የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
276 subscribers
366 photos
3 videos
137 files
97 links
ይህ የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት ቻናል ስለኢትዮጵያ ሕጎች)ማብራሪያ የሚሰጥበት፣ አዳዲስ ሕጎች የሚጋሩበት፣ ሕግ ነክ ዜናዎችና መረጃዎች የሚተላለፉበት፣ በዳይሬክቶሬቱ የተሰጡ የንቃተ-ሕግ ስልጠናዎች፣ የሕግ መልዕክቶች፣ በራሪ ጽሑፎች እና መሰል ሰነዶች የሚለቀቁበት ነው።
መልካም ቆይታ!
Download Telegram
ተጠርጣሪን ፍርድ ቤት በ48 ሰዓት አለማቅረብ ወንጀል መሆኑን ያውቃሉ? ከአገራችን የህግ
ማዕቀፍ አኳያ እንዴት ይታያል?
____________________________
ወንጀል በሚፈጸምበት ጊዜ አንድን ተጠርጣሪ በህግ ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ፍርድቤት በ48 ሰዓት ቀርቦ በቁጥጥር የዋለበትን ምክኒያት የማወቅ መብቱ እንደሚጠበቅ በአገራችን የህግ ማእቀፍ ላይ ተካቷል፡፡
በወንጀል ድርጊት በመፈፀም ተጠርጥረው በፖሊስ ወይም በህግ አስከባሪ አካላት የተያዙ ሰዎች በአርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ በአቅርቢያ በሚገኝ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብታቸው
በሚጣስበት ጊዜ በህግ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብታቸውን ማስከበር የሚችሉበት ስርዓት አለ፡፡ እንዲሁም ይህንን በፈፀመው ህግ አስከባሪ ወይም ፖሊስ ላይ የሚያስከትለው
ተጠያቂነትም አለ፡፡
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት በአንቀጽ 19 (4) በግልፅ እንደተደነገገው ተጠርጣሪዎችን የያዛቸው የፖሊስ መኮንን ወይም የህግ አስከባሪ በጊዜ ገደቡ ፍርድ ቤት አቅርቦ የተያዙበትን ምክንያት ካላስረዳ የተያዙ ሰዎች ለፍርድ ቤት የአካል ነፃነታቸውን እንዲያስከብርላቸው የመጠየቅ ሊጣስ የማይችል መብት አላቸው፡፡
ይህ የተያዙ ሰዎች በጊዜ ገደብ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ሲቀር የሚኖረው መብት የአካል ነፃነትን ማስከበር /Habeas Corpus/ የሚመለከት ሲሆን የሚቀርብበት ስርዓትም በፍትሐብሔር ስነ-ስርዓት ህግ በክፍል 7 ተገድዶ የመያዝን ህጋዊነት ለማጣራት ስለሚፈፀም ስነ ሰርዓ ርእስ ስር ከአንቀፅ 177 – 179 በተመለከተው መሰረት ነው፡፡ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ህጉ አንቀጽ 177 ላይ በወንጀል ህግ የተደነገገውን መሰረት በማድረግ ሳይወሰንበት ወይም ሳይፈርድበትና ማናቸውንም ሌላ ትዕዛዝ ሳይሰጥ የተያዘ ወይም የታሰረ ሰው ፍርድ ቤት እንዲቀርብ በማመልከቻ የተገደደው ሰው እራሱ ወይም ማናቸውም ሌላ ሰዉ በቃላ መሃላ ማመልከቻ ማቅረብ ይችላል፡፡
የአካል ነፃ ለመውጣት የሚቀርብ አቤቱታን የመመልከት ስልጣን የፌደራል ፍርድ ቤቶች በአዋጅ ቁጥር 25/1988 በአንቀጽ 5(10)የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ለክልሎች
በህገ መንግስቱ አንቀጽ 80/2/ በተሰጣቸዉ የዉክልና ስልጣን መሰረት ጉዳዩ የሚመለከተው በጠቅላይ ፍርድ ቤት ይሆናል፡፡
ማመልከቻው የቀረበለት ፍርድ ቤት የአቤቱታውን እውነተኛነት ለማጣራት በቁጥጥር ስር የዋለው ፖሊስ ወይም የህግ አስከባሪ ተጠርጣሪውን በአካል ፍርድ ቤት ይዞት እንዲቀርብ
እና እንዲያስረዳ በማድረግ ጉዳዩን ይመረምራል (ፍ/ስ/ስ/ህ ቁጥር 178)፡፡
በፍትሐብሄር ስነ ስርዓት ህጉ አንቀጽ 179 (2) መሰረት የተያዘው ሰው በህገ ወጥ መሆኑን ካረጋገጠ ወዲያዉኑ ከእስር እንዲለቀቅ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ይህ ትዕዛዝም ያለቅድመ ሁኔታ
መፈፀም እንዳለበት በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ መጨረሻ በፓራግራፍ ላይ ተገልፆል፡፡  ነገሩ ባጠራጠረ ጊዜ የተያዘ ሰው በተፈለገ ጊዜ እንዲቀርብ የሚያስችል ዋስ ጠርቶ እንዲለቀቅ ይህም የገንዘብ ወይም የሰዉ ዋስ እንዲጠራ ትዕዛዝ ሊሰጥ እንደሚችል በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ህግ ከአንቀጽ 179 (3) ተደንግጓል፡፡
ሆኖም ግን አንድ ፖሊስ ወይም የህግ አስከባሪ ከአርባ ስምንት ሠዓት በላይ ተጠርጣሪውን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማስሩ ምክንያት በግለሰብ መብት እንዲሁም በህዝብና በመንግስት
ሰላም፣ ደህንነትና ጥቅም ላይ ከባድ ወንጀል ፈፅሟል ተብሎ የተያዘው ተጠርጣሪ በሥነ ሥርዓት ግድፈት ምክንያት ቢለቀቅ የሚደርሰውን ጉዳት ማመዛዘን የሚገባ በመሆኑ በህገ
መንግስቱ አንቀጽ 19 (4) ላይ ፍትሕ እንዳያጓድል ሁኔታው የሚጠይቅ ከሆነ ፍርድ ቤቱ የተያዘው ሰው በጥበቃ ሥር እንዲቆይ ለማዘዝ ወይም ምርመራ በማካሄድ ተጨማሪ ጊዜ
ሲጠየቅ አስፈላጊ በሆነ መጠን ብቻ ሊፈቅድ እንደሚችል ተቀምጦል፡፡ ይህንን ሲወስንም ፖሊስ ምርመራ ወይም የህግ አስከባሪ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ምርመራውን አጣርተው የተያዘው ሰው በተቻለ ፍጥነት መደበኛ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ያለውን መብት የሚያስከብር መሆን እንዳለበት በዚሁ አንቀጽ ላይ ተደንግጓል፡፡
የወንጀል ተጠያቂነትበተመለከተ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 423 እንተደነገገው ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ በህግ ከተመለከተው ውጭ ወይም ህጋዊ ስርዓትና ጥንቃቄ ሳይከተል ሌላውን ሰው በመያዝ ወይም በማሰር ነፃነቱን ያሳጣው እንደሆነ ከአስር ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና መቀጮ ይቀጣል፡፡ ስለዚህ ፖሊስ ወይም የህግ አስከባሪ በቁጥጥር ስር የዋለውን ተጠርጣሪ በህግ በተወሰነው 48 ሰዓት ውስጥ በአቅራቢያ የሚገኝ ፍርድ ቤት ያለውን ስልጣን በመጠቀም ባያቀርበው የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል ነው፡፡

