ እንደሆነ ነው፡፡
የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ሥልጣንና ተግባር የሚደነግገው የማህበሩ መመስረቻ ፅሁፍ ሲሆን ይህም መመስረቻ ፅሁፍ ተቃራኒ ስምምነተ ከሌለ በአባላት ሁለት ሶስተኛ (2/3) ድምፅ በሚሰጥ ውሳኔ ሊሻሻል ይችላል፡፡ ሌላ ማንኛውም ውሳኔ በአብዛኛዎቹ አባላት የድምፅ ድጋፍ ማለትም (50+1) ሊፀድቅ ይችላል፡፡ የማህበሩ ዜግነት ወይም የሥራ መስክ ለመለወጥ የሚሰጥ ውሳኔ የሚፀናው በ3/4ኛ (ሶስት አራተኛ) ድጋፍ ድምፅ ነው፡፡

የማህበሩ እና የአባላት ኃላፊነት ሌላኛው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነጥብ ነው ፡፡ በመሠረቱ ህጋዊ ሰውነት እና የማህበሩ ኃላፊነት ውስንነት የማይነጣጠኑ ሀሳቦች ናቸው (corporate existence and limited liability are inseparable):: ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማህበርን የሚለው ስም በቁሙ ስንመለከተው ኃላፊነቱ የተወሰነው የሚመስለው የማህበሩ ነው ነገር ግን ዝርዝሩን ስንመለከት ኃላፊነቱ የተወሰነው የሽሪኮች ነው ምክንያቱም የሽሪኮች ኃላፊነት በመዋጮዋቸው የተወሰነ ነው፡፡ በእርግጥ የማህበሩ ኃላፊነትም ቢሆን በግልፅ አልተጠቀሰም እንጂ የኃላፊነቱ መጠን በማህበሩ ሀብት (Asset) ልክ ነው፡፡
ሥራ አስኪያጅ ወይም ሸሪክ ከመዋጮ ባለፈ ኃላፊ ሊሆን የሚችልበት አግባብ አለ፡፡ እንዲህ አይነት ሁኔታዎች የኩባንያውን ጭምብል መግለጥ ወይም (Pericing the corporate Veil) ይባላል፡፡ ሥራ አስኪያጁ ከሥልጣኑ በላይ ለሚሠራው ሥራ ሁሉ ኃላፊነቱ የማህበሩ ሳይሆን የሥራ አስኪያጁ ብቻ ነው፡፡ ሸሪኩ ወይም ሠራተኛው የማህበሩን ሥራ በሚያከናውንበት ወቅት ሆን ብሎ ወይም የማታለል ተግባር በመፈፀም ወይም በቸልተኝነት ለሚፈፅመው ጥፋት ወይም ለሚያደርሰው ጉዳት ጥፋቱን ካደረሰው ሸሪክ ወይም ሠራተኛ ጋር ማህበሩ በአንድነትና በተናጠል ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ማህበሩ ጉዳት የደረሰበት አካል ጉዳት አድራሹ ሥልጣን ያልተሠጠው መሆኑን ያስረዳ እንደሆነ ከኃላፊነት ነፃ ይወጣል፡፡ ማህበሩ ይህን መሠል ዕዳዎች ለመሸፈን የመድን ሽፋን እንዲኖረው በህግ ይገደዳል፡፡
ኦምኒኤል (12/02/2014 ዓ.ም)
ክፍል 4፡- አባል ከማህበሩ ስለሚወጣበት መንገድ እና ስለማህበሩ መፍረስ
አንድ አባል ከማህበሩ ሊወጣ የሚችለው የሶስት ወር ቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠት (ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ) ፣ ሲሞት ወይም ህጋዊ ሰውነት ሲያጣ ፣ ድርሻው በገንዘብ ጠያቂዎች ሲወሰድ ፣ የሞያ ፈቃዱ ሲሰረዝ ወይም ለረጅም ጊዜ ሲታገድ፣ በሕመም ወይም አካል ጉድለት ወይም ሌሎች ምክንያቶች ግዴታውን ለመወጣት የማያስችለው ሲሆን ወይም ፍርድ ቤት በበቂ ምክንያት ከማህበሩ እንዲወጣ ሲወስን ነው፡፡ አንድ ሸሪክ ከማህበሩ ከመውጣቱ በፊት ለሶስተኛ ወገኖች የነበረበት ዕዳ ኃላፊነት ከማህበሩ በመውጣቱ ቀሪ አይሆንም ፡፡
