የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
276 subscribers
366 photos
3 videos
137 files
97 links
ይህ የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት ቻናል ስለኢትዮጵያ ሕጎች)ማብራሪያ የሚሰጥበት፣ አዳዲስ ሕጎች የሚጋሩበት፣ ሕግ ነክ ዜናዎችና መረጃዎች የሚተላለፉበት፣ በዳይሬክቶሬቱ የተሰጡ የንቃተ-ሕግ ስልጠናዎች፣ የሕግ መልዕክቶች፣ በራሪ ጽሑፎች እና መሰል ሰነዶች የሚለቀቁበት ነው።
መልካም ቆይታ!
Download Telegram
ሰላም ጤና ይስጥልኝ እንደምን አደራችሁ ባለፈው ጽሁፍ የሙስና ወንጀሎች በተመለከተ ክስ ለመመስረት እና ክርክር ለማካሄድ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሥልጣንና ተግባር በሚዘረዝረው አንቀጽ 8 (2) ለ መሰረት ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተሰጠ መሆኑን አንብበን ያቆምን መሆናችን ይታወሳል፡፡ በዚህ ጽሁፍ ደግሞ መነሻ ወደሆነን የሙስና ወንጀሎች ከመግባታችን በፊት ስለ ሙስና ወንጀሎች ለማውራት መሰረት ስለሚሆነን አዋጅ ቁጥር 881/2007 መውጣት ምክንያት ብናነብ መልካም ነው፡፡
ለዚህ አዋጅ መውጣት በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ፡-
1. በ1996 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ የተደነገጉ የሙስና ወንጀሎች ውስጥ በአፈፃፀም ወቅት የተስተዋሉ ግልጽነት የሚጎላቸውን ድንጋጌዎች ግልጽ ማድረግና ማሻሻል በማስፈለጉ
2. የሙስና ወንጀሎቹ ማካተት የነበረባቸውን ተመሳሳይ ተግባራት በተለይም ከህዝብ የተሰባሰበ ወይም ለህዝብ ተብሎ የተሰባሰበ ሀብት በሚያስተዳድሩ የግል ዘርፍ አካላት የሚፈጸሙ ተመሳሳይ ተግባራትን በአግባቡ ያላካተቱ በመሆናቸው እነዚሁ ማካተት በማስፈለጉ
3. ሀገራችን ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው የተባበሩት መንግስታት የፀረ-ሙስና ኮንቬንሽን እና የአፍሪካ ህብረት የሙስና መከላከያና መዋጊያ ኮንቬንሽን በግል ዘርፍ ተቋማት ውስጥ የሚፈፀሙ የጉቦኝነት፣ የምዝበራ እና ተመሳሳይ ተግባራት በሙስና ወንጀልነት መፈረጅ እንዳለባቸው በፈራሚ አገሮች ላይ ግዴታ የሚጥል በመሆኑ ሕጉን ከዚህ አኳያ ማሻሻል በማስፈለጉ
4. በተግባር የታዮ ችገሮችን በመፍታት የተሟላ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ማድረግ የፀረ ሙስና ትግሉን ለማጠናከር እና ሀገራችን ያለባትን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ግዴታ በአግባቡ እንድትወጣ ለማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ
5. የሙስና ወንጀሎች በፈጣን ሁኔታ የመቀያየር ባህሪ ስላላቸው አጠቃላይ ወንጀሎችን በሚደነግገው የወንጀል ህግ ውስጥ እንዲካተቱ ከማድረግ ይልቅ ራሱን በቻለ አዋጅ እንዲደነገጉ ማድረግ ተመራጭ ሆኖ በመገኘቱ
የሚሉት ምክንያቶች ይገኙበታል፡፡ ሰላም ቆዮኝ!
አርብ 10/11/2012 ዓ.ም
ህድአት ጌታቸው
ሕ/ስ/ም/ዳ/ዐቃቤ ሕግ
ሰላም!ዛሬ ስለ አባይ ሕግ ላይ( አለም አቀፍ ስምምነት ላይ) ተመርኩዤ ትንሽ ላውጋችሁ።
11 ተፋሰስ ሀገራትን(ኢትዮጵያ፣ታንዛንያ፣ኡጋንዳ፣ኬንያ፣የመሀል ተፋሰስ ሀገራት፣ደቡብ ሱዳን፣ኤርትራ፣ሩዋንዳ፣ብሩንዲ፣ሱዳን እና ግብጽ) የሚያቋርጥ የአለማችን ረዥሙ ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ሲሆን ነጭ ናይል፣ሰማያዊ ናይል እና አትባራ የሚባሉ ገባር ወንዞች ሲኖሩት ከገባሮቹ ውስጥ እጅግ ብዙውን ፐርሰንት የሚሸፍነው ከኢትዮጵያ በመነሳት ከሚገብሩት ወንዞች ነው።ሆኖም አጠቃቀም ላይ ግን የኢትዮጵያ መብት ችላ የተባለ ይመስላል።ይሄ የሆነበት ምክንያት አባይን በማስመልከት የተደረጉ አብዛኞቹ ስምምነቶች የኢትዮጵያን መብት ከግንዛቤ ያልወሰዱ በመሆናቸው ነው።እነዚህ ስምምነቶችን ለመጥቀስ ያህል የ 1891 የጣልያንና የእንግሊዝ ስምምነት፣የ1901 የእንግሊዝና የጣልያን ስምምነት፣የ1902 የእንግሊዝና የኢትዮጵያ ስምምነት፣የ1906 የቤልጂየም እና የእንግሊዝ ስምምነት፣የ1906 የእንግሊዝ፣የጣልያን እና የፈረንሳይ ስምምነት፣የ1925 የእንግሊዝና የግብጽ ስምምነት፣የ1929 የእንግሊዝና የግብጽ ስምምነት፣የ1952 የእንግሊዝና የግብጽ ስምምነት፣የ1959 የግብጽና የሱዳን ስምምነት ናቸው።እነዚህ ስምምነቶች የናይልን ጥቅም ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ለግብጽ ለማዋል የሚጥሩ ናቸው።እነዚህ ስምምነቶች ግን በአለም አቀፍ ስምምነት ደረጃ ተቀባይነት የማይኖራቸው ዋነኛው ምክንያት ብዙ አለም አቀፍ ስምምነቶችን የሚቃረኑ በመሆናቸው ነው።
ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ የተደነገጉ አለም አቀፍ ስምምነቶች ፍትሀዊና ምክንያታዊ የመጠቀምን መብት እንዲሁም ደግሞ ሌሎች ላይ ጉልህ ጉዳት ያለማድረስን ግዴታ ይደነግጋሉ።ይሄንን ከ ለመጓጓዣነት የማያገለግሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ለማስተዳደር ከወጣው አለም አቀፍ ስምምነት አንቀጽ 5 እና 7 መረዳት ይቻላል።
የቬና ቃልኪዳን የስምምነት ሕግ አንቀጽ 11 እና 34ን በምንመለከትበት ጊዜ ደግሞ በሀገራት መካከል የሚከናወን ማንኛውም አይነት ስምምነት በስምምነቱ ላይ አቋሟን ባልገለጸች ሀገር ላይ ስምምነቱ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው በግልጽ ተቀምጧል።እነዚህ እና ሌሎች አለም አቀፍ ስምምነቶችን በምናገላብጥ ጊዜ ኢትዮጵያ የናይልን ጥቅም የማትቋደስበት ምንም ሕጋዊ ምክንያት እንደሌለ እንረዳለን።

