የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
275 subscribers
366 photos
3 videos
137 files
97 links
ይህ የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት ቻናል ስለኢትዮጵያ ሕጎች)ማብራሪያ የሚሰጥበት፣ አዳዲስ ሕጎች የሚጋሩበት፣ ሕግ ነክ ዜናዎችና መረጃዎች የሚተላለፉበት፣ በዳይሬክቶሬቱ የተሰጡ የንቃተ-ሕግ ስልጠናዎች፣ የሕግ መልዕክቶች፣ በራሪ ጽሑፎች እና መሰል ሰነዶች የሚለቀቁበት ነው።
መልካም ቆይታ!
Download Telegram
የመንግስት ( የቀበሌ/የኪራይ) ቤቶችን በተመለከተ የፌደሬሽን ምክር ቤት የሰበር ውሳኔን በመሻር ውሳኔ አስተላለፈ።
***
#Daniel Fikadu Law Office

ከዚህ ቀደም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስንት ሰሚ ችሎት በሠ/መ/ቁ. 189707 እና በሠ/መ/ቁ. 228002 ጠቅለል ሲደረግ
ቤትን ለረጅም ግዜ መያዝ ብቻውን የባለቤትነት መብት አያጎናጽፍም ሠ/መ/ቁጥር 228002     አንድን ቤት ለረጅም ግዜ መያዝ ብቻውን የባለቤትነት መብት የማያጎናጽፍ በመሆኑ እንዲሁም ቤቱ የቀበሌ / የመንግስት / ቤት መሆኑን የሚያሳይ ቅጽ 003 እና ቅጽ 004 በሌሉበትሁኔታ በተቋሙ የመረጃ ስርአት ቅጽ 008 በቀበሌ ቤትነት መመዝገቡ ብቻ ቤቱ በመንግስትየተወረሰ የቀበሌ /የመንግስት ቤት ነው ሊያስብለው አይችልም። በአዋጅ ቁጥር 47/67 ተወርሶ ለረጅም ግዜ በመንግስት እጅ የነበረ ቤትን በሚመለከት በስህተት አላግባብ ያለህጋዊ ምክንያት ተሰጥቷል የተባለው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የመከነና በመንግሰት ባለቤትነት የሚታወቅ ስለመሆኑ በተገለጸበት በአዋጅ ቁጥር 47/67 መሰረት መንግስት የወረሰው መሆኑን የሚያሳይ ቅጽ 003 እና ቅጽ 004 በሌለበት ቤቱን የመንግስት ንብረት አያሰኘውም።
የሚል ውሳኔ ወስኖ የነበረ ሲሆን ይህንን ውሳኔ የኢፌድሪ የፌደሬሽን ምክር ቤት መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ባደረገው 6ተኛ የፓርላማ ዘመን 3ተኛ አመት 1ኛ መደበኛ ጉባኤው በህገ መንግስት አጣሪው በቀረበለት መሰረት በመ/ቁጥር 108/15 የሠ/መ/ቁ .189707 ህገመንግስታዊነት አጣርቶ ውሳኔውን ሽሮታል።
ስለሆነም የመንግስት ቤትን ለረጅም ጊዜ ከአዋጅ 47/67 በኋላ ይዞ ያስተዳድር የነበረ ሁለቱ ቅፃች ቅፅ 003 እና 004 ባይኖሩትም ባለይዞታነቱ ይቀጥላል።
የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 223፣ 137 እና 256
አንድ ክርክር ያቀረበ ሰው ያቀረበውን ክስ ወይም መልስ በማስረጃ መደገፍ አለበት። ለፍርድ ቤት አቤቱታ ስለቀረበ ብቻ ይወሰናል ማለት አይደለም። በፍትሐብሔር ክርክር ወቅት 50+1 ያስረዳ ወገን የክርክሩ አሸናፊ ይሆናል። በወንጀል ክርክር ከዚህ በተቃራኒ ከጥርጣሬ ነፃ በሆነ (beyond reasonable doubt) ወንጀሉ መፈፀሙ በማስረጃ መረጋገጥ ይኖርበታል።
በፍትሐብሔር ክርክር ማስረጃ መቼ መቅረብ ይኖርበታል??
1. ክስ የመሰረተ ሰው ካቀረበው አቤቱታ ጋር ያቀረበ ሰው የሰነድ ወይም የሰው ማስረጃ ሊያቀርብ ይችላል። የክስ መልስ በተመሳሳይ። አንቀፅ 223 እና 234
2. ከክስ መሠማት በፊት ከላይ በተጠቀሱት ድንጋጌዎች ያልቀረቡ ማስረጃዎችን ማያያዝ ይቻላል።አንቀፅ 137
3. ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት(ከባድና በቂ በሆኑ ምክንያት) ያልቀረበ ማስረጃ ፍርድ ቤቱ አግባብነት ካለው የኪሳራ አከፋፈል ትዕዛዝ ጋር እንዲቀርብ ሊያዝ ይችላል። አንቀፅ 256
4. አንድ ተከራካሪ በራሱ ጥረት ማግኘት የማይችለውን ማስረጃ በፍርድ ቤት ትእዛዝ እንዲቀርብለት በማስረጃ ዝርዝር ላይ ገልጾ ሊያቀርብ ይችላል። አንቀፅ 145
👍1
የሰ/መ/ቁጥር 235371 //ያልታተመ/ጥቅምት 05 ቀን 2016 ዓ/ም///