ለዛሬ ያዘጋጀንላችሁን ጽሁፍ በዚሁ አበቃን በቀጣይ በሌላ አርዕስት እስክንገናኝ መልካም ጊዜን ተመኘን፡፡

ፌናን ተጊበሉ
የሚያዝበት በቂ ገንዘብ ሳይኖረዉ ቼክ መፃፍ የሚያስከትለዉ የህግ ተጠያቂነት

በቼክ አጭበርብሮ ተያዘ፤ ደረቅ ቼክ ፃፈ እየተባለ ሲነገር ብዙ ጊዜ ይሰማል፤ ለመሆኑ አንድ ሰዉ በራሱ ስም ከባንክ ባወጣዉ ቼክ እራሱ ፅፎ እና ራሱ ፈርሞ የማጭበርበር ወንጀል
የሚፈፅመዉ እንዴት ነዉ? በቂ ገንዘብ ሳይኖር ቼክ መፃፍ ከህግ አንፃር የሚያስጠይቅበት አግባብ ምን ይመስላል?

ቼክ ሲባል በባንክ ተቀማጭ ገንዘብ ያለዉ ሰዉ ለራሱ ወይም ለሌላ ሰዉ ገንዘብ እንዲከፈል ትእዛዝ ለባንክ የሚያቀርብበት ሰነድ ማለት ሲሆን፤ በዚህ መነሻነትም ግለሰቡ በቼክ ለመጠቀም በቅድሚያ በባንክ የተቀመጠ ሊያዝበት የሚያስችለው በቂ የሆነ ገንዘብ በአካዉንቱ ዉስጥ ሊኖረዉ ይገባል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ግለሰቡ በቼክ እንዲከፈል
የሚያዘዉ ገንዘብ በባንክ ከተቀመጠው አጠቃላይ ሂሳቡ የማይበልጥ ወይም በግሉ ካለዉ ከተቀመጠ ገንዘብ ጋር እኩል ሊሆን ይገባል፡፡ ነገር ግን ይህሳይሆን ቀርቶ በቂ ገንዘብ
እንደሌለዉ እያወቀ ቼክ ፅፎ መስጠት በህግ የሚያስጠይቅ ወንጀል ይሆናል ማለት ነዉ፡፡

