የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
275 subscribers
366 photos
3 videos
137 files
97 links
ይህ የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት ቻናል ስለኢትዮጵያ ሕጎች)ማብራሪያ የሚሰጥበት፣ አዳዲስ ሕጎች የሚጋሩበት፣ ሕግ ነክ ዜናዎችና መረጃዎች የሚተላለፉበት፣ በዳይሬክቶሬቱ የተሰጡ የንቃተ-ሕግ ስልጠናዎች፣ የሕግ መልዕክቶች፣ በራሪ ጽሑፎች እና መሰል ሰነዶች የሚለቀቁበት ነው።
መልካም ቆይታ!
Download Telegram
የፍትሐብሔር ክስ አዘገጃጀት እና በክሱ ላይ መገለጽ የሚገባቸው ነገሮች ከፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 222-225

በአንድ ክርክር የሚዘጋጀው ክስ የአንድን ሰው መብት ማስገኘትም ማሳጣትም ይችላል። የከሳሽ ሀሳብ ግልጽ ካልሆነ ለፍርድ ቤት የተጠየቀውን ዳኝነት በአግባቡ የማይገልጽ ከሆነ ማግኘት የሚገባውን መብት ያሳጣል። አንድ ክርክር ስኬታማ እንዲሆን የሚዘጋጀው ክስ ወሳኝነት አለው። በመሆኑም ከዚህ ቀጥሎ ያሉት አንድ ክስ ስዘጋጅ መያዝ የሚገባቸው ነገሮች ናቸው:-
1. #በክስ ጽሑፍ ላይ ስለሚሰፍሩ ነገሮች
⨳ማናቸውም የክስ ጽሑፍ ከዚህ ቀጥሎ የተመለከቱን ነገሮች የያዘ መሆን አለበት፡፡
⨳ክሱ የሚቀርብለት ፍርድ ቤት የሚያስችልበትን ቦታና ስሙን፡፡
⨳የክሱን አርዕስት፡፡
⨳የከሳሹንና የተከሳሹን ሥም ልዩ መግለጫውን የሚኖርበት ⨳ቦታና መጠሪያው የሚሰጥበትን አድራሻ፡፡
⨳ከሳሽ ወይም ተከሳሽ በሕግ ችሎታ የለውም የተባለ ሲሆን ይህንኑ መግለጽ፡፡
⨳ከሳሹ ክስ የሚያቀርበው በጠበቃነት በነገር ፈጅነት ወይም በወኪልነት እንደሆነ ክሱን ለማቅረብ ያለውን ሥልጣን መግለጽ፡፡
⨳ለክሱ ምከንያት የሆትን ነገሮችና እነዚሁም የተፈጠሩበት ጊዜና ስፍራ፡፡
⨳ፍርድ ቤቱ ነገሩን ለመቀበል ሥልጣን ያለው ስለመሆኑ የሚያስረዳውን ሁኔታ፡፡
⨳ተከሳሹ ለክሱ ምክንያት በሆነው ነገር ውስጥ አግባብ እንዳለው ወይም ተጠሪ የሚሆንበትን ምክንያት ወይም ለሚቀረበው ክርክር በአላፊነት የሚጠየቅበትን ሁኔታ፡፡
⨳አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ለክሱ ምክንያት የሆነውን ነገር ግምት፡፡
⨳መንግስት የሚከስበት ወይም የሚከሰስበት ጉዳይ ሲሆን ከዚህ በላይ እንደተነገረው ዝርዝር ነገር መስጠት አስፈላጊ አይሆንም ነገር ግን የከሳሹን ወይም የተከሳሹ መስሪያ ቤትና የባለስልጣኑ ስም ብቻ መግለጽ በቂ ነው፡፡
2.#ከክስ ማመልከቻ ጋር ተያይዘው ስለሚቀርቡ ጽሑፎችና መግለጫዎች
⨳ከሳሹ ከሚያቀርበው የክስ ማመልከቻ ጋር ከዚህ ቀጥሎ የተመለከቱትን ነገሮች አያይዞ ማቅረብ አለበት፡፡
⨳ክርክሩ በሚሰማበት ጊዜ ምስክር ይሆኑኛል የሚላቸውን ሰዎች የስም ዝርዝር ከነ አድራሻው፤የሚጠሩበትን ምክንያት እንዲሁም ማስረጃ ይሆኑኛል የሚላቸውን ጽሑፎች ጽሑፎቹም በእጁ የማይገኘ ሲሆኑ የሚገኙበትን ስፈራና በማን እጅ እንደሚገኙ በመግለጽ አያይዞ ካቀረበው ዝርዝር በቀር ሌላ አስረጅ ወይም ማስረጃ የሌለው መሆኑን አረጋግጦ በማስታወቅ፡፡
⨳ለክሱ መነሻ ወይም መሠረት የሆነውን ሰነድ ዋናውን ወይም ትክክል ግልባጩን፤
⨳የሚያቀርበው ምሰስክር ወይም የጽሑፍ ሰነድ የሌለው ስሆን ይህንኑ ገልጾ ማረጋገጥ፡፡
⨳በክሱ ማመልከቻ ላይ ለተጠቀሱት ተከሳሾች ሁሉ በቂ የሆነ የክስ አቤቱታ ግልባጭ ከዚህ ጋር ተያይዘው የቀረቡትን የጽሑፎችና ሌሎችም ማስረጃወች የምስክሮች ስም ዝርዝር ማናቸውም ለፍርድ ቤቱ የደረሱትን መግለጫዎች ትክክል ግልባጫቸው እንዲደርሳቸው ማድረግ፤
⨳ከዚህ በላይ ባለው ንዑስ ቁጥር የተነገረው ድንጋጌ እንደተበቀ ቢሆንም እንኳ ፍርድ ቤቱ የፈቀደ እንደሆነ ለክሱ መሰረት የሆነውን ሰነድ ትክክል ግልባጭ ለተከሳሹ እንዲደርሰው ከማድረግ ይልቅ ዋናው በፍርድ ቤቱ መዝገብ ቤት እንዲቀመጥና ተከሳሹ መጥቶ እንዲያየው ለማዘዝ ይችላል፡፡