#Daniel Fikadu Law Office
የመሬት ካሳ ምትክ ይሰጠኝ አቤቱታ ሰሚ ጉባኤ በየወረዳው ወይም በየከተማው አስተዳደር ስር የሚቋቋም ሲሆን በዚህ አግባብ የተቋቋመው አቤቱታ ሰሚ ጉባዔ ይዞታው ለህዝብ ጥቅም ሲባል ተወሰደብኝ የሚል ቅሬታ አቅራቢ የሚያቀርበውን ከካሳ እና/ወይም ምትክ ቦታ ጋር በተያያዘ ቅሬታ ተመልክቶ ተገቢውን ውሳኔ የመስጠት ስልጣን ያለው አለው።
ይህ ከሆነ ደግሞ የስር ፍርድ ቤቶች የካሳና ምትክ መሬት ጥያቄ ከመነሻውም የመመልከት ስልጣን የላቸውም።
በቦሌ ክፍለ ከተማ ስር ለሚገኙ የምክር ቤት አባላት በቀን 11/03/2016 ዓ.ም በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል መከላከል እና መቆጣጠር የትብብር ጥምረት አባላት እና ምክር ቤት ምንነት ላይ እንዲሁም ለዚሁ ወንጀል መቆጣጠር ሲባል በወጣው ደንብ ቁጥር 126/2014 ላይ ስልጠና ተሰጥቷል። ይህንም መሠረት አድርገው በተለያዩ ጽ/ቤቶች ለክትትል እና ድጋፍ በሚወርዱበት ጊዜ ጽ/ቤቶቹ በትብብር ጥምረቱ ሆነ በምክር ቤቱ ላይ የተጣለውን ግዴታ እየተወጡ እንደሆነ በማጣራት የበኩላቸውን ጥረት ወንጀሉን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እንዲያደርጉ መልክት ተላልፏል።
👍3
Forwarded from Daniel Fikadu √
ችሎታ (capacity) በህግ እይታ
   
ሰዎች በማህበራዊ መስተጋብር እርስ በርሳቸው በሚኖራቸው ግንኙነት ህጋዊ ተግባራትን ለመፈፀም፣ መብታቸውን ለማስከበር፣ ግዴታቸውን ለመወጣት እንዲሁም ህጋዊ ሀላፊነት ወይም ተጠያቂነትን ለመውሰድ ችሎታ ሊኖራቸው ይገባል።

በ1960 እ.ኢ.አ በወጣው የኢትዮጵያ ፍሐሀብሔር ህግ እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው ችሎታ የሌለው መሆኑ በሕግ ተወስኖ ካልተገለፀ በቀር ማንኛውንም ዓይነት የማህበራዊ ኑሮውን ተግባር ለመፈፀም ችሎታ አለው። ይህም የሚያሳየው ህግ የሚወስደው ግምት ማንኛውም ሰው በመርህ ደረጃ ችሎታ እንዳለው ነው። በዚህ አጭር የንቃተ-ህግ ፅሁፍ የሰዎች ችሎታ ምንነት፣ የችሎታ ጠቀሜታ ወይም አስፈላጊነት እንዲሁም የሰዎች ችሎታ የማይኖርባቸውን ሁኔታዎች ከፍሐሀብሔር ህጉ አንፃር እንዳስሳለን።

  የሰዎች ችሎታ ምንነት

የህግ መዝገበ ቃላት በሆነው መሪያም ዌብስተር እንደተሰጠው ትርጉም ህጋዊ ችሎታ ማለት አንድ ሰው በሕግ መሠረት አንድን የተወሰነ ሁኔታ ወይም ግንኙነት ከሌላው ጋር የማድረግ ወይም በአንድ የተወሰነ ሥራ ወይም ግብይት ላይ የመሳተፍ ችሎታ እና ኃይል ነው። በተጨማሪም ችሎታ ውሳኔ ለማድረግ መረጃን የመጠቀም እና የመረዳት ችሎታ እና ማንኛውንም ውሳኔ ማስተላለፍ አቅም ማለት ነው። አንድ ሰው አእምሮው ከተዳከመ ወይም  በሆነ መንገድ ጤናው ከተጓደለ አቅም ይጎድለዋል። ይህም ማለት በዚያን ጊዜ ውሳኔ ማድረግ አይችልም ማለት ነው። የሕግ ችሎታ በሕጉ መሠረት በእኩልነት የመስተናገድ መሠረታዊ የሰብአዊ መብት አካል ነው። በመሆኑም ችሎታ ያለው ሰው በፍትሐብሔር ሥነ ስርዓት ህግ ቁጥር 33(1) መሰረት ፍትሐብሔር ክስ ማቅረብ የሚችል ሲሆን የፈፀመው የወንጀል ድርጊትም ካለ የወንጀል ህጉ መሰረት ሀላፊነት ይሆናል ማለት ነው።