ቼክ ባንክ እንዲከፍል ትእዛዝ የሚሰጥበት ሰነድ እንደመሆኑ የእራሱ የሆነ የሚያዝበት በቂ ገንዘብ ሳይኖረዉ ቼክ ፅፎ እና ፈርሞ መስጠት በወንጀል ተጠያቂ እንደሚያደርግ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 693 (1)ላይ "ማንም ሰው ቼክ በሚያወጣበት ወይም ቼኩ ለባንክ በሚቀርብበት ጊዜ የሚያዝበት በቂ ገንዘብ አለመኖሩን እያወቀ ቼክ ያወጣ
ወይም የሰጠ እንደሆነ በቀላል እስራት ወይም እንደነገሩ ክብደት ከ10 አመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እና መቀጮ ይቀጣል” በሚል ይደነግጋል እንዲሁም በዚሁ አንቀፅ ቁጥር (2) መሰረት ደግሞ አድራጎቱ የተፈፀመዉ በቸልተኛነት እንደሆነ በመቀጮ ወይም ከአንድ አመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ያስቀጣል" በሚል የሚያስከትለዉን የህግ ተጠያቂነት
ያብራራዋል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር ለማግኘት በጊዜዉ ገንዘብ በእጃቸዉ ላይ ስለሌላቸዉ ብቻ ወይም እንደ ጥሩ አማራጭ በመዉሰድ ቼክ ፅፈዉ እንደዋስትና የሚያሲዙበት ሁኔታ አለ፤ ከህግ አንፃር ግን ቼኩ በማስያዣነት የተሰጠ መሆኑን የቼኩ ባለቤት እና ቼኩ የተፃፈለት ግለሰብ የሚያዉቁ መሆኑ ግንዛቤዉ ስላላቸዉ የማታለል ወንጀል ተፈፅሟል ለማለት ባይቻልም እንኳን፤ ተከሳሹ ጥፋተኛ ለመሆኑ የሚያዝበት ገንዘብ አለመኖሩን ወይም ተቀማጭ ያደረገዉ ገንዘብ ማለቁን እያወቀ፤ ወይም ቼኩ ለክፍያ ባንክ በሚቀርብበት ጊዜ በቂ ገንዘብ አለመኖሩን እያወቀ ቼክ ፅፎ እና ፈርሞ በመስጠቱ በወንጀል ህጉ ተጠያቂ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

በአጠቃላይ የወንጀል ህጉ በቼክ አማካኝነት የሚታለል ሰው እንዳይኖር ለመጠበቅ ወይም ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን በመገንዘብ ጥቅም ለማግኘትም ይሁን ባንክ ያለዉን ቀሪ
ገንዘብ ምን ያህል መሆኑን ሳያረጋግጡ አሊያም በቸልተኝነት ቼክ ፅፎ እና ፈርሞ መስጠት ዞሮ ዞሮ ከተጠያቂነት የሚያድን አለመሆኑን በመገንዘብ እንደዚህ አይነት ተግባራትን የሚፈጽሙ አካላት ቼክ ከመጻፋቸው በፊት በቂ ገንዘብ እንዳላቸው በማረጋገጥ እራሳቸውን ከወንጀል አድራጊነት ቢከላከሉ መልካም ነው፡፡

መልካም ቀን ተመኘን!!
ፌናን ተጊበሉ
ሰላም ዉድ ተከታታዬቻችን በዛሬው እለት የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ
አዋጅ እና አዋጁን ለማስፈጸም የወጣውን ደንብ ለማስፈጸም በሚኒስትሮች ኮሚቴ የወጣውን መመሪያ ቁጥር 6/2012ን pdf አዉርዳችሁ እንድታነቡት አዘጋጅተናል፡፡

