የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
275 subscribers
366 photos
3 videos
137 files
97 links
ይህ የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት ቻናል ስለኢትዮጵያ ሕጎች)ማብራሪያ የሚሰጥበት፣ አዳዲስ ሕጎች የሚጋሩበት፣ ሕግ ነክ ዜናዎችና መረጃዎች የሚተላለፉበት፣ በዳይሬክቶሬቱ የተሰጡ የንቃተ-ሕግ ስልጠናዎች፣ የሕግ መልዕክቶች፣ በራሪ ጽሑፎች እና መሰል ሰነዶች የሚለቀቁበት ነው።
መልካም ቆይታ!
Download Telegram
Forwarded from Daniel Fikadu √
347)። የአእምሮ ጉድለቱ በግልፅ ያልታወቀ ሰው ወራሾች ወይም ባለገንዘቦች ይህ ሰው ለፈፀመው ውል ጉድለት የሌለበት ፈቃድ ቃል አልሰጠበትምና ውሉ ሊፈርስ ይገባዋል ሲሉ የአእምሮ ጉድለት ያለበቱን ምክንያት በማድረግ የውሉን መፍረስ ለመጠየቅ አይችሉም። ይሁንና የውል አድራጊው የአእምሮ ጉድለት ከተደረገው የውል ቃል የሚታወቅ እንደሆነ ይህ ደንብ ተፈፃሚ አይሆንም (የፍ/ሕ/ቁ. 348 እና 349)።

• በፍርድ የሚደረግ ክልከላ (Judicial interdiction)

መከልከሉ ለጤናውና ለጥቅሙ የሚያስፈልግ ሆኖ ሲገኝ አእይምሮው የታወከ ሰው/የፍትሐብሔር ህጉ እንደሚያስቀምጠው እብድ ሰው/ እንዲከለከል(እንዲጠበቅ) ዳኞች ፍርድ ለመስጠት ይችላሉ (የፍ/ሕ/ቁ.351)። እንዲሁም ስለ ዕብዱ ሰው ወራሾች ጥቅም ዳኞች የእብዱን መከልከል ሊፈርዱ ይችላሉ። በፍርድ ስለሚደረግ ክልከላ የክልከላ ውሳኔ እንዲሰጥ ዕብድ የሆነው ሰው ወይም ከባልና ሚስት አንዱ ወይም ከስጋ ወይም ከጋብቻ ዘመዶች አንዱ ወይም ዐቃቤ ህግ ሊጠይቅ ይችላል። ዳኞች የክልከላ ፍርድ ሲሰጡ በሚሰጠው ውሳኔ ውስጥ ጊዜውን በመወሰን የተባለው ሰው ዕብደት የጀመረው ከእንደዚህ ያለው ጊዜ ጀምሮ ነው ሲሉ ለማስታወቅ ይችላሉ። በተሰጠው ውሳኔ ውስጥ የተቆጠረው ቀን ስለ ክልከላው ከቀረበው ጥያቄ በፊት ከሁለት ዓመት የበለጠ ጊዜ ሊኖረው አይችልም (የፍ/ሕ/ቁ.352)። 

በሌላ በኩል ዳኞች የክልከላ ፍርድ ሲሰጡ ወይም ውሳኔ ከሰጡ በኋላ የክልከላውን ውጤቶች ማጥበብ የሚችሉ ሲሆን ለተከለከለው ሰው እርሱ ራሱ እንዳንዶቹን ውሎች እንዲያደርግ ሊፈቅዱለት ይችላሉ። የተከለከለ ሰው የፈፀማቸውና ከስልጣኑ በላይ የሆኑት ሥራዎች መቃወም ይቻላል። እንዲሁም የተከለከለ ሰው ችሎታ የሌለው መሆኑን ከማያውቅ ቅን ልቦና ካለው ሰው ጋር ያደረገ እንደሆነ ውሉ በመፍረሱ ምክንያት በዚህ በቅን ልቡና በተዋዋለው ሰው ላይ ስለሚደርስ ጉዳት የተከለከለው ሰው አሳዳሪ በሀላፈነት ይጠየቃል (የፍ/ሕ/ቁ.374)።