• የችሎታ ጠቀሜታ ወይም አስፈላጊነት

ችሎታ ህጋዊ ግንኙነቶችን በራስ ለማከናወን ጠቀሜታ አለው። ለአብነት ያክል አንድ ሰው ውል በራሱ ለመዋዋል ለምሳሌ ሽያጭ ለመፈፀም ችሎታ ሊኖረው ይገባል። ይኸውም እድሜው በህግ በተወሰነው ልክ መሆን ያለበት እንዲሁም የአይምሮው የጤንነት ሁኔታ ጤነኛ መሆን ይኖርበታል። ያለበለዚያ ግን ህጉ በሚያስቀምጠው ሥርዓት ወይም በወኪል በኩል ህጋዊ ግንኙነቶችን ለመፈፀም ይገደዳል። እንዲሁም በወንጀል ጉዳይ የወንጀል ህግን መሰረት በማድረግ ተጠያቂነትን ወይም ተከሳሽነትን ለመወሰን ወይም ሀላፊ እና ኢ-ሀላፊን ለመለየት የአንድ ሰው ችሎታ መኖር ወይም አለመኖር ማወቅ አስፈላጊ ነው።

• ሰዎች ችሎታ የሚያጡበት ሁኔታ

በፍትሐብሄር ህግ ቁጥር 193 ስር እንደተደነገገው ጠቅላላ የችሎታ ማጣት ሁኔታ የሚያስከትሉ ምክንያቶች ዕድሜ ወይም የሰው አእምሮ ሁኔታ ወይም በተሰጠ የፍርድ ቅጣት ናቸው። በተጨማሪም የፍትሐብሔር ህጉ የተለየ የችሎታ ማጣት ሁኔታን የያዘ ሲሆን ይኸውም የተለየ ችሎታ ማጣትን ለመወሰን በግምት ውስጥ ለማስገባት የሚቻለው የሰውዬውን ዜግነት በመመልከት ወይም የሚያከናውነውን ሥራ መሰረት አድርጎ በመያዝ ነው። የችሎታ ማጣት አስረጂን በተመለከተ ሰው ሁሉ ችሎታ እንዳለው የሚገመት ሲሆን ይህ ሰው ችሎታ የሌለው ነው ብሎ ማስረዳት የሚገባው ሰውዬው ችሎታ የለውም ብሎ የሚከራከር ወገን ነው (የፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 196)። ከተፈጥሮ ሰዎች በተጨማሪ የሰውነት መብት የተሰጣቸው ድርጅቶችና ለልዩ አገልግሎት የተመደቡ ንብረቶች ችሎታ ያላቸው መሆኑ የሚረጋገጠው እንደ አይነታቸው ለነዚሁ የሰውነት መብት በሚሰጧቸው ድንጋጌዎች መሰረት ነው። ችሎታ የሚያሳጡ ሁኔታዎችን እንደሚከተለው በዝርዝር እንመለከታለን።

• በእድሜ ምክንያት ችሎታ ማጣት (Minors)

በእድሜያቸው ምክንያት ችሎታ የሌላቸው ሰዎች ወይም አካለመጠን ስላልደረሱ ሰዎች ሁኔታ በፍትሐብሔር ህጉ የተደነገጉት ድንጋጌዎች የተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ህግ ተፈፃሚ በሚሆንባቸው መስተዳድሮች ተፈፃሚ እንደማይሆን በቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 319 ስር ተደንግጎ ይገኛል። በመሆኑም በቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 215 ስር እንደተደነገገው በእድሜያቸው ምክንያት ችሎታ ያጡ ሰዎች ወይም አካለመጠን ያልደረሰ ሰውን በተመለከተ ትርጉም የሰጠ ሲሆን በትርጉሙ መሰረት አካለመጠን ያልደረሰ ሰው ማለት ፆታ ሳይለይ እድሜው አሥራ ስምንት ዓመት ያልሞላው ልጅ ነው። በእድሜው ምክንያት ችሎታ ያጣ አካለመጠን ያልደረሰ ሰው ህጋዊ ግንኙነቶቸን በራሱ ማከናወን ህጉ ስለማይፈቅድለት ስለመልካም አስተዳደጉና ደህንነቱ ጉዳይ በአሳዳሪው የሚጠበቅ ሲሆን ንብረት ነክ ጥቅሞቹንና በአጠቃላይ የንብረቱን አስተዳደር በሚመለከት በሞግዚት ይወከላል (የቤተሰብ ህግ አንቀፅ 216)። ስለአሳዳሪ እና ሞግዚት አስተዳደር በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ከአንቀፅ 215 እስከ 318 በዝርዝር ተደንግጎ ይገኛል።

• በአእምሮ ሁኔታ ችሎታ ማጣት
አዕምሮዋቸው ስለ ጎደለ ሰዎች፡- የፍትሐብሔር ህጉ ትርጉም የሰጠ ሲሆን አዕምሮው ጎደሎ ነው የሚባለው በተፈጥሮ ዕውቀቱ ያልተስተካከለ በመሆኑ ወይም በአእምሮ መናወጥ ወይም በእርጅና ምክንያት የሚሰራውን ሥራ የሚያደረሰውን ለማወቅ የማይችል ነው። የአእይምሮ ደካሞች ሰካራም ወይም በመጠጥ አፍዛዥ በሆኑ ነገሮች ልማድ የተመረዙና ገንዘብ ያለ አግባብ የሚያባክኑ ሰዎች አእምሮዋቸው እንደጎደለ ሰዎች ይቆጠራሉ (የፍ/ሕ/ቁ. 339)።