መልካም ቀን ተመኘን
ሰላም ውድ ተከታታዮቻችን!የወንጀል ሕጋችን ከአንቀጽ 620 ጀምሮ ባሉት አንቀፆች በግብረ ሥጋ ነፃነትና ንፅህና ላይ ለሚፈፀሙ ወንጀሎች የተለያዩ ቅጣቶችን አስቀምጧል።የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል ማንም ሰው የተበዳዩን ችሎታ ማጣት እያወቀ በኃይል፣አእምሮውን ካጣ፣የአእምሮ ደካማ ወይም ዘገምተኛ ከሆነ፣ከእብድ ወይም አእምሮውን ከሳተ ወይም በማናቸውም ሌላ ምክንያት የድርጊቱን ምንነት ወይም ድርጊቱ የሚያስከትለውን ውጤት ለይቶ ለማወቅ ከማይችል ሰው ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የፈፀመ ወይም ወይም ይህን መሰል ወይም ሌላ ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆነ ተግባር የፈፀመ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እሥራት ወይም ከአሥራ አምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት ይቀጣል።
አሥራ ሦስት ዓመት ባልሞላቸው ህፃናት ላይ የሚፈፀምን ጾታዊ ጥቃት በተመለከተ ማንም ሰው ከእርሱ ጋር ተቃራኒ ጾታ ካላት ዕድሜው አስራ ሦስት ዓመት ካልሞላት ልጅ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የፈፀመ ወይም ይህችው ልጅ እንዲህ አይነቱን ድርጊት ከእርሱ ጋር እንድትፈጽም ያደረገ እንደሆነ ከአስራ አምስት ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስራት ይቀጣል።ይሄው ድርጊት የተፈፀመው በሴት ከሆነ ደግሞ ከአስር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ትቀጣለች። ተመሳሳይ ጾታ ባለው ሰው ላይ የሚፈፀምን ጾታዊ በተመለከተ ማንም ሰው ከእርሱ ጋር አንድ ዓይነት ጾታ ባለውና ለአካለ መጠን ባልደረሰ ልጅ ላይ የፈፀመ እንደሆነ እንደተበዳዩ ዕድሜ( አስራ ሦስት ዓመት ሆኖ አስራ ስምንት ዓመት ያልሞላው አልያም ደግሞ ከአስራ ሦስት ዓመት በታች) ከሦስት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት አልያም ደግሞ ከአስራ አምስት ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል።
የወንጀል ሕጋችን ጾታዊ ጥቃትን በተመለከት ያካተታቸው ነጥቦች እኚ ብቻ አይደሉም።ብዙ ናቸው።ድርጊቱ ሴትም ላይ ሆነ ወንድ ላይ የተፈፀመው፣የድርጊቱ ፈጻሚ ወንድም ሆነ ሴት እንደሚያስጠይቅ በግልፅ ተቀምጧል።
ሆኖም ዛሬም ጾታዊ ጥቃትን በተመለከተ የምንሰማቸው ዜናዎችም ሆኑ የምናያቸው ድርጊቶች ሰላምን ይነሳሉ።ጾታዊ ጥቃት ማድረስ ሳይሆን አለማድረስ ብርቅ ሆኗል።ለዚህ ደግሞ እንደምክንያት በተደጋጋሚ እየተጠቀሰ ያለው የወንጀል ሕጋችን ብዙ ትኩረት አልሰጠውም፤ጾታዊ ጥቃት በሚያደርሱ ሰዎች ቅጣቱ ሊጨምር ይገባል የሚሉት ናቸው።ነገር ግን ሕጉ በመሻሻሉ ብቻ አጥጋቢ ውጤት ይመጣል ወይ? አይመስለኝም።ከሕጉ መሻሻል በላይ ህብረተሰቡ እንዲህ አይነት ድርጊትን አምርሮ በማውገዝ መሰል ድርጊቶን የሚፈፅሙ ሰዎች ከእስር ቤትም ሆነ ከሞት ቅጣት በላይ ህብረተሰቡን በማክበር እና በመፍራት ጾታዊ ጥቃት ፈፅሜ የት አባቴ ልገባ የሚል አቋም እንዲኖራቸው ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ ብንጫወት መልካም ነው።