ፌናን ተጊበሉ
ታህሳስ 15/2014 ዓ.ም
የፍትሐብሔር ክስ አዘገጃጀት እና በክሱ ላይ መገለጽ የሚገባቸው ነገሮች ከፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 222-225

3. #የሚጠየቀውን ዳኝነት በዝርዝር ስለ መግለጽ
⨳ከሳሽ በሚያቀርበው የክስ ማመልከቻ ላይ በተለየ ወይም በምትክ ወይም በተለዋዋጭ የሚጠይቀውን ዳኝነት መግለጽ አለበት ነገር ግን ከሳሹ በክሱ ላይ እንዲሰጠው የሚጠይቀው ዳኝነት ጠቅላላ ሲሆን ፍርድ ቤቱ የክሱን ጭብጥና የማስረጃውን አካባቢ ሁኔታ መሰረት በማድረግ ትክክለኛ መስሎ የታየውን ፍርድ ሊሰጠው ይችላል፡፡
⨳ከሳሹ ክሱን የመሰረተው በብዙ ጉዳዮች ወይም በተለያዩ ነገሮች ላይ የሆነ እንደሆነ በተለይ በየአንዳንዱ ጉዳይ እንዲታይለት የሚጠይቀውን ዳኝነት መግለጽ አለበት፡፡
4. #ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን ነገር ለይቶ ስለ መግለጽ
⨳ለክርክሩ መሠረት ወይም መነሻ የሆነው ጉዳይ የተወሰነ ወይም የተለየ ነገር ስሆን በማመልከቻው ላይ ነገሩን አብራርቶ በመለየት መግለጽ አለበት፡፡
⨳ክሱ የሚመለከተው የማይንቀሳቀስ ንብረትን የሆነ እንደሆነ በክሱ ማመልከቻ ላይ ንብረቱን ለይቶ ለማወቅ የሚያስችሉት ምልክቶች መገለጽ ይኖረባቸዋል፡፡ ይኸውም ንብረት የሚለው በአካባቢው ወሰን ወይም በርስት መመዝገቢያ ላይ በተሰጠው ተራ ቁጥር በሆነ ጊዜ የወሰኑ ምልክት ወይም በመዝገብ ላይ የተሰጠው ቁጥር መገለጽ ይገባዋል፡፡
5. #ገንዘብን ለመጠየቅ በሚቀርብ ክስ ላይ ስለሚቀርቡ ዝርዝር መግለጫዎች
⨳ክስ የሚቀርበው በገንዘብ የሆነ እንደሆነ ከሳሹ የሚጠይቀውን ገንዘብ በማመልከቻው ላይ በትክክለኛ ሁኔታ ገልጾ ማስታወቅ አለበት፡፡
⨳ከሳሹ የሚጠይቀው ገንዘብ ልኩ ሊታወቅ የሚችለው በርሱና በተከሳሹ መካከል የሂሳብ ማጣራት ተግባረ ከተፈጸመ በኋላ የሆነ እንደሆነ በሚያቀርበው የክስ ማመልከቻ ላይ ሊጠይቅ የሚገባውን ገንዘብ በግምት ለመግለጸ ይችላል፡፡
⨳ክሱ የቀረበው ተለይቶ የታወቀ ዕቃ ወይም ሌላ ነገር ለማስመለስ የሆነ እንደሆነ ለክሱ መሠርት የሆነውን ነገር ትክክለኛ ዋጋ በማመልከቻው ላይ መገለጽ አለበት፡፡
⨳የቀረበው ክስ የሚያልቅ ወይም የሚበላሽ ወይም እለታዊ አገልግሎት ያለው ነገር የሚመለከት ስሆን በማመልከቻው ላይ የዚሁኑ የዕለት ዋጋ መግለጽ ያስፈልጋል፡፡