  በግልፅ ስለታወቀ የአእምሮ ጉድለት ያለበት ሰው፡- የአእምሮ ጉድለት ያለበት ዕብደቱ በግልፅ እንደ ታወቀ ሰው ሆኖ በህግ የሚቆጠረው ይህ የተባለው ሰው በሆስፒታል ውስጥ ወይም በአንድ የአእምሮ ጉድለት ያለባቸው ሰዎች መኖሪያ ቦታ ውስጥ በአእምሮው ሁኔታ ምክንያት በአንድ የጤና ጥበቃ ቤት ውስጥ ተዘግቶበት በዚህ በተዘጋበት ቦታ እስከሚቆይበት ጊዜ ነው (የፍ/ሕ/ቁ. 341)። በግልፅ የታወቀ እብድ የሚሰራቸውን ሥራዎች በተመለከት እብደቱ ግልፅ በሆነበት ጊዜና ቦታ ላይ የሠራቸውን ሥራዎች እርሱ ወይም ወኪሎቹ ወይም ወራሾቹ ሊቃወሟቸው ይችላሉ (የፍ/ሕ/ቁ. 343)። ተቃራኒ የሚሆን አስረጂ ከሌለ በቀር የነዚህ ሰዎች ሥራና ፈቃድ የውለታን ፈራሽነት የሚያስከትል ጉድለት ያለበት ነው ተብሎ ይገመታል። እንዲሁም በስህተት መገኘት ምክንያት የሥራዎችና የውሎች መፍረስ የሚመለከቱት የፍትሐብሔር ህግ ደንቦች በተመሳሳይ ተፈፃሚዎች ይሆናሉ (የፍ/ሕ/ቁ. 344)። ይሁንና የአእምሮ ጉድለት ያለበት ሰው ከእርሱ ጋር የተደረጉት ውሎች በመፍረሳቸው ምክንያት በቅን ልቡና በተዋዋዮች ሦስተኛ ወገኖች ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ሀላፊ ይሆናሉ። በሌላ በኩል ከውል ውጪ ሀላፊነትን በተመለከተ ለጤናማ ሰው እንዳለው ሀላፊነት የሚኖርበት ከመሆኑ በተጨማሪ ይህ የአእምሮ ጉድለት ያለበት ያለ አግባብ ካገኘው ብልፅግና የተነሳ ላሉት ግዴታዎች ጤናማ ለሆነ ሰው ያሉበት ግዴታዎች ይኖሩበታል (የፍ/ሕ/ቁ. 350)።

  የአእምሮ ጉድለት ያለበቱ በግልፅ ስላልታወቀ ሰው፡- የአእምሮ ጉድለቱ በግልፅ ያልታወቀ ሰው የፈፀማቸው የህግ ሥራዎች ውሎች በዚሁ ሰው የአእምሮ ጉድለት ምክንያት ሊሻሩ አይችሉም። ሆኖም የአእምሮ ጉድለት ያለበት ሰው እነዚህን ውሎች በፈፀመበት ጊዜ ጉድለት የሌለበት ፈቃድ ለመስጠት በማይችልበት ሁኔታ እንደ ነበረ ለማስረዳት ከቻለ ውሎቹን ለማፍረስ ይችላል (የፍ/ሕ/ቁ.
Forwarded from Daniel Fikadu √
347)። የአእምሮ ጉድለቱ በግልፅ ያልታወቀ ሰው ወራሾች ወይም ባለገንዘቦች ይህ ሰው ለፈፀመው ውል ጉድለት የሌለበት ፈቃድ ቃል አልሰጠበትምና ውሉ ሊፈርስ ይገባዋል ሲሉ የአእምሮ ጉድለት ያለበቱን ምክንያት በማድረግ የውሉን መፍረስ ለመጠየቅ አይችሉም። ይሁንና የውል አድራጊው የአእምሮ ጉድለት ከተደረገው የውል ቃል የሚታወቅ እንደሆነ ይህ ደንብ ተፈፃሚ አይሆንም (የፍ/ሕ/ቁ. 348 እና 349)።

• በፍርድ የሚደረግ ክልከላ (Judicial interdiction)

መከልከሉ ለጤናውና ለጥቅሙ የሚያስፈልግ ሆኖ ሲገኝ አእይምሮው የታወከ ሰው/የፍትሐብሔር ህጉ እንደሚያስቀምጠው እብድ ሰው/ እንዲከለከል(እንዲጠበቅ) ዳኞች ፍርድ ለመስጠት ይችላሉ (የፍ/ሕ/ቁ.351)። እንዲሁም ስለ ዕብዱ ሰው ወራሾች ጥቅም ዳኞች የእብዱን መከልከል ሊፈርዱ ይችላሉ። በፍርድ ስለሚደረግ ክልከላ የክልከላ ውሳኔ እንዲሰጥ ዕብድ የሆነው ሰው ወይም ከባልና ሚስት አንዱ ወይም ከስጋ ወይም ከጋብቻ ዘመዶች አንዱ ወይም ዐቃቤ ህግ ሊጠይቅ ይችላል። ዳኞች የክልከላ ፍርድ ሲሰጡ በሚሰጠው ውሳኔ ውስጥ ጊዜውን በመወሰን የተባለው ሰው ዕብደት የጀመረው ከእንደዚህ ያለው ጊዜ ጀምሮ ነው ሲሉ ለማስታወቅ ይችላሉ። በተሰጠው ውሳኔ ውስጥ የተቆጠረው ቀን ስለ ክልከላው ከቀረበው ጥያቄ በፊት ከሁለት ዓመት የበለጠ ጊዜ ሊኖረው አይችልም (የፍ/ሕ/ቁ.352)። 