ሰናይ 10/11/2012 ዓ.ም!(ኦምኒኤል)
ሰላም ውድ ተከታታዮቻችን እንዴት ሰነበታችሁ ከዛሬ ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት የማቀርበው ቀረጥ ሳይከፈልባቸው ወደ ሀገር ገብተው በባንክ በመያዣ ለተያዘ ህንፃ ግብዓትነት ስለሚውሉ ዕቃዎች የቀዳሚነት መብት ላይ የተዘጋጀ ጽሑፍን ይሆናል፡፡ መልካም ንባብ

ከግብር እና ቀረጥ ነፃ መብትን በመጠቀም ግብር እና ቀረጥ ሳይከፈልባቸው ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ ግብዓቶችን በመጠቀም የተገነባን ለምሳሌ ሆቴልን አንድ አበዳሪ ባንክ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ፈቃድ ሳያገኝ የሆቴሉን ህንፃ ለዕዳ መያዣ ቢያደርግ ባለሥልጣኑ መያዣው(ሆቴሉ) ሳይሸጥ ወይም ባንኩ የባለቤትነት ስሙን ወደ ራሱ ሳያዞር (before it is acquired by the bank) ከባንኩ ዕዳ ቀድሞ የግብዓቶቹ ቀረጥና ታክስ እንዲከፈለው መጠየቅ ይችላል ወይም አይችልም?

ጥያቄውን ለመመለስ ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን የጉምሩክ ሕጎች (law of customs)፣ የፎርክሎዠር ሕግ (Foreclosure laws)፣ የንብረት ሕግ ስለዕቃዎች (law of property on goods) እና ሌሎችንም መፈተሽ ያለባቸውን ሕግጋቶች ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው ሕጎች አንዱ የሆነውን የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006ን ስንመለከት የአዋጁ አንቀፅ 130(6) “ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልበት ወደ አገር የገባን ዕቃ በዋስትና ማስያዝ የሚቻለው ከባለሥልጣኑ ጋር በቀረጥና ታክስ አከፋፈል ረገድ ላይ ስምምነት ሲደረስ ይሆናል” ሲል ይደነግጋል ይህ ማለት የዕቃው ባለቤት ቀረጥና ታክሱን የሚከፍል መሆኑንና ስለአከፋፈሉ ሁኔታ ከባለሥልጣኑ ጋር ስምምነት ላይ ሳይደርስ ዕቃው ለዕዳ መክፈያነት በመያዣ መስጠት አይችልም ማለት ነው፡፡ እዚህ ጋር አብሮ መነሳት ያለበት ጉዳዩ “ዕቃ” ማለት ምን ማለት ወይም አዋጁ ይህን ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠው ለየትኞቹ ዕቃዎች ነው የሚለው ነው፡፡ የአዋጁ የትርጓሜ አንቀፅ የሆነው አንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ(1) “ዕቃ ማለት ማናቸውም ተንቀሳቃሽ ንብረት ሲሆን ግዙፍነት የሌላቸው በሕግ እንደተንቀሳቃሽ ንብረት የሚታወቁትን ንብረቶች፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን በአገልግሎት ላይ የዋሉ የተፈጥሮ ኃይልንና ሀብቶችን የሚያካትት ሲሆን ገንዘብን ይጨምራል” ይላል፡፡ በአዋጁ አንቀፅ 130(6) የተገለፀው ቅደመ ሁኔታ ከቀረጥ ነፃ በገቡ ማናቸውም ተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው ለሆቴል ግንባታ ፕሮጀክት የሚገቡ ዕቃዎችን ባንኮች በዋስትና የሚይዙ ከሆነ ተበዳሪው ዕቃዎቹን ለማስያዝ ከባለሥልጣኑ ፈቃድ ማቅረብ አለበት፡፡