ፌናን ተጊበሉ
ታህሳስ 15/2014 ዓ.ም
ብዙ ሰላምና ከዘላቂም ሆነ ከጊዚያዊ አካል ጉዳት እንዲጠብቀወ ልባዊ ምኞቴ ነው!
በዚች መልዕክት ስለአለማቀፉ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት ጠቅላላ ይዘት ባጭሩ ይሕችን እንላለን፡፡!
ይህ ከአለማችን ጠቅላላ ህዝብ 1 ቢሊዎን፣ ከ20 አመታት በፊት በተደረገ ጥናት ከሀገራችን ጠቅላላ ህዝብ ከ15/20 የሚደርሰው የአለፉት የቅርብ አመታትን ግጭት ጉዳተኞች ሳይጨምር አካል ጉዳተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡
ይህም ለመጀመሪያ ጊዜ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ መብቶች በመደንገግ በፈረንጆች አቆጣጠር በ2006 በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ የጸደቀ፣ ኢትዮጵያም ከአራት አመታት በኋላ በተወካዮች ምከር ቤት በአዋጅ 676/2010 በማጽደቅ የሕጓ አካል አድርጋዋለች፡፡
በዚህ ስምምነት እታዲያ አካል ጉዳተኞችና ጉዳተኚነት ተገቢውን እውቅና አግኚተው ሀገራት በሚያደጉት ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በአካታችነት እንዲሰሩ እንደየአስፈላጊነቱም ልዩ ድጋፍ በማድረግ አካልጉዳተኖች ዜጎች በሀገራቸው የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ እንቅስቃሴዎች ሁሉ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችል ከባቢ ለመፍጠር ተስማምተዋል፡፡
በአንቀጽ 4 የመንግስታት ጠቅላላ ግዴታዎች በሚለው በተደነገገው መሰረት ሀገራት ነባር ሕጎቻቸው ከልካይና የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ የሚገድቡ ከሆኑ እንዲያሻሽሉ፤ አዳዲስ ሕጎችን ሲያወጡ አካልጉዳተኞችን ያካተተ መሆኑን ማረጋገጥ፤
መንገዶች፣ የህዝብ መገልገያ ህንጻዎች ሲገነቡ አካታችና ዘመኑ የሚጠይቀውን መስፈርት ያሟሉ መሆናቸውን በአስገዳጅ ሕጎችና አሰራሮች መቆጣጠር፤የሕዝብ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የምልክት ቋንቋ የሚያስተረጉሙ ሰራተኞች በቋሚነት እንዲኖሩ ማድረግ፤
በሀገሪቱ የሚደረጉ ፈጠራዎችን በልዩ ሁኔታ የበጀትና የሌሎችንም አስፈላጊ ድጋፎች በማድረግ ለአካል ጉዳተኖች ሂዎት ምቹ የሆነ ሀገር ይሆን ዘንድ መስራት፤
የትምህርትና የፍትህ አካላት በተቋም ግንባታም ሆነ በአገልግሎት አሰጣጥ አካል ጉዳተኞችን አካታች በሆነ መልክ እንዲያገለግሉ በትኩረት መስራት፤ አካል ጉዳተኞች ሰርተው ራሳቸውን እንዲችሉ የሕግና የነባራዊ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፤
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በ2000 አመተምህረት የአካል ጉዳተኞች የስራስምሪት (568/2000አዋጅን አውጥታለች፡፡
ነገር ግን ለሲ ረ ፒ ዲ ኮሚቴ ሪፖርት በተዘጋጀ ዘገባ ላይ በኢትዮጵያ በስራላይ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች 5554 ወይም6000 እንኳን የማይሞሉ መሆናቸውን ያሳያል፡፡
ውድ አንባቢ የአካቶ ትምህርት ከተጀመረ ከ10 አመታት በላይ ያለፈው ቢሆንም በ2012 ከትምህርት ሚንስቴር በተገኘ አመታዊ የሀገሪቱን የትምህርት ተደራሽነት በሚያሳየው ዘገባ እድሚያቸው ለትምህርት ከደረሱት አካል ጉዳተኛ ህጻናት የትምህርትቤትን በር ለመርገጥ እድል ያገኙት 11.5 ብቻመሆናቸውን ሲያሳይ 89.5 ፐርሰንቱ ቤት ተዘግቶበባቸው እንደሚገኝ ያሳያል፡፡
በሌላ በኩል አካል ጉዳተኞች በህግ ፊት በበቂሁኔታ እውቅና ያላገኙ በመሆናቸው ከባንክና ከሌሎችም የፋይናስ ተቋማት መበደርም ሆነ ንብረታቸውን አሲዘው መዋዋል እንደማይችሉ፤ ዋስ ወይም ምስክር መሆን እንደሚቸገሩ፤ ፍርድቤት ተካሰወው መቅረብ በተለይም እንቅስቃሴ ችግር ላለባቸው የችሎት ቦታዎች የማይመቹ ከፍተኛ ፎቆች መሆናቸው፤ ሊፍቶች ለአይነስውራን የድንጽ ፣ የብሬል ጽሁፍ የሌላቸው መሆኑ፤ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ከጥቂቶቹ በስተቀር ዋናውን የብሄራዊ ቴሌቪዥን ጨምሮ የምልክት ቋንቋ የሌላቸው በመሆኑ፤ የምልክት ቋን፻፻ቋ የሚያስተረጉም ባለሙያ የሌለ መሆኑ፤ ሀገራችን ስምምነቱን ከመተግበር አንጻር ብዙ ገና ብዙ የሚቀራት በመሆኑ በተለይም ለሀገራቸው ሲሉ አካለላቸውን በማጣት ላይ ላሉት ዜጎች ስንል ሁላችንም የየድርሻችንን በመወጣት ምቹ ሀገር እንድትኖረን ያገባኛል እንበል፡፡!
