የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
275 subscribers
366 photos
3 videos
137 files
97 links
ይህ የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት ቻናል ስለኢትዮጵያ ሕጎች)ማብራሪያ የሚሰጥበት፣ አዳዲስ ሕጎች የሚጋሩበት፣ ሕግ ነክ ዜናዎችና መረጃዎች የሚተላለፉበት፣ በዳይሬክቶሬቱ የተሰጡ የንቃተ-ሕግ ስልጠናዎች፣ የሕግ መልዕክቶች፣ በራሪ ጽሑፎች እና መሰል ሰነዶች የሚለቀቁበት ነው።
መልካም ቆይታ!
Download Telegram
ጤና ይስጥልኝ ፡-
ማንም ሰው የመንግሥት ሥራን ማሰናከልና የመተባበር ግዴታ እያለበት ካልተባበረ በኢትዮጵያ የወንጅል ሕግ አንቀጽ 438 መሠረት በወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑን በተመለከተ ከደነገገው በመነሳት የሚከተለውን እንበል፤
መልካም ምንባብ
ማንም ሰው በሚያሽከረክር ጊዜ የትራፊክ ደንብ መተላለፍ ጋር በተያያዘ የክስ ወረቀትን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆን ከዚህ በላይ በጠቀስነው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 438 መሠረት የሚያስጠይቅ ነው፡፡ ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!
ደረጀ ማርቆስ
ጥር 2014 ዓ.ም
መሠየም ምን ማለት ነው?
መሠየም ማለት የተወሰነበትን ቅጣት የፈፀመ ቅጣቱ በይርጋ በይቅርታ የቀረለት፣ በአመክሮ ወይም በገደብ የታገደለት ማንኛውም ሰው በሚያቀርበው ጥያቄ መሠረት ከቅጣቱ በፊት የነበረው ስም እንዲመለስና ፍርዱ አንዲሰረዝለት በወ/ሕ/አ 232 መሠረት የሚጠይቅበት ስርዓት ነው። የወንል ሕጋችን በግልጽ እንደተደነገገው መሠየም የሚገኘው በመልካም ስራ እንጂ እንደ መብት ይገባኛል በማለት አይደለም፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ተቀጪው ከሞተ ወይም ችሎታ ካጣ የቅርብ ዘመዶቹ ወይም ወኪሉ ጥያቄውን ሊያቀርብ ይችላል።
መሰየም የሚፈቀደው ቅጣቱ ካለቀበት ወይም ከተቋረጠበት ጊዜ ጀምሮ ቢያንስ አምስት ዓመት ወይም በሌላ ቀላል ሁኔታዎች የሁለት ዓመት ጊዜ ካለፈ በኋላ ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ፀባዩ መልካም ከሆነና ወንጀል ካልፈፀመ እንዲሁም አቅሙና ሁኔታው በሚፈቅድለት መልኩ በፍርድ የተወሰነበትን ወይም ሊከፈል ይገባዋል ተብሎ የሚገመትበትን ካሳ፣ የዳኝነትና ማናቸውንም ኪሳራ ከከፈለ በመሰየም መልካም ስሙን ማስመለስ የሚችል ሲሆን ቅጣቱ በይርጋ የታገደለት ሰው ደግሞ ቅጣቱ ቢፈፀም ከሚጠናቀቅበት ጊዜ በፊት ልዩ ወይም የሚያስመሰግን ወታደራዊ ወይም ማኅበራዊ አስተዋፅኦ ካበረከተ መሰየም ይፈቀድለታል፡፡ ሆኖም ግን በወ/ሕ/አ 237 መሠረት መሰየም ከተፈቀደ በአምስት ዓመት ጊዜ እንደገና በሞት ወይም በፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል የሰራና የተፈረደበት ሰው መሰየሙ ይሰርዝበታል። ዳግመኛም የመሰየም ጥያቄ ማቅረብ አይችልም።
ጥር 12/2014 ዓ.ም (ኦምኒኤል)
በአመክሮ መፈታት ም ማለት ነው?