በሌላ በኩል ዳኞች የክልከላ ፍርድ ሲሰጡ ወይም ውሳኔ ከሰጡ በኋላ የክልከላውን ውጤቶች ማጥበብ የሚችሉ ሲሆን ለተከለከለው ሰው እርሱ ራሱ እንዳንዶቹን ውሎች እንዲያደርግ ሊፈቅዱለት ይችላሉ። የተከለከለ ሰው የፈፀማቸውና ከስልጣኑ በላይ የሆኑት ሥራዎች መቃወም ይቻላል። እንዲሁም የተከለከለ ሰው ችሎታ የሌለው መሆኑን ከማያውቅ ቅን ልቦና ካለው ሰው ጋር ያደረገ እንደሆነ ውሉ በመፍረሱ ምክንያት በዚህ በቅን ልቡና በተዋዋለው ሰው ላይ ስለሚደርስ ጉዳት የተከለከለው ሰው አሳዳሪ በሀላፈነት ይጠየቃል (የፍ/ሕ/ቁ.374)።

በፍርድ የተከለከለ ሰው ጥበቃን በተመለከተ ለአካለመጠን ስላልደረሰ ሰው የሚደረግ ጥበቃ ማለትም በአሳዳሪና በሞግዚት የሚተዳደርበት ህግ ተፈፃሚ ይሆናል። በፍርድ ስለተከለከለ ሰው ክልከላ የማሳወቅ ግዴታ የአሳዳሪው ሲሆን ይህም የተከለከለው ሰው በሚኖርበት ቦታ ወይም ተቀማጭ ሆኖ እንዲኖር በተጠራበት ስፍራ ይሆናል። የተከለከለው ሰው አሳዳሪ ይህ የተከለከለ ሰው ችሎታ የሌለው ለመሆኑ በህግ መሰረት ማስታወቂያ በወጣበት ቦታ ተቀማጭ ሆኖ እንዲኖር መጠበቅ አለበት (የፍ/ሕ/ቁ.362)። የመኖሪያ ቦታውንም የለወጠ እንደሆን በአዲሱ መኖሪያ ማስታወቂያ እንዲወጣ ማድረግ አለበት። ይህን በፍርድ ከተከለከለ ሰው ጋር ህጋዊ ግንኙነት መፈፀም የሚፈልጉ ሰዎች ስለ ሁኔታው እውቀት እንዲኖራቸው እና አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል።

በፍርድ የተከለከለ ሰው ህጋዊ ግንኙነቶች

ስጦታ፡-

የተከለከለ ሰው ሞግዚት በተከለከለ ሰው ስም ለተከለከለው ሰው ተወላጆች ልጆች ስጦታ ለማድረግ የሚችሉ ሲሆን እነዚህ ስጦታዎች በተከለከለው ሰው ቤተ ዘመድ ምክር ጉባኤ የተፈቀዱ ካልሆኑ በቀር ፈራሾች ናቸው (የፍ/ሕ/ቁ.367)።

ኑዛዜ፡-

የተከለከለ ሰው ክልከላው በፍርድ ከተነገረ በኋላ ኑዛዜ ለማደረግ የማይችል ሲሆን ከተከለከለበት ቀን በፊት የተናዘዘው ኑዛዜ ይፀናል። ነገር ግን የኑዛዜው ቃላት ለርትዕ ተቃራኒ መስለው ለዳኞች የታዩ እንደሆነና የተናዘዘውም የጤናው ሁኔታ ያስደረገው መስሎ የታያቸው እንደሆነ ዳኞቹ ኑዛዜውን በሙሉ ወይም በከፊል ፈራሽ ሊያደርጉት ይችላሉ(የፍ/ሕ/ቁ.368)።

ጋብቻ፡-

በፍርድ የተከለከሉ ሰዎች ፍርድ ቤት ካልፈቀደ በቀር የጋብቻ ውል መዋዋል አይችሉም። ከፍርድ ቤት ፍቃድ ውጪ የተደረገ የጋብቻ ውል በማንኛውም ጥቅሜ ይነካል በሚል ወገን ተቃውሞ ሊቀርብበት ይችላል (የፍ/ሕ/ቁ.369)። ፍቺና ልጅ መካድን በተመለከተ
ያሳዳሪው ፍቃድ አስፈላጊ እንደሆነ የፍትሐብሔር ህጉ ይደነግጋል።

የክልከላ መቅረት

ስለክልከላ የተሰጠው ፍርድ ሲሻር የችሎታ ማጣት ፍፃሜ ሲሆን የክልከላው ውሳኔ መቅረት አካለመጠን ያልደረሰ ልጅ ከሞግዚት አስተዳደር መውጣት ያለው ውጤት ይኖረዋል። ይህም የሚሆነው ክልከላው እንዲወሰን ያደረጉት ምክንያቶች በቀሩ እና የተከለከለው ሰው ንብረቱን ለመምራት እና ለማስተዳደር ሲችል ነው። አእምሮው ከጎደለው ሰው በቀር ስለ ክልከላው ፍርድ እንዲሰጥ ለመጠየቅ የሚችሉ ሰዎች በማናቸውም ጊዜ የክልከላው ውሳኔ እንዲቀር ጥያቄ ለማቅረብ የሚችሉ ሲሆን አሳዳሪው ወይም ሞግዚቱም የክልከላው ውሳኔ እንዲቀር ለመጠየቅ ይችላሉ (የፍ/ሕ/ቁ.377)።