አንድ ሽሪክ ድርሻውን በሌሎች ማህበርተኞች ተቀባይነት ላገኘ ሌላ ማህበርተኛ ወይም ሶስተኛ ወገን ሳያስተላልፍ የወጣ እንደሆነ ህጋዊ መብት ያለው ወራሽ ወይም ባለመብት ድርሻው ተሰልቶ እንዲሰጠው ከመጠየቅ ውጪ አባል ለመሆን የሚያቀርበው ጥያቄ ተቀባይነት የለውም
በንግድ ሕግ ቁጥር 181 ንግድ ማህበራት ከሚፈርሱበት ሁኔታ በተጨማሪ የማህበሩ አባላት ቁጥር ወደ አንድ ዝቅ ያለ እንደሆነ እና በስድስት ወራት አሊያም ዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ ሁለት ከፍ ካላለ ማህበሩ ሊፈርስ ይገባል።
ኦምኒኤል (12/02/2014 ዓ.ም)
ጤና ይስጥልኝ ፡-
አንድን ልጅ የእገሌ ልጅ ነው ለማለት በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 የተመለከተውን እንዲህ እናቅርብ፡፡

መልካም ምንባብ፡-
ልጅነትን ለማረጋገጥ የልደት የምሥክር ወረቀት በማቅረብ የሚፈጸም ሲሆን ይህም የምሥክር ወረቀት የሌለ እንደሆነም በማህበረሰቡ ዘንድ የእርሱ ወይም የእርሷ ልጅ ነው እየተባለ የሚገመት መሆኑን በማሳየት የሚረጋገጥ ሲሆን ሆኖም ይህንን የሕግ ግምትንም ልጅ እንዳልሆነ በማስረዳት ማፍረስ የሚችል መሆኑን የተደነገገ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
ጥቅምት 18/2014
ደረጀ ማርቆስ
ጤና ይስጥልኝ ፡-

ማንኛውም ሰው ሕጋውያን ድርጊት (ለምሣሌ፡- ለመዋዋል፣በስሙ ለመክሰስ ወይም ለመከሰስ፣--)ለመፈጸም በሕግ ችሎታ ሊኖረው የሚገባና ይህም ማለት ማንኛውም ሰው ችሎታ እንዳለው በሕግ ግምት የሚያዝበት ቢሆንም በዚሁ ልክም ሕጉ ከዕድሜ፣ ከአዕምሮ ሁኔታ ወይም በሰውዬው ላይ በሚደርስ (በሚጣል) የፍርድ ቅጣት መሰረት የችሎታ ማጣት ሊኖር እንደሚችል ከፍ/ብ/ሕጉ ላይ ከተረዳን በዚሁ አካል መጠን ያልደረስን(ዕድሜው አሥራ ስምንት ዓመት ያልሞላው) በንብረት ረገድ የሚደረግለትን ጥበቃ እንደሚከተለው እናቅርብ፡፡

መልካም ምንባብ፡-
አካለ-መጠን ያልደረሰው ልጅ እናት ወይም አባት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ሞግዚት የልጁን ንብረት ለመሸጥ ከፈለገ ከፍርድ ቤት መመሪያ መጠየቅ እንደሚኖርበት ከተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ቁጥር 277 መረዳት ይቻላል፡፡
ጥቅምት 18/2014
ደረጀ ማርቆስ
ቅሬታ አቀራረብና አፈታት
ጤና ይስጥልኝ!
ከዚህ በፊት በአዋጅ 56/2010 በከባድ የዲስፕሊን ጥፋትነት ሊያስቀጡ ስለሚችሉ ጥፋቶች በዚሁ መገናኛ ዘዴ አስነብቢያችሁ እንደነበረው ዛሬ ደግሞ በሰራተኛ ስለሚቀርቡ ቅሬታዎችና አፈታታቸውእንዲህ አቅርቢያለሁና በፈቀዳችሁት ልክ አንብቡልኝ!!
74. ቅሬታ
ቅሬታ ማለት የመንግስት ሰራተኛ ከቅርብ ሃላፊው ወይም ከሚመለከተው የሥራ ሃላፊ ጋር በሚደረገው ውይይት ሊፈታ ያልቻለና በመደበኛ የማጣራት ሂደት ምላሽ ሊያገኝ የሚገባው አቤቱታ ነው.
