Co.Market / ኮ-ገበያ
541 subscribers
5.06K photos
81 videos
3 files
2.47K links
  📲+251 9 11 81 16 72
https://ermitheethiopia.com

👉
Download Telegram
#ኮንዶሚኒየም_የሚሸጠዉ_እንዴት_ነዉ

የኮንዶሚኒየም ሽያጭ ከሌሎች የቤት ሽያጭ ውሎች የሚለየው ባህርይ ያለው ሲሆን ይህም ዕጣው የወጣለት ግለሰብ በስሙ ቤቱን ቢረከብም እስከ 5 ዓመት ለሚደርስ ጊዜ መሸጥም ሆነ መለወጥ የማይችል በመሆኑ በቀጥታ የቤት ሽያጭ ውል ለመፈፀም ህጉ የማይፈቅድለት በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ክልከላ ወደጎን በመተው ግን በርካታ ባለዕድለኞች ቤት ሲሸጡና ቤት ፈላጊዎችም ሲገዙ መመልከት የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

#ዕጣው ደርሶት ቤቱን ከተረከበ 5 ዓመት ያልሞላው ሰው በየትኛው የህግ አግባብ ነው መሸጥ መለወጥ የሚችለው?

የፍትሃብሄር ህጉ አንቀፅ 3117 -3130 ድረስ ያሉት ስለ ወለድ አገድ የሚያወሩ ድንጋጌዎች ናቸዉ : በብዛት አሁን ላይ ኮንዶሚኒየም የቤት ሽያጭ ውል ተብሎ የሚዘጋጀዉም በዚህ መሠረት ነዉ ነገር ግን ይህ አሰራር ሕጋዊ መሠረት የለዉም ::

#ወለድ_አገድ ማለት አንድ ባለዕዳ ግዴታዉን መፈፀም መቻሉን ለማረጋገጥ የማይንቀሳቀስ ንብረቱን ለአበዳሪው ለማስረከብ የሚገደድበት ዉል ነው፡፡ በዚህ መሰረት ኮንዶሚንየም ቤቱን መግዛት የሚፈልገው ሰው ብር አበዳሪ እንደሆነ ፤ ሻጭ ደግሞ ተበዳሪ እንደሆነ በማስመሰል የብድር ውል ይዋዋሉና ለብድሩ ዋስትና እንዲሆን በሻጭ እጅ የሚገኘውን የኮንዶሚኒየም ቤት ለገዥ እንዲተላለፍ በማድረግ ነው፡፡ ቤቱን በእጁ ያስገባ ገዢ ብድሩ እስኪመለስለት ድረስ የቤቱ ሙሉ ተጠቃሚ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የ5 ዓመት ጊዜው እንዳለቀ እንደማንኛውም ቤት የሽያጭ ውል ተዋውለው ሙሉ ስሙን በገዥ ማዞር ይቻላል፡፡

#እንዲህ_አይነቱ ውል_በገዢ_ላይ_ምን_አይነት_ተፅዕኖ_ይኖረዋል?

1) በወለድ አገድ ውል መሰረት ኮንዶሚኒየም የተረከበ ሰው ስሙን ወደ እራሱ እስከ 5 ዓመት ድረስ ማዛወር የማይችል በመሆኑ ገዛሁት ያለዉ ቤት ላይ ጠንካራ ዋስትና ማግኘት አይችልም :: ይህ ማለት ቤቱን ለሌላ ሰዉ መሸጥ ፤ ማስያዣ አድርጎ ገንዘብ መበደር እና የመሳሰሉት ጥቅሞች ይቀሩበታል፡፡

2) የቤት ዋጋ በባህሪው ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የሚሄድ በመሆኑ ሻጭ ብድሩን በመክፈል ቤቱን መልሶ የሚረከብበት ዕድል ዝግ አይደለም ፡፡

3) በተጨማሪም ትልቁ ጉዳት (Risk) ❗️ የወለድ አገድ ውል እንደተፈፀመ ውሉ ወዲያው ቤቱ በሚገኝበት ከተማ ማዘጋጃ ቤት ወይም አስተዳደር ከሚገኘው የቤቱ ማህደር ጋር መመዝገብ እንደሚኖርበት እና የማይመዘገብ ከሆነ ውሉ ውጤት እንደማይኖረው የፍትሃብሄር ህጉ አንቀፅ 3118 እና 3052 በአንድነት ይደነግጋሉ፡፡ ይህ ማለት የወለድ አገድ ውሉን በቤቱ ማህደር ላይ እንዲመዘገብ ያላስደረገ ገዢ ቤቱ ላይ የሚኖረውን ህጋዊ መብት ያጣል ማለት ነው፡፡

በአጠቃላይ የኮንዶሚኒየም ሽያጭ ውሎች በጥንቃቄ መደረግ አለባቸዉ : ገዢዎችም ገንዘባቸውን ከማፍሰሳቸው በፊት ከላይ የተገለጸዉን የህግ አካሄድ አስቀድመዉ ቢያዉቁት መልካም ነዉ ::

ሳሙኤል ግርማ