የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርፀትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት
276 subscribers
366 photos
3 videos
137 files
97 links
ይህ የቦሌ ክ/ከተማ የሕግ ስርጸትና ምክር መስጠት ዳይሬክቶሬት ቻናል ስለኢትዮጵያ ሕጎች)ማብራሪያ የሚሰጥበት፣ አዳዲስ ሕጎች የሚጋሩበት፣ ሕግ ነክ ዜናዎችና መረጃዎች የሚተላለፉበት፣ በዳይሬክቶሬቱ የተሰጡ የንቃተ-ሕግ ስልጠናዎች፣ የሕግ መልዕክቶች፣ በራሪ ጽሑፎች እና መሰል ሰነዶች የሚለቀቁበት ነው።
መልካም ቆይታ!
Download Telegram
ወድ የቻናላችን ተከታታዮች በዛሬው እለት አዲሱን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ መመሪያ ቁጥር 30/2013ን በpdf አዘጋጅተናል፡፡ መመሪያውን አውርዳችሁ እንድታነቡት በአክብሮት እንጠይቃለን
                               ስለሕክምና ስህተት

በዚህ አጭር ጽሑፍ የሕክምና ስህተት ምን ማለት ነው በሀገራችን ሕግስ እንዴት ተካቷል የሕክምና ስህተት ተፈጽሟል የሚባለው ምን ምን ሲሟላ ነው የሚሉትን ነጥቦች ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡ 

                   የሕክምና ስህተት ሕግ ምን ማለት ነው?
የሕክምና ስህተት ሕግ(MedicalMalpracticeLaw) ዶክተሮች ወይም ሌላ የሕክምና አገልግሎት ሰጪ አካላት የሕክምና አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት በታማሚው ላይ በችልተኝነት ለሚያደርሱት ጉዳት ያለባቸውን ተጠያቂነት የሚገዛ ሕግ ነው፡፡ ይህ የሕግ ዘርፍ ከሀገር ሀገር የተለያየ ይዘት ቢኖረውም በአብዛኛው ሀገር ግን በሕክምና ስህተት ግለሰቦች ለሚደርስባቸው ጉዳት ጉዳቱን ያደረሰው አካል ተጠያቂ የሚሆንበት የአሠራር ሥነ ሥርዓት አላቸው፡፡ አንድ የሕክምና ባለሙያ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ በተመሳሳይ ጉዳይ ሌሎች የሕክምና ባለሙያዎች ሊያከብራቸው ወይም ሊፈጽሟቸው የሚገባውን መደበኛ ጥንቃቄ (“standard of care”) ሊያከናውን ወይም ሊከተል ባለመቻሉ ምክንያት በታማሚው ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ የሕክምና ባለሙያው ለጥፋቱ ተጠያቂ የሚሆንበት አሠራር የሕክምና ስህተት ሕግ ይባላል፡፡

ሁሉም ስህተቶች የሕክምና ስህተት አይባሉም፡፡ አንድ ታካሚ የሚጠብቀውን የሕክምና ውጤት አላገኘሁም በማለት የሕክምና ባለሙያን ለመክሰስ አይችልም፡፡ በአጭሩ የሙያ ስህተት የሚባለው በአንድ የሙያ ዘርፍ የተሠማራ ባለሙያ ሥራውን በሚያከናውንበት ጊዜ ሊከተላቸው ወይም ሊመራባቸው የሚገባውን የሙያ ደንቦችና መመሪያዎች አውቆ ወይም በቸልተኝነት ሳያከብር መቅረት ወይም የሙያ ደንቦችን ባለማክበሩ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ማድረስ እንደሆነ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2031 እና 2035 ይደነግጋል፡፡

በመሆኑም አንድ የሕክምና ባለሙያ የሕክምና ስህተት ፈጽሟል ለማለት የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎች በሙሉ መሟላታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