በሰላም ቆዮኝ!!
ፌናን
ዉድ ተከታዮቻችን በዛሬው እለት ቀረጥ ሳይከፈልባቸው ወደ ሀገር ስለገቡ እቃዎች ክፍል ሁለት ይዘን ቀርበናል መልካም ንባብ፡፡

ባንኮች ከላይ የተጠቀሰውን ፈቃድ በተበዳሪው ሳይቀርብላቸው ቀረጥና ታክስ ያልተከፈለባቸው ዕቃዎቹን በመያዣ ይዘው ቢገኙ እና ደንበኛው ዕዳውን በውሉ መሰረት ባይከፍል ምን ይሆናል? ባለሥልጣኑ በቁጥር 5.0/269/02 ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ለቅርንጫፍ ፅ/ቤቶቹ በፃፈው እና በግልባጭ ለሁሉም ባንኮች ባሳወቀበት ደብዳቤ ቀረጥና ታክስ ያልተከፈለባቸው ዕቃዎች በዕዳ ሲያዙ ተበዳሪው አስቀድሞ ከባለሥልጣኑ ፈቃድ ማቅረብ ያለበት መሆኑን እንዲሁም ባንኮቹ ዕቃዎቹን በመያዣ መያዛቸውን ለባለሥልጣኑ መግለፅ ያለባቸው መሆኑን ይገልፃል፡፡ ነገር ግን ይህ ተሟልቶ ብድሩ ከተለቀቀ በኋላ ተበዳሪው በውሉ መሠረት ግዴታውን ካልተወጣ ባለሥልጣኑ ቀረጥና ታክሱን መያዣው በባንኩ ከተሸጠ በኋላ ሥመ ሀብቱ ለገዢ ሳይዘዋወር የሚከፈለው መሆኑን በደብዳቤው ተ.ቁ.3 ላይ ተገልጿል፡፡ ይህ ሁኔታ ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው በባንኮች ፋይናንስ ለተደረጉ ፕሮጀክቶች ግብዓትነት ወደ ሃገር ውስጥ ለሚገቡ ዕቃዎችም ጭምር ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ ባንኮችን ተበዳሪው ባለሥልጣኑ ዕቃዎቹ ለዋስትና እንዲያዙ ፈቃድ ሳያቀርብላቸው ዕቃዎቹ በመያዣ መያዛቸው አዋጁን የሚጥስ ተግባር በመሆኑ ባለሥልጣኑ መያዣው (ሆቴሉ) ሳይሸጥ ወይም ባንኩ የባለቤትነት ስሙን ወደራሱ ሳያዞር (Acqired by the bank) ከባንኩ ዕዳ ቀድሞ የግብዓቶቹን (ዕቃዎቹን) ቀረጥና ታክሱ እንዲከፈለው መጠየቅ ይችላል፡፡

ጥያቄውን ለመመለስ ከሚያስፈልጉን ሕጎች አንዱ የሆነውን የጉምሩክ ህግን የተመከለትን ቢሆንም አዋጁ የማይመልሳቸው ጥያቄዎች አሉ እነዚህን ጥያቄዎች ከፎርክሎዠር ሕግ (Foreclosure laws) እና የንብረት ሕግ ስለዕቃዎች (law of property on goods) ድንጋጌ አንፃር መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ የመጀመሪያው ባንኮች በአዋጅ ቁጥር 97/90 እና 98/90 መሠረት የማይንቀሳቀስ ወይም ተንቀሳቃሽ ንብረት፣ ንግድ መደብርን (Business) ወይም ዕቃን (Merchandise) በመያዣ ሊይዙ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ባንኮች ከቀረጥ ነፃ መብትን በመጠቀም ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ የግንባታ ግብዓቶችን (የሆቴል ቤት የግንባታ ዕቃዎችን) በመጠቀም የተገነባን ሆቴል (የማይንቀሳቀስ ንብረት) በመያዣ ለመያዝ ህንፃውን ከዕዳ ዕገዳ ነፃ መሆኑን ከማረጋገጥ ውጪ ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሃገር የገቡ ዕቃዎችን በመጠቀም ተገንብቷል አልተገነባም የሚለውን ማጣራት አለባቸው ወይስ የለባቸውም? ይህን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ከመመለሳችን በፊት ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሃገር ውስጥ የገቡት እቃዎች ግንባታ ላይ ከመዋላቸው በፊት እና ከዋሉ በኋላ ከንብረት ሕግ ስለዕቃዎች (law of property on goods) አንፃር እንዴት ይታያሉ የሚለውን መመለስ የቀደመውን ጥያቄ ለመመለስ ይረዳል፡፡