ቸር ይግጠመን!!!
ታህሳስ 18/2014
ሲሳይ ሰማኝ
ሰላም !!!
በዚች መልዕክት በኢፌድሪ ሕገመንግስት የሕግ አውጭነት ስልጣን ካላቸው ሁለት ምክር ቤቶች ስለፌደሬሽን ምክርቤት የሕገመንግስት መተርጎም ስልጣን በተለይም ስለሕገመንግስት አጣሪ ጉባኤ ጥቂት እንላለን፡፡
ፌዴረሽን ምክርቤት በአንቀጽ 62/2 በተሰጠው ስልጣን መሰረት አጣሪ ጉባኤው ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ብሎ የውሳኔ ሀሳብ ሲያቀርብለት መርምሮ ጉዳዩ በቀረበለት በ30 ቀናት ውስጥ ትርጉሙን ይሰጣል፡፡
የሕገመንግስት አጣሪ ጉባኤ፡-
ከህዝቡ በሕግ እውቀታቸውና ስነምግባራቸው እውቅናን ያገኙ ወይም የተመሰከረላቸው 6 ሰዎችን በተወካዮች ምክርቤት አቅራቢነት በሪፓብሊኩ ፕሬዝዳንት የሚሾሙ፣ ከፌደሬሽን ምክርቤት አባላት 3 ሰወች፣ እንዲሁም በዋና ሰብሳቢነትና በምክትል ሰብሳቢነት የኢፌድሪ ጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት፣ ባጠቃላይ 11 አባላት ያሉት ሆኖ ይዋቀራል፡፡
የዚህ ጉባኤ ስልጣንና ተግባርም በአንቀጽ 84 ተመልክቷል፡፡
1, የሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሕገመንግሥታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ሥልጣን ይኖረዋል፡፡ በሚያደርገው ማጣራት መሰረት ሕገመንግሥቱን መተርጎም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ለፌዴሬሽን ምክርቤት በጉዳዩ ላይ የውሳኔ ሃሳብ ያቀርባል፡፡
2, በፌዴራሉ መንግሥትም ሆነ በክልል ሕግአውጪ አካላት የሚወጡ ሕጎች ከዚህ ሕገመንግሥት ጋር ይቃረናሉ የሚል ጥያቄ ሲነሳና ጉዳዩም በሚመለከተው ፍርድቤት ወይም በባለጉዳዩ ሲቀርብለት መርምሮ ለመጨረሻ ውሳኔ ለፌዴሬሽኑ ምክርቤት ያቀርባል፡፡
3, በፍርድቤቶች የሕገመንግሥት ትርጉም ጥያቄ ሲነሳ
ሀ) ሕገመንግሥቱን መተርጎም አስፈላጊ ሆኖ ሳያገኘው ሲቀር ጉዳዩን ለሚመለከተው ፍርድቤት ይመልሳል፣ በአጣሪ ጉባዔው ውሳኔ ቅር የተሰኘ ባለጉዳይ ቅሬታውን ለፌዴሬሽኑ ምክርቤት በይግባኝ ማቅረብ ይችላል፡፡
ለ) የትርጉም ጥያቄ መኖሩን ያመነበት እንደሆነ በጉዳዩ ላይ የሚሰጠውን ሕገመንግሥታዊ ትርጉም ለፌዴሬሽን ምክርቤት ለመጨረሻ ውሳኔ ያቀርባል፡፡
4, የሚመራበትን ሥነሥርዓት አርቅቆ ለፌዴሬሽኑ ምክርቤት ያቀርባል፤ ሲፈቀድም ተግባራዊ ያደርጋል፡፡
ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም!!!
ሲሳይ ሰማኝ
ታህሳስ 18/2014
ስለጽኑ ዕስራትና የሞት ፍርድ ስለሚታገድባቸው ምክንያቶች፡-
ውድ ተከታዮቻችን በያላችሁበት የህሊናም ሆነ የፈጣሪ ሰላም ይብዛላችሁ፡፡! በዚች መልዕክት
በኢፌድሪ የወንጀል ሕግ አዋጅ ቁጥር 414/1996 ከጽኑ እስራትና የሞት ፍርድን ሊያሳግዱ ወይም ሊያስቀሩ ስለሚችሉ ጉዳዮች የደነገገውን ብናይ ጠቃሚ ስለመሰለኝ ይህችን ተጋበዙልኝ፡፡!
አንቀጽ 108 ጽኑ እሥራት
1 የጽኑ እሥራት ቅጣት የሚወሰነው ከባድ ወንጀል ባደረጉና በተለይም ለህብረተሰቡ አደገኛ በሆኑ ወንጀለኞች ላይ ነው፡፡
የጽኑ እሥራት ቅጣት ግቡ ተቀጪው እንዲታረምና ወደ ማህበራዊ ኑሮ እንዲመለስ ከማድረግ በተጨማሪ በተለይ ለህብረተሰቡ ደህንነት በጥብቅ ቁጥጥር ሥር እንዲቆይ ለማድረግ ነው፡፡
ይህ ቅጣት የሚቆይበት ጊዜ ከአንድ ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት ሊደርስ ይችላል፡፡ በሕጉም ተገልጾ የተደነገገ ሲሆን የዕድሜ ልክ እሥራት ሊወሰን ይችላል፡፡ ቢሆንም ስለአመክሮ የተወሰኑት ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ናቸው፡፡
2 የጽኑ እሥራት ቅጣት የሚፈጸመው በተለይ ለዚህ ቅጣት መፈጸሚያ እንዲሆኑ ታስበው በተሰሩና ለዚሁ በተሰናዱ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ብቻ ነው፡፡
የጽኑ እሥራት ቅጣት የአፈጻጸም ሁኔታ ከቀላል እሥራት የአፈጻጸም ሁኔታ በይበልጥ ይከብዳል፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ በወንጀሉ አስከፊነት ምክንያት ሞት የተፈረደባትን ወንጀለኛ ፍርድ እንዳይፈጸምባት ሊያደርጉ የሚችሉ ምክንያቶች-