በፍርድ የተከለከለ ሰው ጥበቃን በተመለከተ ለአካለመጠን ስላልደረሰ ሰው የሚደረግ ጥበቃ ማለትም በአሳዳሪና በሞግዚት የሚተዳደርበት ህግ ተፈፃሚ ይሆናል። በፍርድ ስለተከለከለ ሰው ክልከላ የማሳወቅ ግዴታ የአሳዳሪው ሲሆን ይህም የተከለከለው ሰው በሚኖርበት ቦታ ወይም ተቀማጭ ሆኖ እንዲኖር በተጠራበት ስፍራ ይሆናል። የተከለከለው ሰው አሳዳሪ ይህ የተከለከለ ሰው ችሎታ የሌለው ለመሆኑ በህግ መሰረት ማስታወቂያ በወጣበት ቦታ ተቀማጭ ሆኖ እንዲኖር መጠበቅ አለበት (የፍ/ሕ/ቁ.362)። የመኖሪያ ቦታውንም የለወጠ እንደሆን በአዲሱ መኖሪያ ማስታወቂያ እንዲወጣ ማድረግ አለበት። ይህን በፍርድ ከተከለከለ ሰው ጋር ህጋዊ ግንኙነት መፈፀም የሚፈልጉ ሰዎች ስለ ሁኔታው እውቀት እንዲኖራቸው እና አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል።

በፍርድ የተከለከለ ሰው ህጋዊ ግንኙነቶች

ስጦታ፡-

የተከለከለ ሰው ሞግዚት በተከለከለ ሰው ስም ለተከለከለው ሰው ተወላጆች ልጆች ስጦታ ለማድረግ የሚችሉ ሲሆን እነዚህ ስጦታዎች በተከለከለው ሰው ቤተ ዘመድ ምክር ጉባኤ የተፈቀዱ ካልሆኑ በቀር ፈራሾች ናቸው (የፍ/ሕ/ቁ.367)።

ኑዛዜ፡-

የተከለከለ ሰው ክልከላው በፍርድ ከተነገረ በኋላ ኑዛዜ ለማደረግ የማይችል ሲሆን ከተከለከለበት ቀን በፊት የተናዘዘው ኑዛዜ ይፀናል። ነገር ግን የኑዛዜው ቃላት ለርትዕ ተቃራኒ መስለው ለዳኞች የታዩ እንደሆነና የተናዘዘውም የጤናው ሁኔታ ያስደረገው መስሎ የታያቸው እንደሆነ ዳኞቹ ኑዛዜውን በሙሉ ወይም በከፊል ፈራሽ ሊያደርጉት ይችላሉ(የፍ/ሕ/ቁ.368)።

ጋብቻ፡-

በፍርድ የተከለከሉ ሰዎች ፍርድ ቤት ካልፈቀደ በቀር የጋብቻ ውል መዋዋል አይችሉም። ከፍርድ ቤት ፍቃድ ውጪ የተደረገ የጋብቻ ውል በማንኛውም ጥቅሜ ይነካል በሚል ወገን ተቃውሞ ሊቀርብበት ይችላል (የፍ/ሕ/ቁ.369)። ፍቺና ልጅ መካድን በተመለከተ
ያሳዳሪው ፍቃድ አስፈላጊ እንደሆነ የፍትሐብሔር ህጉ ይደነግጋል።

የክልከላ መቅረት

ስለክልከላ የተሰጠው ፍርድ ሲሻር የችሎታ ማጣት ፍፃሜ ሲሆን የክልከላው ውሳኔ መቅረት አካለመጠን ያልደረሰ ልጅ ከሞግዚት አስተዳደር መውጣት ያለው ውጤት ይኖረዋል። ይህም የሚሆነው ክልከላው እንዲወሰን ያደረጉት ምክንያቶች በቀሩ እና የተከለከለው ሰው ንብረቱን ለመምራት እና ለማስተዳደር ሲችል ነው። አእምሮው ከጎደለው ሰው በቀር ስለ ክልከላው ፍርድ እንዲሰጥ ለመጠየቅ የሚችሉ ሰዎች በማናቸውም ጊዜ የክልከላው ውሳኔ እንዲቀር ጥያቄ ለማቅረብ የሚችሉ ሲሆን አሳዳሪው ወይም ሞግዚቱም የክልከላው ውሳኔ እንዲቀር ለመጠየቅ ይችላሉ (የፍ/ሕ/ቁ.377)።