ሰላም ቆዩኝ
ፌናን
ዉድ ተከታዮቻችን በዛሬው እለት ቀረጥ ሳይከፈልባቸው ወደ ሀገር ስለገቡ እቃዎች የመጨረሻ ክፍል ይዘን ቀርበናል መልካም ንባብ፡፡

ለሆቴል ፕሮጀክት ግንባታ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ የግንባታ ዕቃዎች ስለንብረቶች አከፋፈል (classification of goods) በሚደነግገው የፍ/ሕጉ አንቀፅ 1126 መሠረት ከተንቀሳቃሽ ዕቃዎች ተርታ የሚመደቡ ናቸው፡፡ እነዚህ ዕቃዎች ለሆቴል በተሰራ ህንፃ ላይ መጥተው ግብዓት በሚሆኑበት ወቅት እንደየሁኔታው የሆቴሉ ሙሉ ክፍሎች (intrinsic element) ወይም ደባል ክፍሎች (Accessory) ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በልማድ የሆቴል አካል ተብለው የሚታሰቡ፣ ከሆቴሉ ህንፃ ጋር በግዙፍነት የተያያዙት እና ህንፃው ሳይጎዳ መነጠል የማይቻለውን የሆቴሉ ሙሉ ክፍሎች (intrinsic element) ሲባል በቋሚነት ለሆቴል አገልግሎት የተቀመጡ እና በግዙፍነት ያልተያያዙት ደባል ክፍሎች (Accessory) ይባላሉ (የፍ/ሕግ ቁጥር 1132 እና 1136ን ይመለከቷል)፡፡ ሙሉ ክፍሎች (intrinsic element) አንድ ከማይንቀሳቀስ ንብረት ጋር የተቀላቀሉ እንደሆነ እራሳቸው እንደቻሉ ንብሮቶች መቆጠራቸው ይቀራል (they cease to exist) እንዲሁም ሶስተኛ ወገኖች በእነዚህ ዕቃዎች ላይ ያሏቸው መብቶች ቀሪ ይሆናሉ የፍ/ሕግ ቁጥር 1134(1) እና (2)ን ይመለከቷል፡፡ የባለቤትነት መብት ጉዳይ አሻሚ በሚሆን ወቅት የዋናው ንብረት ወይም የሆቴሉ ህንፃ ላይ የተቋቋመ መብት ደባል ክፍሎች (Accessory goods)ን ይጨምራል (የፍ/ህግ አንቀፅ 1135)፡፡ ስለዚህም የሶስተኛ ወገኖች መብት የማይኖር ከሆነ (cease to exist) ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ የግንባታ ግብዓቶችን (የሆቴል ቤት የግንባታ ዕቃዎችን) በመጠቀም የተገነባን ሆቴል (የማይንቀሳቀስ ንብረት) በመያዣ ለመያዝ ህንፃውን ከዕዳ ዕገዳ ነፃ መሆኑን ከማረጋገጥ ውጪ ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ ዕቃዎችን በመጠቀም ተገንብቷል አልተገነባም የሚለውን ማጣራት አያስፈልግም፡፡ የሙሉ ክፍሎች (intrinsic element) ወይም ደባል ክፍሎች (Accessory) ላይ መብት የነበራቸው ሶስተኛ ወገኖችን መብታቸውን ስለጉዳት ኃላፊነት ወይም አላግባብ መበልፀግ የተደነገጉትን ድንጋጌዎች በመጠቀም መጠየቅ ይችላሉ(የፍ/ሕጉን አንቀፅ 1134(3) እና 1138 (1)ን ይመለከቷል)፡፡ ይህን የፎርክሎዠር ህግ (Foreclosure laws) እና ንብረት ሕግ ስለዕቃዎች (law of property on goods) ትንታኔ ስንከተል ባንኮች የሆቴል ህንፃን በመያዣ ከያዙ የሆቴሉ ሙሉ ክፍሎች (intrinsic element) የሆኑ ዕቃዎች ላይ ጭምር የመያዣ መብት ያቋቁማሉ፡፡ መያዣውን በመሸጥ ዕዳቸውን ማስመለስ ይችላሉ፡፡ ባለሥልጣኑ እንደ ሶስተኛ ወገን ዕዳ ጠያቂ በመቅረብ በጉምሩክ አዋጁ አሊያም በፍ/ሕጉ ከተበዳሪው ቀረጥና ታክሱን ሊጠይቅ ይችላል ወደሚል ድማዳሜ ላይ እንደርሳለን፡፡