ሰናይ 8/11/2012 ዓ.ም ( ኦምኒኤል)
ሰላም ጤና ይስጥልኝ እንደምን አደራችሁ ባለፈው ጽሁፍ የሙስና ወንጀሎች በተመለከተ ክስ ለመመስረት እና ክርክር ለማካሄድ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሥልጣንና ተግባር በሚዘረዝረው አንቀጽ 8 (2) ለ መሰረት ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተሰጠ መሆኑን አንብበን ያቆምን መሆናችን ይታወሳል፡፡ በዚህ ጽሁፍ ደግሞ መነሻ ወደሆነን የሙስና ወንጀሎች ከመግባታችን በፊት ስለ ሙስና ወንጀሎች ለማውራት መሰረት ስለሚሆነን አዋጅ ቁጥር 881/2007 መውጣት ምክንያት ብናነብ መልካም ነው፡፡
ለዚህ አዋጅ መውጣት በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ፡-
1. በ1996 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ የተደነገጉ የሙስና ወንጀሎች ውስጥ በአፈፃፀም ወቅት የተስተዋሉ ግልጽነት የሚጎላቸውን ድንጋጌዎች ግልጽ ማድረግና ማሻሻል በማስፈለጉ
2. የሙስና ወንጀሎቹ ማካተት የነበረባቸውን ተመሳሳይ ተግባራት በተለይም ከህዝብ የተሰባሰበ ወይም ለህዝብ ተብሎ የተሰባሰበ ሀብት በሚያስተዳድሩ የግል ዘርፍ አካላት የሚፈጸሙ ተመሳሳይ ተግባራትን በአግባቡ ያላካተቱ በመሆናቸው እነዚሁ ማካተት በማስፈለጉ
3. ሀገራችን ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው የተባበሩት መንግስታት የፀረ-ሙስና ኮንቬንሽን እና የአፍሪካ ህብረት የሙስና መከላከያና መዋጊያ ኮንቬንሽን በግል ዘርፍ ተቋማት ውስጥ የሚፈፀሙ የጉቦኝነት፣ የምዝበራ እና ተመሳሳይ ተግባራት በሙስና ወንጀልነት መፈረጅ እንዳለባቸው በፈራሚ አገሮች ላይ ግዴታ የሚጥል በመሆኑ ሕጉን ከዚህ አኳያ ማሻሻል በማስፈለጉ
4. በተግባር የታዮ ችገሮችን በመፍታት የተሟላ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ማድረግ የፀረ ሙስና ትግሉን ለማጠናከር እና ሀገራችን ያለባትን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ግዴታ በአግባቡ እንድትወጣ ለማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ
5. የሙስና ወንጀሎች በፈጣን ሁኔታ የመቀያየር ባህሪ ስላላቸው አጠቃላይ ወንጀሎችን በሚደነግገው የወንጀል ህግ ውስጥ እንዲካተቱ ከማድረግ ይልቅ ራሱን በቻለ አዋጅ እንዲደነገጉ ማድረግ ተመራጭ ሆኖ በመገኘቱ
የሚሉት ምክንያቶች ይገኙበታል፡፡ ሰላም ቆዮኝ!
አርብ 10/11/2012 ዓ.ም
ህድአት ጌታቸው
ሕ/ስ/ም/ዳ/ዐቃቤ ሕግ
ሰላም!ዛሬ ስለ አባይ ሕግ ላይ( አለም አቀፍ ስምምነት ላይ) ተመርኩዤ ትንሽ ላውጋችሁ።
11 ተፋሰስ ሀገራትን(ኢትዮጵያ፣ታንዛንያ፣ኡጋንዳ፣ኬንያ፣የመሀል ተፋሰስ ሀገራት፣ደቡብ ሱዳን፣ኤርትራ፣ሩዋንዳ፣ብሩንዲ፣ሱዳን እና ግብጽ) የሚያቋርጥ የአለማችን ረዥሙ ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ሲሆን ነጭ ናይል፣ሰማያዊ ናይል እና አትባራ የሚባሉ ገባር ወንዞች ሲኖሩት ከገባሮቹ ውስጥ እጅግ ብዙውን ፐርሰንት የሚሸፍነው ከኢትዮጵያ በመነሳት ከሚገብሩት ወንዞች ነው።ሆኖም አጠቃቀም ላይ ግን የኢትዮጵያ መብት ችላ የተባለ ይመስላል።ይሄ የሆነበት ምክንያት አባይን በማስመልከት የተደረጉ አብዛኞቹ ስምምነቶች የኢትዮጵያን መብት ከግንዛቤ ያልወሰዱ በመሆናቸው ነው።እነዚህ ስምምነቶችን ለመጥቀስ ያህል የ 1891 የጣልያንና የእንግሊዝ ስምምነት፣የ1901 የእንግሊዝና የጣልያን ስምምነት፣የ1902 የእንግሊዝና የኢትዮጵያ ስምምነት፣የ1906 የቤልጂየም እና የእንግሊዝ ስምምነት፣የ1906 የእንግሊዝ፣የጣልያን እና የፈረንሳይ ስምምነት፣የ1925 የእንግሊዝና የግብጽ ስምምነት፣የ1929 የእንግሊዝና የግብጽ ስምምነት፣የ1952 የእንግሊዝና የግብጽ ስምምነት፣የ1959 የግብጽና የሱዳን ስምምነት ናቸው።እነዚህ ስምምነቶች የናይልን ጥቅም ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ለግብጽ ለማዋል የሚጥሩ ናቸው።እነዚህ ስምምነቶች ግን በአለም አቀፍ ስምምነት ደረጃ ተቀባይነት የማይኖራቸው ዋነኛው ምክንያት ብዙ አለም አቀፍ ስምምነቶችን የሚቃረኑ በመሆናቸው ነው።
ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ የተደነገጉ አለም አቀፍ ስምምነቶች ፍትሀዊና ምክንያታዊ የመጠቀምን መብት እንዲሁም ደግሞ ሌሎች ላይ ጉልህ ጉዳት ያለማድረስን ግዴታ ይደነግጋሉ።ይሄንን ከ ለመጓጓዣነት የማያገለግሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ለማስተዳደር ከወጣው አለም አቀፍ ስምምነት አንቀጽ 5 እና 7 መረዳት ይቻላል።
የቬና ቃልኪዳን የስምምነት ሕግ አንቀጽ 11 እና 34ን በምንመለከትበት ጊዜ ደግሞ በሀገራት መካከል የሚከናወን ማንኛውም አይነት ስምምነት በስምምነቱ ላይ አቋሟን ባልገለጸች ሀገር ላይ ስምምነቱ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው በግልጽ ተቀምጧል።እነዚህ እና ሌሎች አለም አቀፍ ስምምነቶችን በምናገላብጥ ጊዜ ኢትዮጵያ የናይልን ጥቅም የማትቋደስበት ምንም ሕጋዊ ምክንያት እንደሌለ እንረዳለን።