በአመክሮ መፈታት ማለት ተቀጪው የተወሰነበትን ቅጣት ቢያንስ ሦስት ሁለተኛውን ካጠናቀቀ በኋላ ይሄም ማለት አንድ ሶስተኛው ሲቀረው የተቀጩውን ፀባይ ማሻሻያና ወደ መደበኛ ኑሮው መመለሻ ይሆነዋል ተብሎ ሲታሰብ የተወሰነበትን የእስር ዘመን በሙሉ ሳያጠናቅቅ ሊፈታበት የሚችልበት አሰራር ሲሆን የእድሜ ልክ የተፈረደበት ሰው ሃያ ዓመት ከታሰረ በኋላ ነው የአመክሮ ጥያቄ ሊያቀርብ የሚችለው። ጥያቄውን እራሱ ተቀጪው ወይም የሚመለከተው አካል ሊያቀርበው የሚችል ሲሆን ጥያቄው የቀረበለት ፍ/ቤትም በወ/ሕ/አ 202 መሠረት በእስር ላይ እያለ የተረጋገጠ የጠባይ መሻሻል ማሳየቱን፣ ለደረሰው ጉዳት በተቻለ መጠን ካሳ መክፈሉን ሲያረጋግጥ እንዲሁም አመሉና ፀባዩ በአመክሮ ሲፈታ መልካም ውጤት ያስገኛል ብሎ ሲያምን እስረኛው በአመክሮ እንዲፈታ ይወስናል።
በአመክሮ መፈታት የፈተና ጊዜ ነው የሚባለው በአመክሮ የወጣው ግለሰብ ከእድሜ ልክ እስራት ባነሱ ቅጣቶች ላይ ቀሪውን የእስራት ዘመኑን ከሁለት እስከ አምስት ዓመት ጊዜ የእድሜ ልክ እስር በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት እስረኛው ከእስር ተለቆ ስለሚፈተን/ክትትል ስለሚደረግበት ነው፡፡ በፈተናው/በክትትሉ ወቅትም የተወሰነለትን የጠባይ ደንብ ከጣሰ ወይመ አዲስ ወንጀል ከፈፀመ በተሰጠው የሙከራ እድል መጠቀም ባለመቻሉ በወ/ሕ/አ 206 መሠረት አመክሮው ተሽሮ ቀሪ ቅጣቱን ይፈፅማል። አዲስ ወንጀል የፈፀመ በአመክሮ ላይ ያለ ሰው የደጋጋሚነት ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆነው በአመክሮ የተቀነሰለት ቅጣትና የአዲሱ ወንጀል ቅጣት ተደርቦ ይፈፀምበታል።
ጥር 12/2014 ዓ.ም (ኦምኒኤል)
5. የንብረት ሕግ ይርጋ

ይዞታዉ የተወሰደበት ወይም በይዞታዉ ላይ ሁከት የተነሳበት ሰዉ የያዘዉ ነገር ከተነጠቀበት ወይም በይዞታዉ ላይ ሁከት ከተነሳበት ቀን አንስቶ እስከ 2 ዓመት ድረስ ካልጠየቀ እጅ ይዛወርልኝ የማለት ክስ መብቱ ይቀርበታል፡፡

6. የስጦታ ዉል ይርጋ

አንድ ስጦታ ከተደረገ ከ2 ዓመት በኋላ ይፍረስልኝ የሚል ጥያቄ ተቀባይነት የለዉም፤የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2441 ስጦታ እንዲቀነስ ወይም እንዲሻር ለመጠየቅ 2 ዓመት ይርጋ እና የስጦታዉ ዉል የተደረገዉ በመንፈስ መጫን ሳይሆን የዉሉ አጠቃላይ ይዘት ለሞራልና ለሕግ ተቃራኒ ስለሆነ ይፍረስልኝ የሚል ጥያቄ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2441 (1) መሰረት 2 ዓመት ሳይሆን በፍትሐብሄር ሕግ ቁጥር 1845 የተመለከተዉ የ10 ዓመት ይርጋ ነዉ፡፡ እንዲሁም የስጦታ ዉል ይፈጸምልኝ ጥያቄ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1676(1) እና 1845 መሰረት በ10 ዓመት ይርጋ ቀሪ ሊሆን ይገባል፡፡

ፌናን ተጊበሉ
ጥር 12/2014 ዓ.ም