ነገር ግን ለአንድ ጉዳይ ሁለት የሕግ ዘርፎች ወይም ድንጋጌዎች አተረጓጎም የተለያየ ውጤት የሚኖራቸው ከሆነ ከጠቅላላው ሕግ ልዩ ሕግ ተቀዳሚነት ሊኖረው የሚገባ ስለመሆኑ the special law prevails over the general የሚለው የሕግ አተረጓጎም መርህ (Rules of interpretation) ያስረዳል፡፡ በዚህ መርህ መሠረት ለጉዳዩ የጉምሩክ አዋጁ ላይ የተሰጠውን ትንታኔ መከተል ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጉምሩክ አዋጁ ለዕቃ የተሰጠው ትርጓሜ ሰፊ በመሆኑ የግንባታ ግባዓቶችንም ስለሚጨምር ከላይ ከጉምሩክ አዋጅ አንፃር በቀረበው ሃሳብ መሠረት አንድ ባንክ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ፈቃድ ሳያገኝ ከቀረጥ ነፃ በሆኑ ዕቃዎች የተገነባ ሆቴል ለዕዳ መያዣ ቢያደርግ ባለሥልጣኑ መያዣው (ሆቴሉ) ሳይሸጥ ወይም ባንኩ የባለቤትነት ስሙን ወደራሱ ሳያዞር (Acqired by the bank) ከባንኩ ዕዳ ቀድሞ የግብዓቶቹን ቀረጥና ታክሱ እንዲከፈለው መጠየቅ ይችላል፡፡ ስለሆነም ባንኮች ብድር በሚሰጡበት ወቅት ግንባታው ከቀረጥ ነፃ በገቡ ዕቃዎች ግብዓትነት የተሰራ መሆን አለመሆኑ የሚረጋገጥበት አሠራር በባንኮች ማህበር እና በባለሥልጣኑ መካከል በሚደረግ ውይይት ሊዘረጋ ይገባል፡፡

መልካም ጊዜን ተመኘን!!
ፌናን
ሰላም! ከላይ በአባይ ዙሪያ የተለያዩ ስምምነቶች ምን እንደሚሉ በብሮሸር መልክ ያካፈልኳችሁን መረጃ ፕሪንት አድርጌ በፎቶ መልክ ከታች አስቀምጬላችኋለው።
ሰናይ 23/11/2012 ዓ.ም!
ሰላም ውድ ተከታታዮቻችን እንዴት ሰነበታችሁ ከዛሬ ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት የማቀርበው የኢሚግሬሽን ህግ በኢትዮጵያ ላይ በሚል የተዘጋጀ ጽሑፍን ይሆናል፡፡ መልካም ንባብ

ሰው በነጻነት ይኖር ዘንድ የተፈጠረ ማህበራዊ እንስሳ ነው፡፡ ከነጻነቶቹ መገለጫዎች አንዱ ደግሞ የመንቀሳቀስ ነጻነት ነው፡፡ እንቅስቃሴዎት ከማንኛውም ሰው ጣልቃ ገብነት የተጠበቀ ነው፡፡ መንግስት የሰዎችን ድንበር ዘለል እንቅስቃሴ በህግና ስርዓት እንዲመራ በማድረግ ህገ-ወጥ የሰዎችን ዝውውርና ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርን መከላከል እና በዚሁ ህገ-ወጥ ጉዞ ምክንያት ሊደርስባቸው ይችል የነበረን አደጋ ማስቀረት አለበት፡፡ በዚህም ምክንያት የሰዎችን ጉዞ ጤናማነት ለማረረጋገጥ ወይም የነኚህን ሰዎች ደህንነት ለማረጋገጥ ሲባል ተጓዥዎች ሊያሟሉት የሚገባ ቅደመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ቅደመ ሁኔታዎቹ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ለሚፈልጉ የውጭ ዜጎችም በተመሳሳይ አስፈላጊ ነው፡፡ የነዚህ ሰዎች መግባት ከብሄራዊ ደህንነትም ጋር ተያይዞ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ እኚህን ቅድመ ሁኔታዎችና የኢትዮጵያን ኢሚግሬሽን ህግ ይዘት ዋና ዋና ጉዳዮች በዚህ ጽሁፍ ለመመልከት ወደናል፡፡

የአለምአቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይ ኦ ኤም) የትርጉም ሰነድ ኢሚግሬሽን የሚለውን ሀረግ ``A process by which non-nationals move into a country for the purpose of settlement`` በሚል ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ ወደ አማርኛ ስናመጣዉ ዜጋ ያልሆኑ ሰዎች ኑሮዋቸውን ለመመስረት ወደ ሌላ ሀገር የሚጓዙበት ሂደት ነው፡፡ ከዚህ ትርጉም የምንገነዘበው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሀገሩን ለቆ ወደ ሌላ ሀገር እንዲሁም የሌላ ሀገር ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ወይም ወደ ሌሎች ማናቸውም ሀገራት የሚያደርጓቸው ጉዞዎች ኢሚግሬሽን ሊባል እንደሚችል ነው፡፡ በመሆኑም የሁለት ሀገርን ድንበር አቋርጦ የሚሄድ ማንኛውም ሰውም ስደተኛ (Immigrant) እንለዋለን፡፡

የኢሚግሬሽን ህግ አላማን ስንመለከት የሰዎችን ከሀገር መውጣትና መግባት ለመቆጣጠር ብሎም ስርዓትን በማስጠበቅ ከብሄራዊ ደህንነት ጋር ተያይዞ ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችል የኢሚግሬሽን ህግ ሊኖር የተገባ ነው፡፡ በዋናነት ህገ-ወጥ የሰዎችን ዝውውርን ከመከላከል አንጻርም ሰዎች ከሀገር የሚወጡበትና የሚገቡበት ሁኔታ በህግ ስርዓት ሊሸፈን የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ሀገራት የኢሚግሬሽን ህግ ሳይኖራቸው የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር ወይም ከዘፈቀደ የሰዎች እንቅስቃሴ መከልከል አይችሉም፡፡ ይህ ደግሞ ማንኛውም የውጭ ዜጋ በፈቀደው ጊዜ እና ሁኔታ ወደ ሀገር እንዲገባ በተመሳሳይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወደ ሌላ ሀገር ለመግባት እንዲችል ያስችለዋል፡፡