• በህግ የተከለከሉ ሰዎች

በህግ የተከለከለ ሰው ማለት አንድ በወንጀል የተቀጣ ሰው በመቀጣቱ ምክንያት ንብረቶቹን እንዳያስተዳድር ህግ የከለከለው ሰው እንደሆነ የፍትሐብሔር ህጉ ቁጥር 380 የሚደነግግ ሲሆን አንድ ሰው በህግ እንደ ተከለከለ ሆኖ የሚቆጠርባቸው ሁኔታዎች በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ህግ ተወስነዋል።

በህግ የተከለከለ ሰው አሳዳሪ የማይኖረው ሲሆን የንብረቶቹ አስተዳደር ዳኞች ለመረጡት ሞግዚት ይሰጣል(የፍ/ሕ/ቁ.382 እና 383)፡፡ በህግ የተከለከለ ሰው በፍርድ ከተከለከለ ሰው በተቃራኒ ጋብቻን ማድረግ፣ ፍቺ መጠየቅ፣ ልጅነት መቀበልና መካድ የሚችል ሲሆን ሞግዚቱ በህግ በተከለከለው ሰው ስም እነዚህን ሥራዎች መፈፀም አይችልም(የፍ/ሕ/ቁ.386)። በህግ የተከለከለው ሰው ያደረጋቸው ሥራዎች ወይም ውሎች ከስልጣኑ በላይ የሆኑ እንደሆነ ፈረሽ ናቸው። በህግ የተከለከለ ሰው ችሎታ ማጣትን ያስከተለው ቅጣት በተፈፀመ ጊዜ በህግ የተወሰነበት ክልከላ ቀሪ ይሆናል(የፍ/ሕ/ቁ.388)።

በአጠቃላይ ችሎታ ህጋዊ ግንኙነትን ለማከናወን መሰረታዊ ጉዳይ ሲሆን ማንኛውም ሰው ህጋዊ ግንኙነቶችን ከሰዎች ጋር ከመፈፀሙ በፊት የሚዋዋለው ሰው ችሎታ ያለው መሆኑን ማረጋገጥ በኃላ ላይ ሊከሰቱ ከሚችሉ እንደ ውል መፍረስ ካሉ ችግሮች የሚታደገው ስለሆነም ተገቢው ጥንቃቄ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው።

ምንጭ:- የኢፈድሪ ፍትህ ሚኒስቴር ንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት።
❤2
የኢፌዲሪ ወንጀል ህግ አንቀፅ 555፣ 556 እና 560 ተፈፃሚ ስለሚሆኑበት አግባብ
***
አከራካሪዉ ጉዳይ፡- ከፊሎቹ ባለሞያዎች የእጅ እልፊት ወንጀል የሚፈፀመዉ በእጅ ብቻ ነዉ ብለዉ ሲያምኑ ሌሎቹ ደግሞ የተፈፀዉ የወንጀል ድርጊት የሚለየዉ ከተገኘዉ ወይም ለማስገኘት ከታሰነዉ የወንጀል ዉጤት ላይ በመመርኮዝ ነዉ ብለዉ ያምናሉ፡፡

#የጠቅላይ_ዐቃቤ_ህግ_አቋም

የወንጀል ድንጋጌዎቹን በአግባቡ በስራ ላይ ለማዋልና በተግባር የሚስተዋሉ የዉሳኔ ልዩነቶች ለመቅረፍ ባለሞያዉ ዉሳኔዎችን በሚሰጥበት ወቅት የሚከተሉትን ነገሮች ከግምት ወስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል፡፡

#ሶስቱም_አንቀፆች_በአካል_ላይ_በደረሰዉ_የጉዳት_መጠን_ብቻ_የሚለያዩ_ስለመሆኑ

የአንቀፆቹ ይዘት በንፅፅርና በጥልቀት በማየት ለመረዳት እንደሚቻለዉ ሶስቱንም የህግ ድንጋጌዎች የሚለያዩት የደረሰዉን የጉዳት መጠን መሰረት በማድረግ ብቻ ነዉ፡፡ ይህም ሲባል አንድ ግለሰብ በሌላ ሰዉ አካል ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ግለሰቡ ሊከሰስ የሚገባዉ ከሶስቱ የወንጀል ህግ ድንጋጌዎች በየትኛዉ ነዉ የሚለዉ ጥያቄ የሚመለሰዉ የጉዳቱን መጠን መሰረት በማድግ ብቻ ነዉ፡፡ የአንቀፆቹን ይዘት በአግባቡ ለመረዳት የሶስቱንም የወንጀል ህግ ድንጋጌዎች ይዘት ስንመለከት