7. የአሰሪና ሰራተኛ ህግ ይርጋ

በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 ቁጥር 163 መሰረት በቅጥር ላይ ከተመሰረተ ግንኙነት የመነጨ ማንኛዉም ክስ የመብቱን ጥያቄ ለማቅረብ ከሚቻልበት ቀን ጀምሮ እስከ 1 ዓመት ድረስ፣ ወደ ሥራ ልመለስ በሚል የሚቀርብ ክስ ዉሉ በተቋረጠ በ3 ወር ጊዜ ዉስጥ፤ የደመወዝ፣የትርፍ ሰዓትና የሌሎች ክፍያዎች ጥያቄ መጠየቅ ከሚገባዉ ጊዜ ጀምሮ እስከ 6 ወር ባለዉ ጊዜ እና የሥራ ዉል በመቋረጡ ምክንያት በሰራተኛዉም ሆነ በአሠሪዉ የሚቀርብ ጥያቄ ሥራ ዉሉ በተቋረጠ በ6 ወር ጊዜ ዉስጥ ካልቀረበ በይርጋ ይታገዳል፡፡

8. የእንደራሴነትና የዉክልና ህግ ይርጋ

በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር. 2187 (2) መሰረት ሿሚዉ (ወካዩ) ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ ማለትም በተሰጠ ዉክልና ላይ የጥቅም ግጭት ተከስቶ ከሆነ ይህ ጥቅም ግጭት ያስነሳዉ ዉል መደረጉን ካወቁ ከ 2 ዓመት በኋላ እንዲፈረስ መጠየቅ በይርጋ የሚታገድ ነዉ፣ ወካይ የሆነ ወገን በተወካይ አማካኝነት የተደረገን ህገ ወጥ ዉል እንዲፈረስ በሚል የሚቀርበዉ አቤቱታ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1845 መሰረት በ10 ዓመት ይርጋ እንጂ በ 2 ዓመት የሚታገድ አለመሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰ/መ/ቁ 67376 ዉሳኔ ሰጥቷል፡፡

ፌናን ተጊበሉ
ጥር 16/2014 ዓ.ም
ሰላም ለሁላችን!!!
በዚች መልዕክት በሕገመንግስታችን በይርጋ ስለማይታገደው በሰው ልጆች ላይ ስለሚፈጸም ወንጀል የተደነገገውን ይኸው ታነቡልኝ ዘንድ!-
አንቀጽ28
በስብዕናላይስለሚፈጸሙወንጀሎች
1 ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና በሌሎች የኢትዮጵያ ሕጎች በሰውልጅ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው የተወሰኑትን ወንጀሎች፣ የሰውዘር የማጥፋት፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ የመውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን የመሰወር፣ ወይም ኢሰብዓዊ የድብደባ ድርጊቶችን በፈጸሙ ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ አይታገድም፡፡ በሕግ አውጪው ክፍልም ሆነ በማንኛውም የመንግሥት አካል ውሳኔዎች በምሕረት ወይም በይቅርታ አይታለፉም፡፡
2 ከዚህ በላይ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተጠቀሱትን ወንጀሎች ፈጽመው የሞት ቅጣት ለተፈረደባቸው ሰዎች ርዕሰብሔሩ ቅጣቱን ወደ ዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ሊያሻሽለው ይችላል፡፡

ከወንጀል የጸዳ ሂወት ለሁላችንም!
