የኛ ግጥም
44 subscribers
2 photos
2 links
#Kehas

#For business

#gitm

#Tarik

#Feta 😁

#Zena😍

#Sak😀

#desta😇
Download Telegram
​​😘የከንቲባው ልጅ😘
ደራሲ ተስፋዬ በትሩ
#የመጨረሻው ክፍል
አሜሪካ እንደማትሄድ ለአባቷ አሳውቃ በሰላምና በዕንባ ተለያይተዋል ። አባቷም ከሚስቱና ከህፃን ልጁ ጋር ወደ አሜሪካ በረዋል ። ከሰኔ #13 እስከ #21 final ፈተና ተፈትነን ስንጨርስ ከመሄዳቸው በፊት አባቷን አግኝቼ አነጋግሬያቸው ነበር ። ስለ ሁሉም ነገር እንዲህ ብለው ነገሩኝ ። "ከአራት ዓመት በፊት ወደ ስልጣን እንደመጣሁ አካባቢ በስራ ላይ አንዲት ሴትን ተዋወኩኝ ። በድሬዳዋ የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ናት ። ሁለታችንን አንድ የሚያመሳስለን ነገር ነበር ። እሷ ባሏን እኔ ደግሞ ሚስቴን በሞት አጥተናል ። በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ውስጤን ሰርስራ ገባች ። በስራና በኑሮዬ ጭምር ገብታ ታግዘኝና ትረዳኝ ጀመር ። በዚህ መሀል ግን አንድ ችግር ነበር ። እሱም በዙሪያችን ያሉ ሰዎች በኛ ስራና ግኑኝነት አለመደሰት ነበር ። የሚገርምህ ሁሉም በአንድነት ይቺን ምስኪን ከተማ ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል ሲስማሙ እሷ ብቻ ነበረች ከጎኔ የነበረችው ። ድሬዳዋ ከተማ በሁለት ክልል መሃል ያለች በመሆኗ በየ አራት ዓመቱ ባለስልጣናት አንዴ ከኦሮሚያ ከአራት ዓመት በዋላ ደግሞ ከሶማሌ ክልል እያለ ተራ በተራ #4 ዓመት እየጠበቀ ስለሚፈራረቅ ሁሉም ባለስልጣናት ሀሳባቸው ድሬን ማልማት ሳይሆን እራሳቸውን ማልማት ነበር ። እኔ ደግሞ ከንቲባ የሆንኩበት ዋነኛው ምክንያት ይህንኑን ስርዓት ለማጥፋት ነበር ። ከዛ በዋላ ያለው ታሪክ ህይወት እንደነገረችህ ነው ። የኛን መንገድ የማይከተሉ ሰዎች በበቀል ተነሳስተው ልጄን ለመግደል ብለው አቤልን ቀጠፉ ። እናም ወጣት ተስፋዬ ባለፈው ተከትለኸኝ ያየሀት ሴት በዛ አስቸጋሪ ጊዜ ከጎኔ የነበረች ጀግና ሴት ናት ። በዛው ወቅት በመሃላችን በተፈጠረው የፍቅር ግኑኝነት ልጅ ፀነሰችልኝና ተወለደ ። ይሄን ሁሉ ታሪክ ደግሞ ለልጄ በጊዜው እንዳልነግራት ለራሷ በጣም መጥፎ ሁኔታ ውስጥ ነበረች ። እንዴት ልጄ ላይ የመግደል ሙከራ ተደርጎ በጣም የምትወደው ጓደኛዋ ሞቶ ስለራሴ ደስታና ሀሴት እነግራታለሁ ...? ምን አይነት ስቃይ ውስጥ እንደነበረች ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው ። አሁን አንተን ስታገኝ ነው እንደዚህ ተቀይራ ያየሀት ። ለማንኛውም ሁሉንም ነገር ወደ ውጪ ስንሄድ ላሳውቃት ነበር የፈለኩት ። ባለቤቴንና ትንሹ ልጄን ከህይወት ጋር አንድላይ አሜሪካ ወስጄ ለሁሉም እውነታውን ልገልጽ ነበር እቅዴ ። እንደምታየው አሁን ሁሉም ነገር ተበላሽቷል ። ልጄም አኩርፋኝ ሸሽታኛለች" አሉኝ በሀዘን ። በስተመጨረሻ ልንለያይ ስንል ያሉኝን ግን እስካሁን ድረስ አምኜ አልተቀበልኩትም ። እንዲህ ነበር ያሉኝ "የህይወትን በህይወት መኖር ከኔና ካንተ ውጪ ማንም ሰው አያውቅም ። ለህይወት በህይወት መኖር ሲባል ይህ ምስጢር እንዲቀጥል እፈልጋለሁ ። እሷን ካንተ ለይቼ ወደ ውጪ ልወስዳት አልችልም ። ስለዚህ ልጄን ላንተ ሰጥቼሃለሁ ። ይዘሃት ወደ ሀገርህ ሂድ ። ከፈለጋችሁ እዛው ፤ ካልሆነም ደግሞ አዲስ አበባ ደስ የሚል ኑሮ መኖር ትችላላችሁ ። ዕድሜያችሁ ከ #20 ስላለፈ እራሳችሁን ችላችሁ መኖር አይከብዳችሁም ። ለብር ደግሞ ብዙም አትጨነቁ ። በባንኳ ውስጥ አንቀባሮ የሚያኖራችሁ በቂ ገንዘብ አለ" ። ታድያ የህይወት አባት እንዲህ ብለው መርቀው ልጃቸውን ሲሰጡኝ እንዴት ብዬ ልመን ...? በሌላ በኩል ደግሞ ማራኪዬ ስለኔ ምን እያሰበች እንደሆነ ለማወቅ በስልክ ሳዋራት "ሙሉ በሙሉ እንደረሳችኝና ሌላ ህንወት እንደጀመረች" ነገረቸኝ ። አሁን ከህይወት ጋር ነኝ ። ከቤተሰቦቼ ጋር አስተዋወኳት ። ለቤተሰቦቼም ሁሉን ነገር ነግሬያቸው ተስማምተን አዲስ አበባ አዲስ ህይወት ከህይወት ጋር ለመጀመር ተዘጋጅተናል ። ልክ እንደባልና ሚስት ሳይሆን እንደ ፍቅር ለመኖር ጉዞ ጀምረናል ። ከህይወት ጋር ስትኖር ፤ በህይወት መኖርህን ትወደዋለህ ። ስለ ህይወት ለማውራት ፣ እኔ ቃል የለኝም ፤ እሷ ካለች አለሁ ፣ ያለዚያ ግን የለሁም ።