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ህግ አንቀፅ 555 መሰረት ከባድ አካል ጉዳት ተፈፀመ የሚባለዉ “የተጎጂዉን ሕይወት በሚያሰጋ ወይም በሰዉነቱም ሆነ በአዕምሮዉ ላይ ለዘወትር ጠንቅ በሚያተርፊ ሁኔታ ጉዳት ካደረሰ ወይም የሌላ ሰዉን አካል ወይም አስፈላጊ ከሆኑት ብልቶቹ ወይም ከህዋሳቶቹ አንዱን የጎደለ ፣ እንዳያገለግሉ ያደረገ ወይም በሚሳሰቅቅና ጉልህ ሆኖ በሚታይ ሁኔታ መልኩን ያበላሸ ወይም በማናቸዉም ሌላ መንገድ ከባድ የሆነ ጉዳትን ያስከተለ እንደሆነ ነዉ” በማለት ሲደነገግ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ህግ አንቀፅ 556 ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት ወንጀል ማለት

“………….በአንቀፅ 555 ከተመለከቱት ሁኔታዎች ዉጪ በሰዉ አካል ወይም ጤና ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ነዉ፡፡” በማለት ይደነግጋል፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የወንጀል ህግ አንቀፅ 560 መሰረት የእጅ እልፊት ተፈፀመ የሚባለዉ ደግሞ

“…..የአካል ጉዳትን ወይም የጤና ጉድለትን ሳያደርስ በሌላ ሰዉ ላይ የእጅ እልፊት ወይም የመጋፋት ወንጀል የፈፀመ እንደሆነ ነዉ፡፡” በማለት የደነገገ ሲሆን አንቀፁ አክሎም “ሰንበሮች፣ የደም መቋጠር ምልክቶች ወይም በቶሎ የሚያልፍ ህመም ወይም ሥቃይ እንደ አካል ጉዳት ወይም እንደ ጤና ጉድለት አይቆጠሩም” በማለት ይደነግጋል፡፡

ከላይ የተገለፁት የወንጀል ድንጋጌዎች የወንጀል ድርጊቱን ሲደነግጉ ጉዳቱን ለማድረስ አገልግሎት ላይ የዋለዉ መሳሪያ ከግምት ዉስጥ ያላስገቡ ቢሆንም ብዙ ግዜ የጉዳቱን መጠን ወደጎን በመተዉ ጉዳቱ የደረሰበትን መሳሪያ ብቻ ከግምት ዉስጥ በማስገባት ክስ ሲመሰርት ይታያል ነገር ግን ሶስቱም የህግ ድንጋጌዎች ከ 556(2) ዉጪ ያሉት የተመሰረቱት በደረሰዉ የጉዳት መጠን እንጂ ጉዳቱን ለማድርስ በተጠቀሙት የመሳሪያ አይነት ላይ አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ የወ/ህ/ቁ 560 ንዑስ አንቀፅ 1 ሶስተኛዉ ዓ.ነገር ላይ

’’ ቀላል የሆኑ ሰንበሮች፣የደም መቋጠር ምልከቶች፣ወይም በቶሎ የሚያልፍ ህመም ወይም ስቃይ እንደ አካል ጉዳት ወይም የጤና ጉድለት አይቆጠሩም”

የሚለዉን አገላፅ የእጅ እልፊት ወንጀል በእጅ ብቻ ሳይሆን በመሳሪያም ሊፈፀም እንደሚችል ለመረዳት ይቻላል፡፡ በሌላ አገላለፅ ጉዳቱን ለማድረስ የተጠቀመዉ መሳሪያ ምንም ይሁን ምንም ድርጊቱ ያስከተለዉ ጉዳት ቀላል የሆኑ ሰንበሮች፣የደም መቋጠር ምልከቶች፣ወይም በቶሎ የሚያልፍ ህመም ወይም ስቃይ እንደሆነ በእጅ እልፊት ስር ሊመደብ እንደሚገባ ለመረዳት ይቻላል፡፡

ሌላዉ ብዙዎች የሚያነሱት መከራከሪያ የወ/ህ/ቁ 560 ርዕሱ የእጅ እልፊት ማለቱ በራሱ ድርጊቱ መፈፀም ያለበት በእጅ መሆኑን ያመለክታል የሚል ቢሆንም ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረዉ ቀላል የሆኑ ሰንበሮች፣የደም መቋጠር ምልከቶች፣ወይም በቶሎ የሚያልፍ የህመም ወይም ስቃይ እንደ አካል ጉዳት ወይም የጤና ጉድለት አይቆጠሩም ማለቱ የእጅ አልፊት የሚለዉ የድንጋጌዉ ርዕስ የሚያደርሰዉ በቀላል የሚያልፍ ህመም መሆኑን እንጂ በእጅ ብቻ መፈፀም እንዳለበት አያመለክትም፡፡