16/05/2014 ዓ.ም
( ሲሳይ ሰማኝ)
ጤና ይስጥልኝ በዚህ ጽሁፍ ስለ ማስረጃ ሕግ ጥቂት ልበላችሁ መልካም ንባብ
የማስረጃ ሕግ ወጥ ሥርዓት ያላቸዉ መሠረተ ሃሣቦች እንደሌሉት ተደርጎ ይቆጠር የነበረና በመሠረተ ሃሣቦቹ እዉቅና እያገኙ በመጡ ጊዜ ደግሞ አነዚሁ በስርዓት ለይቶ መመደቡና መተንተኑ ላይ ስምምነት ያልነበረበት ነዉ፡፡
አፈጻጸሙን በተመለከተ ደግሞ፤ ዋናዉ ችግር የሕጉ የተለያዩ መሠረተ ሃሣቦች ተመሳሳይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያላቸዉን አግባብነትና ተፈጻሚነት መወሰኑ ላይ ነዉ፡፡ በኮንቲኔንታል ሕግ ስርዓት (civil law) ተከታይ በሆኑ ሃገሮች ማስረጃ ነክ ሊባሉ የሚችሉ ሕጎች የሚገኙት በከፊል መሠረታዊ ሕጎች በሚባሉት ዉስጥ ሲሆን በከፊል ደግሞ ሥነ-ሥርዓት ሕግ በሚበሉት ዉስጥ እንጂ ራሱን ችሎ እንደቆመ አንድ የሕግ ዘርፍ አይደለም፡፡
ህድአት ጌታቸዉ ጥር/2014 ዓ.ም
…….የቀጠለ
የማስረጃ ሕግ ምንነት
ማስረጃ (evidence) መሠረቱ "evidentia" የሚለዉ የላቲን ቃል ሲሆን ትርጉሙም በግልጽ ማሳየት/የተረጋገጠ እንዲሆን ማድረግ፤ ማስረዳት የሚል ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ማስረጃ የአንድን አከራካሪ ነገር መኖር ወይም አለመኖር (existence or non-existence) የዳኛዉ አእምሮ እንዲያምን (persuade) የሚያደርግ ነገር ነዉ፡፡
በኢትዮጽያ የማስረጃ ሕግ ረቂቅ እና በሌሎች የሕግ መጸሃፎች የማስረጃ ትርጉም ሲሰጥ ማስረጃን እና የማስረጃ ሕግን ለይቶ የሚያስቀምጥ ሲሆን፡-
ማስረጃ፡- ማለት አንድ በፍ/ቤት መርረመራ ላይ ያለ በጭብጥ የተያዘ አከራካሪ ጉዳይ እዉነት መሆኑን እና አለመሆኑን በሚያሳምን ማረጋገጥ እንዲያስቸል በግብአትነት የሚቀርብ ማረጋገጫ ነዉ፡፡ ይህም
• በምስክሮች ቃል
• በሰነዶች
• በኤግዚቪቶች
• በፍ/ቤት ግንዛቤ በሚወሰድባቸዉ ነገሮች
• በህሊና ግምት እና በመሣሠሉት የሚገለጽ ነዉ፡፡
የማስረጃ ሕግ፡- በሁለት ክፍል የሚያይ ሲሆን
የመጀመሪያዉ ክፍል፡- ለአንድ ፍ/ቤት የቀረቡ ማስረጃ የሚያስፈልጋቸዉ በጭብጥ የሚያዙ ፍሬ ነገሮችን እና እነዚህ ፍሬ ነገሮች ለማስረዳት የሚቀርቡት ማረጋገጫዎች አግባብነት (relevancy) ተቀባይነት(admissibility ) ያላቸዉ መሆናቸዉን የሚወስነዉ ደንብ ነዉ፡፡
ሁለተኛዉ ክፍል፡-ማስረጃ የተባለዉ በግዙፍ ነገር፤ በሠነድ፤ በቃል፤ በዳኞች ግንዛቤ፤ በህሊና ግምት በተከራካሪዎች እምነት አማካይነት የሚቀርበዉን የማስረጃ አይነት ወይም ዘዴ እንዲሁም አከራካሪዉ ጉዳይ እዉነት መሆኑንና አለመሆኑን ፍ/ቤት እንዲያሳምን የሚደረግበትን መንገድ የሚገዛ ደንብ ነዉ፡፡
ህድአት ጌታቸዉ ጥር/2014 ዓ.ም
…….የቀጠለ