1 ያረገዘች ሴት ሕይወት ያለው ልጅ የወለደች ስትሆንና ይህንኑም ልጅ መመገብና ማሳደግ ሲኖርባት የሞት ቅጣቱ በዕድሜ ልክ ጽኑ እሥራት ይለወጥላታል፡፡
2 በዚህ ሕግ ውስጥ በተመለከቱት ድንጋጌዎች (አንቀጽ 229 እና 103) መሠረት የሞት ቅጣት በይቅርታ ወይም በምህረት ሊለወጥ ወይም ቀሪ ሊሆን ይችላል፡፡

አልሚዎች እንጂ አጥፊዎች ከመሆን ይጠብቀን!!!
ሲሳይ ሰማኝ
1. የዉል ህግ ይርጋ

የይረጋ ጊዜን የሚመለከት የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1845 ህግ በሌላ አኳኋን ካልወሰነ በቀር ዉሉ እንዲፈፀም ወይም ካለመፈፀሙ የተነሳ ስለሚደረስ ጉዳት ወይም ዉሉ እንዲፈርስ የመጠየቅ መብት በ10 ዓመት ይርጋ ይቀራል ሲል ደንግጎ ይገኛል፡፡

2. ከዉል ዉጪ ኃላፊነት ይርጋ

ከዉል ዉጪ ኃላፊነት የዉል ግንኙነት ሳይኖር ወይም ዉል ላይ ባለተመሰረተ ግንኙነት በአንድ ሰዉ ጥቅም ወይም መብት ጉዳት ሲደርስ ለዚህ ጉዳት ኃላፊነት የሚደርስበትን አካል የሚለይና ጉዳት በካሳ መልክ እንዲስተካከል የሚያደርግ ሕግ ነዉ፡ እንዲሁም ጥፋት ሳይኖር የሚመጣ ኃላፊነትን ፣በሌላ ሰዉ ተግባር ኃላፊነትን እና በጥፋት ላይ የተመሰረተ ኃላፈነትን የሚያጠቃልል ሲሆን የኃላፊነቱ ምንጮች ተብለዉ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2027 ተደንግጓል፡፡

የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2143 ተበዳዩ ክስ ማቅረብ የሚችለዉ ካሳ የሚጠየቅበት ጉዳቱ ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 2 ዓመት ድረስ ሲሆን ጉዳቱ በወንጀል የሚያስቀጣ ሆኖ የይርጋ ዘመኑ ርዝመት የበለጠ እንደሆነ የካሳዉ ጉዳይ ክስ የይርጋ ዘመን ልክ በዚሁ መሰረት ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2065 መሰረት አንድ ሰዉ በባለይዞታነቴ  ወይም በይርጋ ደንብ መከሰስ ቀርቶልኛል ብሎ ቢከራከር ጥፋተኛ አይደለም በሚል ተደንግጎ ይገኛል፡፡

ፌናን ተጊበሉ
ጥር 2/2014 ዓ.ም
3. የቤተሰብ ህግ ይርጋ

ባል ወይም ሚስት በመሞታቸዉ ጋብቻ በሚፈርስበት ጊዜ ተጋቢዎች የግል ሀብታቸዉን በማስረዳት የራስን ድርሻ የመዉሰድ መብት አለዉ በማለት የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 884 ይደነግጋል፡፡ ይህ ድንጋጌ ጥያቄዉ በምን ያህል ጊዜ መቀረብ እንዳለበት ባይደነግም በጋብቻ ወቅት የተፈራ የግልም ሆነ የጋራ ንብረት ሳይከፈል ለረጅም ጊዜ ቆይቶ ጥያቄዉን ከረጅም ጊዜ በኋላ ማቅረብ የሕግ ዓላማ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1677(1) የጠቅላላ የዉል ሕግ ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት እንዳላቸዉ ስለሚደነግግ በጠቅላላ የዉል ሕጉ ደግሞ ዋናዉ የይርጋ ጊዜ በ1845 መሰረት 10 ዓመት ጊዜ ዉስጥ ካልተጠየቀ በይርጋ ይታገዳል፡፡የተሻሻለዉ የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 69. የተገባዉን የዉል ግዴታ እንዲፈርስ ለመጠየቅ ግዴታዉ መግባቱን ካወቀበት ቀን ጀምሮ 6 ወር፣ ጋብቻዉ ከተፈጸመ ጀምሮ 2 ዓመት የይርጋ ጊዜ እንዳለዉ ያስቀምጣል፡፡