75. የቅሬታ አቀራረብና አፈታት አላማ
የመንግስት ሰራተኞች ቅሬታ አቀራረብና አፈታት የሚከተሉት አላማዎች ይኖሩታል
- ለቅሬታዎች አፋጣኝ መፍትሄ የመስጠት
- ለቅሬታዎች መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ስህተቶችንና ድክመቶችን የማረም እና
- ሁሉንም የመንግስት ሰራተኞች በእኩልነት ለማስተናገድ የሚያስችል እና ፍትሃዊ የሆነ አሰራር በማስፈን የሰመረ የስራ ግንኙነት የማዳበር.
76. የቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ ማቋቋም
ማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት የመንግስት ሰራተኞች የሚያቀርቡትን ቅሬታ እየተቀበለ በማጣራት የውሳኔ ሀሳብ ለመስሪያ ቤቱ የበላይ ሃላፊ የሚያቀርብ የቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ ማቋቋም አለበት.
77. የቅሬታ አጣሪ ኮሚቴው ተግባር
የቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ ከሚከተሉት ጋር በተያያዘ የመንግስት ሰራተኛው የሚያቀርባቸውን ቅሬታዎች እያጣራ የውሳኔ ሃሳብ የማቅረብ ሃላፊነት አለበት
- ከህጎችና ከመመሪያዎች አተረጓጎም ወይም አፈጻጸም
- ከመብቶችና ጥቅሞች አጠባበቅ
- ከስራ አካባቢ ጤንነትና ደህንነት ሁኔታዎች
- ከስራ ምደባና ደረጃ አሰጣጥ
- ከስራ አፈጻጸም ምዘና
- በስራ ሃላፊ ከሚፈጸሙ፣ ተገቢ ያልሆኑ ተጽእኖዎች
- በዚህ አዋጅ አንቀጽ 69 ንኡስ አንቀጽ (1)(ሀ) እና (ለ) በቀላል የዲስፕሊን ቅጣት በቅርብ አለቃ ስለሚወሰኑ ቅጣቶች መደጋገም ) በተመለከቱት መሰረት ከሚወሰዱ የዲሲፕሊን እርምጃዎች
- የሥራ ሁኔታዎችን ከሚመለከቱት ሌሎች ጉዳዮች

ከቅሬታ የራቀ የስራ ቦታ ይግጠመወት፡፡
ሲሳይ ሰማኝ
የክስና የቅጣት ይርጋ
ሰላም ከወንጀልና ከወንጀለኝነት እንዲጠብቀወት ከልቤ ባሉበት እየተመኘሁ!!
በዚች መልዕክት በወንጀል ሕጋችን ስለፍርድና ቅጣት ይርጋ መታገድ የተደነገገውን በጥቂቱ ሙሉውን ከመጽሀፉ እንዲያነቡት ለማነሳሳት በጣም በትንሹ እነሆ፡!!
ንዑስ ክፍል አንድ የክስ ይርጋ
አንቀጽ 216 መርህ እና ውጤቱ
1. በሕግ በሌላ አኳኋን (በልጦ ወይም አንሶ) ካልተደነገገ በስተቀር ከዚህ በታች የተመለከተው የይርጋ ዘመን ካለፈ በኋላ በማናቸውም ወንጀል የግል አቤቱታን ወይም የወንጀል ክስን መቀበልና ጉዳዩን በዳኝነት ማየት አይቻልም፡፡
የይርጋ ዘመኑ ማለፍ ለማናቸውም የወንጀል ተካፋይ ቅጣትን ያስቀራል፡፡ ለይርጋ የተወሰነም ጊዜ ካለፈ የጥፋተኛነት ውሳኔ ወይም ቅጣት ወይም የጥንቃቄ እርምጃ ሊወሰን አይቻልም፡፡
2. ክሱ በይርጋ ስለመታገዱና ክሱን ለመቀበል የማይገባ ስለመሆኑ ተከሳሹ ባያመለክትም ዐቃቤ ሕጉ ወይም ፍርድ ቤት በማናቸውም ጊዜ ማንሳት አለበት፡፡