1.     የአካሚና ታካሚ ሕጋዊ ግንኙት መኖሩን ማረጋገጥ
የሕክምና ስህተት አለ ብሎ ክስ ለመመሥረት የአካሚና ታካሚ ሕጋዊ ግንኙነት መኖሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡በሕክምና ባለሙያ እና በታካሚ መካከል ለሚኖረው ግንኙነት መሠረቱ የሕክምና አገልግሎት ውል ነው፡፡ታካሚው ከሕክምና ባለሙያው ወይም ከሕክምና ተቋሙ ጋር የሚኖረው የሕክምና ግንኙነት የሚመሠረተው በውል እንደሚሆን የፍትሐብሔር ሕግ ከቁጥር 2639-2652 ያስረዳል፡፡ በአንድ የመዝናኛ ሥፍራ አንድ ዶክተር በሰጠዎት መድኃኒት ምክንያት ጉዳት ደርሶብኛል ለማለት አይቻልም፡፡ በሕክምና ተቋሙ ካርድ አውጥተው የሕክማ ባለሙያውን አግኝተውት እንደሆነ ግን የአካሚ ታካሚ ሕጋዊ ግንኙነት እንዳለ ማስረጃ ይሆናል፡፡

ይቀጥላል
ፌናን
ሰላም!
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈፃሚ አካላትን እንደገና ለማደራጀት፣ስልጣንና ተግባራቸውን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 64/2011 እንዲሁም ተከታትለው በወጡት ማሻሻያዎች አዋጅ ቁጥር 67/2012 እና አዋጅ ቁጥር 70/2012 ዙሪያ በራሪ ጽሑፍ በማዘጋጀት ከታች አስቀምጬላችኋለው።ለበለጠ መረጃ አዋጆቹም ሊያስፈልጋችሁ ስለሚችል 3ቱንም አዋጆች ከታች ታገኟችኋላችሁ።

ሰናይ 16/2/2013 ዓ.ም!
ጤና ይስጥልኝ፡-

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በአዋጅ ቁጥር 1133/2011 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የሚያስፈጽማቸውንና በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 ስለተጠቀሱት አምስት የምርጫ ዓይነቶች (የሕዝበ-ውሳኔን ጨምሮ) በባለፈው ጽሑፋችን መጠነኛ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሞከርን ሲሆን በዚህ ጽሑፍ ደግሞ የምርጫ ማስፈጸሚያ አደረጃጀቶችን የምንመለከት ይሆናል፡፡

ቦርዱ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን በሁሉም ክልሎችና ከዚያ በታች ባሉ የአስተዳደር እርከኖች በማደራጀት አስፈላጊ የሆኑ የጽ/ቤት ሥራዎችን የሚያሰራ ሲሆን እንደዚሁም የምርጫ ጣቢያዎች በአግባቡ ተግባራቸውን ስለማከናወናቸው የሚቆጣጠርና ከምርጫ ጣቢያ የሚላኩ የምርጫ ውጤቶችን በመደመር አሸናፊዎችን ለይቶ ጊዜያዊ ውጤት ለሕዝብ ይፋ የሚያደርጉ የምርጫ ክልሎችን እንደዚሁም የተሰጠውን የድምጽ ቆጠራ በማካሄድ ጊዜያዊ የምርጫ ውጤትን የሚያሳውቅና ለሚከሰቱ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ፈጣን ምላሽ የሚሰጥና የማስተካከያ እርምጃ የሚወስዱ እና ታዛቢዎች የሚገኙባቸው የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚኖሩ ከተመለከትን ለወደፊቱ ስለምርጫ አፈጻጸም የምንመለከተው ይሆናል፡፡