ፌናን ተጊበሉ
ጥር 4/2014 ዓ.ም
❤1
ሠራተኛን በውጭ አገር ለሥራ ለማሰማራት የሁለትዮሽ ሰምምነት ስለማስፈለጉ፡-
በየኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ሰምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 አንቀጽ 12 መሠረት ሠራተኛን በውጭ አገር ለሥራ ማሰማራት የሚቻለው በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በተቀባይ አገር መካከል የሁለትዮሽ ስምምነት ሲኖር ብቻ ፡፡
ጥር 4/2014 ዓ.ም (ኦምኒኤል)
ስለ ይርጋ
በየኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ሰምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 አንቀጽ 73 መሠረት በአሠሪ፣ በኤጀንሲ፣ በኤጀንሲ ወኪል ወይም በሠራተኛ በሚፈፀም ጥፋት ምክንያት የሚቀርብ ማንኛውም አስተዳደራዊ አቤቱታ ጥፋቱ ከተፈፀመበት ወይም ጥፋቱ መፈፀሙ ከታወቀበት ቀን አንስቶ እስከ ሦስት ዓመት ድረስ ለሚኒስቴሩ ወይም አግባብነት ያለው ባለሥልጣን ካልቀረበ በይርጋ ይታገዳል፡፡
4. የዉርስ ይርጋ

በኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሕግ 5ኛ ክፍል የሀገሪቱ የዉርስ ሕግ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ዉርስ በአብዛኛዉ ያለ ኑዛዜ የሟች ዉርስ ለሟች ዘመዶች የሚፈጸምበት እና የሟች ዉረስ በሟች ኑዛዜ መሰረት የሚፈፀመበት ሥርዓት ነዉ፡፡

ኑዛዜ አይጸናም በማለት የሚቀርብ ክስ ወይም በሂሳብ አጣሪዉ የቀረበዉን የድልድልን አመዳደብ ሀሳብ ለመቃወም ኑዛዜዉ ከተነበበት አንስቶ የሚቆጠር የ15 ቀናት ጊዜ፤ ለዉርስ አጣሪዉ ከገለጹ በኋላ ባሉት ቀጣይ 3 ወራት ዉስጥእንደሆነ እና በማናቸዉም ምክንያት ቢሆን ግን ከ5 ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ዉስጥ ጥያቄዉን ማቅረብ እንዳለባቸዉ የፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥሮች 973 እና 974 ያስገነዝባሉ፡፡

ያለአግባብ የዉርሱን ንብረት በእጁ ካደረገዉ ሰዉ ላይ ንብረቱን ለማስመለስ የሚቀርበዉ ጥያቄም እንደዚሁ የሚቀርብበት የጊዜ ገደብ ያለዉ ሲሆን ከሳሹ የዉርሱ ንብረቶች በተከሳሹ መያዛቸዉን ባወቀ በ3 ዓመት ጊዜ ዉስጥ እንደሆነ በቁጥር 1000(1) ተገልጿል፡፡ ከሳሹ ይህን ጉዳይ አወቀም አላወቀም ሟቹ ከሞተ ወይም ከሳሹ በመብቱ ለመስራት ከቻለበት ቀን አንስቶ 15 ዓመት ካለፈ በኋላ የዉርስ ንብረት ለማስመለስ ጥያቄ ለማቅረብ እንደማይቻል ቁጥር 1000(2) ይናገራል፡፡ ከዚህ አነፃር የሰበር ዉሰኔ በሰ/መ/ቁ 59539 አንዱ ማሳያ ነዉ፡፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወራሽ ካልሆነ ሰው ላይ የውርስ ንብረት ለማስመለስ የሚቀርብ ጥያቄ በ1845 መሰረት በአስር አመት ውስጥ መቅረብ አለበት፡፡