መልካም ቆይታ
ፌናን
ዉድ ተከታዮቻችን በዛሬው እለት የኢሚግሬሽን ሕግ በኢትዮጵያ ክፍል ሁለት ይዘን ቀርበናል መልካም ንባብ፡፡

ስለ ሰዎች ከሀገር መውጣት እና መግባት በተመለከተ

በአገራችን በስራ ላይ ያሉ ህጎችን ስንመለከት የኢሚግሬሽን አዋጅ ቁጥር 354/1995 እና ይህንኑ አዋጅ ለማፍታታት የወጣው የኢሚግሬሽን ደንብ ቁጥር 114/1997 ናቸው፡፡ ከዚህ በዘለለ የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2009 የውጭ ሀገር ስራ ስምሪትን ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ሲሆን የሰዎች አወጣጥን በተመለከተ ግን ከላይ በተጠቀሰው የኢሚግሬሽን አዋጅ መሰረት ይሆናል፡፡ በነዚህ ተፈጻሚነት ባላቸው ህጎች (የኢሚግሬሽን ህጎች) ላይ የተመለከቱትን ዋና ዋና ፍሬ ጉዳዮች እንመልከት፤

ወደ ኢትዮጵያ ስለ መግባት

የኢሚግሬሽን አዋጅ ቁጥር 354/1995 አንቀጽ 3 ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ሊያሟሉ የሚገቧቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡ ከነኚህ ቅድመሁኔታዎች የመጀመርያው የጉዞ ሰነድ ነው፡፡ የጉዞ ሰነድ ሰዎች ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር ጉዞ ለማድረግ ወይም ለመጓጓዝ ፈቃድ ያላቸው መሆኑን የሚገልጽ ከኢሚግሬሽን መምርያ ለተጓዥ የሚሰጥ ሰነድ ነው፡፡ በመሆኑም በሌላ በህግ በተቀመጠ ልዩ ሁኔታ የማይጠየቁ ሰዎች ካልሆኑ በስተቀር ይህንን ሰነድ ሳይዙ መግባት አይቻልም፡፡

ቪዛ ስለመከልከል/ ስለመሰረዝ

ማንኛውም ሰው ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ሲል የሚያቀርበው የቪዛ ጥያቄ ሁሉ ቪዛውን በመስጠት ላይጠናቀቅ ይችላል፡፡ የኢሚግሬሽን ህጉ ቪዛ የሚከለከልበትን እንዲሁም ከተሰጠም በኋላ የሚሰረዝበትን ምክንያቶች በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ በዚህም መሰረት የመጀመርያው ራስን ከመቻል ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል የቪዛ ይሰጠኝ ጠያቂው ከአደገኛ ወንጀል አድራጊነት መጠበቅ ወይም ከዚሁ ችግር የጸዳ መሆን አለበት፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ቪዛን የሚያስከለክል ወይም የሚያሰርዝ ምክንያት የአመልካቹ በአደገኛ ዕጽ ሱስ ተገዢ መሆን ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ስለመውጣትና ዕግድ

ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት መሟላት ስላለባቸው ጉዳዮች የኢሚግሬሽን ህጉ ያስቀመጣቸው ጉዳዮች ሁሉ ከኢትዮጵያ ወደ ሌላ ሀገር ለሚወጣ ሰውም ተፈጻሚነት አላቸው፡፡ ይሁንና ሰዎች ከኢትዮጵያ እንዳይወጡ ሊታገዱ የሚችሉት ፍርድ ቤቶች በህገ መንግስቱ በተሰጣቸው የዳኝነት ስልጣን መሰረት ህግን መሰረት አድርገው የዕገዳ ውሳኔ ሲሰጡ ብቻ ነው፡፡

በሁለት ተከታታይ ክፍል ያቀረብኩላችሁ ይህን ይመስላል በቀጣይ በሌላ ጽሑፍ እስከምንገናኝ መልካም ቆይታን ተመኘው፡፡

ፌናን
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 523፡-
ችግር ወይም ረሀብ እንዲደርስ ማድረግ

1. ማንም ሰው አስቦ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ በተለይም በመደበቅ፣ ያለአግባብ በማከማቸት፣ በማጥፋት ወይም ለሰው ወይም ለቤት እንስሳት ሕይወት ወይም ጤና አስፈላጊ የሆኑትን የእህልን፣ የምግብን፣ የቀለብን፣ የመድሃኒትን፣ ወይም አስፈላጊ የሆኑትን ሌሎች ነገሮች ማመላለስን ወይም ማከፋፈልን በመከልከል በአገር ውስጥ ከባድ መከራ፣ እጦት፣ ረሀብ፣ ተላላፊ በሽታ፣ የእንስሳት በሽታ ወይም ችግር እንዲደርስ ያደረገ እንደሆነ፤
ከአሥራ አምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት ይቀጣል፡፡
ጤና ይስጥልኝ፡-