• በህግ የተከለከሉ ሰዎች

በህግ የተከለከለ ሰው ማለት አንድ በወንጀል የተቀጣ ሰው በመቀጣቱ ምክንያት ንብረቶቹን እንዳያስተዳድር ህግ የከለከለው ሰው እንደሆነ የፍትሐብሔር ህጉ ቁጥር 380 የሚደነግግ ሲሆን አንድ ሰው በህግ እንደ ተከለከለ ሆኖ የሚቆጠርባቸው ሁኔታዎች በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ህግ ተወስነዋል።

በህግ የተከለከለ ሰው አሳዳሪ የማይኖረው ሲሆን የንብረቶቹ አስተዳደር ዳኞች ለመረጡት ሞግዚት ይሰጣል(የፍ/ሕ/ቁ.382 እና 383)፡፡ በህግ የተከለከለ ሰው በፍርድ ከተከለከለ ሰው በተቃራኒ ጋብቻን ማድረግ፣ ፍቺ መጠየቅ፣ ልጅነት መቀበልና መካድ የሚችል ሲሆን ሞግዚቱ በህግ በተከለከለው ሰው ስም እነዚህን ሥራዎች መፈፀም አይችልም(የፍ/ሕ/ቁ.386)። በህግ የተከለከለው ሰው ያደረጋቸው ሥራዎች ወይም ውሎች ከስልጣኑ በላይ የሆኑ እንደሆነ ፈረሽ ናቸው። በህግ የተከለከለ ሰው ችሎታ ማጣትን ያስከተለው ቅጣት በተፈፀመ ጊዜ በህግ የተወሰነበት ክልከላ ቀሪ ይሆናል(የፍ/ሕ/ቁ.388)።

በአጠቃላይ ችሎታ ህጋዊ ግንኙነትን ለማከናወን መሰረታዊ ጉዳይ ሲሆን ማንኛውም ሰው ህጋዊ ግንኙነቶችን ከሰዎች ጋር ከመፈፀሙ በፊት የሚዋዋለው ሰው ችሎታ ያለው መሆኑን ማረጋገጥ በኃላ ላይ ሊከሰቱ ከሚችሉ እንደ ውል መፍረስ ካሉ ችግሮች የሚታደገው ስለሆነም ተገቢው ጥንቃቄ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው።

ምንጭ:- የኢፈድሪ ፍትህ ሚኒስቴር ንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት።
❤2
የኢፌዲሪ ወንጀል ህግ አንቀፅ 555፣ 556 እና 560 ተፈፃሚ ስለሚሆኑበት አግባብ
***
አከራካሪዉ ጉዳይ፡- ከፊሎቹ ባለሞያዎች የእጅ እልፊት ወንጀል የሚፈፀመዉ በእጅ ብቻ ነዉ ብለዉ ሲያምኑ ሌሎቹ ደግሞ የተፈፀዉ የወንጀል ድርጊት የሚለየዉ ከተገኘዉ ወይም ለማስገኘት ከታሰነዉ የወንጀል ዉጤት ላይ በመመርኮዝ ነዉ ብለዉ ያምናሉ፡፡

#የጠቅላይ_ዐቃቤ_ህግ_አቋም

የወንጀል ድንጋጌዎቹን በአግባቡ በስራ ላይ ለማዋልና በተግባር የሚስተዋሉ የዉሳኔ ልዩነቶች ለመቅረፍ ባለሞያዉ ዉሳኔዎችን በሚሰጥበት ወቅት የሚከተሉትን ነገሮች ከግምት ወስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል፡፡

#ሶስቱም_አንቀፆች_በአካል_ላይ_በደረሰዉ_የጉዳት_መጠን_ብቻ_የሚለያዩ_ስለመሆኑ

የአንቀፆቹ ይዘት በንፅፅርና በጥልቀት በማየት ለመረዳት እንደሚቻለዉ ሶስቱንም የህግ ድንጋጌዎች የሚለያዩት የደረሰዉን የጉዳት መጠን መሰረት በማድረግ ብቻ ነዉ፡፡ ይህም ሲባል አንድ ግለሰብ በሌላ ሰዉ አካል ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ግለሰቡ ሊከሰስ የሚገባዉ ከሶስቱ የወንጀል ህግ ድንጋጌዎች በየትኛዉ ነዉ የሚለዉ ጥያቄ የሚመለሰዉ የጉዳቱን መጠን መሰረት በማድግ ብቻ ነዉ፡፡ የአንቀፆቹን ይዘት በአግባቡ ለመረዳት የሶስቱንም የወንጀል ህግ ድንጋጌዎች ይዘት ስንመለከት