በአጠቃላይ የማስረጃ ሕግ እንደማንኛዉም የሥነ ሥርዓት ሕግ መብትና ግዴታን የሚወስነዉ የመሠረታዊ ሕግ (substantive law) ማስፈጸሚያ ሲሆን፤ በፍ/ቤት ክርክር በሚደረግበት ጊዜ በጭብጡ ላይ ዉሳኔ ለመስጠት እንዲረዳ በማስረጃ መረጋገጥ የሚገባቸዉ ምን ምን ፍሬ ነገሮች እንደሆኑ፤ የሚቀርቡትስ ማስረጃዎች ምን አይነት መሆን እንደሚገባቸዉ፤ ማስረጃዎቹን ማን ማቅረብ እንዳለበት፤ እንዴትስ መቅረብ እንዳለባቸዉ፤ የማስረጃዎቹን አግባብነት፤ ተቀባይነትና ክብደት፤ እነደዚህ የመሳሰለዉ ጉዳይ እንዴት እንደሚወሰን የሚመራ ሕግ ነዉ፡፡
ህድአት ጌታቸዉ ጥር/2014 ዓ.ም
ጤና ይስጥልኝ
ባልና ሚስት ትዳራቸው ፀንቶ እስካለ ድረስ የሚያፈሩት ንብረት የጋራቸው ሲሆን ለትዳራቸው እስከሆነ ድረስም የሚያወጡት ወጪም ለጋራ ጥቅም እንደዋለ የሚገመትበት አግባብ ያለ ሲሆን ስለዚሁ ከተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 85 እስከ 93 እንዲህ እንመልከት ፡- ባልና ሚስት የየግል ንብረታቸውን በተመለከተ በጋብቻ ውላቸው ለመወሰን የሚችሉ ሲሆን ስምምነት ከሌለ ግን ሕጉ ንብረቱን የጋራቸው አድርጎ እንደሚወሰደው ልብ እንበል ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ !
ደረጀ ማርቆስ
ጥር 2014 ዓ.ም
ጤና ይስጥልኝ!
በትናንሽም ሆነ ትላልቅ ንግድ ስራዎች አገናኞች ወይም ደላሎች የማያስፈልጉበት ዘርፍ አለ ማለት ያስቸግራል፡፡
በመሆኑም በአዲሱ የንግድ ሕግ አዋጅ 1243/2013 በሚከተለው መልኩ ስለደላላና ድለላ የደነገገውን እነሆ!!!
ስለ ደላሎች
1. ደላሎች ማለት ውል የሚዋዋሉ ሰዎችን በተለይም እንደ ሺያጭ፤ ኪራይ፤ ኢንሹራንስ፤ እንደ የማመላለሻ ያሉትን ውሎች የሚዋዋሉ ሰዎችን ፈልገው የሚያገናኙና የሚያዋውሉ፤ ራሱን የቻለ የሙያ ተግባራቸው አድርገው ጥቅም ለማግኘት የሚሠሩ ሰዎች ወይም ይህንኑ የደላላነት ሥራ የሚሠራ የንግድ ማኅበር ነው፤
2. ደላሎች አስማሚ ሆነው የሚያስፈጽሟቸው ውሎች ዓይነትና ግብ ወይም የሚያገናኙዋቸው ሰዎች ማንነት ወይም ሁኔታ ሳይታይ ነጋዴዎች ይባላሉ፤
3. ደላላ ሁለቱም ተስማሚዎች በውላቸው በግልጽ ያስቀመጡት ድንጋጌ ከሌለ በስተቀር ሁለቱን ተስማሚዎች በመወከል እነሱን ተክቶ ገንዘብ ለመቀበልም ሆነ ማንኛውንም ወደ ተግባር የሚያስገባ እንቅስቃሴ ማድረግ የለበትም፡፡
ለተዋዋዮች ስለ ማስታወቅ
በልማድ የታወቀ ካልሆነ ወይም ሌላ ስምምነት ካልተደረገ በስተቀር ተዋዋዮቹ በጉዳዩ ውል ለማድረግ የተስማሙ እንደሆነ ውሉ የሚደረግበትን ሁኔታ ለተዋዋዮች ሁሉ ወዲያውኑ ደላላው ማስታወቅ አለበት፤
2. በልማድ የታወቀ ካልሆነ ወይም ሌላ ስምምነት ከሌለ በስተቀር በዚህ ዓይነት የተዘጋጀውን ውል ባለጉዳዮቹ ካላጸደቁት በስተቀር በእነርሱ ላይ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡
ስለ ደላላው ኀላፊነት
ደላላው በሁለቱም ወገኖች ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት ኀላፊ ይሆናል፡፡