ፌናን ተጊበሉ
ጥር 9/2014 ዓ.ም
ጤና ይስጥልኝ፡-
የፍትሕ ሥርዓቱን በእጅጉ ይደግፋሉ ይረዳሉ ተብለው ከሚወሰዱት አንዱ የጥብቅና አገልግሎት የሚያበረከቱ ጠበቆች ሲሆኑ እነዚሁ ጠበቆችንም ለማስተዳደር በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “የፌደራል ጥበቅና አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1249/2013” ወጥቶ በሥራ ላይ የዋለና በዚህ ድንጋጌ ላይም ጠበቆች ሊከተሉት የሚገባውን ሥርዓትንና ተላልፈው ከተገኙም እንደጥፋቱ ክብደት ቀላል እና ከባድ የዲስፕሊን ቅጣትን የሚጣልባቸው መሆኑን ያስቀመጠ ሲሆን ለዛሬ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሚከተለውን እናስፍር፤
መልካም ምንባብ፡-
በታገደ ወይም በተሰረዘ የጥብቅና ፍቃድ መታገዱን ወይም መሰረዙን እያወቀ የጥብቅና አገልግሎት መስጠትና ለዚህም ገንዘብ መቀበል ከባድ የዲስፕሊን ቅጣትን የሚያስከትል ሲሆን እንደዚሁም እንዲህ ዓይነት ድርጊት ማታለልም ስለሆነ የወንጀል ኃላፊነትንም የሚያስከትል መሆኑንም ልብ ይላል፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!
ደረጀ ማርቆስ
ጥር 2014 ዓ.ም
ጤና ይስጥልኝ ፡-
ማንም ሰው የመንግሥት ሥራን ማሰናከልና የመተባበር ግዴታ እያለበት ካልተባበረ በኢትዮጵያ የወንጅል ሕግ አንቀጽ 438 መሠረት በወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑን በተመለከተ ከደነገገው በመነሳት የሚከተለውን እንበል፤
መልካም ምንባብ
ማንም ሰው በሚያሽከረክር ጊዜ የትራፊክ ደንብ መተላለፍ ጋር በተያያዘ የክስ ወረቀትን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆን ከዚህ በላይ በጠቀስነው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 438 መሠረት የሚያስጠይቅ ነው፡፡ ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!
ደረጀ ማርቆስ
ጥር 2014 ዓ.ም
መሠየም ምን ማለት ነው?
መሠየም ማለት የተወሰነበትን ቅጣት የፈፀመ ቅጣቱ በይርጋ በይቅርታ የቀረለት፣ በአመክሮ ወይም በገደብ የታገደለት ማንኛውም ሰው በሚያቀርበው ጥያቄ መሠረት ከቅጣቱ በፊት የነበረው ስም እንዲመለስና ፍርዱ አንዲሰረዝለት በወ/ሕ/አ 232 መሠረት የሚጠይቅበት ስርዓት ነው። የወንል ሕጋችን በግልጽ እንደተደነገገው መሠየም የሚገኘው በመልካም ስራ እንጂ እንደ መብት ይገባኛል በማለት አይደለም፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ተቀጪው ከሞተ ወይም ችሎታ ካጣ የቅርብ ዘመዶቹ ወይም ወኪሉ ጥያቄውን ሊያቀርብ ይችላል።
መሰየም የሚፈቀደው ቅጣቱ ካለቀበት ወይም ከተቋረጠበት ጊዜ ጀምሮ ቢያንስ አምስት ዓመት ወይም በሌላ ቀላል ሁኔታዎች የሁለት ዓመት ጊዜ ካለፈ በኋላ ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ፀባዩ መልካም ከሆነና ወንጀል ካልፈፀመ እንዲሁም አቅሙና ሁኔታው በሚፈቅድለት መልኩ በፍርድ የተወሰነበትን ወይም ሊከፈል ይገባዋል ተብሎ የሚገመትበትን ካሳ፣ የዳኝነትና ማናቸውንም ኪሳራ ከከፈለ በመሰየም መልካም ስሙን ማስመለስ የሚችል ሲሆን ቅጣቱ በይርጋ የታገደለት ሰው ደግሞ ቅጣቱ ቢፈፀም ከሚጠናቀቅበት ጊዜ በፊት ልዩ ወይም የሚያስመሰግን ወታደራዊ ወይም ማኅበራዊ አስተዋፅኦ ካበረከተ መሰየም ይፈቀድለታል፡፡ ሆኖም ግን በወ/ሕ/አ 237 መሠረት መሰየም ከተፈቀደ በአምስት ዓመት ጊዜ እንደገና በሞት ወይም በፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል የሰራና የተፈረደበት ሰው መሰየሙ ይሰርዝበታል። ዳግመኛም የመሰየም ጥያቄ ማቅረብ አይችልም።
ጥር 12/2014 ዓ.ም (ኦምኒኤል)
በአመክሮ መፈታት ም ማለት ነው?
በአመክሮ መፈታት ማለት ተቀጪው የተወሰነበትን ቅጣት ቢያንስ ሦስት ሁለተኛውን ካጠናቀቀ በኋላ ይሄም ማለት አንድ ሶስተኛው ሲቀረው የተቀጩውን ፀባይ ማሻሻያና ወደ መደበኛ ኑሮው መመለሻ ይሆነዋል ተብሎ ሲታሰብ የተወሰነበትን የእስር ዘመን በሙሉ ሳያጠናቅቅ ሊፈታበት የሚችልበት አሰራር ሲሆን የእድሜ ልክ የተፈረደበት ሰው ሃያ ዓመት ከታሰረ በኋላ ነው የአመክሮ ጥያቄ ሊያቀርብ የሚችለው። ጥያቄውን እራሱ ተቀጪው ወይም የሚመለከተው አካል ሊያቀርበው የሚችል ሲሆን ጥያቄው የቀረበለት ፍ/ቤትም በወ/ሕ/አ 202 መሠረት በእስር ላይ እያለ የተረጋገጠ የጠባይ መሻሻል ማሳየቱን፣ ለደረሰው ጉዳት በተቻለ መጠን ካሳ መክፈሉን ሲያረጋግጥ እንዲሁም አመሉና ፀባዩ በአመክሮ ሲፈታ መልካም ውጤት ያስገኛል ብሎ ሲያምን እስረኛው በአመክሮ እንዲፈታ ይወስናል።
በአመክሮ መፈታት የፈተና ጊዜ ነው የሚባለው በአመክሮ የወጣው ግለሰብ ከእድሜ ልክ እስራት ባነሱ ቅጣቶች ላይ ቀሪውን የእስራት ዘመኑን ከሁለት እስከ አምስት ዓመት ጊዜ የእድሜ ልክ እስር በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት እስረኛው ከእስር ተለቆ ስለሚፈተን/ክትትል ስለሚደረግበት ነው፡፡ በፈተናው/በክትትሉ ወቅትም የተወሰነለትን የጠባይ ደንብ ከጣሰ ወይመ አዲስ ወንጀል ከፈፀመ በተሰጠው የሙከራ እድል መጠቀም ባለመቻሉ በወ/ሕ/አ 206 መሠረት አመክሮው ተሽሮ ቀሪ ቅጣቱን ይፈፅማል። አዲስ ወንጀል የፈፀመ በአመክሮ ላይ ያለ ሰው የደጋጋሚነት ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆነው በአመክሮ የተቀነሰለት ቅጣትና የአዲሱ ወንጀል ቅጣት ተደርቦ ይፈፀምበታል።
ጥር 12/2014 ዓ.ም (ኦምኒኤል)
5. የንብረት ሕግ ይርጋ