አንቀጽ 217 መደበኛ የክስ ማቅረቢያ የይርጋ ዘመን
1. በወንጀል ተግባር ክስ የማቅረብ የይርጋ ዘመን የሚፀናው፡-
ሀ/ የሞት ፍርድ ወይም የዕድሜ ልክ ፅኑ እሥራት ለሚያስቀጣ ወንጀል ሃያ አምስት ዓመት፣
ለ/ ከአሥር ዓመት በላይ እስከ ሃያ አምስት ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እስራት ለሚያስቀጣ ሃያ ዓመት፣
ሐ/ ከአምስት ዓመት በላይ እስከ አሥር ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እስራት ለሚያስቀጣ አሥራ አምስት ዓመት፣
መ/ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል አሥር ዓመት፣
ሠ/ ከአንድ ዓመት በላይ በቀላል እሥራት ለሚያስቀጣ ወንጀል አምስት ዓመት፣
ረ/ እስከ አንድ ዓመት በቀላል እሥራት ለሚያስቀጣ ወይም በመቀጮ ብቻ ለሚያስቀጣ ወንጀል ሦስት ዓመት፡፡
2 ተደራራቢ ወንጀሎች ተፈጽመው ሲገኙ፡-
ሀ/ የወንጀሎቹ ከፍተኛ ቅጣቶች ተመሳሳይ በሚሆኑበት ጊዜ የአንዱ ወንጀል የክስ ማቅረቢያ የይርጋ ዘመን በሁሉም ወንጀሎች ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
ለ/ የወንጀሎቹ ከፍተኛ ቅጣቶች የተለያዩ በሚሆንበት ጊዜ ከሁሉም ከባድ የሆነው ወንጀል የክስ ማቅረቢያ የይርጋ ዘመን በሌሎች ወንጀሎች ላይም ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
አንቀጽ 218 ልዩ የግል አቤቱታ ማቅረቢያ የይርጋ ዘመን
የአንቀጽ 213 ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ በግል አቤቱታ ብቻ የሚያስቀጣ የማናቸውም የወንጀል ክስ የይርጋ ዘመን ሁለት ዓመት ነው፡፡
አንቀጽ 219 የይርጋ ዘመን አቆጣጠር
1 የይርጋ ዘመን የሚታሰበው የቅጣት ማክበጃ ወይም ማቅለያ ሁኔታዎች ግምት ውስጥ ሳይገቡ በዚህ ሕግ ልዩ ክፍል የተደነገገውን ከፍተኛ ቅጣት መሠረት በማድረግ ነው፡፡
የተፈፀመው ወንጀል በተለዋጭ ወይም በተደራራቢ ተፈፃሚነት በሚኖራቸው ቅጣቶች የሚያስቀጣ ሲሆን የይርጋ ዘመኑ የሚታሰበው ከሁሉም ከባድ ለሆነው ወንጀል በዚህ ሕግ ልዩ ክፍል የተደነገገውን ከፍተኛ ቅጣት መሠረት በማድረግ ነው፡፡
2 የይርጋ ዘመኑ መቆጠር የሚጀምረው ጥፋተኛው የወንጀሉን ድርጊት ከፈጸመበት ቀን አንስቶ ነው፡፡
የወንጀሉ ድርጊት እየተደጋገመ ተፈፅሞ እንደሆነ የይርጋ ዘመኑ መቆጠር የሚጀመረው የመጨረሻው የወንጀል ድርጊት ከተፈፀመበት ቀን አንስቶ ነው፡፡ እንዲሁም የወንጀሉ ድርጊት ለረጅም ጊዜ ሲፈፀም የቆየ እንደሆነ የየርጋ ዘመኑ መቆጠር የሚጀምረው የወንጀሉ ድርጊት ካቆመበት ቀን ጀምሮ ነው፡፡
ወንጀሉ ተደርጓል ለማለት የሚቻለው ከጠባዮቹ አንዱ የወንጀሉ ውጤት የሆነ እንደሆነ የይርጋ ዘመኑ መቆጠር የሚጀምረው የወንጀሉ ውጤት ከተገኘበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡
አንቀጽ 220 የይርጋ ዘመን መታገድ
1 በሕጉ ወይም በፍሬ ነገር ክሱ እንዳይጀመር ወይም እንዳይቀጥል የሚያግድ መሰናክል እስካለ ድረስ የይርጋ ዘመን መቆጠሩ ታግዶ ይቆያል፡፡
እንዲሁም ክስ ቀርቦ ነገሩ በዳኝነት በመታየት ላይ እንደሆነ ወይም በሌላው ችሎት የቀረበው ክስ ሳይፈፀም ተከሳሹ በተከሰሰበት የወንጀል ክስ ላይ ውሳኔ ሊሰጥ የማይገባ እንደሆነ የይርጋ ዘመኑ መቆጠር ታግዶ ይቆያል፡፡
መሰናክሉም እንደተወገደ ወዲያውኑ የይርጋ ዘመኑ መቆጠር ይቀጥላል፡፡
2 ስለክሱ መከታተል አቤቱታ እንዲቀርብ ማስፈለጉ በሕግ ተመልክቶ በተገኘ ጊዜ አቤቱታ አለማቅረቡ የይርጋውን መቆጠር አያግደውም፡፡
እንዲሁም ክሱ እንዳይጀምር ወይም እንዳይቀጥል ጥፋተኛው በራሱ ፍላጐት የሚፈፅመው ተግባር የይርጋ ጊዜውን መቆጠር አያግደውም፡፡
አንቀጽ 221 የይርጋ ዘመን መቋረጥ
ከወንጀሉ ወይም ከወንጀለኞቹ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ምርመራ እንዲካሄድ፣ ብርበራ እንዲደረግ፣ መጥሪያ እንዲሰጥ ወይም ክስ እንዲቀርብ የሚሰጥ ትዕዛዝ፣ የሚፈፀም ድርጊት ወይም የሚሰጥ ውሳኔ የይርጋ ዘመኑን መቆጠር ያቋርጣል፡፡
የይርጋ ዘመኑ መቋረጥ ፍጹም የሆነ ውጤት አለው፤ በወንጀሉ ተካፋይ መሆናቸው ለታወቀውም ሆነ ላልታወቀው ሁሉ መቋረጡ ይፀናባቸዋል፡፡
አንቀጽ 222 ፍፁም የሆነ የይርጋ ዘመን
በማናቸውም ምክንያት መደበኛ የክስ ማቅረቢያ የይርጋ ዘመን /አንቀጽ 217/ አጠፌታ ጊዜ ካለፈ ወይም ልዩ የግል አቤቱታ ማቅረቢያ የይርጋ ዘመን ሲሆን /አንቀጽ 218/ ከዚሁ ዘመን በግማሽ የሚበልጥ ጊዜ አልፎ እንደሆነ በወንጀሉ ላይ የሚቀርበው ክስ ወይም የሚደረገው መከታተል በይርጋ ቀሪ ይሆናል፡፡
ንዑስ ክፍል ሁለት የቅጣትና የጥንቃቄ እርምጃዎች ይርጋ
አንቀጽ 223 መርህ እና ውጤቱ
1. በሕግ በሌላ አኳኋን በግልጽ ካልተደነገገ በስተቀር በተቀጪው ላይ የተወሰነው ቅጣት በማናቸውም በተቀጪው ላይ የተወሰነው ቅጣት በማናቸውም ምክንያት ከዚህ በታች ከአንቀጽ 224‐228 በተመለከቱት ጊዜያት ውስጥ ሳይፈጸም የቆየ እንደሆነ ቅጣቱን የማስፈጸም መብት ቀሪ ይሆናል፤ የተወሰነውም ቅጣት ወይም የጥንቃቄ እርምጃ ሊፈጸም አይችልም፡፡
የዋነኛው ቅጣት የይርጋ ዘመን የተጨማሪ ቅጣቶችና የጥንቃቄ እርምጃዎች መፈፀምንም ያስቀራል፡፡ እንዲሁም የዋናው ቅጣት የይርጋ ዘመን ከቅጣቱ ጋር ለተያያዘ የንብረት መውረስ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡ ሆኖም የጥንቃቄ እርምጃዎች ያለዋነኛ ቅጣት በሚወሰኑበት ጊዜ የአንቀጽ 224(1)(መ) ድንጋጌዎች ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡
2. ጉዳዩ የሚመለከታቸው የዳኝነት ወይም የአስተዳደር ባለሥልጣኖች በራሳቸው ተነሳሽነት የቅጣት የይርጋ ደንብን አክብሮ የመጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
3. የተወሰነው ቅጣት በይርጋ ዘመኑ መታገድ ምክንያት ሳይፈፀም ቢቀርም በወንጀለኞች መዝገብ ውስጥ እንደተመዘገበ ይቆያል፡፡
አንቀጽ 224 መደበኛ የቅጣት ይርጋ ዘመን
1. የቅጣትና የጥንቃቄ እርምጃዎች ይርጋ ዘመን የሚፀናው በሚከተለው ሁኔታ ይሆናል፤
ሀ/ ለሞት ፍርድ፣ ወይም ለዕድሜ ልክ ፅኑ እሥራት ሰላሳ ዓመት
ለ/ ከአሥር ዓመት በላይ ለሆነ ነፃነትን የማሳጣት ቅጣት ሃያ ዓመት
ሐ/ ከአንድ ዓመት በላይ ለሆነ ነፃነትን የማሳጣት ቅጣት አሥር ዓመት
መ/ ሰማናቸውም ሌላ ቅጣት ወይም የጥንቃቄ እርምጃ ውሳኔ አምስት ዓመት
2. ተደራራቢ ቅጣቶች ተወስነው እንደሆነ ቀላል የሆኑት ቅጣቶች በይርጋ ቀሪ የሚሆኑት ከሁሎም ከባድ የሆነው ቅጣት በይርጋ ቀሪ በሚሆንበት ጊዜ ነው፡፡
አንቀጽ 225 የቅጣት የይርጋ ዘመን አቆጣጠር
1. የቅጣት የይርጋ ዘመን መቆጠር የሚጀምረው፣ ፍርዱ የመጨረሻ ሆኖ ተፈፃሚ መሆን ይችል ከነበረበት ቀን ወይም ፍርዱ መፈፀም ጀምሮ እንደሆነ ተቀጪው ይኸው ፍርድ እንዳይፈፀምበት ካመለጠበት ቀን ጀምሮ ነው፡፡
ተቀጪው ፍርዱ ከታገደለት በኋላ የፍርድ መታገድ ትዕዛዝ የተሻረ እንደሆነ የይርጋው ጊዜ የሚቆጠረው የቅጣቱ አፈፃፀም እንዲቀጥል ከታዘዘበት ቀን ጀምሮ ነው፡፡
2. ተደራራቢ ቅጣቶች ተወስነው እንደሆነ ለይርጋው ጊዜ አቆጣጠር መሠረት የሚሆነው ከሁሉም ከባድ የሆነው የቅጣት የይርጋ ጊዜ ነው
አንቀጽ 226 የቅጣትና የጥንቃቄ እርምጃ የይርጋ ዘመን መታገድ
የቅጣት ይርጋ ዘመን ታግዶ የሚቆየው፡
ሀ/ የቅጣቱ ወይም የጥንቃቄ እርምጃው አፈፃፀም እንደ ሕጉ ሊፈፀም ወይም አፈፃፀሙ ሊቀጥል ባልቻለ ጊዜ፣ ይህ መሰናክል እስከሚቆይበት ጊዜ ድረስ፣
ለ/ ተቀጪው ፍርዱ ታግዶለት፣ በአመክሮ ተፈትቶ ወይም የዕዳ መክፈያ ጊዜ ተሰጥቶ እንደሆነ የተወሰነው ጊዜ እስካላለቀ ድረስ፣
ሐ/ ነፃነትን በማሳጣት ቅጣት ወይም በሌላ የጥንቃቄ እርምጃ ለማስፈጸም ታስሮ እስከሚቆይበት ጊዜ ድረስ፣ ነው፡፡
አንቀጽ 227 የቅጣት የይርጋ ዘመን መቋረጥ
የቅጣት ይርጋ ዘመን የሚቋረጠው የማስፈፀም ኃላፊነት በተሰጠው ባለሥልጣን ቅጣቱን ለማስፈፀም የሚደረግ ወይም ወደ ቅጣቱ አፈፃፀም የሚያመራ ተግባር በሥራ ላይ እንዲውል ከተጀመረበት ቀን አንስቶ ነው፡፡
አንቀጽ 228 ፍፁም የሆነ የቅጣትና የጥንቃቄ እርምጃ፣ ይርጋ ዘመን
ለመደበኛ ሕጋዊ ቅጣት ከተወሰነው የይርጋ ዘመን /አንቀጽ 224/ በግማሽ የሚበልጥ ጊዜ ካለፈ ጥፋተኛው በዚህ ጊዜ ውስጥ ቢያንስ በፅኑ እሥራት የሚያስቀጣ ወንጀል አስቦ በመፈፀም አደገኛ መሆኑን ካላሳየ በቀር የቅጣት ወይም የጥንቃቄ ተግባር አፈፃፀም ውሳኔ በማናቸውም ምክንያት ቢሆን ቀሪ ይሆናል፡፡
የበዛ ሰላም ለርሰዎ!!