ስለ ደላላው አበል
1. ደላላው አስማሚ ሆኖ ውሉን ካስጨረሰ ወይም ካዋዋለ በኋላ ውሉ ቢፈጸምም ባይፈጸምም አበል ሊከፈለው ይገባል፤
2. በልማድ የታወቀ ካልሆነ ወይም ሌላ ስምምነት ካልተደረገ በስተቀር አበሉን የሚከፍለው የደላላውን አገልግሎት የጠየቀው ወገን ብቻ ነው፤
3. አበሉ በስምምነቱ ውስጥ ይወሰናል፤ወይም ባልተወሰነበት ጊዜ በልማድ መሠረት ይቆረጣል፤የተስማሙበት አበል ከባድ መስሎ ሲታየው ወይም ደላላው ከሰጠው አገልግሎት ጋራ ተመዛዛኝ አለመሆኑ ሲታየው ፍርድ ቤቱ ለመቀነስ ሥልጣን አለው፡፡
4. ደላላው ለደምበኛው ወይም አገልግሎቱን ለጠየቀው ወገን ያሉበትን ግዴታዎች ተላልፎና ይልቁንም የደምበኛውን ጥቅም በሚጎዳ አኳኃን ለሌላ ሦስተኛ ወገን ጥቅም የሠራ እንደሆነ ወይም ደምበኛው ሳያውቅ ከሦስተኛው ወገን ክፍያ የተቀበለ እንደሆነ አበል የማግኘት መብቱ ቀሪ ይሆናል፡፡
ቸርይግጠመን!!
ሲሳይ ሰማኝ
ጥር 2014 ዓ.ም
ሰላም ሰላም!!!
በንግድ አለም ውስጥ በግል ከሚካሄዱ ንግዶች በተጨማሪ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች መስርተው የሚያካሂዷቸው የንግድ አይነቶችን አዲሱ የንግድ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1243/2013እውቅና መስጠቱን እናገኛለን፡፡
እታዲያ መመስረት እንዳለ ማፍረስም የሚኖር በመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 181 የንግድ ማህበራት እንዴት መፍረስ እንዳለባቸው የተደነገገውን እነሆ!!!
የንግድ ማኅበር በሚከተሉት ምክንያቶች ይፈርሳል፡-
1. የተቋቋመበትን ዓላማ ሲፈጽም ወይም ለመፈጸም ሳይችል ሲቀር፣
2. የማኅበሩ አባላት እንዲቀጥል ካልተስማሙ በስተቀር የማኅበሩ የቆይታ ጊዜ ሲጠናቀቅ፣
3. ማኅበርተኞች የንግድ ማህበሩ እንዲፈርስ ሲስማሙ፣
4. በማኅበሩ አባላት መካከል ተቃራኒ ስምምነት ቢኖርም እንኳ በማኅበሩ አባላት ጥያቄ ፍርድ ቤት በበቂ ምክንያት ማኅበሩ እንዲፈርስ ሲወስን፤ ወይም
5. የማኅበሩ መክሰር በፍርድ ቤት ሲወሰን፡፡
6. ለዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 4 አላማ በቂ ምክንያት ማለት በማህበሩ አበላት መካከል ብርቱ አለመግባባት ኖሩ አለመግባባቱ የማህበሩ አላማ ከግብ እንዳይደረስ የሚያስተጓጉል ሲሆን ነው፣
7. በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 6 ላይ የተደነገገው ቢኖርም የተወሰኑትን የማህበሩ አባላት ድርሻቸውን ይዘው ከማህበሩ እንዲወጡ በማድረግ በቀሪ አባላት ማህበሩ አላማውን ለማሳከት በሚችልበት ሁኔታ ማስቀጠል የሚቻል በሆነ ጊዜ አለመግባባቱ ማህበሩን ለማፍረስ እንደ በቂ ምክንያት ተደርጎ አይወሰድም፡፡
አብሮ ለመስራት እውቀቱንና ጥበቡን ከፍቅር ጋር ያድለን!