ሰናይ 10/11/2012 ዓ.ም!(ኦምኒኤል)
ሰላም ውድ ተከታታዮቻችን እንዴት ሰነበታችሁ ከዛሬ ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት የማቀርበው ቀረጥ ሳይከፈልባቸው ወደ ሀገር ገብተው በባንክ በመያዣ ለተያዘ ህንፃ ግብዓትነት ስለሚውሉ ዕቃዎች የቀዳሚነት መብት ላይ የተዘጋጀ ጽሑፍን ይሆናል፡፡ መልካም ንባብ

ከግብር እና ቀረጥ ነፃ መብትን በመጠቀም ግብር እና ቀረጥ ሳይከፈልባቸው ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ ግብዓቶችን በመጠቀም የተገነባን ለምሳሌ ሆቴልን አንድ አበዳሪ ባንክ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ፈቃድ ሳያገኝ የሆቴሉን ህንፃ ለዕዳ መያዣ ቢያደርግ ባለሥልጣኑ መያዣው(ሆቴሉ) ሳይሸጥ ወይም ባንኩ የባለቤትነት ስሙን ወደ ራሱ ሳያዞር (before it is acquired by the bank) ከባንኩ ዕዳ ቀድሞ የግብዓቶቹ ቀረጥና ታክስ እንዲከፈለው መጠየቅ ይችላል ወይም አይችልም?

ጥያቄውን ለመመለስ ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን የጉምሩክ ሕጎች (law of customs)፣ የፎርክሎዠር ሕግ (Foreclosure laws)፣ የንብረት ሕግ ስለዕቃዎች (law of property on goods) እና ሌሎችንም መፈተሽ ያለባቸውን ሕግጋቶች ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው ሕጎች አንዱ የሆነውን የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006ን ስንመለከት የአዋጁ አንቀፅ 130(6) “ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልበት ወደ አገር የገባን ዕቃ በዋስትና ማስያዝ የሚቻለው ከባለሥልጣኑ ጋር በቀረጥና ታክስ አከፋፈል ረገድ ላይ ስምምነት ሲደረስ ይሆናል” ሲል ይደነግጋል ይህ ማለት የዕቃው ባለቤት ቀረጥና ታክሱን የሚከፍል መሆኑንና ስለአከፋፈሉ ሁኔታ ከባለሥልጣኑ ጋር ስምምነት ላይ ሳይደርስ ዕቃው ለዕዳ መክፈያነት በመያዣ መስጠት አይችልም ማለት ነው፡፡ እዚህ ጋር አብሮ መነሳት ያለበት ጉዳዩ “ዕቃ” ማለት ምን ማለት ወይም አዋጁ ይህን ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠው ለየትኞቹ ዕቃዎች ነው የሚለው ነው፡፡ የአዋጁ የትርጓሜ አንቀፅ የሆነው አንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ(1) “ዕቃ ማለት ማናቸውም ተንቀሳቃሽ ንብረት ሲሆን ግዙፍነት የሌላቸው በሕግ እንደተንቀሳቃሽ ንብረት የሚታወቁትን ንብረቶች፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን በአገልግሎት ላይ የዋሉ የተፈጥሮ ኃይልንና ሀብቶችን የሚያካትት ሲሆን ገንዘብን ይጨምራል” ይላል፡፡ በአዋጁ አንቀፅ 130(6) የተገለፀው ቅደመ ሁኔታ ከቀረጥ ነፃ በገቡ ማናቸውም ተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው ለሆቴል ግንባታ ፕሮጀክት የሚገቡ ዕቃዎችን ባንኮች በዋስትና የሚይዙ ከሆነ ተበዳሪው ዕቃዎቹን ለማስያዝ ከባለሥልጣኑ ፈቃድ ማቅረብ አለበት፡፡

በሰላም ቆዮኝ!!
ፌናን
ዉድ ተከታዮቻችን በዛሬው እለት ቀረጥ ሳይከፈልባቸው ወደ ሀገር ስለገቡ እቃዎች ክፍል ሁለት ይዘን ቀርበናል መልካም ንባብ፡፡