ሲሳይ ሰማኝ 22/02/2014
የከተማ ቦታ በሊዝ ስለሚፈቀድባቸዉ ሁኔታዎች
• በጨረታ
• በምደባ
በጨረታ፡- በገበያ የዉድድር ሥርዓት በሚወጡ የዉድድር መስፈርቶች መሰረት አሸናፊ ለሚሆነዉ ተጫራች የከተማ መሬት በሊዝ የሚተላለፍበት መንገድ ነዉ
በምደባ፡- በጨረታ ሊስተናገዱ ለማይችሉ ተቋማት የከተማ ቦታ በሊዝ የሚተላለፍበት መንገድ ነዉ፡፡ ከነዚህ ተቋማት መካከል
• ለባለ በጀት የመንግስት መሥሪያ ቤቶቸ ለቢሮ አገልግሎት የሚዉሉ ቦታዎች፤ በመንግስት ወይም በበበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለሚካሄዱ ማህበራዊ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት የሚዉሉ ቦታዎች፤
• በመንግስት ለሚካሄዱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ልማት ፕሮግራሞች እና በመንግስት እየተወሰነ ለሚካሄዱ ለራስ አገዝ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታዎች የሚዉሉ ቦታዎች፤
• ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ልማት የሚዉሉ ቦታዎች፤
• ከመንግስት ጋር በተደረጉ ስምምነቶች ለኤምባሲዎችና ለአለምአቀፍ ድርጅቶች አገልግሎት የሚዉሉ ቦታዎች፤ ልዩ አገራዊ ፋይዳ ላላቸዉ ፕሮጀክቶች የሚዉሉ ቦታዎች ናቸዉ
ህድአት
ጥቅምት/2014 ዓ.ም
ነባር ይዞታዎች ወደ ሊዝ ስሪት ስለሚቀየሩበት ሁኔታ
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚንስተር በሚያቀርበዉ ጥናት ላይ ተመስርቶ የሚወሰን ሆኖ ከዉርስ በስተቀር በማንኛዉም መንገድ ለሌላ ሰዉ ከተላለፈ ንብረቱ የተላለፈለት ሰዉ የቦታዉ ባለይዞታ ሊሆን የሚችለዉ በሊዝ ሥሪት መሰረት ይሆናል፡፡ ነባር ይዞታ ወደ ሊዝ በሚቀየርበት ወቅት በከተማዉ ፕላን መሠረት በሚደረግ ሽንሻኖ
• የሚቀነስ ወይም የሚጨመር የከተማ ቦታ ሊኖር ይችላል፡፡
የሚቀነስ ቦታ ሲኖር ከይዞታዉ ላይ ለሚነሣዉ ንብረት ካሣ የሚከፈለዉ ሲሆን
የሚጨመር ይዞታ ሲኖር ደግሞ ለተጨመረዉ ይዞታ በሊዝ ክፍያ የሚስተናገድ ይሆናል፡፡
ህድአት
ጥቅምት/2014 ዓ.ም
ሰላም ውድ የቴሌግራም ተከታታዮቻችን በቅርቡ የወጡ ሁለት አዋጆችን (የሀገር ህልው እና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነ አደጋን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወስን የወጣውን አዋጅ ታነባቸው ዘንድ ላካፍላችሁ ወደድኩኝ
መልካም ምንባብ!
የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ

ውድ አንባቢያን በያላችሁበት ሰላም እንድትሆኑ የዘወትር ምኞታችን ነው፡፡
በዛሬው መልዕክት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን አስፈጻሚ አካላት እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ 74/2014 ከተቋቋሙት ቢሮዎች አንዱ ስለሆነውና በተለይም ከዚህ ቀደም በሰራተኛና ማህበራዊ ቢሮ ስር የነበሩ ተግባራትን ወደዚህ ቢሮ የተዛወሩ በመሆኑ እንግልትን ለመቀነስ ይረዳል በሚል ከዚህ እንደሚከተለው አቅርቢያለሁ!!፡፡
በአሰሪና ሠራተኛ መካከል የሥራ ቦታ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል፤ የወል የሥራ ክርክሮች እና የኅብረት ስምምነት ድርድር ልዩነቶች በመግባባት እልባት እንዲያገኙ ያደርጋል፤ የህብረት ስምምነቶችንና ማሻሻያቸውን ይመዘግባል፤
በአሰሪና ሠራተኛ መካከል የሥራ ቦታ ሰላም እንዲሰፍን የትምህርትና የሥልጠና አገልግሎት ይሰጣል፣ የሙያ ምክር አገልግሎት ስለሚስፋፋበት፣ ክፍት የሥራ መደቦች ስለሚመዘገቡበትና ሥራና ሠራተኛ ስለሚገናኙበት ዘዴ ይቀይሳል፤ ሲጸድቅም ተግባራዊ መሆኑን ያረጋግጣል፤
አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር በከተማው ውስጥ በሥራ ላይ ስለተሰማራውና ሥራ አጥ ስለሆነው የሰው ኃይል፣ ስለሙያ መደብ፣ የከተማውን የስራ ሰምሪት እንዲሁም የሙያ አመዳደብ ጥናትና ምርምር ያደርጋል፤ መረጃዎችን ይይዛል፤ የስራ ገበያ መረጃዎች ስርዓት ይዘረጋል፣ ይሰበስባል፣ ያጠናክራል፤ ያሰራጫል፤
በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ህግ በተደነገገው መሰረት በከተማው ውስጥ የሚደራጁ የአሰሪና ሰራተኛ የሙያ ማህበራትን ይመዘግባል፤ ድጋፍ ይሰጣል፤ ሲፈርሱ ምዝገባውን ይሰርዛል፤
አሰሪዎች የስራ ሁኔታን፣ የሙያ ደህንነትና ጤንነትንና የስራ አካባቢን ለመጠበቅ የወጡ የስራ ሁኔታ ደረጃዎችና የመከላከያ ዘዴዎች በሥራ ላይ ማዋላቸውን ይቆጣጠራል፤
ሥራና ሠራተኛ ለሚያገናኙ ኤጀንሲዎች የብቃት ማረጋገጫ በህግ መሰረት ይሰጣል፤ ድጋፍ ያደርጋል፤ መሥራታቸውን ያረጋግጣል፤ ይሰርዛል፤
በአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ ህግ መሰረት የከተማው አስተዳደር የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ያቋቁማል፤ የቦርዱን አባላት ይሰይማል፤ ያሰናብታል፤ ተግባርና ኃላፊነታቸውን ይከታተላል፤
የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነትን፣ የሥራ ሥምሪት አግልግሎትና የሥራ አፈጻጸም እያጠና ምክር የሚሰጠው የመንግሥት፣ የአሠሪዎች ማህበራትና የሠራተኛ ማህበራት ተወካዮችን ያካተተ ቋሚ የሆነ አማካሪ ቦርድ ሊያቋቁም ይችላል፤
የከተማ ነዋሪው ስለውጭ አገር ሥራ ስምሪት እና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጨባጭ ሁኔታ፤ ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኝ የመገናኛ ብዙኃንንና ሌሎች አማራጭ ዘዴዎችን በመጠቀም ቀጣይነት ያለው ከተማ አቀፍ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎችን ያከናውናል፤
ለሥራ ወደ ውጭ አገር ለመሄድ ፍላጎት ላላቸው ዜጎች ስለተቀባይ አገር ሁኔታ በሚሰማሩበት የስራ መስክ ሊኖራቸው ስለሚገባ ክህሎት፣ ስለመብታቸውና ኃላፊነታቸው እና ስለመሳሰሉት ጉዳዩች የቅድመ-ስምሪትና የቅድመ ጉዞ ግንዛቤ ማሰደጊያ ስልጠና እንዲያገኙ ያደርጋል፤
ለዚህ አንቀጽ አፈጻጸም "ሥራ" ማለት አግባብ ባለው ሕግ የአሰሪና ሠራተኛ ግንኙነት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የስራ ገበያ መረጃ፣ የሙያ ደህንነት ጤንነትና የሥራ አካባቢ፣ የሠራተኛና የአሰሪዎች ማህበር፣ ማህበራዊ ምክክር ሥርዓት፣ የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ እና መሠረታዊ የሥራ ላይ መብቶችና ግዴታዎችን አካትቶ የያዘ ነው፡፡

ሲሳይ ሰማኝ
ቸርይግጠመን!!!
በዛሬዉ ዕለት ህዳር 7/2014ዓም የቦሌ ክፍለ ከተማ የህግ ሰርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት በሀገር ህልዉና እና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014 አስቸከኳይ አዋጁን በተመለከተ ለሕብረተሰቡ በስፋት ተደራሽ ይሆን ዘንድ ሙሉቀን የፈጀ ገለጻ በቦሌ ክ/ከተማ በር አጠገብ በመዉጣት ለህብረተሰቡ ገለጻ በማድረግና አዋጁን በብሮሸር መልክ በማዘጋጀት 6640 (ስድስት ሺ ስድስት መቶ አርባ ) ብሮሸሮችን በመበተን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ተችሎል፡፡