የደረሰዉ የጉዳት መጠን ሳይሆን ጉዳት አድራሹ ለማድረስ ያሰበዉን የጉዳት መጠን አብሮ መመርመር አስፈላጊ ስለመሆኑ፡- ብዙ ግዜ የሚስተዋለዉ ችግር ተከሳሹ ሊያደርሰዉ የፈለገዉ ጉዳት ከነገሮች ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ለመረዳትና በማስረጃ ለማስደገፍ እየተቻለ በደረሰዉ ጉዳት ላይ ብቻ በመመሰረት ዉሳኔዎችን መስጠት ሌላዉ የችግሩ መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡ ምንም እንኳን የደረሰዉ ጉዳት በእጅ እልፊት ወይም በቀላል አካል ጉዳት ስር የሚሸፈን ቢሆንም ከአጠቃላይ ነባራዊዉ ሁኔታ በመነሳት ማለትም፡ ተከሳሹ ወንጀሉን ለመፈፀም የተጠቀመዉ መሳሪያ ፣ የግል ተበዳዩ የሚገኝበት ሁኔታና የተከሳሹ ያለዉ ግንዛቤ ፣ ተበዳዩና ጉዳት አድራሹ ተነፃፃሪ ጉልበት ፣ የህክምና ምርመራ ዉጤት ፣ ከደረሰዉ በላይ ጉዳት ያልደረሰበት ምክንያት እና የመሳሰሉትን አከባቢያዊ ሁኔታዎችን በጋራ በመመዘን የተከሳሹ ድርጊት በታወቀ ወይም በተለመደ ሂደት (In the normal course of things) ሊያስገኝ የሚችለዉን ዉጤት ግምት ዉስጥ በማስገባት ተገቢ የሆነዉን ወሳኔ መስጠት ተገቢ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ክስ ሲመሰረት ተከሳሹ የተጠቀመው መሳሪያ ብቻ በመመርኮዝ ሳይሆን ከአጠቃላይ ነባሪ ሁኔታ በመነሳት የደረሰውን ወይም ሊያደርስ ያሰበውን ጉዳት ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡

ምንጭ:- 👉 የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በወንጀል ጉዳዮች የአተረጓጎም ልዩነት ያለባቸውን ድንጋጌዎች ላይ ወጥነት ያለው ትርጉም ለማምጣት እንዲቻል ከተዘጋጀ የሕግ ማብራሪያ ላይ የተወሰደ 🙌
👍1
በጫኝ እና አውራጅ ዘርፍ ላይ የወጣው መመሪያ ፀደቀ

ለእያንዳንዱ እቃ ዋጋ ተቀምጦለታል

" ማንኛውም ግለሰብ እኔ ከልጆቼና ከቤተሰቦቼ ጋር እራሴ አወርዳለሁ ካለ #አይገደድም " - የአ/አ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር

በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ የማህበር ቤቶች፣ ሪል ስቴት ያሉባቸው አካባቢዎች ላይ ጫኝ እና አውራጆች በሚጠይቁት ያልተመጣጠነ ክፍያና በሚፈጥሩት ግብግብ በርካቶች እንደሚማረሩ ይታወቃል።

" እቃዬን እኔ እራሴ አወርዳለሁ " ሲባልም አንዳንድ ጫኝ እና አውራጆች ከአፃያፊ ቃላት ውርወራ ጀምሮ ለግብግብ እና ፀብ እስከማጋበዝም ይደርሳሉ።

" መንግስት እስካደራጀን ድረስ ባለቤቱ ፈለገም አልፈለገም እቃውን የምናወርደው እኛ ነን " እስከማለትም ይደርሳሉ።

አንዳንዴም እቃዎች እንዲጎዱ ፣ እነሱ ካላወረዱት እዛ አካባቢ ላይ በነፃነት ለመንቀሳቀስ ስጋት እንስከመሆንም ይደርሳል።

በዚህ ላይ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር ይቀርፋል፣ ነዋሪዎችንም ከምሬት እና እንግልት ያታደጋል የተባለው መመሪያ ማንኛውም ህገወጥና ነዋሪዎችን የሚያማርሩ ተግባራትን ይከለክላል።

" ግለሰቡ እኔ ከልጆቼ፣ ከቤተሰቤ ጋር ሆኜ አወርዳለሁ ካለ አይገደድም ፤ እራሱ ማውረድ ይችላል። ማህበራቱም እኛ ነን የተደራጀነው ማስወረድ አትችሉም ማለት አይችሉም " ሲሉ አቶ ማስረሻ ሃብቴ የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አማካሪ ተናግረዋል።

የባለቤቱን መብት መጠበቅ የማህበራቱ ግዴታ እንዳሆነ ገልጸዋል።

በስምምነት  እቃው የሚወርድ ከሆነ ደግሞ ጫኝ እና አውራጅ ማህበሩ ሙሉ ኃላፊነት ለእቃው ይወስዳል ብለዋል።

አቅምን ያላገናዘበ ፣ ከእቃው ጋር ያልተመጣጠነ ክፍያም እንዳይኖር የዋጋ ተመን መውጣቱን አቶ ማስረሻ ገልጸዋል።

" ለእያንዳንዱ እቃ ዋጋ ተቀምጦለታል "  ያሉት አቶ ማስረሻ " የራሱ የሆነ ርቀት አለው ለምሳሌ ከተሽከርካሪ ከወረደበት 50 ሜትር የመጀመሪያ ዋጋ አለ ከዛ በኃላ እያጨመረ ይሄዳል። ኮንዶሚየም ላይ የሚወጣ ከሆነ እስከ ብሎክ ስር 50 ሜትር ከሆነ ከታች ወደላይ ዋጋው እያጨመረ ይሄዳል።  " ብለዋል።

ቢሮው ተግባራዊ ስለተደረገው መመሪያ በጫኝ እና አውራጅ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች እና ማህበራት የ2 ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት መጀመሩን ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ያገኘው መረጃ ያሳያል።

@tikvahethiopia