ደረጀ ማርቆስ
ጥቅምት 17/2013 ዓ.ም
ስለኪራይ ውል
-------------------------
የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት እንደወሰነው "የኪራይ ውል የተለየ ፎርም መከተል እንዳለበት የሚያስገድድ የህግ ድንጋጌ የሌለ በመሆኑ በሁለት ተዋዋይ ወገኖች መካከል የሚፀና ውል ህጋዊ ውጤት ያለው ውል ለመመስረት በሁለቱም መካከል ስምምነት መኖሩ ብቻ በቂ ስለመሆኑ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1719(1),-1930,2898(3) በማጣቀስ በቅፅ 7 በመቁ 25938 አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል።
⚖♦️እንዲሁም ደግሞ ከኪራይ ቤቶች አስተዳደር ጋር የተደረገን የኪራይ ውል መሠረት በማድረግ የተያዘ ቤትን ያለአከራይ ፍቃድ ለሌላ ወገን ማስተላለፍ ለኪራይ ውሉ መሠረዝ በቂ ምክንያት ስለመሆኑ በቅፅ 7 በመ/ቁ 24221 ላይ አስገደዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል።
ምንጭ
በይነ መረብ
የሰበር ውሳኔ ቅፅ 7
Mr z
ከ ፍርድ በፊት ስለሚሰጥ የዕግድ ትዕዛዝ
፨ለግዜው የሚሰጥ የማገድ ትዕዛዝ(temporary injunction) ክርክሩ ተጀምሮ ነገሩ በፍርድ እስኪወሰን ወይም የተለየ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ ያሉትን ሁኔታዎች በነበሩበት አኳኋን ጠብቆ ለማቆየት ሲባል ከሚሰጡት ግዜያዊ ትዕዛዞች አንዱ ነው።
፨ንብረት እንዳለ እንዲቆይ፣ከመጥፋት እንዲድን፣እንዳይበላሽ፣ለሌላ ሰው ተላልፎ እንዳይሰጥ፣ወደሌላ ስፍራ እንዳይዘዋወር እንዳይባክን ለማድረግ ሲሆን ዓላማው ክርክሩ ተጠናቆ የሚሰጥ ፍርድ ለአፈፃፀሙ ዋስትና እንዲኖረው ውጤት እንዲያገኝ ለማስቻል ነው።
ይህ ዓይነቱ ትዕዛዝ የሚሰጠውም ክሱ በመጀመሪያ ደረጃ ተቀብሎ በሚያየው ፍ/ቤት ሲሆን ትዕዛዙ በ ሁለት ምክንያቶች ላይ የተመሰረተ ነው ።
1. በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 154(ለ) እንደተጠቀሰው ግዜያዊ የማገጃ ትዕዛዝ የሚሰጠው በክርክሩ ምክንያት በሆነው ንብረት ላይ ሆኖ ይኸው ክርክር የተነሳበት ንብረት የሚጠፋ፣የሚበላሽ ወይም ተከሳሹ በማንኛውም ምክንያት ለሌላ አሳልፎ ለመስጠት ያቀደ መሆኑ በቃለ መሃል ሲረጋገጥ ሲሆን፣
2. ግዜያዊ የዕገዳ ትዕዛዝ ይሰጥበት የሚባለው ንብረት የክርክሩ ምክንያት(መነሻ) ባይሆንም ተከሳሹ የባለመብቶችን ጥቅም ለመጉዳት ሲል ንብረቱን ለማጥፋት፣ለሌላ ሰው አሳልፎ ለመስጠት ያቀደ የዛተ ወይም ያሰበ መሆኑ የተረጋገጠ እንደሆነ ነው። ይህ ግዜያዊ የዕግድ ትዕዛዝ ከሳሽ በቃለ መሃላ በሚያረጋግጠው አቤቱታ መነሻነት የሚሰጥ ነው።
ምንጭ
ከበይነ መረብ
mr z
ውድ አንባቢዎች ጤና ይስጥልኝ!
መልካም ንባብ!
በሀገራችን ለሚከናወነው ምርጫ መራጮችም ሆኑ ዕጩ ተመራጮች መመዝገብ ያለባቸውና ለዚህም መራጮችም ሆኑ ተመራጮቹ ማሟላት የሚገባቸውን መስፈርቶች ከኢትዮጵያ የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ከአንቀጽ 18 እና ተከታዮቹ የሚከተለውን እንበል:-
መራጭ ለመሆን:-ኢትዮጵያዊ መሆን፣በምዝገባው ዕለት ዕድሜ 18 ዓመትን ከዚያ በላይ መሆን እና በምርጫ ክልሉ ቢያንስ ስድስት ወር መኖር የሚጠበቅበት ሲሆን መራጩ ወደ ምርጫ ጣቢያ ማንነቱን የሚገልጽ ያልታደሰ ቢሆንም የቀበሌ መታወቂያ ካርድ ወይም ፓስፖርት እነዚህም በሌሉ ጊዜ እንደመንጃ ፈቃድ የመሳሰሉ ሰነዶች ወይም በአከባቢ የሚታወቅ መሆኑን በቃለ-ጉባኤ በመያዝ እንዲመዝገብ የሚደረግና የመራጮች ምዝገባ መታወቂያ ካርድ እንዲሰጠው ይደረጋል፤ማንኛውም ሰው ምዝገባን በመቃወም ለምርጫ ጣቢያው ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ተቃውሞን ከእነምክንያቱ ሊያቀርብ የሚችልና ቅሬታውም በአዋጁ ላይ በተመለከተው መሠረት የሚወሰንና መራጭ ከምዝገባ የሚሰረዘውም ሕጉ እንዳይመዘገቡ ክልከላ ያደረገባቸው የአዕምሮ ሕመም ያለባቸው ወይም በሕግ ወይም በፍ/ቤት ውሣኔ የተገደበበት ተመዝግቦ ከተገኘ ነው።