ይዞታዉ የተወሰደበት ወይም በይዞታዉ ላይ ሁከት የተነሳበት ሰዉ የያዘዉ ነገር ከተነጠቀበት ወይም በይዞታዉ ላይ ሁከት ከተነሳበት ቀን አንስቶ እስከ 2 ዓመት ድረስ ካልጠየቀ እጅ ይዛወርልኝ የማለት ክስ መብቱ ይቀርበታል፡፡

6. የስጦታ ዉል ይርጋ

አንድ ስጦታ ከተደረገ ከ2 ዓመት በኋላ ይፍረስልኝ የሚል ጥያቄ ተቀባይነት የለዉም፤የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2441 ስጦታ እንዲቀነስ ወይም እንዲሻር ለመጠየቅ 2 ዓመት ይርጋ እና የስጦታዉ ዉል የተደረገዉ በመንፈስ መጫን ሳይሆን የዉሉ አጠቃላይ ይዘት ለሞራልና ለሕግ ተቃራኒ ስለሆነ ይፍረስልኝ የሚል ጥያቄ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2441 (1) መሰረት 2 ዓመት ሳይሆን በፍትሐብሄር ሕግ ቁጥር 1845 የተመለከተዉ የ10 ዓመት ይርጋ ነዉ፡፡ እንዲሁም የስጦታ ዉል ይፈጸምልኝ ጥያቄ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1676(1) እና 1845 መሰረት በ10 ዓመት ይርጋ ቀሪ ሊሆን ይገባል፡፡

ፌናን ተጊበሉ
ጥር 12/2014 ዓ.ም
7. የአሰሪና ሰራተኛ ህግ ይርጋ

በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 ቁጥር 163 መሰረት በቅጥር ላይ ከተመሰረተ ግንኙነት የመነጨ ማንኛዉም ክስ የመብቱን ጥያቄ ለማቅረብ ከሚቻልበት ቀን ጀምሮ እስከ 1 ዓመት ድረስ፣ ወደ ሥራ ልመለስ በሚል የሚቀርብ ክስ ዉሉ በተቋረጠ በ3 ወር ጊዜ ዉስጥ፤ የደመወዝ፣የትርፍ ሰዓትና የሌሎች ክፍያዎች ጥያቄ መጠየቅ ከሚገባዉ ጊዜ ጀምሮ እስከ 6 ወር ባለዉ ጊዜ እና የሥራ ዉል በመቋረጡ ምክንያት በሰራተኛዉም ሆነ በአሠሪዉ የሚቀርብ ጥያቄ ሥራ ዉሉ በተቋረጠ በ6 ወር ጊዜ ዉስጥ ካልቀረበ በይርጋ ይታገዳል፡፡

8. የእንደራሴነትና የዉክልና ህግ ይርጋ

በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር. 2187 (2) መሰረት ሿሚዉ (ወካዩ) ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ ማለትም በተሰጠ ዉክልና ላይ የጥቅም ግጭት ተከስቶ ከሆነ ይህ ጥቅም ግጭት ያስነሳዉ ዉል መደረጉን ካወቁ ከ 2 ዓመት በኋላ እንዲፈረስ መጠየቅ በይርጋ የሚታገድ ነዉ፣ ወካይ የሆነ ወገን በተወካይ አማካኝነት የተደረገን ህገ ወጥ ዉል እንዲፈረስ በሚል የሚቀርበዉ አቤቱታ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1845 መሰረት በ10 ዓመት ይርጋ እንጂ በ 2 ዓመት የሚታገድ አለመሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰ/መ/ቁ 67376 ዉሳኔ ሰጥቷል፡፡

ፌናን ተጊበሉ
ጥር 16/2014 ዓ.ም
ሰላም ለሁላችን!!!
በዚች መልዕክት በሕገመንግስታችን በይርጋ ስለማይታገደው በሰው ልጆች ላይ ስለሚፈጸም ወንጀል የተደነገገውን ይኸው ታነቡልኝ ዘንድ!-
አንቀጽ28
በስብዕናላይስለሚፈጸሙወንጀሎች
1 ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና በሌሎች የኢትዮጵያ ሕጎች በሰውልጅ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው የተወሰኑትን ወንጀሎች፣ የሰውዘር የማጥፋት፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ የመውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን የመሰወር፣ ወይም ኢሰብዓዊ የድብደባ ድርጊቶችን በፈጸሙ ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ አይታገድም፡፡ በሕግ አውጪው ክፍልም ሆነ በማንኛውም የመንግሥት አካል ውሳኔዎች በምሕረት ወይም በይቅርታ አይታለፉም፡፡
2 ከዚህ በላይ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተጠቀሱትን ወንጀሎች ፈጽመው የሞት ቅጣት ለተፈረደባቸው ሰዎች ርዕሰብሔሩ ቅጣቱን ወደ ዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ሊያሻሽለው ይችላል፡፡

ከወንጀል የጸዳ ሂወት ለሁላችንም!
16/05/2014 ዓ.ም
( ሲሳይ ሰማኝ)