ሲሳይ ሰማኝ
ጥር 2014 ዓ.ም
የአፍሪካ ሕብረት ሰንደቅ ዓላማ አሰቃቀል
በየአፍሪካ ሕብረት ሰንደቅ ዓላማ መዝሙር እና የአፍሪካ ቀን አዋጅ 1209/2012 አንቀጽ 4 መሠረት የሕብረቱን ሰንደቅ ዓላማ መውለብለብ የሚያግድ ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት ካላጋጠመ በስተቀር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣የክልል ቢሮዎች፣የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣የሌሎች አስፈጻሚ አካት ጽህፈት ቤቶች፣ፍርድ ቤቶች፣በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ በትምህርት ቤቶች፣የሃገር መከላከያ ተቋማት፣አውሮፕላን ማረፊያዎች፣የፖሊስና የጠረፍ ጥበቃ ተቋሞች፣የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች የአምባሰደሮች መኖሪያ ቤት ሕንፃዎች እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የባህር ላይ ሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀም ደንቦች ጋ በተጣጣመ አኳኋን የኢትዮጵያ ንግድ መርከቦች እ ጀልባዎች በየቀኑ የሕብረቱን ሰንደቅ ዓላማ ይሰቅላሉ፡፡ እንዲሁም ከላይ ያልተመለከቱት የመንግስት መስሪ ቤቶች የአፍሪካ ቀንን ጨምሮ በህዝብ በዓላት ቀን የሕብረቱን ሰንደቅ ዓላማ ይሰቅላሉ፡፡
በዚህው አንቀጽ ላይ ከተደነገጉት ድንጋጌዎች ሌላው የሕብረቱ ሰንደቅ ዓላማ በሚከተሉት የተለዩ ስፍራዎች የሚሰቀል ይሆና፡-
1. በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቅጥር ግቢ አደባባይ
2. በፌዴሬሽን ምክር ቤት ቅጥር ግቢ አደባባይ
3. በኢትዮጵያ ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና በመኖሪ ቤቶቻቸው ሕንፃዎች
4. በሚኒስቴሩ ለሚኒስቴሩ ተጠሪ በሆኑ ተቋማት ሕንፃዎች
5. የሕብረቱ ጉባኤዎች እ ስብሰባዎች በሚስተናገዱባቸው ከተማዎች አደባባዮች እ ዋና ዋና መንገዶች
ኦምኒኤል ከበደ ጥር 25/2014 ዓ.ም
👍1
በብሔራዊ ሃዘን ጊዜ ስለሚኖር የህብረቱ ሰንደቅ ዓላማ አሰቃቀል ሥነ-ሥርዓት
በአዋጅ ቁጥር 1209/2012 አንቀጽ 6 መሠረት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የህዝ ተወካዮች ምክር ቤት ብሐየራዊ የሃዘን ቀን ሲያውጅ የሕብረቱ ሰንደቅ ዓላማ አይሰቀልም፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ህብረቱ ሰንደቅ ዓላማው ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ሲወስን ሰንደቅ ዓላማው ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ደረጋል፡፡