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ህግ አንቀፅ 555 መሰረት ከባድ አካል ጉዳት ተፈፀመ የሚባለዉ “የተጎጂዉን ሕይወት በሚያሰጋ ወይም በሰዉነቱም ሆነ በአዕምሮዉ ላይ ለዘወትር ጠንቅ በሚያተርፊ ሁኔታ ጉዳት ካደረሰ ወይም የሌላ ሰዉን አካል ወይም አስፈላጊ ከሆኑት ብልቶቹ ወይም ከህዋሳቶቹ አንዱን የጎደለ ፣ እንዳያገለግሉ ያደረገ ወይም በሚሳሰቅቅና ጉልህ ሆኖ በሚታይ ሁኔታ መልኩን ያበላሸ ወይም በማናቸዉም ሌላ መንገድ ከባድ የሆነ ጉዳትን ያስከተለ እንደሆነ ነዉ” በማለት ሲደነገግ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ህግ አንቀፅ 556 ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት ወንጀል ማለት

“………….በአንቀፅ 555 ከተመለከቱት ሁኔታዎች ዉጪ በሰዉ አካል ወይም ጤና ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ነዉ፡፡” በማለት ይደነግጋል፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ህግ አንቀፅ 560 መሰረት የእጅ እልፊት ተፈፀመ የሚባለዉ ደግሞ

“…..የአካል ጉዳትን ወይም የጤና ጉድለትን ሳያደርስ በሌላ ሰዉ ላይ የእጅ እልፊት ወይም የመጋፋት ወንጀል የፈፀመ እንደሆነ ነዉ፡፡” በማለት የደነገገ ሲሆን አንቀፁ አክሎም “ሰንበሮች፣ የደም መቋጠር ምልክቶች ወይም በቶሎ የሚያልፍ ህመም ወይም ሥቃይ እንደ አካል ጉዳት ወይም እንደ ጤና ጉድለት አይቆጠሩም” በማለት ይደነግጋል፡፡

ከላይ የተገለፁት የወንጀል ድንጋጌዎች የወንጀል ድርጊቱን ሲደነግጉ ጉዳቱን ለማድረስ አገልግሎት ላይ የዋለዉ መሳሪያ ከግምት ዉስጥ ያላስገቡ ቢሆንም ብዙ ግዜ የጉዳቱን መጠን ወደጎን በመተዉ ጉዳቱ የደረሰበትን መሳሪያ ብቻ ከግምት ዉስጥ በማስገባት ክስ ሲመሰርት ይታያል ነገር ግን ሶስቱም የህግ ድንጋጌዎች ከ 556(2) ዉጪ ያሉት የተመሰረቱት በደረሰዉ የጉዳት መጠን እንጂ ጉዳቱን ለማድርስ በተጠቀሙት የመሳሪያ አይነት ላይ አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ የወ/ህ/ቁ 560 ንዑስ አንቀፅ 1 ሶስተኛዉ ዓ.ነገር ላይ

’’ ቀላል የሆኑ ሰንበሮች፣የደም መቋጠር ምልከቶች፣ወይም በቶሎ የሚያልፍ ህመም ወይም ስቃይ እንደ አካል ጉዳት ወይም የጤና ጉድለት አይቆጠሩም”

የሚለዉን አገላፅ የእጅ እልፊት ወንጀል በእጅ ብቻ ሳይሆን በመሳሪያም ሊፈፀም እንደሚችል ለመረዳት ይቻላል፡፡ በሌላ አገላለፅ ጉዳቱን ለማድረስ የተጠቀመዉ መሳሪያ ምንም ይሁን ምንም ድርጊቱ ያስከተለዉ ጉዳት ቀላል የሆኑ ሰንበሮች፣የደም መቋጠር ምልከቶች፣ወይም በቶሎ የሚያልፍ ህመም ወይም ስቃይ እንደሆነ በእጅ እልፊት ስር ሊመደብ እንደሚገባ ለመረዳት ይቻላል፡፡