ኢትዮጵያ ሀገራችን የረጅም ዓመታት ሕግ የማውጣት ልምድ ያላት ቢሆንም ይህንን ልምድና የሕግ አወጣጥ ሥርዓትን ባልተከተለ ሁኔታ እየወጡ የሚገኙ ድንጋጌዎችን በመመልከቴ በዚህ ጉዳይ ላይ ወዳጅ ወገኖቼ የየበኩላችንን እንድትሉ እንድንል ለማለት ሲሆን፤ በዚህ ረገድ በቀዳሚነት የሚነሳውና አሁን ባለውና እየተሰራበት በሚገኘው በአዋጅ ቁጥር 3/1987 ላይ ከተጠቀሰው የነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ ተደንግጎ ከወጣበትና በዚሁ መሠረትነት ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ወደ ስድስት ጊዜ እየተሻሻለ የሚገኘውን የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የሚወጣውን ድንጋጌንና በየአዋጁ የሚቋቋሙ ተቋማትን (መስሪያ ቤቶች) እና እነዚህኑ መስሪያ ቤቶችን በምን ስያሜ (ባለስልጣን፣ ኮሚሽን፣ ጽ/ቤት፣……) መጥራት እንዳለብንም ይሁን ይህው ስያሜያቸው ግብራቸውን (ሥራቸውን) ስለመግለፁ እና ስለዚህ ጉዳይም ልንከተል የሚገባውን በመርህ ደረጃም እንኳን አመላካች በሌለበት እንዲሁ የሚሰጥበት የሚያስመስል ሁኔታን በመፍጠሩ በዚህም ጉዳይ ላይ የየበኩላችንን ብንል በማለት ነው፡፡

ማንኛውም መንግሥት እንደሚያደርገው ሁሉ ኢትዮጵያም የራሷን መሥሪያ ቤቶችን (ተቋማት) ማቋቋሟ ግድ ቢላትም እዚህ ጋር ግን የሚቋቋመው መ/ቤት በምን ደረጃና ስያሜ ይሁን የሚለውን ለሥራው ከሚበጀውና ከሚፈልገው ውጤት አኳያ መታየት ያለበትና መ/ቤቱን በሚኒስቴር ወይም ከዚህ በታች ባለ ደረጃ ስያሜ ይሰጠው የሚለውን ሀገሪቱ ከያዘችው የረጅም ጊዜ ዕቅዶች፣ ከብሔራዊ ፖሊሲ፣ መርህ እና ዓላማ እና እንዲሁም ካለው ጉዳይ ሁሉ ትኩረት ተሰጥቶት ሊተገበር ይገባል የሚባል ጉዳይን በመለየት ስያሜ እና ማዕረጋቸውንም ከዚህ አንጻር ቢሰጥ እንደዚሁም ለየመ/ቤቱ የሚሰጠው ስያሜም ይሁን መ/ቤቱን በበላይነት የሚመራውን ግለሰብን የምንጠራበት ስያሜ ኢትዮጵያዊ ቢሆን ማለት “ዳይሬክተር” ይሻላል ወይስ “ሥራ አስኪያጅ”? ወይም “ኃላፊ”? አሁንማ ይህው አጠራር ከውጪ ዜጎች ጋር (ምናልባት ከዚሁ አንጻር መጥቶ ከሆነ) የማያገናኘው የየበታች የሥራ ኃላፊ ሁላ “ዳይሬክቶሬት” ይባልልኛላ፤ አረ በሕግ አማላክ!!! ለኢትዮጵያዊ ተቋም ኢትዮጵያዊ ስም (ስያሜ) መስጠቱ ቢታሰብበት፡፡

ሌላው ከዚህ በላይ በምሳሌነት ስለተጠቀሰው የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ስንመለከት ይህ አዋጅ በ1987 ዓ.ም ከወጡት ውስን አዋጆች አንዱና በቁጥር 4/1987 የተመዘገበው ሲሆን ይህ አዋጅ በውስጡ 15 (አስራ አምስት) የሚኒስቴር መ/ቤቶች መቋቋማቸውን በመግለጽ የተደነገገና በ1994 ዓ.ም በወጣው አዋጅ ቁጥር 256/1994 አዋጅ ላይ የሚኒስቴር መ/ቤቶቹን የአቅም ግንባታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ 18 በማድረግ ቢሻሻልም ለአስራ አንድ ዓመታት ተሰርቶበት አዋጅ ቁጥር 4/1987 እና ማሻሻያው አዋጅ ቁጥር 256/1994 በአዋጅ ቁጥር 471/1998 ዓ.ም ተሽሯል፤ በዚህ በአዋጅ ቁጥር 471/1998 ላይም የሚኒስቴር መ/ቤቶችን ቀደም ባለው አዋጅ ላይ በጽ/ቤት ስያሜ የተጠራውን የአቅም ግንባታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤትን በሚኒስቴር መ/ቤትነት በመሰየም የሚኒስቴር መ/ቤቶቹን ቁጥር 20 (ሃያ) በማድረግ እና በተለምዶ ከነበረው በሚኒስትርነት በም/ሚኒስትርነት ሲመራ የነበረውን ተቋም ሚኒስትር ዴኤታ እንደሚኖር ከመደንገጉ ውጪ ይኸው ሚኒስትር ዴኤታ ለምን እንዳስፈለገ፣ ከቀድሞ በተለየ ምንንና እንዴት እንዲያከናውን ተፈልጎ እንደሆነ ባልተገለጸበት ወይም በሁኔታ እንዲገመት በሚያስችል መንገድ ሳይገለጽ በኃላፊነት ማዕረግ ውስጥ የተካተተበት እንደዚሁም ከዚሁ አዋጅ ጋር አባሪ በተደረገ ሰንጠረዥ ሌሎች የአስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎቻቸው ላይ የስያሜ ማሻሻያ የተደረገበትን በማካተት ለሦስት ዓመታት እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ ሥራ ላይ ውሏል፡፡