ኦምኒኤል ከበደ ጥር 25/2014 ዓ.ም
በየጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀጽ 20 መሠረት በፍቃድ የተያዘ የጦር መሳሪያ ለሌላ ሰው ሊተላለፍ ስለሚችልበት ሁኔታ እንደተደነገገው
1. የጦር መሳሪያ ፍቃድ የተሰጠው ሰው የጦር መሳሪያ ለሌላ ሰው በማናቸውም መልኩ አሳልፎ መስጠት የለበትም፡፡
2. የጦር መሳሪያ ፍቃድ የተሰጠው ሰው የጦር መሳሪያውን አገልግሎት ያልፈለገ እንደሆነ ለተቆጣጣሪ ተቋም ማስረከብ አበት፡፡
3. ባለፍቃዱ የሞተ እንደሆነ በፍርድ ቤት የመውረስ መብት ያረጋገጠ መስፈርቱን የሚያሟላ ወራሽ የጦር መሳሪያው እንዲተላለፍለት ለመጠየቅ ይችላል፡፡ይህ ድንጋጌ እስኪፈፀም ድረስ የጦር መሳሪያው በእጁ የገባ ሰው በ30 የሥራ ቀናት ውስጥ ለተቆጣጣሪው ተቋም ማስረከብ አለበት፡፡

ኦምኒኤል ከበደ (የካቲት 1ቀን 2014 ዓ.ም)
ሰላም ለሁላችን!
በ1954 ወጥቶ እስከዛሬም ድረስ በስራ ላይ በሚገኘው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስነስርዓት ፖሊስ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተጠርጣሪን መያዝ የሚችልባቸው ምክንያቶች በሕግ ቁጥር 51 እንዲህ የተዘረዘሩት ናቸው፡፡
1. ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ የፖሊስ ሠራዊት ባልደረባ መያዝ የሚችለው
(ሀ) ከአንድ ዓመት በማያንስ እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል ለመሥራት ዝግጁ የሆነውን ወይም ሠርቷል ተብሎ በሚገባ የተጠረጠረውን ሰው
(ለ) የሕዝብን ጸጥታ በማበላሸት ላይ የሚገኘውን ሰው
(ሐ) የፖሊስ ሠራዊት ባልደረባ ሥራውን በሚፈጽምበት ጊዜ ተቃዋሚነትን በማሳየት የሚከላከለውን ወይም በሕግ ከታሰረበት የሚያመልጠውን ወይም ለማምለጥ የሚሞክረውን ሰው፤
(መ) ከፖሊስ ተጠባባቂነት የሚያመልጥ ወይም አምልጦ የሄደ ለመሆኑ በሚገባ የሚጠረጠረውን ሰው፤
(ሠ) ከወታደርነት ወይም ከፖሊስ ሠራዊት ከድቶ የሄደ ለመሆኑ በሚገባ የሚጠረጠረውን ሰው፤
(ረ) ሕግ የማይፈቅድለትን የቤት መሠርሠሪያ ወይም ቤትን ሰብሮ መግቢያ መሣሪያ የተገኘበት ሰው፤
(ሰ) ሕግ የማይፈቅድለትን የተሰረቀ ዕቃ የያዘ ለመሆኑ በሚገባ የሚያስጠረጥር ሆኖ ወይም ወንጀል በመፈጸም ረገድ ያገኘው ዕቃ በይዞታው የተገኘበት ሰው፤
(ሸ) በወንጀል ሕግ አንቀጽ 477 እንደተመለከትነው አደገኛ ሥራ ፈት መሆኑ በሚገባ የሚጠረጠረውን ሰው ነው።
2. የመንግሥት ባለሥልጣን ሠራተኞች ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ሰውን ለመያዝ በሌላ በልዩ ሕግ የሚሰጣቸው ሥልጣን የተጠበቀ ነው።
ለሰላምና ለሕግ የበላይነት የድርሻችንን መወጣትን አንርሳ!!!
ቸር ይግጠመን
ሲሳይ ሰማኝ የካቲት (7/6/14 ዓ.ም)