ሌላዉ ብዙዎች የሚያነሱት መከራከሪያ የወ/ህ/ቁ 560 ርዕሱ የእጅ እልፊት ማለቱ በራሱ ድርጊቱ መፈፀም ያለበት በእጅ መሆኑን ያመለክታል የሚል ቢሆንም ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረዉ ቀላል የሆኑ ሰንበሮች፣የደም መቋጠር ምልከቶች፣ወይም በቶሎ የሚያልፍ የህመም ወይም ስቃይ እንደ አካል ጉዳት ወይም የጤና ጉድለት አይቆጠሩም ማለቱ የእጅ አልፊት የሚለዉ የድንጋጌዉ ርዕስ የሚያደርሰዉ በቀላል የሚያልፍ ህመም መሆኑን እንጂ በእጅ ብቻ መፈፀም እንዳለበት አያመለክትም፡፡

የደረሰዉ የጉዳት መጠን ሳይሆን ጉዳት አድራሹ ለማድረስ ያሰበዉን የጉዳት መጠን አብሮ መመርመር አስፈላጊ ስለመሆኑ፡- ብዙ ግዜ የሚስተዋለዉ ችግር ተከሳሹ ሊያደርሰዉ የፈለገዉ ጉዳት ከነገሮች ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ለመረዳትና በማስረጃ ለማስደገፍ እየተቻለ በደረሰዉ ጉዳት ላይ ብቻ በመመሰረት ዉሳኔዎችን መስጠት ሌላዉ የችግሩ መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡ ምንም እንኳን የደረሰዉ ጉዳት በእጅ እልፊት ወይም በቀላል አካል ጉዳት ስር የሚሸፈን ቢሆንም ከአጠቃላይ ነባራዊዉ ሁኔታ በመነሳት ማለትም፡ ተከሳሹ ወንጀሉን ለመፈፀም የተጠቀመዉ መሳሪያ ፣ የግል ተበዳዩ የሚገኝበት ሁኔታና የተከሳሹ ያለዉ ግንዛቤ ፣ ተበዳዩና ጉዳት አድራሹ ተነፃፃሪ ጉልበት ፣ የህክምና ምርመራ ዉጤት ፣ ከደረሰዉ በላይ ጉዳት ያልደረሰበት ምክንያት እና የመሳሰሉትን አከባቢያዊ ሁኔታዎችን በጋራ በመመዘን የተከሳሹ ድርጊት በታወቀ ወይም በተለመደ ሂደት (In the normal course of things) ሊያስገኝ የሚችለዉን ዉጤት ግምት ዉስጥ በማስገባት ተገቢ የሆነዉን ወሳኔ መስጠት ተገቢ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ክስ ሲመሰረት ተከሳሹ የተጠቀመው መሳሪያ ብቻ በመመርኮዝ ሳይሆን ከአጠቃላይ ነባሪ ሁኔታ በመነሳት የደረሰውን ወይም ሊያደርስ ያሰበውን ጉዳት ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡

ምንጭ:- 👉 የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በወንጀል ጉዳዮች የአተረጓጎም ልዩነት ያለባቸውን ድንጋጌዎች ላይ ወጥነት ያለው ትርጉም ለማምጣት እንዲቻል ከተዘጋጀ የሕግ ማብራሪያ ላይ የተወሰደ 🙌
👍1
በጫኝ እና አውራጅ ዘርፍ ላይ የወጣው መመሪያ ፀደቀ

ለእያንዳንዱ እቃ ዋጋ ተቀምጦለታል

" ማንኛውም ግለሰብ እኔ ከልጆቼና ከቤተሰቦቼ ጋር እራሴ አወርዳለሁ ካለ #አይገደድም " - የአ/አ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር

በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ የማህበር ቤቶች፣ ሪል ስቴት ያሉባቸው አካባቢዎች ላይ ጫኝ እና አውራጆች በሚጠይቁት ያልተመጣጠነ ክፍያና በሚፈጥሩት ግብግብ በርካቶች እንደሚማረሩ ይታወቃል።

" እቃዬን እኔ እራሴ አወርዳለሁ " ሲባልም አንዳንድ ጫኝ እና አውራጆች ከአፃያፊ ቃላት ውርወራ ጀምሮ ለግብግብ እና ፀብ እስከማጋበዝም ይደርሳሉ።