ይቀጥላል
ደረጀ ማርቆስ
የቀጠለ፡-

ከዚህ በኃላ የወጣው አዋጅ ቁጥር 691/2003 ሲሆን በዚህ አዋጅ ላይ የሚኒስቴር መ/ቤቶቹ ቁጥር ከቀድሞው ሕግ ጋር በተመሳሳይ መልኩ ሃያ (20) ቢሆንም ከዚህ በላይ አንዴ በጽ/ቤት አንዴ በሚኒስቴር መ/ቤትነት ሲጠራ የነበረው የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር መ/ቤት ከሃያዎቹ ውስጥ ያልተካተተና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መ/ቤት በአዲስ መልክ መዋቀሩን ሌሎቹ የተቀሩትም አንዳንድ መጠሪያ ስማቸውን ከሌላው ጋር በማዳበል ወይም ከስማቸው ላይ በማውጣት (በመቀነስ) የተቋቋሙ መሆናቸውን በመግለጽ ለአምስት ዓመታት ሲሰራባቸው ቆይተው በ2008 ዓ.ም ተሽረዋል፡፡

አዋጅ ቁጥር 916/2008 የሚኒስቴር መ/ቤትን ቁጥር ሃያ አምስት (25) በማድረግ ሲቋቋም ከምን አንጻር ታይቶ እንደሆነ በማይታወቅበት የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር መ/ቤትን የፌደራል እና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር እንደተካው ቢገለጽም ይህው የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በስሩ ከሚያስተዳድራቸው ተቋማት የከተማ አስተዳደር እንዳሉ የተገለጸውንና የእነዚሁ ተቋማትን በበላይነት ስለከተማ ልማት የተቋቋመው እንደሚመለከተው በተዘወዋዋሪ ከመግለጽ ባለፈ የፌ/ጉ/ሚ/ር ፌደራል የምትለዋን ቃል በመተው ሀልዎቱን ያጣ ሲሆን ሌሎቹ ሚ/ቴር መ/ቤቶችም ለምሳሌ የግብርና ሚ/ቴር መ/ቤትን ዓሳ፣ እርሻ፣ የተፈጥሮ ሀብት፣….. በማለት ቃላቶቹን በመውሰድ ሚ/ቴር መ/ቤቶቹን ያበዛ መሆኑንና የሌሎቹንም ተቋማት በዚሁ ሁኔታ የተቀመጡና ይህው አዋጅም ከሁለት ዓመታት በኃላ ስለዓሳ፣… የጠቃቀሳቸውን በመሻር የሚ/ቴር መ/ቤቱን መጠሪያ የግብርና እና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር ተብሎ ተጠቃሎ የተጠራ መሆኑን በመግለጽ በአዋጅ ቁጥር 1084/2010 በማሻሻያ ታውጆለት እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ ሲሰራበት ቆይቷል፡፡

ይህ ጽሁፍ በተዘጋጀበት ጊዜ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ቁጥር 1097/2011 ሲሆን በዚህ አዋጅ ላይ በኢትዮጵያ ታሪክ ፈጽሞ ባልተለመደና ምናልባትም በሀገራችን ከነበረው ነባራዊ ሁኔታ የሐይማኖት ተቋማትም ሆነ የሀገር ሽማግሌዎች ነገሮችን የማመላለስና የማለዘብ ሁኔታ ላይ በመቀዛቀዛቸው የእነርሱን ሚና ለመጫወት በሚመስል መልኩ የሰላም ሚኒስቴር መ/ቤትን ጨምሮ አሥራ ዘጠኝ (19) የተቋቋሙና የተለያዩ በአንድ ሊገቡ የሚችሉ መ/ቤቶችንም በተቻለ መጠን በአንድ ላይ በማድረግ ለምሳሌ የግብርና ሚኒስቴር መ/ቤትን መውሰድ የምንችልና ለመደፊቱም ይህው እየታየና እየተጠና እንደዚሁም ከአስፈጻሚው መ/ቤት በላይ ራሱ ምክር ቤቱ (ፓርላማው) ስለየተቋማቱ በራሱ መንገድ የሚያጠናበትና የሚመለከትበት ክፍሎችን በማቋቋም እንዲታወጁ የሚመጡለትን ድንጋጌዎች ከብዙ አቅጣጫ በማየት ተግባራዊ ቢደረግ በማለት ጽሁፉን እቋጫለሁ፡፡    

ቸር ሰንብቱ!!
ደረጀ ማርቆስ