ባንኮች ከላይ የተጠቀሰውን ፈቃድ በተበዳሪው ሳይቀርብላቸው ቀረጥና ታክስ ያልተከፈለባቸው ዕቃዎቹን በመያዣ ይዘው ቢገኙ እና ደንበኛው ዕዳውን በውሉ መሰረት ባይከፍል ምን ይሆናል? ባለሥልጣኑ በቁጥር 5.0/269/02 ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ለቅርንጫፍ ፅ/ቤቶቹ በፃፈው እና በግልባጭ ለሁሉም ባንኮች ባሳወቀበት ደብዳቤ ቀረጥና ታክስ ያልተከፈለባቸው ዕቃዎች በዕዳ ሲያዙ ተበዳሪው አስቀድሞ ከባለሥልጣኑ ፈቃድ ማቅረብ ያለበት መሆኑን እንዲሁም ባንኮቹ ዕቃዎቹን በመያዣ መያዛቸውን ለባለሥልጣኑ መግለፅ ያለባቸው መሆኑን ይገልፃል፡፡ ነገር ግን ይህ ተሟልቶ ብድሩ ከተለቀቀ በኋላ ተበዳሪው በውሉ መሠረት ግዴታውን ካልተወጣ ባለሥልጣኑ ቀረጥና ታክሱን መያዣው በባንኩ ከተሸጠ በኋላ ሥመ ሀብቱ ለገዢ ሳይዘዋወር የሚከፈለው መሆኑን በደብዳቤው ተ.ቁ.3 ላይ ተገልጿል፡፡ ይህ ሁኔታ ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው በባንኮች ፋይናንስ ለተደረጉ ፕሮጀክቶች ግብዓትነት ወደ ሃገር ውስጥ ለሚገቡ ዕቃዎችም ጭምር ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ ባንኮችን ተበዳሪው ባለሥልጣኑ ዕቃዎቹ ለዋስትና እንዲያዙ ፈቃድ ሳያቀርብላቸው ዕቃዎቹ በመያዣ መያዛቸው አዋጁን የሚጥስ ተግባር በመሆኑ ባለሥልጣኑ መያዣው (ሆቴሉ) ሳይሸጥ ወይም ባንኩ የባለቤትነት ስሙን ወደራሱ ሳያዞር (Acqired by the bank) ከባንኩ ዕዳ ቀድሞ የግብዓቶቹን (ዕቃዎቹን) ቀረጥና ታክሱ እንዲከፈለው መጠየቅ ይችላል፡፡

ጥያቄውን ለመመለስ ከሚያስፈልጉን ሕጎች አንዱ የሆነውን የጉምሩክ ህግን የተመከለትን ቢሆንም አዋጁ የማይመልሳቸው ጥያቄዎች አሉ እነዚህን ጥያቄዎች ከፎርክሎዠር ሕግ (Foreclosure laws) እና የንብረት ሕግ ስለዕቃዎች (law of property on goods) ድንጋጌ አንፃር መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ የመጀመሪያው ባንኮች በአዋጅ ቁጥር 97/90 እና 98/90 መሠረት የማይንቀሳቀስ ወይም ተንቀሳቃሽ ንብረት፣ ንግድ መደብርን (Business) ወይም ዕቃን (Merchandise) በመያዣ ሊይዙ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ባንኮች ከቀረጥ ነፃ መብትን በመጠቀም ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ የግንባታ ግብዓቶችን (የሆቴል ቤት የግንባታ ዕቃዎችን) በመጠቀም የተገነባን ሆቴል (የማይንቀሳቀስ ንብረት) በመያዣ ለመያዝ ህንፃውን ከዕዳ ዕገዳ ነፃ መሆኑን ከማረጋገጥ ውጪ ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሃገር የገቡ ዕቃዎችን በመጠቀም ተገንብቷል አልተገነባም የሚለውን ማጣራት አለባቸው ወይስ የለባቸውም? ይህን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ከመመለሳችን በፊት ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሃገር ውስጥ የገቡት እቃዎች ግንባታ ላይ ከመዋላቸው በፊት እና ከዋሉ በኋላ ከንብረት ሕግ ስለዕቃዎች (law of property on goods) አንፃር እንዴት ይታያሉ የሚለውን መመለስ የቀደመውን ጥያቄ ለመመለስ ይረዳል፡፡

ሰላም ቆዩኝ
ፌናን
ዉድ ተከታዮቻችን በዛሬው እለት ቀረጥ ሳይከፈልባቸው ወደ ሀገር ስለገቡ እቃዎች የመጨረሻ ክፍል ይዘን ቀርበናል መልካም ንባብ፡፡