" መንግስት እስካደራጀን ድረስ ባለቤቱ ፈለገም አልፈለገም እቃውን የምናወርደው እኛ ነን " እስከማለትም ይደርሳሉ።

አንዳንዴም እቃዎች እንዲጎዱ ፣ እነሱ ካላወረዱት እዛ አካባቢ ላይ በነፃነት ለመንቀሳቀስ ስጋት እንስከመሆንም ይደርሳል።

በዚህ ላይ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር ይቀርፋል፣ ነዋሪዎችንም ከምሬት እና እንግልት ያታደጋል የተባለው መመሪያ ማንኛውም ህገወጥና ነዋሪዎችን የሚያማርሩ ተግባራትን ይከለክላል።

" ግለሰቡ እኔ ከልጆቼ፣ ከቤተሰቤ ጋር ሆኜ አወርዳለሁ ካለ አይገደድም ፤ እራሱ ማውረድ ይችላል። ማህበራቱም እኛ ነን የተደራጀነው ማስወረድ አትችሉም ማለት አይችሉም " ሲሉ አቶ ማስረሻ ሃብቴ የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አማካሪ ተናግረዋል።

የባለቤቱን መብት መጠበቅ የማህበራቱ ግዴታ እንዳሆነ ገልጸዋል።

በስምምነት  እቃው የሚወርድ ከሆነ ደግሞ ጫኝ እና አውራጅ ማህበሩ ሙሉ ኃላፊነት ለእቃው ይወስዳል ብለዋል።

አቅምን ያላገናዘበ ፣ ከእቃው ጋር ያልተመጣጠነ ክፍያም እንዳይኖር የዋጋ ተመን መውጣቱን አቶ ማስረሻ ገልጸዋል።

" ለእያንዳንዱ እቃ ዋጋ ተቀምጦለታል "  ያሉት አቶ ማስረሻ " የራሱ የሆነ ርቀት አለው ለምሳሌ ከተሽከርካሪ ከወረደበት 50 ሜትር የመጀመሪያ ዋጋ አለ ከዛ በኃላ እያጨመረ ይሄዳል። ኮንዶሚየም ላይ የሚወጣ ከሆነ እስከ ብሎክ ስር 50 ሜትር ከሆነ ከታች ወደላይ ዋጋው እያጨመረ ይሄዳል።  " ብለዋል።

ቢሮው ተግባራዊ ስለተደረገው መመሪያ በጫኝ እና አውራጅ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች እና ማህበራት የ2 ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት መጀመሩን ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ያገኘው መረጃ ያሳያል።

@tikvahethiopia
Forwarded from አለ ሕግ
በመስተንግዶ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ያልተገባ አለባበስ እንዳይለብሱ የሚከለክል ረቂቅ ደንብ ወጣ
*******

በሆቴል እና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች የአለባበስ ሥነ-ሥርዓት ሊኖራቸው እንደሚገባ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው በሆቴል እና መሰል አገልግሎቶች ሰጪ ተቋማት የሚሠሩ ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣ ጌጥ እና የመዋቢያ አጠቃቀም ደንብ የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲስ ረቂቅ ደንብ አውጥቷል።

አዲሱ ረቂቅ ደንብ በሆቴል እና መሰል አገልግሎቶች ሰጪ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያዎችን አለባበስ፣ የፀጉር አያያዝ፣ በሚታዩ የሰውነት አካላት ላይ የሚደረጉ ጌጣ ጌጦች አጠቃቀምን እና የሚጠቀሟቸው ሽቶዎች መጠንን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን ይዟል።

ኢቢሲ ሳይበር ሚዲያ ይህንኑ ደንብ በተመለከተ በአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪስት አገልግሎቶች እና ብቃት ማረጋገጥ ደረጃ ምደባ ዳይሬክተሮት ዳይሬክተር ከሆኑት ወ/ሮ ገነት ይመር ጋር ቆይታ አድርጓል።

ወ/ሮ ገነት በጉዳዩ ላይ በሰጡት ሐሳብ፣ የማኅበረሰቡ አካል እንደመሆናችን በዕለት ተዕለት እቅስቃሴያችን ውስጥ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያለውን የሠራተኞች ያልተገባ አለባበስ አስተውለናል፤ ጉዳዩ ከምልከታችን በተጨማሪ የማኅበረሰቡ ቅሬታ ጭምር ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህም በመስተንግዶ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች የተራቆተ እና ሰውነታቸውን ከልክ በላይ የሚያሳይ ልብስ መልበስ እንደየማይችሉ ደንቡ ላይ መቀመጡን ገልጸዋል።