ለዕጩነት ለመመዝገብ:-
ኢትዮጵያዊ መሆንና ለመምረጥ የተመዘገበ፣በምዝገባው ዕለት ዕድሜው 21 ዓመትና ከዚያ በላይ መሆን በምርጫ ክልሉ ውስጥ በመደበኛነት አንድ ዓመት ከኖረ ወይም የትውልድ ቦታው በዕጩነት ሊቀርብበት በፈለገበት የምርጫ ክልል ውስጥ ከሆነ ወይም የአዕምሮ ሕመም የሌለበት ከሆነ ወይም በሕግ ወይም በፍርድ ቤት ውሣኔ የመምረጥ ወይም የመመረጥ መብቱ ያልተገፈፈ እና ከአምስት ሺ የማያንስ የመራጮች የድጋፍ ፊርማ የሚያቀርብ በፖለቲካ ፓርቲ ዕጩ ከሆነ በሚወዳደርበት የምርጫ ክልል ከሚኖሩ መራጮች ሁለት ሺ የድጋፍ ፊርማ ማቅረብ ይኖርበታል፤ለምርጫ የሚወዳደረው የመንግሥት ሠራተኛ ከሆነ የምርጫ ቅስቀሳ በሚካሄድበት ወቅትና ምርጫው በሚከናወንበት ጊዜ ያለደመወዝ ፈቃድ የሚያገኝ ሲሆን ሆኖም ግን ዳኞች፣ዐቃብያነ ሕግ፣ወታደር፣ፖሊስ እና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች፣የደህንነት ሠራተኞች፣የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሠራተኛ ከሆኑ ግን መወዳደር የሚችሉት ሥራቸውን ለቀው ሲሆን እነዚሁ ሰራተኞች ሌላ ማንኛውም ተወዳዳሪን ለማስመረጥ በመደገፍ፣በመናገር፣ በመጻፍና በመሳሰሉት ተሳታፊ መሆንም የለባቸውም።
ማንኛውም ለምርጫ የሚወዳደር የራሱ የሆነ የመለያ ምልክትን መያዝና አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ለመለወጥና ለመተካት ጥያቄ ማቅረብ የሚችል የመሆኑን ያህል አንድ ዕጩ ወይም የፖለቲካ ፖርቲ የራሱን ከውድድር ውጪ ማድረግ የሚችል ሲሆን ለምርጫ የተመዘገቡ ዕጩዎች ከባድ ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ ካልተያዙ በስተቀር ምርጫው እስከሚጠናቀቅ ድረስ በወንጀል ተጠርጥረው አይያዙም። ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው የሚችለው የምርጫ ውጤቱ ከተገለጸ ብቻ ነውና
ዕጩ ተወዳዳሪ በእጩነት ተመዝግቦ የመታወቂያ ካርድ ካገኘበት ቀን አንስቶ ምርጫው አራት ቀን እስኪቀረው ድረስ ከአስተዳደሩም ሆነ ከማዘጋጃ ቤት ፈቃድ መጠየቅ ሳያስፈልገው በጽሑፍ በማሳወቅ ብቻም ሕጋዊ ግዴታዎቹን በማክበር በራሱም ሆነ በደጋፊዎቹ አማካኝነት የድጋፍ ስብሰባዎችን የመጥራት ወይም ሰላማዊ ሰልፍ የማደራጀት መብት፣ሕግን በማክበርና ምርጫው አራት ቀን እስኪቀረው ድረስ የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ ዘመቻ ማድረግ የሚቻል ሲሆን ሆኖም በቤተ-ክርስቲያናት፣በመስጊዶች፣በወታደራዊ ካምፖችና ፖሊስ ጣቢያዎች፣፣በትምህርት ቤቶች የገበያ አከባቢ በሁለት መቶ ሜትር ርቀት ዙሪያ፣የመንግሥት ወይም የሕዝብ መደበኛ ሥራ በመከናወን ላይ የሚገኙባቸው የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማት ሥራቸውን በሚያከናውኑበት መደበኛ የሥራ ሰዓትና ቦታ እንደዚሁም ሌላ ሕዝባዊ ስብሰባ እየተካሄደ ባለባቸው ቦታዎችና አከባቢዎች የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ እንደማይቻል በመግለጽ ጽሑፋችንን እንቋጫለን።
መልካም ቀን!
ደረጀ ማርቆስ(24/2/2013 ዓ.ም)
እንደ አሠሪ ወይም እንደ ሠራተኛ ያለብን ግዴታ

ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኛ ከሆኑ መሠረታዊ ሕጋዊ መብትና ግዴታ አለበዎት፡፡ ከአሠሪና ሠራተኛ መብትና ግዴታ ተያይዘው ያሉ መብቶች እጅግ በርካታ ቢሆኑም ዋና ዋና የሚባሉትን የአሠሪና ሠራተኛ ግዴታዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

የአሠሪ ግዴታዎች

አሠሪ የሚከተሉት ግዴታዎች አሉበት፡፡

ሥራ የመስጠትና በውሉ በሌላ ሁኔታ ካልገለጸ በስተቀር መሣሪያና ጥሬ ዕቃ የማቅረብ ግዴታ፣
ደሞዝና ሌሎች ክፍያዎችን የመፈጸም ግዴታ፣
የሰራተኛውን ሰብአዊ ክብር፣ ከስራ ጋር የተያያዘ ጤንነትና ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ፣
ሕጉ በሚያዘው መሰረት የተለያዩ ሁኔታዎችን በመዝገብ የመያዝ እና አግባብ ባለው አካል ሲጠየቅ መዝገብ የማቅረብ ግዴታ፣
የስራ ዓይነቱን ዘመንና ሲከፈለው የነበረውን ደሞዝ የሚያሳይ የምስክር ወረቀት ለሰራተኛው የመስጠት ግዴታ፣ እና
በሕጎችና በሥራ ውል ደንቦች እና መመሪያዎችን እንዲሁም ትዕዛዞችን የማክበር ግዴታዎች አሉበት፡፡

የሠራተኛ ግዴታዎች

ሠራተኛየሚከተሉት ግዴታዎች አሉበት፡፡

ሥራውን እራሱ የመስራት (በሌላ ሰው ማሠራት የተከለከለ ነው)፣ በአካልና በአዕምሮ ሁኔታ በስራ ቦታ ብቁ ሆኖ መገኘትና ትዕዛዝን የመፈጸም፡፡ አሠሪው የሚሰጣቸው ትዕዛዛት ግን ሁልጊዜም በስራ ውሉና በስራ ደንቡ መሠረት የተሰጡ መሆን አለባቸው፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉ ትዕዛዛትን ሠራተኛው የመፈጸም ግዴታ የለበትም፣
መሣሪያዎችና ዕቃዎችን ሁሉ በጥንቃቄ የመጠበቅ፣
የንብረትና የህይወት አደጋ እንዳይደርስ ወይም አስጊ ሁኔታ ሲፈጠር ተገቢውን ዕርዳታ የመስጠትና እነዚህ እና የድርጅቱን ጥቅም የሚነኩ ሌሎች ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ወዲያውኑ ለአሠሪው የማስታወቅና፣
በሕጎችና በሥራ ውል ደንቦች እና መመሪያዎችን እንዲሁም ትዕዛዞችን  የማክበር ግዴታዎች ናቸው፡፡

እነዚህን ግዴታዎች አለመወጣት እንደሁኔታው ከስራ እስከማባረር የሚያደርስ ውጤት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ ሰራተኛ የአሰሪውን ንብረት ከአደጋ መከላከል የሚገባው ሆኖ ሳለ በተቃራኒው በአሰሪው ንብረት ላይ ሆነ ብሎ ወይም በከባድ ቸልተኝነት ጉዳት ማድረስ ያለ ማስጠንቀቂያ ከስራ የሚያስባርር ድርጊት ነው፡፡ 


መልካም ቀን
ፌናን ተጊበሉ
ጥቅምት 27/2013 ዓ.ም