ለሆቴል ፕሮጀክት ግንባታ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ የግንባታ ዕቃዎች ስለንብረቶች አከፋፈል (classification of goods) በሚደነግገው የፍ/ሕጉ አንቀፅ 1126 መሠረት ከተንቀሳቃሽ ዕቃዎች ተርታ የሚመደቡ ናቸው፡፡ እነዚህ ዕቃዎች ለሆቴል በተሰራ ህንፃ ላይ መጥተው ግብዓት በሚሆኑበት ወቅት እንደየሁኔታው የሆቴሉ ሙሉ ክፍሎች (intrinsic element) ወይም ደባል ክፍሎች (Accessory) ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በልማድ የሆቴል አካል ተብለው የሚታሰቡ፣ ከሆቴሉ ህንፃ ጋር በግዙፍነት የተያያዙት እና ህንፃው ሳይጎዳ መነጠል የማይቻለውን የሆቴሉ ሙሉ ክፍሎች (intrinsic element) ሲባል በቋሚነት ለሆቴል አገልግሎት የተቀመጡ እና በግዙፍነት ያልተያያዙት ደባል ክፍሎች (Accessory) ይባላሉ (የፍ/ሕግ ቁጥር 1132 እና 1136ን ይመለከቷል)፡፡ ሙሉ ክፍሎች (intrinsic element) አንድ ከማይንቀሳቀስ ንብረት ጋር የተቀላቀሉ እንደሆነ እራሳቸው እንደቻሉ ንብሮቶች መቆጠራቸው ይቀራል (they cease to exist) እንዲሁም ሶስተኛ ወገኖች በእነዚህ ዕቃዎች ላይ ያሏቸው መብቶች ቀሪ ይሆናሉ የፍ/ሕግ ቁጥር 1134(1) እና (2)ን ይመለከቷል፡፡ የባለቤትነት መብት ጉዳይ አሻሚ በሚሆን ወቅት የዋናው ንብረት ወይም የሆቴሉ ህንፃ ላይ የተቋቋመ መብት ደባል ክፍሎች (Accessory goods)ን ይጨምራል (የፍ/ህግ አንቀፅ 1135)፡፡ ስለዚህም የሶስተኛ ወገኖች መብት የማይኖር ከሆነ (cease to exist) ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ የግንባታ ግብዓቶችን (የሆቴል ቤት የግንባታ ዕቃዎችን) በመጠቀም የተገነባን ሆቴል (የማይንቀሳቀስ ንብረት) በመያዣ ለመያዝ ህንፃውን ከዕዳ ዕገዳ ነፃ መሆኑን ከማረጋገጥ ውጪ ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ ዕቃዎችን በመጠቀም ተገንብቷል አልተገነባም የሚለውን ማጣራት አያስፈልግም፡፡ የሙሉ ክፍሎች (intrinsic element) ወይም ደባል ክፍሎች (Accessory) ላይ መብት የነበራቸው ሶስተኛ ወገኖችን መብታቸውን ስለጉዳት ኃላፊነት ወይም አላግባብ መበልፀግ የተደነገጉትን ድንጋጌዎች በመጠቀም መጠየቅ ይችላሉ(የፍ/ሕጉን አንቀፅ 1134(3) እና 1138 (1)ን ይመለከቷል)፡፡ ይህን የፎርክሎዠር ህግ (Foreclosure laws) እና ንብረት ሕግ ስለዕቃዎች (law of property on goods) ትንታኔ ስንከተል ባንኮች የሆቴል ህንፃን በመያዣ ከያዙ የሆቴሉ ሙሉ ክፍሎች (intrinsic element) የሆኑ ዕቃዎች ላይ ጭምር የመያዣ መብት ያቋቁማሉ፡፡ መያዣውን በመሸጥ ዕዳቸውን ማስመለስ ይችላሉ፡፡ ባለሥልጣኑ እንደ ሶስተኛ ወገን ዕዳ ጠያቂ በመቅረብ በጉምሩክ አዋጁ አሊያም በፍ/ሕጉ ከተበዳሪው ቀረጥና ታክሱን ሊጠይቅ ይችላል ወደሚል ድማዳሜ ላይ እንደርሳለን፡፡

ነገር ግን ለአንድ ጉዳይ ሁለት የሕግ ዘርፎች ወይም ድንጋጌዎች አተረጓጎም የተለያየ ውጤት የሚኖራቸው ከሆነ ከጠቅላላው ሕግ ልዩ ሕግ ተቀዳሚነት ሊኖረው የሚገባ ስለመሆኑ the special law prevails over the general የሚለው የሕግ አተረጓጎም መርህ (Rules of interpretation) ያስረዳል፡፡ በዚህ መርህ መሠረት ለጉዳዩ የጉምሩክ አዋጁ ላይ የተሰጠውን ትንታኔ መከተል ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጉምሩክ አዋጁ ለዕቃ የተሰጠው ትርጓሜ ሰፊ በመሆኑ የግንባታ ግባዓቶችንም ስለሚጨምር ከላይ ከጉምሩክ አዋጅ አንፃር በቀረበው ሃሳብ መሠረት አንድ ባንክ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ፈቃድ ሳያገኝ ከቀረጥ ነፃ በሆኑ ዕቃዎች የተገነባ ሆቴል ለዕዳ መያዣ ቢያደርግ ባለሥልጣኑ መያዣው (ሆቴሉ) ሳይሸጥ ወይም ባንኩ የባለቤትነት ስሙን ወደራሱ ሳያዞር (Acqired by the bank) ከባንኩ ዕዳ ቀድሞ የግብዓቶቹን ቀረጥና ታክሱ እንዲከፈለው መጠየቅ ይችላል፡፡ ስለሆነም ባንኮች ብድር በሚሰጡበት ወቅት ግንባታው ከቀረጥ ነፃ በገቡ ዕቃዎች ግብዓትነት የተሰራ መሆን አለመሆኑ የሚረጋገጥበት አሠራር በባንኮች ማህበር እና በባለሥልጣኑ መካከል በሚደረግ ውይይት ሊዘረጋ ይገባል፡፡

መልካም ጊዜን ተመኘን!!
ፌናን