የሚታይ የሰውነት አካል ላይ ያለ ንቅሳት በአግባቡ መሸፈን እንዳለበት እና ሊታይ እንደማይገባውም በደንቡ መቀመጡን ገልጸዋል።
በቦሌ ክፍለ ከተማ ፍትህ ጽ/ቤት ስር የሚገኘው የህግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት በዛሬው እለት ማለትም ታህሳስ 5 ቀን 2016 በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 11 ለሚገኙ የማህበራዊ ፍ/ቤት ዳኞች፣ የምክር ቤት አባላት እና ለተመረጡ የወረዳው ነዋሪዎች በኢ/ፌ/ዲ/ሪፐብሊክ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 ላይ ስልጠና ሰጠ! በስልጠናውም ማንኛውንም የጦር መሳርያ ለመያዝ ፈቃድ የሚያስፈልግ ስለመሆኑ፣ ፈቃድ እንዲሰጣቸው የሚጠይቁ ሰዎች በቅድሚያ ሊያሟሏቸው ስለሚገቡ መስፈርቶች፣ ስለተፈቀዱ የጦር መሳርያ አያያዝና አጠቃቀም ሁኔታዎች፣ ፈቃድ ሊታገድና ሊሰረዝ ስለሚችልባቸው ምክንያቶች እና አዋጁን የሚጥሱ ሰዎች ስለሚጠብቃቸው የወንጀል ተጠያቂነት ግንዛቤ መፍጠር የተቻለ ሲሆን መድረኩ በተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት በስኬት ተጠናቅቋል።
🔥1
Forwarded from የአ.አ ስርጸት ዐቃቢያን ሕግ መረጃ ልውውጥ (Wubalem Mesfin)
የቦሌ ክ/ከተማ ፍትህ ጽ/ቤት የህግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት በየአመቱ ታህሳስ 5 የሚከበረውን አለም አቀፍ የስደተኞች ቀን በማስመልከት ከየካ ክ/ከተማ ፍትህ ጽ/ቤት የህግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር መገናኛ በሚገኘው ዲያስፖራ አደባባይ ላይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር በድምቀት አከበረ!
በመርሃ-ግብሩም ላይ በአዲስ አበባ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት በሰዉ መነገድ እና ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር  ወንጀል መከላከል ማስተባበሪያ ጽ/ቤተ ሃላፊ አቶ ታደሰ ፈይሳን ጨምሮ የክ/ከተሞቹ የህግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዐቃብያነ-ህግ ተገኝተውበታል። ፕሮግግራሙን የቦሌ ክ/ከተማ ፍትህ ጽ/ቤት ተወካይ ሃላፊ አቶ ሙሉቀን አዲሱ በመክፈቻ ንግግር  ያስጀመሩት ሲሆን በመቀጠልም የማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሃላፊ  በወንጀሉ አስከፊነት ዙሪያ መልክታቸዉን አስተላልፈዋል። 
በግንዛቤ ፈጠራዉ ላይ ካስማ እና ብሩህ የተባሉ የበጎ አድራጊ ድርጅቶች ተሳታፊ የሆኑበት ሲሆን የነዚህ ድርጅቶች አባል የሆኑ የስደት ተመላሾች በግንዛቤ ፈጠራዉ ላይ የራሳቸዉን የስደት ልምድ ለህብረተሰቡ አካፍለዋል።  በዚህም ስደት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ከተቻለ በአገር ሰርቶ ለመለወጥ ካልሆነም ስደት ምርጫዉ የሆነ ሰዉ ህጋዊ መንገድ እንዲጠቀም አመክረዉ መልክታቸዉን አስተላልፈዋል።  
ከዚህ በተጨማሪም የወንጀሉን አስከፊነት እና በሰው የመነገድ ሆነ በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ማለት ምን ማለት እንደሆነ ወንጀሉንም ፈጽሞ የተገኘ የሚጠብቀዉን የእስርም ሆነ የገንዘብ ቅጣት ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል እንዲሁም  ወንጀሉም ሲፈጸም ያየ ወይም የሰማ በነጻ የስልክ መስመር 6370 ላይ ጥቆማ መስጥ እንደሚችል የሚያስረዳ መልእክት ለህብረተሰቡ  በበራሪ ጽሁፍና በድምጽ ማስተላልፍ ተችሏል።