ህይወት መዝሙር ነች ፤ ዘምራት
ህይወት ሰቀቀን ነች ፤ ቻላት
ህይወት ተግባር ነች ፤ ተወጣት
ህይወት ሽፍንፍን ነች ፤ ግለጣት
ህይወት ሀዘን ነች ፤ ተቋቋማት
ህይወት ስጦታ ነች ፤ ተቀበላት
ህይወት ውርርድ ነች ፤ ተወራረዳት
ህይወት ትግል ነች ፤ ታገላት
ህይወት ምስጢር ነች ፤ ፍታት
ህይወት ውበት ነች ፤ አጊጣት
ህይወት ጉዞ ነች ፤ አጠናቃት
ህይወት ቃል ነች ፤ አሟላት
ህይወት አጋጣሚ ነች ፤ ተጠቀማት
ህይወት ጀብዱ ነች ፤ ድፈራት
ህይወት ፍቅር ነች ፤ ፈልጋት ።
.
.
.
.
✍🏽~~~ተፈፀመ~~~~✍🏽 ☞ የስው ልጅ መጨረሻው ሲያምር ነውና ፤ ፈጣሪ መጨረሻችንን ያሳምርልን! እኔ አሜን ብያለሁ፡፡

#እኔም የተስፋዬና የህይወት ፍቅር አብቦ ወደሌላኛው የህይወት ምእራፍ እንደሚሸጋገሩ...ትዳራቸው ሰምሮም ፍሬ እንደሚያዩ ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ ...አመሰግናለሁ።።😘